Friday, April 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በከፍተኛ ሁኔታ ተጎድቶ የነበረው የሆቴሎች ገበያ መነቃቃት እያሳየ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

በከፍተኛ ሁኔታ ተጎድቶ የነበረው የሆቴሎች ገበያ በዳያስፖራዎች መምጣት ምክንያት መነቃቃት ማሳየቱ ተገለጸ፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጥሪ መሠረት ዳያስፖራዎች ወደ አገር ቤት ሲመጡ፣ በተለይ በአገልግሎት ዘርፉ ላይ መነቃቃት እንደሚፈጠር ሆቴሎች ተስፋ አድርገው ነበር። ከእንግዶቹ መምጣት ጋር ተያይዞም በአዲስ አበባና በመላ አገሪቱ የሚገኙ ሆቴሎች፣ በአገልግሎት ዋጋቸው ላይ 30 በመቶ ቅናሽ በማድረግና አዳዲስ ሁነቶችን በማዘጋጀት ጎብኝዎቻቸው ለመሳብ መሞከራቸውን ይገልጻሉ።

የጎልደን ቱሊፕ ሆቴል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ደረጀ ቦጋለ የሆቴሉ የክፍሎች የመያዝ ምጣኔ (Occupancy Rate) ሃያ በመቶ በታች እንደነበር ገልጸው፣ በአሁኑ ወቅት ግን በዳያስፖራዎች መምጣት ምክንያት ቁጥሩ ወደ 40 በመቶ ከፍ ማለቱን አስረድተዋል፡፡

የዳያስፖራዎች መምጣት በገበያው ላይ ካደረገው ቀጥተኛ አስተዋጽኦ በተጨማሪ፣ ከውጭ አገር በሚመጡ የሌላ አገር ዜጎችም ዘንድ የነበረው እምነት እንዲጨምር፣ በሌሎች ደንበኞች ቁጥር ላይም ከፍተኛ ለውጥ እንዲመጣ ማድረጉን አቶ ደረጀ  ገልጸዋል።

ላለፉት ሃያ ዓመታት በአገልግሎት ዘርፉ ላይ የቆየው ኩሪፍቱ ሪዞርት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ጦርነት፣ እንዲሁም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ከፍተኛ የገበያ ዕጦት ካጋጠማቸው መካከል አንዱ ነበር። በጦርነቱ ምክንያት አንዳንድ ቅርንጫፎቹ ሙሉ ለሙሉ ተዘግተው እንደነበር የድርጅቱ የማርኬቲንግ ኃላፊ አቶ ሚካኤል ተስፋዬ ገልጸዋል።

ነገር ግን ዳያስፖራዎች ከመጡ በኋላ የደንበኞች ቁጥር በእጥፍ መጨመሩን አስረድተዋል። ‹‹በኮቪድ-19 እና በሰሜናዊው የኢትዮጵያ ክፍል ጦርነት፣ በሁሉም ቅርንጫፎቻችን ላይ ከፍተኛ የገበያ ውድቀት ነበረ፣ አሁን ግን መሻሻል እየታየ ነው፤›› ብለዋል።

‹‹የአገር ውስጥ ደንበኞቻችን ቁጥር መቀነስ ምክንያት ጦርነቱና የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ቢሆኑም፣ በአሁኑ ወቅት የዳያስፖራዎች መምጣት በራስ መተማመንን በማሳድጉ የአገር ውስጥ ደንበኞቻችን ቁጥር እየጨመረ ነው፤›› ሲሉም አክለዋል።

የዳያስፖራው መምጣት ሆቴሎችን በገበያ ብቻ ሳይሆን በአስተሳሰብም አነቃቅቷቸዋል የሚሉት የኦዚ የሆቴልና ማኔጅመንት አማካሪ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ቁምነገር ተከተል፣ የአገልግሎት አሰጣጣቸው ላይም መሻሻል መታየቱን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት የታየው መነቃቃት የአገር ውስጥ ደንበኞችንም የሳበና በተለይ በአገር ውስጥ ከፍተኛ አቅም መኖሩን ያሳየ በመሆኑ፣ ለዚህም የተመቸ የዋጋና የአገልግሎት ዓይነቶችን በማቅረብ ዘርፉ በድጋሚ የገበያ መቀዛቀዝ እንዳይገጥመው ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ሆቴሎች በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ከደረሰባቸው ጉዳት ለማገገምና የሠራተኞችን ደመወዝ ለመክፈል ከብሔራዊ ባንክ በዝቅተኛ ወለድ የወሰዱት 3.3 ቢሊየን ብር መመለሻ ጊዜ በመድረሱ፣ ለብሔራዊ ባንክ የብድር መክፈያ ጊዜው ለአምስት ዓመታት እንዲራዘምላቸው በመጠየቃቸው፣ ብሔራዊ ባንክ የሆቴሎቹን የመክፈል አቅም እያጠና መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች