Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትበዕድሳት ላይ የሚገኘው የአዲስ አበባ ስታዲየም ያስከተለው ሥጋት

በዕድሳት ላይ የሚገኘው የአዲስ አበባ ስታዲየም ያስከተለው ሥጋት

ቀን:

በዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) እና የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ዕውቅና ያላቸው የእግር ኳስ ጨዋታዎች እንዳይካሄዱባቸው ክልከላ ከተደረገባቸው ስታዲየሞች አንጋፋው የአዲስ አበባ ስታዲየም ይጠቀሳል፡፡  በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን የተገነባው ስታዲየሙ የአገልግሎቱን ያህል ተገቢው ዕድሳት ሳይደረግለት መቆየቱ አግባብ አይደለም ብለው የሚተቹ አልጠፉም፡፡

በተለያዩ ከተሞች  ከፍተኛ ወጪ ወጥቶባቸው የተገነቡ ስታዲየሞች ቢኖሩም ካፍ እና ፊፋ ያስቀምጧቸውን መሥፈርቶች ባለማሟላታቸው እንደታገዱ ናቸው፡፡
የአዲስ አበባ ስታዲየም የማሻሻያ ግንባታ በሚመለከት በሐሳብ ደረጃ መግባባት ላይ የተደረሰው በፊፋና በካፍ የዕገዳ ውሳኔ ሰለባ ከመሆኑ ከዓመታት በፊት እንደነበር የሚናገሩ አሉ፡፡ ከእነዚህ አስተያየት ሰጪዎች መካከል በአዲስ አበባ ስታዲየም በተለይ የስታዲየሙን ሳር ውኃ በማጠጣትና በመንከባከብ ለዓመታት የሚታወቁ ሙያተኞች፣ ‹‹ስታዲየሙ የማሻሻያ ግንባታውን ጨምሮ ሌሎች መሠረተ ልማቶች እንዳይሟሉለት አንዱና መሠረታዊ ችግር ባለቤት አልባ መሆኑ ነው፤›› ይላሉ። የፊፋና የካፍ ውሳኔ ተከትሎ በአሁኑ ወቅት እንኳ የማሻሻያ ግንባታው ሒደት የሚፈለገውን ያህል እየተፋጠነ አለመሆኑን ጭምር ይናገራሉ፡፡

ይሁንና በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ፋሲሊቲ ዳይሬክተር አቶ አዝመራ ግዛው በበኩላቸው፣ የአዲስ አበባ ስታዲየም በአሁኑ ወቅት ፊፋና ካፍ ባስቀመጡት መሥፈርት መሠረት የማሻሻያ ግንባታው ሒደት በዕቅዱ መሠረት እየተከናወነ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ እንደ ኃላፊው፣ ‹‹ለአዲስ አበባ ስታዲየም የማሻሻያ ግንባታ ተብሎ የያዘው በጀት የለውም፡፡ የማሻሻያ ግንባታው እየተከናወነ ያለው በልዩ ሁኔታ በተፈቀደ በጀት ነው፤›› ብለው ፊፋና ካፍ በሰጡት አቅጣጫ መሠረት በአሁኑ ወቅት የግንባታው የመጀመሪያ ምዕራፍ በዕቅዱ መሠረት መከናወኑን ገልጸዋል።
ፕሪሚየር ሊጉን በባለቤትነት የሚያስተዳድረው የሊጉ አክሲዮን ማኅበር በውድድር ዓመቱ መጀመሪያ ለውድድር በዕቅድ ከያዛቸው ስታዲየሞች መካከል የአዲስ አበባ ስታዲየም ይጠቀሳል፡፡ እንዲያውም የፕሪሚየር ሊጉ የመጨረሻ የጨዋታ መርሐ ግብር የሚጠናቀቀው በአዲስ አበባ ስታዲየም እንደሚሆን ነው፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ አቶ አዝመራው ግዛው፣ ‹‹በእኛ እምነት በስታዲየሙ እንደሚካሄድ የሚጠበቀው የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ በሚያዝያና በግንቦት በመሆኑ ለዚያ ጨዋታ ሜዳውን ሳር ማልበሱ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ይሆናል ብለን ነው የምናምነው፤›› ይላሉ፡፡

በሌላ በኩል የፕሪሚየር ሊጉ አክሲዮን ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፈ በበኩላቸው፣ ‹‹አሁን ላይ ስታዲየሙ በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ የአደባባይ ምስጢር ነው፣ ታርሶ ነው ያለው፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ የሚገኝ ስታዲየም ከሦስት ወር በኋላ የሚደረግን የፕሪሚየር ሊግ የጨዋታ መርሐ ግብር ያስተናግዳል የሚል እምነት ባይኖረኝም፣ እውነት ከሆነ ግን የምናየው ስለሚሆን ችግር የለውም፤›› በማለት ሥጋታቸውን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ አገላለጽ፣  በመጀመሪያው የግንባታ ምዕራፍ የሚጠናቀቁት የስታዲየሙ የውስጥ ክፍሎች ማለትም የተጫዋቾች መልበሻና መቀመጫ፣ የዳኞች መልበሻ ክፍሎች፣ የክብር እንግዶች ቦታ፣ የስብሰባ አዳራሾች፣ የሚዲያ ማዕከልና  መፀዳጃ ክፍሎች ናቸው። ለዚህም ተገቢው ግምገማና ክትትል መደረጉን አፈጻጸሙም ከዕቅድ በላይ መሆኑንም አመልክተዋል።

ሜዳውን በሚመለከትም የሳር መረጣ  እየተከናወነ እንደሚገኝ፣ በዚህ ላይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሳሩ በተቻለ መጠን የተፈጥሮ ሆኖ ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን የበኩሉን አስተያየት መስጠቱን ገልጸዋል። በጀቱን በሚመለከት በአሁኑ ወቅት ያለውን ገበያ ግምት ውስጥ በማስገባት ጥናት እየተደረገ እንደሚገኝ፣ እስከዚያው ግን በተያዘው በጀት መሠረት እንዲቀጥል መደረጉን ጭምር ያስረዳሉ፡፡

ከበጀት ጋር በተያያዘ ኃላፊው ምን ያህል እንደሆነ ባይናገሩም ምንጮች ለሪፖርተር እንደሚገልጹት ከሆነ፣ የስታዲየሙን ክፍሎች ጨምሮ ሙሉ ዕድሳት እንዲደረግለት 439 ሚሊዮን ብር ገደማ በጀት ተይዟል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...