Wednesday, March 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉኢትዮጵያዊነትና የሰላም ፋይዳው

ኢትዮጵያዊነትና የሰላም ፋይዳው

ቀን:

በዓባይነህ ግርማ

በዚህ ዘመን ስለኢትዮጵያዊነት ብዙ እየተባለ ነው፡፡ መልካም ነውና ይበል የሚባል ነው፡፡ በቀድሞ ዘመናት ኢትዮጵያዊነት ጥያቄ ውስጥ ገብቶ ስለማያውቅ ብዙ የሚነገርበት አልነበረም፡፡ ዛሬ ብዙ ሲባል የምንሰማው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ የብሔርና የብሔርተኝነት ፖለቲካ በተጋነነባቸው ባለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት ኢትዮጵያዊነት ጥያቄ ውስጥ ገብቶ ስለነበር ነው፡፡ የኢትዮጵያዊነትን መፈክር ከፍ አድርጎ ማሰማት አስፈላጊና ተገቢ ስለመሆኑ ብዙ ማለት ባያሻም፣ ትልቅ መነጋገሪያ ከመሆኑ አንፃር የምልከታዬ አንዱ ጉዳይ ላደርገው ፈለግሁ፡፡

ስለኢትዮጵያዊነት የሚደረግ ንግግርና የሐሳብ ልውውጥ የሚከተሉትን ጥያቄዎች የሚያነሳና መልስ የሚሰጥ መሆን አለበት፡፡ ኢትዮጵያዊነት ምንድነው? ኢትዮጵያዊነት በምንና እንዴት ይገለጻል? ኢትዮጵያዊነትን ማነው ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባው? ኢትዮጵያዊነት የማን ጉዳይ ነው? ኢትዮጵያዊነት ያልሆነው ምንድነው? የኢትዮጵያዊነት ሥነ ልቦና እንዴት ነው መጠናከር ያለበት?

ኢትዮጵያዊነት በኢትዮጵያ አገራዊ ሉዓላዊነት ውስጥ ያሉ የኢትዮጵያውያን ሁሉ የአንድነት መገለጫችን ነው፡፡ ከዜግነትም በላይ ሰፊና ጥልቅ ሥነ ልቦና ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ያለፈውንም፣ የአሁኑንም፣ የወደፊቱንም የሚያይ ሥነ ልቦና፣ ምግባርና ተግባር ነው ሊባል ይችላል፡፡ የኢትዮጵያዊነት ምግባርና ተግባር ከብሔራዊነትና ክልላዊነት የዘለለ የአገራዊነት፣ የሕዝብ አንድነትና የእምነት መገለጫ ነው፡፡ የሁላችንንም ማንነቶች አቅፎ የሚይዝ ማንነት ነው፡፡ ሁላችንም በተለያዩ ማንነቶቻችን ላይ የምንደርበውና በአንድ ደረጃና መልክ የምንቆምበት ማንነት ነው፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ደሃውም፣ ሀብታሙም፣ ባለሥልጣኑም፣ ተራውም፣ የተማረውም፣ ያልተማረውም፣ በተለያየ ሙያና ተልዕኮ የተሰማራው፣ የተለያየ ሃይማኖትና እምነት የሚከተለውም ሁሉ በጋራ የሚገለጽበት፣ የሚታወቅበትና የሚጋራው እውነታ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ሕጋዊነትም ነው፡፡ የኢትዮጵያዊነት ትውፊታዊና ተቋማዊ መግለጫዎች ጥንታዊነቷ፣ የአንድነት ባለታሪክነቷ፣ ብዝኃነቷ፣ ሰንደቅ ዓላማዋ፣ አየር መንገዷ፣ ቀን መቁጠሪያዋ፣ ፊደሏ፣ የባህል ሙዚቃ መሣሪያዎቿ፣ የባህል ምግቦቿ፣ መልክዓ ምድሯ፣ ወዘተ ሁነኛ ምሳሌዎች ናቸው፡፡   

በሌላ በኩል እየተጠናከረ የመጣውን የኢትዮጵያዊነት ሥነ ልቦና በተንሸዋረረ ዕይታ ያልሆነውን ነው የሚል ትርጓሜ ሲሰጥ ይደመጣል፡፡ ይህ አስተሳሰብ ትክክል አይደለም ሊባል ይገባል፡፡ የኢትዮጵያዊነት ማንነትና መገለጫ ያልሆኑ አንዳንድ ትርክቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ምንም እንኳ ቀደም ሲል የሰሜኑ ኢትዮጵያ፣ የኦርቶዶክስ ሃይማኖትና ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ ታሪክ የጎላ ሚና የተጫወቱ ናቸው ቢባልም፣ ኢትዮጵያዊነት ከተወሰነ የአገሪቱ አካባቢ፣ ከተወሰነ ሃይማኖት፣ ከተወሰነ ብሔር ጋር ብቻ በመያያዝ የሚገለጽ አልነበረም፣ አይደለም፡፡

ሌላው ኢትዮጵያዊነት ያልሆነው በብሔርተኛ ፖለቲካ አስተሳሰብ እንደሚለው ሳይሆን፣ ብዝኃነትን የማይቃረንና አንድ ዓይነትነት አለመሆኑ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት የብሔርን ማንነት ያስረሳል? ወይም ያስንቃል? የሚባል አይደለም፡፡ አንዳንድ የሩቅም የቅርብም ተቺዎች እንደሚሉት ድህነትና ኋላቀርነት የኢትዮጵያዊነትና የኢትዮጵያ የገጽታ መገለጫ አይደሉም፡፡ ኢትዮጵያዊነት ምንም ቅደመ ሁኔታንና ምክንያታዊነትን የሚጠይቅ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያዊነት የብሔራዊ መግባቢያ አጀንዳ የሚሆን አይደለም፡፡ ኢትዮጵያዊነት የዜግነት መገለጫ ብቻ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያዊነት ከወቅቶችና ሁኔታዎች ጋር የሚለዋወጥ አይደለም፡፡

የኢትዮጵያዊነት ምግባርና ተግባር፣ ሥነ ልቦናና እምነት የሕዝብ ኅብራዊ አንድነትና የመብት እኩልነት ሲረጋገጥ የሚጠናከር ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያዊነት ሕጋዊነትም እንደ መሆኑ መጠን የሁሉንም ኢትዮጵያዊ የዜግነት መብት፣ ግዴታና ተሳትፎ በሕግ የበላይነትና በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ክቡር ደጃዝማች ወልደ ሰማዕት ገብረ ወልድ ‹‹ሕይወቴ›› በሚለው መጽሐፋቸው (2012፣ ገጽ 162) የወላሞ አውራጃ (የአሁኑ ወላይታ ዞን) ገዥ (አስተዳዳሪ) ሆነው ሲሾሙ (በ1955 ዓ.ም.) ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት የሰጧቸውን ምክር ጠቅሰዋል፡፡ “አንተን አደራ የምልህ ሕዝቡ መልካም አስተዳደር እንዲያገኝና ኢትዮጵያዊነቱን እንዲያውቅ እንድታደርግ ነው፡፡ ዜጎቻችን ሁሉ ኢትዮጵያዊነታቸውን ካላወቁ አገሪቱ እንዳሰብነው ልታድግ አትችልም፡፡ ዜጎቻችን ሁሉ በኢትዮጵያዊነታቸው አምነው አንዱ ከሌላው እበልጣለሁ ሳይል እኩል መሆናቸውን እንዲገነዘቡና እንዲተባበሩ ነው የምንጥረው፡፡ ከሩቅም በዙሪያችንም ጠላቶች አሉን፡፡ የምናሸንፋቸው ስንተባበር ነው፡፡ ዜጎቻችንን ሁሉ ሳናበላልጥ ሁሉንም እኩል ካስተዳደርናቸው እየተቀራረቡ ይተባበራሉየራስን ጥቅም ትቶ ለሕዝብ ጥቅም የሚሆን ሥራ ከተሠራ ጥቅሙ የተነካበትም ቢሆን በፍቅር ይሸነፋል፤” የሚል ነው፡፡ ይህን ምክር ዛሬም ኢትዮጵያዊነትን ለማጠናከር ሁነኛ የምግባርና ተግባር መመርያ አድርገን ከሠራንበት ኢትዮጵያዊነትና ኢትዮጵያ ያሸንፋሉ፡፡                 

ሰላም ግለሰባዊም፣ ኅብረተሰባዊም፣ አገራዊም ዓላማና ፍላጎት ነው፡፡ ሰዎችና ኅብረተሰብ ጤንነትን በመፈለግ ጤናማ ኑሮ ለመኖር እንደሚፈልጉት ሁሉ፣ ሰላምንም ይፈልጉታል፣ የሚቻለውን ሁሉ የሚያደርጉለትም ነው፡፡ በግለሰብና በኅብረተሰብ ብሎም በአገር ደረጃ ሰላምን የሚነሱ ምክንያቶች ብዙ ናቸው፡፡ ድህነት፣ ሥራ አጥነት፣ ኢፍትሐዊነት፣ ኢሰብዓዊነት፣ ኢዴሞክራሲያዊነት፣ የነፃነት ዕጦት፣ ተገላይነትና ባይተዋርነት፣ የብሔር ማንነት ፖለቲካ፣ የመልካም አስተዳደር ጉድለት፣ አለፍ ሲልም ሽብርና ነውጥ፣ ግጭትና ሁከት፣ የጽንፈኝነት ጥላቻና ፍራቻ የሰላም ዕጦት ምክንያቶችና መገለጫዎች ናቸው፡፡ እነዚህና ሌሎችም ምክንያቶችና መገለጫዎች በአገራችን ብቻ ሳይሆን፣ በተለያየ መጠንና ደረጃም ቢሆን በሁሉም አገሮችና ኅብረተሰቦች የሰላም ዕጦት እውነታዎች ናቸው፡፡ በአገራችን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሰላም ዕጦት ጎልቶ የሚታየው በብሔር የማንነት፣ ፖለቲካዊ ደባና ሴራ ምክንያት ኅብረተሰብ ውስጥ በሚከሰት ግጭት፣ መፈናቀልና መገዳደል ነው፡፡ በዚህ መልክ የሚፈጸሙ ኢሰብዓዊ ድርጊቶች በብሔር ማንነት ፖለቲካ ሽፋን የሚፈጸሙ የሥልጣንና የኢኮኖሚ ጥቅም ሽሚያና የሙስና ድርጊቶች ናቸው፡፡ ከዚያም ባለፈ የሰላም ዕጦት ወይም በኅብረተሰብ ውስጥ የሚፈጠር ሁከት የዓለም አቀፍ ኃይሎች መነገጃ ሲሆን ይታያል፡፡    

ስለሆነም ከመፍትሔ ፍለጋና ዕርምጃ አወሳሰድ አንፃር፣ የሰላም ዕጦት ምክንያቶችንና ባህሪያቱን በውል መረዳት ያሻል፡፡ የዘር፣ የብሔር፣ የቋንቋ፣ የሃይማኖትና ሌሎች የብዝኃነት ልዩነቶች ባሉበት እንደኛ አገርና ኅብረተሰብ ለሰላም ጦት ምክንያት የሚሆኑት ልዩነቶች ሳይሆኑ፣ ይልቁንም በልዩነቶቹ አያያዝ ላይ የሕግና የአስተዳደር አፈጻጸም ስህተቶች መሆናቸውንም ማመን ይገባል፡፡ የሰላም መታወክ ሲፈጠር የዕርምጃዎች አወሳሰድ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ መሆኑንና የውጤቱም ዘላቂነት ከወዲሁ እየተረጋገጠ ካልሆነ ችግሮች ይባባሳሉ፡፡ የተለመደው የእሳት ማጥፋት ዓይነት የዕርምጃ አወሳሰድ ለተመሳሳይ ችግር በር ሊከፍት የሚችል መሆኑን መገንዘብ ያሻል፡፡ ችግርን በአስቸጋሪነቱ ብቻ ማየት ችግር ችግርን እንዲወልድ ዕድል መስጠት ይሆናልና የሰላም ዕጦት ከችግርነቱ አንፃር ብቻ የሚታይ ጉዳይ መሆን የለበትም፡፡ ለምሳሌ ሰላም ከሌለ ሊደርስ የሚችል ጉዳትን ወይም አደጋን አጉልቶ ማሳየት ፍራቻን ሊፈጥር ይችላል፡፡ በፍራቻ ምክንያት እውነተኛ ሰላም ይፈጠራል ተብሎ መታሰብ የለበትም፡፡ የኃይል አገዛዝና አስተዳደር ባለበት ሥርዓት ፍራቻ የሚፈጥረው ሰላማዊ መሰል ሁኔታ ሊኖር ቢችልም፣ የሕዝብ ሰላማዊ አኗኗር የውሸት ነው ሊባል ይችላል፡፡

በሰላም ጉዳይ ኢኮኖሚያዊ መሥፈርቶችንም ታሰቢ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ረገድ በተለይ ከንብረት ባለቤትነትና የኑሮ ዋስትና ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ወሳኝ ናቸው፡፡ በየገጠር ወረዳዎች የሚፈጠሩ ሁከቶች ከሪሶርስ ማለትም ከመሬት፣ ከውኃ፣ ከግጦሽ መሬት አጠቃቀምና በአጠቃላይ ከኑሮ ዋስትናና ህልውና ጋር የተያያዙ ስለሆነ ጥልቅና ሰፋ ያለ የገጠር መሬት ልማትና ምርታማነት ፕሮግራምን በማጠናከር ሕዝብ ሁሉ የንብረት ባለቤትነትና የኑሮ ዋስትና እንዲኖራቸው ማድረግን ይጠይቃል፡፡ ስለሆነም የሰላም ፍለጋ (Quest for Peace) ትኩረትና ሥልት ድህነትን፣ ሥራ አጥነትን፣ ጠባብነትን፣ ጥላቻን፣ የንዋይ ስግብግብነትን፣ የሞራል ዝቅጠትንና በሐሳብ ልዩነት የሚፈጠር አለመቻቻልን በመዋጋት ላይ መሆን አለበት፡፡ ለሕግና ደንብ ማስከበርና ለልማት ሲባል የሚፈርሱና የሚገነቡ የመሠረተ ልማት ሥራዎችን ተከትሎ በሚፈጠር የሕዝብ መፈናቀል ምክንያት የሚሰማ ከፍተኛ እሮሮ፣ ዋይታና የሥነ ልቦና ስብራት በመጠለያ ዝግጅትና በዕለት ዕርዳታ ብቻ ሊታከም የሚችል አይደለምና ከእነዚህ ዕርምጃዎች ጎን ለጎን ተጎጂዎችን በሥነ ልቦና ማዘጋጀትና በአማራጭ አኗኗር መርዳት ይገባል፡፡     

ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ ሲባል የተለመደውንና ከፍተኛ የወጪ አቅምን የሚጠይቅ መንግሥታዊ የአስተዳደር ዕርከኖችን ማዋቀር ሳይሆን፣ ራሱ ሕዝቡ ከብሔር ማንነት አስተሳሰብ ውጪ በሆነ ዘይቤ የራሱን አስተዳደርና አመራር እንዲፈጠር ማድረግና የክልልም ሆኑ የፌዴራል መንግሥት አካላት የልማት ሥራዎችንና አገልግሎቶችን ብቻ እንዲያስተባብሩና እንዲተገብሩ ማድረግ የሚመረጥ ሥልት ሊሆን ይገባል፡፡ የአካባቢ ግጭቶችን በቅድሚያና በወቅቱ ለመከላከል ከሕዝብ ለሚቀርቡ የድረሱልን ጥሪዎች የክልልና የፌዴራል የደኅንነትና የፀጥታ መዋቅሮች አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ያላቸው ዝግጁነት አስተማማኝ እንዳልሆኑ እየታየ ከመሆኑ አንፃር፣ የኮሙዩኒቲ ሕዝባዊ መከላከያ (Community Defence) አቅም መፍጠር አስፈላጊ ይሆናል፡፡

ግጭቶች በሽምግልና ብቻ የሚፈቱ አድርጎ መውሰድ በቂ ስለማይሆን፣ ሕጋዊና ፖለቲካዊ መሥፈርቶችንም ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ለሰላምና ለሕጋዊነት ሲባል ቢቆጡ፣ ቢመክሩና ቢያመሠግኑ የሚያምርባቸውና የሚከበሩ የሃይማኖት መሪዎችና የባህል ሽማግሌዎች ቢሆኑም፣ የሙያ ማኅበራትን፣ የሠራተኛ ማኅበራትን፣ የመምህራን ማኅበራትን፣ የወጣት ማኅበራትን፣ የሴቶች ማኅበራትን፣ የተማሪዎች ማኅበራትን፣ ዕድሮችንና ሰንበቴ ማኅበራትን፣ ወዘተ ልንጠቀምባቸው ይገባል፡፡ ዛሬ አገራችን የእነዚህን አቅምና ሚና የምትፈልግበት ወቅት ነውና ለዴሞክራሲና ለሰላም መጠናከር ሲባል ጭምር የአባሎቻቸውን ጥቅምና መብት ከማስከበር ባሻገር ለሕዝባዊና አገራዊ አንድነት መጠበቅ፣ ለዴሞክራሲና ለሰላም መከበር፣ እንዲሁም በልማት ሥራዎች እስካሁን የተጫወቱትን ሚና በተለየ መንፈስና ተነሳሽነት እንዲያስቀጥሉ ማበረታታት ያስፈልጋል፡፡ ሌሎችም የሲቪል ማኅበር ተቋማት የበጎ ተፅዕኖ ፈጣሪነት አቅማቸውንና ሚናቸውን ያለ ገደብ እንደጠቀሙበት መፍቀድ ይገባል፡፡ የንግዱ ማኅበረሰብ እስከ ዛሬ ድረስ በሰላም አጀንዳ ዙሪያ እንዲወያይ የተደረገው ጥረት አነስተኛና እንዲያውም እንዳለ አይቆጠርም፡፡

ግጭቶችን ተከትሎ የሚደረጉ ስብሰባዎችና ውይይቶች የግጭቶችና የጥፋት ተዋናይ ኃይሎችን የሚያካትቱ አለመሆናቸው ግድፈት ነውና እነሱም እንዲሳተፉ መደረግ አለበት፡፡ ድንጋይ ወርዋሪው፣ መንገድ ዘጊውና እሳት ለኳሹ በሌለበት የሰላም ኮሚቴዎች የሚያደርጉት የተናጠል ውይይትና የሚሰጧቸው ማሳሰቢያዎች በስማ በለው ዕርባና ሊኖራቸው አይችልም፡፡    

በማጠቃለል የሰላም ጉዳይ የእያንዳንዱና የሁሉም ዜጋ ጉዳይ እንዲሆን ለማድረግ ቁልፉ እያንዳንዱና ሁሉም ሰው፣ ‹‹ሰላም ከሌለ አጣዋለሁ፣ ስለሆነም አስጠብቀዋለሁ›› የሚለው ነገር እንዲኖረውና እንዲያስብ ለማድረግ የሚያስችል ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡ ሰላምን በሚያውኩም፣ ሰላምን በሚፈጥሩም፣ ሰላምን በሚያዘልቁም ዕርምጃዎች መንግሥትና ሕዝብ ጠንካራ መግባባትና አቋም ሊኖራቸው ግድ ይላል፡፡ በሰላም ጉዳይ የማኅበረሰባዊ እሴችንም አጥብቆ መያዝ ያስፈልጋል፡፡ የሰላም ጉዳይ ከፋይዳው ወዲህና ወዲያ ሲባልም ይህንን ሁሉ ለማለት ነው፡፡ የሰላም ጉዳይ ዘመን በጠባ ቁጥር ሊዘመርለት የሚገባ ነው፡፡

‹‹አዲስ ሕይወት ስንጀምር በዚህ አዲስ ዓመት፣

በምድር እንዲበዛልን ፀጋና በረከት፣

ስለኢትዮጵያ ሰላም ሰአሊ ለነ ቅድስት”

“ሰላም ለኢትዮጵያ፣ ሰላም ለአገራችን፣

ይላክልን፣ ይላክልን ቸሩ አምላካችን››

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...

አወዛጋቢነቱ የቀጠለው የአዲስ አበባ የጤፍ ገበያ

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጤፍ የተከሰተውን የዋጋ ንረት...