Saturday, December 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹በፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ጊዜ የነበሩ አንዳንድ ግለሰቦች በግል ግንኙነትና ጓደኝነት ተነሳስተው ነው ሕወሓትን የሚደግፉት›› አቶ ዮም ዓብይ ፍሰሐ፣ የአሜሪካ ኢትዮጵያ ፐብሊክ አፌርስ ኮሚቴ የቦርድ አባልና ዋና ጸሐፊ

በርካታ የዳያስፖራ ተቋማትና ግለሰቦች በተለይም ባፈው አንድ ዓመት በተለያዩ ዘርፎች ከኢትዮጵያ ጎን ሲቆሙ ተስተውሏል፡፡ በቅርቡም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ባደረጉላቸው ጥሪ መሠረት፣ በርካታ የዳያስፖራ አባላት ወደ ትውልድ አገራቸው ጎርፈዋል፡፡ ከእነዚህ ዳያስፖራዎች መካከል አቶ ዮም ዓብይ ፍሰሐ ይገኙበታል፡፡ አቶ ዮም የአሜሪካ ኢትዮጵያ ፐብሊክ አፌርስ ኮሚቴ የቦርድ አባልና ዋና ጸሐፊ ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2021 የተቋቋመው ይኼ ኮሚቴ በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው የሆነ፣ በአሜሪካ የምርጫ ኮሚሽን አማካይነት የተመሠረተና የምርጫ ዘመቻ ድጋፍ ማድረግ የሚያስችል ፈቃድ ያገኘ ድርጅት ነው፡፡ የተቋማቸውን ሥራና ወቅታዊ ሁኔታዎችን በተመለከተ ከብሩክ አብዱ ጋር የሚከተለውን ቆይታ አድርገዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ባለፈው አንድ ዓመትና ከዚያም በላይ እንደ አገር ለኢትዮጵያ ከባድ የነበረበት ጊዜ ነበር፡፡ የኢትዮጵያን ጥቅም አስጠብቃለሁ ብሎ እንደተነሳ ተቋም ዓመቱን እንዴት ይገመግሙታል? በአገሪቱ የታየውን ከፍተኛ የሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት ያደረሰው ጦርነትስ መወገድ ይችል ነበር ይላሉ?

አቶ ዮም፡በኢትዮጵያ ታሪክ እንዲህ ያለ ከባድ ችግር ገጥሞን አያውቅም፡፡ እኛ በውጭ ያለን ኢትዮጵያውያን ጥቃቱ በተከሰተበት ጊዜ እጅግ በጣም ነበር የደነገጥነው፡፡ ሕዝቡ ሁሉ አንድ የሆነበት ታሪካዊ ጊዜም ነበር፡፡ እርግጥ ነው በመንግሥት በኩል ምንም ምርጫ አልነበረውም፡፡ የኢትዮጵያ ጦር ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ተጠቅቶ ስለነበር በግድ ሕግ ማስከበር ነበረበት፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብም እንዲሁ ምርጫ አልነበረውም፡፡ በየትኛውም አገር የሚገኝ መንግሥት እንዲህ ያለ ጥቃት ቢመጣበት ሕግ የማስከበር ግዴታ ይኖርበታል፡፡ ይኼ በታሪካችን የመጀመሪያው ነው፡፡ ከአሁን ቀደም የጣሊያን ወረራ ነበር፡፡ ጣሊያን የውጭ ኃይል ነው፡፡ የሶማሊያ ወረራም ነበር፣ እሱም እንዲሁ የውጭ ኃይል ነው፡፡ ይኼኛው ግን ከውስጥ የመጣ ስለሆነ በጣም አስቸጋሪና ከባድ ነበር፡፡ ስለዚህም ብዙዎቻችንን አስደንግጦናል፡፡ ምክንያቱም በየትም አገር ቢሆን ይሆናል ተብሎ የማይጠበቅ ነገር ነው፡፡ ስለዚህ ሕዝቡ በተለይ ውጭ ያለው ጉዳዩ ስላሳዘነውና ስላስደነገጠው፣ አንድ ላይ ሆኖ ኢትዮጵያን ለመርዳት የተባበረበት ነው፡፡ ስለዚህ ያለፈው አንድ ዓመት ታሪካዊ ነው ብዬ ነው የማምነው፡፡ ጦርነቱን ማስቀረት ይቻላል ወይ ለሚለው ግን፣ ምንም ምርጫ ስላልነበረ በግድ ሕግ ማስከበር ነበረበት ብዬ ነው የማምነው፡፡

ሪፖርተር፡በድረ ገጻችሁ ካነበብኳቸው ጽሑፎች አንዱ በተለይ ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ላይ ያልተገባ ተፅዕኖ እየደረሰ እንዳለ የሚያትት ጽሑፍ ይገኝበታል፡፡ በተለይም ከምዕራቡ ዓለም የሚመጡ ተፅዕኖዎች እንደሆኑም ተቀምጧልና እንዲያው በኢትዮጵያ ላይ ያልተገባ ተፅዕኖ ደርሷል ለማለት የሚያስችሉ ማሳያዎች ምንድናቸው? የምዕራቡ ዓለም ሊያሳካው የሚፈልገው ነገር ካለስ ያልተገባ ተፅዕኖ ነው ብሎ ማጣጣል ይቻላል?

አቶ ዮም፡ ልክ ነው በኢትዮጵያ ላይ ፍትሐዊነት የጎደለውና አድሏዊ ጫና ተደርጓል፡፡ የዚህ ዋናው መሠረቱ ደግሞ ብዙ የመረጃ ማዛባትና የውሸት መረጃ ስለኢትዮጵያ በመነገሩ ነው፡፡ በዚያ ምክንያት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ምክር ቤታቸው በኢትዮጵያ ላይ ጫና አድርገዋል፡፡ ለምሳሌ ጦርነቱን ማን እንደጀመረው ግልጽ የሆነ ሲሆን፣  የሕወሓት አመራር ራሱ አስቀድመን የመታነው እኛ ነን ብለው ተናግሯል፡፡ ግን በምዕራቡ ዓለምና በመገናኛ ብዙኃን ልክ ኢትዮጵያ እንዳጠቃችና እንደወረረች ተደርጎ ነው ይነገር የነበረው፡፡ እና ይኼ ሁሉ የተዛባ መረጃ ስላለ ነው ፍትሐዊ አይደለም ያልነው፡፡ በውሸት ላይ የተመረኮዘ ስለሆነና ዋናው ወንጀለኛ ሳለ ተጠያቂው እንደ ወንጀለኛ ስለተወሰደ ነው፡፡

ስለዚህ ሲጀመር የነበረው ይህ ነው፡፡ ለምሳሌ በአሜሪካ እ.ኤ.አ. በ2020 ጃንዋሪ 6 ምርጫ ከተደረገ በኋላ የሕዝብ ምርጫ የጣሱ ሰዎች ምክር ቤት ገብተው የሕዝብን ምርጫ ለመለወጥ በመሞከራቸው፣ እነዚያ ሰዎች ወንጀለኛ ተብለው ተፈርዶባቸዋል፡፡ የኢትዮጵያንም ስትመለከተው በሕጋዊ መንገድ የተመረጠ መንግሥትን ለመገልበጥ ያለመ ነው፡፡ ለዚህ ነው እንግዲህ ያልተገባ ተፅዕኖ ተመልክተናል ለማለት የቻልነው፡፡

ሪፖርተር፡- እንግዲህ በኢትዮጵያ ላይ ያልተገባ ተፅዕኖ ያሳድራሉ የሚባሉት አሜሪካና የምዕራቡ ዓለም አገሮች ናቸው፡፡ ይኼም በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ፍላጎት ነው የሚሉ የተለያዩ ተቃውሞዎች በሠልፎችና በተለያዩ መድረኮች ሲስተጋቡ ቆይተዋል፡፡ እናንተ አሜሪካና የተቀረው የምዕራቡ ዓለም በኢትዮጵያ ላይ ይኼንን ያህል ተፅዕኖ ያሳድራል ስትሉ፣ ከኢትዮጵያ ምን ፈልገው ነው ከሚል ግምገማ በመነሳት ነው?

አቶ ዮም፡እንግዲህ እኔ የሚመስለኝ ኢትዮጵያ ትልቅና ወደ 117 ሚሊዮን ሕዝብ የሚኖርባት አገር ናት፡፡ ለአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት፣ እንዲሁም ለቀይ ባህር ትልቅ ጠቀሜታ ያላት አገር ናት፡፡ ይህ ለአሜሪካም ጭምር የሚሠራ ጥቅም ነው፡፡ ቀጣናው ደግሞ ብዙ አገሮች ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ አለው ብለው የሚያስቡት ነው፡፡ ስለዚህ በኢትዮጵያ ላይ ተፅዕኖ ማድረግ ይፈልጋሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ ላይ የበለጠ ጫና ማድረግ ይፈልጋሉ፡፡

ነገር ግን ይህ ዕሳቤ የተሳሳተ አቋም ነው ብዬ ነው የምወስደው እኔ፡፡ የአሜሪካ መንግሥት መደገፍ የነበረበት ኢትዮጵያ እንድትጠናከር እንጂ እንድትዳከም አልነበረም፡፡ ከዚህ ባለፈም በፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ጊዜ የነበሩ አንዳንድ ግለሰቦች በግል ግንኙነትና በግል ጓደኝነት ተነሳስተው ነው ሕወሓትን የሚደግፉት፡፡ በረዥም ርቀት የአሜሪካን፣ የኢትዮጵያንም ሆነ የአካባቢውን ፍላጎቶች አስበው አይመስለኝም በግሌ፡፡

ሪፖርተር፡እንግዲህ ኢትዮጵያና አሜሪካ ከ100 ዓመታት በላይ የዘለቀ ግንኙነት ያላቸውና በተለያዩ ዘርፎች ባላቸው ትብብር ወዳጅነታቸውን ያሳዩ አገሮች ናቸው፡፡ ነገር ግን አሁን እየታየ ባለው ቅራኔ ሳቢያ ይህ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት የሚበላሽ ይመስልዎታል?

አቶ ዮም፡- ኢትዮጵያና አሜሪካ ከ100 ዓመታት በላይ የዘለቀ ወዳጅነት አላቸው፡፡ ስታራቴጂካዊ ወዳጆችም ነበሩ፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር ከንጉሡ (ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ) ጊዜ አንስቶ በተለያዩ መስኮች ጥብቅ ግንኙነት ነበር፡፡ በቅርብ ደግሞ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ አሸባሪነትን ለመዋጋት ወታደራዊ አበርክቶን ጨምሮ ብዙ አስተዋጽኦ አድርጋለች፡፡ ኢትዮጵያ ከሶማሊያ አንስቶ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን፣ በአጠቃላይ መላው አካባቢ እንዲረጋጋ ሠርታለች፡፡ ሌላው ደግሞ ለሰላም ማስከበር ከፍተኛ ኃይል ከሚያበረክቱ አገሮች ኢትዮጵያ አንዷ ናት፡፡ ስለዚህ በዚህ መልክ ኢትዮጵያ ለሰላም ብዙ አበርክታለች፡፡ በፖለቲካው ብቻ ሳይሆን በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በዲፕሎማሲ ጥሩ ግንኙነት ነበር፡፡

ሆኖም አሁን ሊበላሽ ይችላል፣ ለወደፊቱም እንሠጋለን ያለውን አመለካከት በተመለከተ፡፡ የአሜሪካ መንግሥት ፍትሐዊ ያልሆነ አቋም ወስዷል፡፡ ይህ እንዲስተካከል ሁላችንም ስንጥር ነበር፡፡ ለአሜሪካ ኮንግረስና ሴኔት ስናሳስብ የቆየነውም፣ ይኼ ነገር ለአሜሪካ የረዥም ጊዜ ፍላጎት ጥቅም አያስገኝም፡፡ ኢትዮጵያ ትልቅና ታሪካዊ የሆነች አገር ናት፡፡ የነበረን ግንኙነትም ረዥም ጊዜ የቆየ ነው፡፡ ኢትዮጵያ እንድትጠናከር እንጂ እንድትዳከም ሳይሆን፣ ከኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ጋር ነው መቆም ያለባችሁ ብለን ብዙ ጊዜ አሳስበናል፡፡

ሪፖርተር፡- የተቋማችሁ አንድ ዓላማ የኢትዮጵያን የአሜሪካ ታማኝና አስተማማኝ አጋርነት ለማረጋገጥ ከአሜሪካ አስተዳደር፣ የሕግ አውጭዎች፣ እንዲሁም ከሲቪል ማኅበረሰብ ጋር ንቁ ውይይት ይደረጋል ይላል፡፡ በዚህ ከባድ ነበር ባሉኝና ጫናዎች በበዙበት አንድ ዓመት ውስጥ የሠራችሁት ምንድነው?

አቶ ዮም፡ባለፈው ዓመት ብዙ ሠርተናል፡፡ አሥራ ሦስት ከሚሆኑ ኢትዮጵያዊ የሲቪል ድርጅቶች ጋር በጋራ በመሆን ወደ 92 የሚሆኑ የኮንግረስና የሴኔት አባላትን አነጋግረን፣ ስለኢትዮጵያ እውነተኛውን ነገር ማስረዳት ችለናል፡፡ አስቀድሞ የኢትዮጵያ መንግሥት እንደ አጥቂ፣ ሕወሓት ደግሞ እንደ ተጠቂ ነበር የሚታዩት፡፡ እኛ ሥራ ከጀመርንና እውነቱ መታወቅ ከጀመረ በኋላ ብዙዎቹ የሴኔትና የኮንግረስ አባላት፣ እውነትም ሕወሓት ጦርነቱን እንደጀመረ ተረድረዋል፡፡ ከዚያም በኋላ የአማራና የአፋር ክልሎችን ወረው ብዙ ሕዝብ እንደገደሉና ብዙ ንብረት እንዳጠፉ፣ ብዙ ሆስፒታሎች፣ ቤተ ክርስቲያናት፣ እንዲሁም መስጂዶች እንዳፈረሱ፣ ሕፃናቶችን በወታደርነት እያሰማሩ ለበርካታ ወጣቶች ሕይወት መጥፋት ምክንያት ሆነዋል፡፡ እኛ ሥራ ስንጀምር እውነቱ መውጣት ጀመረ፡፡ ብዙዎቹ የኮንግረስና የሴኔት አባላት እኛ በማስረጃ አስደግፈን ያቀረብንላቸውን እውነት ተቀብለው ሐሳባቸውን የለወጡ አሉ፡፡ እንዲያውም እኛን ደግፈው መጽሔቶችና ጋዜጦች ላይ ያወጧቸው ጽሑፎች አሉ፡፡ ለፕሬዚዳንት ባይደንም ኢትዮጵያን ደግፈው የጻፉ አሉ፡፡ በዚህ ረገድ አንደኛው ሥራችን ማሳወቅ ነበር፡፡

ሌላው ድግሞ ሜርኩሪ የተባለ የሎቢ (ወትዋች) ድርጅት መቅጠር ነው፡፡ ይህ ድርጅት እንግዲህ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋ ሄዶ ስለእኛ ጉዳይ የሚያስረዳ ነው፡፡ ለዚህም በወር 50 ሺሕ ዶላር እየከፈልን ኢትዮ-አሜሪካውያን እንዲህ ያለ ችግር አለባቸው፣ በአገራቸው ላይ እየደረሰ ያለውም ተፅዕኖ ትክክል አይደለም እያሉ በማስረዳት ለማሳመን ይጥራሉ፡፡ በየጊዜው እስከ 250 ከሚሆኑ ጋዜጠኞች ጋር በመጋገር እስከ 40 መጣጥፎች ስለኢትዮጵያ እንዲወጡ ተደርጓል፡፡ ይኼም ስለኢትዮጵያ እውነቱ እንዲነገር ተደርጓል፡፡ በማይካድራ፣ በኮምቦልቻ፣ በሸዋ ሮቢት የተሠራው ግፍ በጋዜጣ እንዲወጣና በማኀበራዊ ድረ ገጾችም እንዲሠራጭ ተደርጓል፡፡ እኛ የቀጠርነው ድርጅት ከሴኔትም ከኮንግረስም ጋር ያገናኘናል፣ የሕዝብ ግንኙነት ሥራም ይሠራል፡፡

ለአሜሪካ መንግሥት ሰዎች የረዳቸው እኛ እውነት ይዘን ስለተነሳንና የተሠራውን ግፍ በማስረጃ ማቅረባችን ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ተባብረን የምንሠራ ብዙ ሰዎች አለን፡፡ ጊዜያቸውንና ገንዘባቸውን በመሰዋት የሚያገለግሉ በርካቶች ናቸው፡፡ የቦርድ አባላትና ተሳታፊ ግለሰቦችን ጨምሮ፡፡ ሌት ተቀን እየሠሩ ያሉ ዲፕሎማቶች፣ እንዲሁም የትልልቅ ድርጅቶች አመራሮችና ባለሙያዎች ይገኙበታል፡፡

ኢትዮጵያ በዘር ማጥፋት ተከስሳ ነበር፡፡ በእኛ ጥረት ይኼ ሙሉ ለሙሉ እንዲሰረዝ አድርገናል፡፡ የአጎዋን (African Growth Oportunity Act) እንዳይሰረዝ በርካታ ጥረት ያደረግን ብንሆንም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ የእኛ ደጋፊዎች የሆኑ እንደ ኮንግረስ ውመን ካረን ባስ የመሳሰሉት ለፕሬዚዳንት ባይደን ደብዳቤ እስከ መጻፍ ደርሰዋል፡፡

ሌሎች ማዕቀቦችም በኢትዮጵያ ላይ እንዳይጣሉ ጥረናል፣ የተሳኩልንም አሉ፡፡ ለምሳሌ የምክር ቤት የውሳኔ ሐሳብ ቁጥር ኤች አር 445 የሚባል አለ፡፡ እሱ ላይ የተጻፈውን ኢትዮጵያን የሚጎዳ ጽሑፍ እንዲነሳ አድርገናል፡፡ አንዱ የኢትዮጵያ ጦር ትግራይን ወረረ የሚል አገላለጽ እንዳይኖር አስደርገናል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት የሰብዓዊ ድጋፍ እንዳይደርስ አደረገ ይልም ነበር፡፡ እሱም በኢትዮጵያ መንግሥት ሳይሆን በሕወሓት ወረራ ምክንያት መንገዱ መዘጋቱን ተናግረናል፡፡ ከዚህ ባለፈ የኢትዮጵያ መንግሥት ብዙ ሺሕ ቶን ድጋፍ ማድረጉን ሳይቀር ቀርበን አስረድተናል፡፡ እንዲሁም ከ450 ተሽከርካሪ በላይ እህል ተሸክሞ ገብቶ የተመለሰው 100 ብቻ መሆኑንም አስረድተናል፡፡ ከዚያ በተጨማሪም ግፍ ተፈጸመ የሚባው በትግራይ ሕዝብ ላይ ብቻ እንጂ፣ የአማራና የአፋር ክልሎች ጉዳቶች አይነገሩም ነበር፡፡ እኛ ይህንን በማስረጃ አስደግፈን የኢትዮጵያ መንግሥት አጥፊዎችን ለፍርድ አቅርቧል ስንል አስረድተናል፡፡

ሪፖርተር፡- የሎቢ (ውትወታ) ሥራ ትውውቅ፣ ገንዘብ እንዲሁም ሌሎች በርካታ ጉዳዮችን የሚጠይቅ ሥራ ነውና እናንተ ይህንን ሀብት ከየት ነው የምታመጡት? እስካሁንስ ምን ያህል አወጣችሁ በቁጥሮች መነጋገር ከቻልን?

አቶ ዮም፡- ሥራው ውስብስብ ነው፡፡ እስካሁን ከ500 ሺሕ ዶላር በላይ ሰብስበናል፡፡ ከራሳችንም ከደጋፊዎቻችንም፡፡ በየወሩ ያለብን ወጪ እስከ 60 ሺሕ ዶላር ይሆናል፡፡ ይኼም ለሎቢ ድርጅቱ ይከፈላል፣ ለጠበቆችና ሌሎች ወጪዎች ይኖሩናል፡፡ ለምሳሌ በቪዲዮ የተደገፉ ማስረጃዎችን ለማቅረብ በምንፈልግበት ጊዜ ፊልም በማሠራት፣ የእኛን ሥራ በሚደግፍ መንገድ እናቀርባለን፡፡ የተጎዱና ግፍ የተፈጸመባቸውን ሰዎች በሚመለከት ያሠራናቸው ፊልሞች አሉ፡፡

የራሳችን የቦርድ አባላት፣ የእኛ አጋር ድርጅቶችና ግለሰቦች የሚያደርጉት አስተዋጽኦ ቢሰላ ከሚሊዮን ዶላር በላይ ያወጣል፡፡ ነገር ግን ሁሉም በበጎ ፈቃደኝነት ነው የሚሠራው፡፡ ለምሳሌ ወደ ኮንግረስም ሆነ ሌላ ቦታ በምንሄድበት ጊዜ የራሳችንን ወጪ ችለን ነው የምንሄደው፡፡ ከዚህ ባለፈም በርካቶች ብዙ የሥራ ልምድ ያላቸውና በትልልቅ ድርጅቶች የሚሠሩ ናቸውና የእነሱ ጊዜ ውድ ነው፡፡ ይኼ ደግሞ ሰፊ ጊዜ የሚጠይቅ ሥራ ነው፡፡ በርካታ ስብሰባዎችን፣ ምክክሮችን ይጠይቃል፡፡ ከሎቢ ድርጅቱ ጋር ብቻ ወደ 80 የሚደርሱ ስብሰባዎች አድርገናል፡፡ እና ይኼ ሁሉ በገንዘብ ቢተመን በርካታ ሚሊዮኖች ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- እናንተ የቀጠራችሁት የሎቢ ድርጅት የኢትዮጵያ መንግሥት ቀጥሮታል ሲባል ከነበረ ድርጅት ጋር እንዴት ነው ተቀናጅቶ የሚሠራው?

አቶ ዮም፡ የእኛ መንግሥታዊ ያልሆነና በትውልደ ኢትዮጵያውያን የተመሠረተ ገለልተኛ ደርጅት ነው፡፡ እንደዚያ መሆኑ ደግሞ በጣም ጥሩ ነገር ነው፡፡ ምክንያቱም የመንግሥትን አቋም ብቻ ይዘን የምንቀርብ ከሆነ እነሱ የመንግሥት አፈ ቀላጤዎች ናቸው ይሉናል፡፡ ስለዚህ እኛ ገለልተኛና ለኢትዮጵያ የሚሟገት ድርጅት ነው የመሠረትነው፡፡ በመንግሥት በኩል የሎቢ ድርጅት የመቅጠር ጥረቶች ቢኖሩም፣ ለአጭር ጊዜ የቆዩ ናቸው፡፡ ረዘም ላለ ጊዜ የቆየ ዘላቂ የውትወታ ሥራ የሠራነው እኛ ነን፡፡

ለኢትዮጵያ የሚሟገቱ እስከሆኑ ድረስ ከሌሎች ድርጅቶች ጋር እንሠራለን፡፡ እኛ ግን የተቋቋምነው በአሜሪካ የምርጫ ኮሚሽን ሕግ ሥር ስለሆነ፣ የእኛ ሥራ ውትወታ ብቻ ሳይሆን ማስመረጥም ነው፡፡ እንደ ኩባና እስራኤል የአሜሪካ ኮንግረስና ሴኔት አባላት በሚወዳደሩበት ጊዜ ኢትዮጵያን የሚጠቅሙ፣ በኢትዮጵያና በአሜሪካ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር የሚሠሩ ከሆነ እነሱን በገንዘብም በድምፅም ማስመረጥ እንችላለን ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ ባለፈው የቨርጂኒያ የገቨርነር ምርጫ ጊዜ ኢትዮጵያውያን የዴሞክራትና የሬፐብሊካን ፓርቲ ዕጩዎችን አናግረን ስለኢትዮጵያ ያላቸውን አቋም ጠየቅን፡፡ ከተመረጡ ኢትዮጵያን እንደ አጎዋ ባሉ ጉዳዮች እንዴት ሊደግፉ እንደሚችሉ ጠየቅናቸው፡፡ ሪፐብሊካኑ ከኢትዮጵያ ጋር ያለኝን ግንኙነት አጠናክራለሁ፣ በተለይም በንግድ ዘርፍ ስላለ እሱን ኢትዮጵያውያን በከፍተኛ ቁጥር መርጠዋል፡፡ የእኛም ድርጅት በዚህ ረገድ ብዙ ሠርቷል፡፡

በሌሎችም ምርጫዎች ለምሳሌ እ.ኤ.አ. በ2020 ምርጫ ኢትዮጵያውያን በርካታ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ የጆርጂያ ግዛትን ውጤት ብትመለከት ፕሬዚዳንት ባይደን በ11,000 ድምፅ ነው ያሸነፉት፡፡ በዚህ ምርጫ ከ35 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያን መርጠዋል፡፡ እናም በድፍረት መናገር የሚቻለው፣ የኢትዮጵያውያን ድምፅ ፕሬዚዳንት ባይደንን አስመርጧል፡፡ ከዚህ ባለፈ በፔንሲልቬኒያ፣ በሜሪላንድ፣ በኒቫዳ፣ በፍሎሪዳ፣ ወዘተ፡፡

አሁን ከኢትዮጵያውያን ጋር ብቻ ሳይሆን የምንሠራው፣ ከሌሎች አሜሪካኖች ጋር አንድ ዓይነት ግንባር ፈጥረናል፡፡ ከካሪቢያን፣ ከኤርትራውያን፣ ከምሥራቅ አፍሪካውያንና ከሌሎች አፍሪካውያን ዜጎች ጋር በጋራ ምርጫን በሚመለከት እየሠራን ነው፡፡ ለወደፊቱም በ50 የአሜሪካ ግዛቶች የምንንቀሳቀስበትን የምርጫ ስትራቴጂ አውጥተናል፡፡ እ.ኤ.አ. በኖቬምበር 2022 የሚድ ተርም ምርጫ አለ፡፡ በዚያን ጊዜ በተለይ ስዊንግ ስቴትስ በሚባሉት በጆርጂያ፣ በፔንሲልቬንያና መሰል ግዛቶች ኢትዮጵያውያን ወሳኝ ዕድል አላቸው፣ ኢትዮጵያን የሚደግፉ ሰዎችን ለማስመረጥ፡፡

ሪፖርተር፡በቅርቡ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባይደን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ጋር በስልክ ተነጋግረዋል፡፡ በዚህም ንግግር ስለወቅታዊ ሁኔታና ስለሁለቱ አገሮች ቀጣይ ግንኙነት ውይይት አድርገዋል፡፡ ምናልባት ይኼ ለእርስዎ የመልካም ግንኙነት ጅማሮ ሊሆን ይችላል ይላሉ?

አቶ ዮም፡- በእኔ ግምት የፕሬዚዳንት ባይደን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ጋር መነጋገራቸው ጥሩ ጅምር ነው፡፡ ካሁን ቀደም የሚነጋገሩት ከሌሎች ሰዎች ጋር ሆኖ፣ ከኢትዮጵያ ጋር በሌላ ሰዎች አማካይነት ነው ይነጋገሩ የነበረው፡፡ አሁን ግን በቀጥታ መነጋገራቸው መልካም ነው፡፡ ለወደፊት ደግሞ ምናልባት የፖሊሲ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል ብለን እንገምታን፡፡ ይኼ ለምን ሆነ ብንል እኛ በሎቢ የሠራነው ሥራ እንዳለ ሆኖ፣ ኢትዮጵያ ደግሞ ጦርነቱን በአሸናፊነት እየተወጣች ነው፡፡ ነገር ግን የአሜሪካን ፖሊሲ እንደገና ተመልክተው ከኢትዮጵያ ጋር እንደገና እንቆማለን የሚል አስተሳሰብ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ይኼንን ባናውቅም መነጋገራቸው መልካም ጅምር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሁለቱ መሪዎች ከተነጋገረሩባቸው ጉዳዮች አንዱ ድርድር ማድረግና የተኩስ አቁም ስምምነት ማድረግ ናቸው፡፡ ይሁንና በርካታ የዳያስፖራ ድርጅቶች ከሕወሓት ጋር ድርድር እንዳይካሄድ የሚል አቋም አላቸው፡፡ በዚህ ላይ የእርስዎ አቋም ምንድነው? ድርድር ቢደረግስ ማነው ተጠቃሚ? ተጎጂውስ ማነው?

አቶ ዮም፡በአሁኑ ጊዜ በጣም ይህ አከራካሪ የሆነ ጥያቄ ነው፡፡ ብዙ የዳያስፖራ ድርጅቶች ከሕወሓት ጋር መደራደር አያስፈልግም፣ ሕወሓት ብዙ ወንጀል ፈጽሟል፣ ንብረት አውድሟል፣ ጥፋት ያጠፋ ወደ ፍርድ መቅረብ አለበት የሚል አቋም ነው ያላቸው፡፡ ስለዚህ ሕወሓት ውስጥ ሆነው ወንጀል የሠሩ ሰዎች ለፍርድ መቅረብ አለባቸው የሚል አቋም አለኝ፡፡

ነገር ግን መቼም ቢሆን አንድ ግጭት በጦርነት ብቻ ሊፈታ አይችልም፡፡ የሆነ ደረጃ ላይ ሲደርስ የሕዝብ ለሕዝብ ውይይትና ዕርቅ ያስፈልጋል፡፡ ያ መደረግ አለበት፡፡ ሰላም የሚመጣው በኃይል ብቻ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ጦርነቱን ማሸነፏ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ግን ሰላም ለመፍጠር ደግሞ መነጋገር ያስፈልጋል ብዬ አምናለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- እስካሁን ከነበረው ሁኔታ በመነሳት የኢትዮጵያና የአሜሪካ ግንኙነት ምን ሊሆን ይችላል ብለው ያስባሉ? እንደ የአሜሪካ ኢትዮጵያ ፐብሊክ አፌርስ ኮሚቴስ ምን ለመሥራት ታስባላችሁ?

አቶ ዮም፡እንግዲህ እኛ ለወደፊትም ከሌሎች የኢትዮጵያ ድርጅቶች ጋር በመሆንና በማስተባበር፣ የጀመርነውን ሥራ ለመቀጠል ነው የምናስበው፡፡ ለኢትዮጵያ መሟገታችንንም እንቀጥላለን፡፡ በሴኔት፣ በኮንግረስ፣ በሕዝብ ግንኙነት ዘርፍ፣ ወዘተ፡፡ ለኢትዮጵያ የሚስፈልጉትን ሁሉ ለዓለም ለማሳወቅ እንሠራለን፡፡ የኢትዮጵያና የአሜሪካ ግንኙነት እንዲጠናከርም እንሠራለን፡፡ በፖለቲካው ዘርፍ ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚም፡፡ ማለትም አሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት እንድታመጣ፣ ኢትዮጵያም ደግሞ ወደ አሜሪካ ሸቀጥና አገልግሎት እንድትልክና እርስ በርስ በመከባበር ያለው ወዳጅነት እንዲኖር እንጥራለን፡፡

ፖለቲካን በሚመለከት ግን ኢትዮጵያ ላይ ማናቸውም ዓይነት ተፅዕኖ፣ ማናቸውም ዓይነት ዕቀባ እንዳይደረግ እንጥራለን፡፡ ይኼንን የምናደርገው በሎቢ ነው፡፡ ሎቢ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለበለፀጉ አገሮች እንኳን አስፈላጊ ነው፡፡ እስራኤል፣ ኩባ፣ ቻይና እንደ አገር ሎቢ የሚያደርጉ ሲሆን፣ ትልልቅ ድርጅቶችም ሎቢ ያደርጋሉ፡፡ ለኢትዮጵያ ሎቢ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ ምክንያቱም ከአሜሪካ ጋር ትልልቅ ፕሮጀክቶችን ለማከናወን ይቻላል፡፡

ሌላው ደግሞ ተሰሚነታችን እንዲጨምር እንሠራለን፡፡ ባለፈው በሠራነው ሥራ ብዙ ለውጥ ዓይተናል፡፡ እስራኤሎች 50 ዓመት ስለሠሩ ብዙ ልምድ አላቸው፡፡ እኛም በቀጣዮቹ አምስትና አሥር ዓመታት ኢትዮጵያን የሚደግፉ ሰዎች እንዲመረጡ እንሠራለን፡፡ ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ለሚቀጥለው ትውልድ ጭምር የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስጠበቅ እንሠራለን፡፡ በዚህም እንዳለፈው ዓይነት የውሸት ታሪክ እንዳይደገም ይደረጋል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹መንግሥት ለአገር ውስጥ የኅትመት ኢንዱስትሪ ገበያ ከመፍጠር ጀምሮ ሥራ የመስጠት ኃላፊነት አለበት›› አቶ ዘውዱ ጥላሁን፣ የኢትዮጵያ አሳታሚዎችና አታሚዎች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ

የኅትመት መሣሪያ በጉተምበርግ ከተፈበረከ ከ400 ዓመታት በኋላ በኢትዮጵያ በ1863 ዓ.ም. በምፅዋ የተጀመረው የኅትመት ኢንዱስትሪ ከአፍሪካ ቀዳሚ ቢሆንም፣ ዕድገቱ ውስን መሆኑ ይነገራል፡፡ ከኢትዮጵያ በኋላ የኅትመት...

‹‹ከጨረታ በስተጀርባ ያሉ ድርድሮችን ለማስቀረት ጥረት እያደረግን ነው›› ሱሌማን ደደፎ (አምባሳደር)፣ የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ (የቀድሞ ሜቴክ) ዋና ሥራ አስፈጻሚ

ሱሌማን ደደፎ (አምባሳደር) በተባበሩት ዓረብ ኤሜሬትስ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ፣ ከጥር 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የቦርድ...

‹‹ባለፉት 25 ዓመታት ባለን አቅም ሁሉ የተለያዩ አጀንዳዎችን ለመዳሰስ ሞክረናል›› የራስወርቅ አድማሴ (ዶ/ር)፣ የፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ

‹‹ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ›› በመባል የሚታወቀውን በኢትዮጵያ ታሪክ ከመንግሥትም ሆነ ከሌላ አካል ገለልተኛ ሆኖ የተቋቋመ ሐሳብ አመንጪ የጥናት ተቋም (ቲንክ ታንክ) ከመሠረቱት አንዱ መሆናቸውን...