Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የንግድ ምክር ቤቶች ከሕገ ደንብ ማፈንገጥ

በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ግለሰብ ነጋዴዎች በየግላቸው ከሚጫወቱት ሚና ባሻገር ተባብረው ወደፊት መራመድ የሚችሉበት ብዙ ዕድል አላቸው፡፡

የግል ዘርፉ የበለጠ ውጤታማ እንዲሆንና ለአገር ትርጉም ያለው ሥራ እንዲሠራ ከተፈለገ  የንግድ ኅብረተሰቡን የሚወክሉ ተቋማት ድርሻ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ በተለይ የንግድና ዘርፍ ምክር ቤቶች በነፃነት እንዲራመዱ የሚያስችላቸው መደላድል ካለ በአገር ኢኮኖሚ ላይ ሊጫወቱ የሚችሉት ሚና ጉልህ ነው፡፡

የሌሎች አገሮች ልምድ የሚያሳየንም ይህንን ነው፡፡ ጠንካራ ንግድ ምክር ቤቶች ያሉት የንግድ ኅብረተሰብ መብቱንም ለማስጠበቅ ያሉበትንም ችግሮች በቶሎ እንዲፈቱለት በማድረግም ተጠቃሾች ናቸው፡፡

በኢትዮጵያም የነዚህ ንግድ ምክር ቤቶች አስፈላጊነት ታምኖ እንዲቋቋሙ ተደርጓል፡፡ እስካሁንም በተለያዩ መጠሪያዎች ወደ 75 ዓመት የዘለቀ ዕድሜ አላቸው፡፡ እነዚህ ንግድ ምክር ቤቶች ግን የዕድሜያቸውን ያህል ለአገር ኢኮኖሚ አበርክቶዋቸው ምን ያህል ነው? ካልን አጥጋቢ መልስ አናገኝም፡፡ ከተሰጣቸው ኃላፊነት እንዲሁም ማድረግ ይችሉ ከነበሩት ሥራ አንፃር ሲመዘኑ እዚህ ግባ የሚባል ውጤት አላቸው ለማለት አያስደፍርም፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤትና የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ደግሞ የበለጠ የሚጠበቅባቸው ቢሆንም፣ በተለያዩ ጊዜያት በውስጥ በሚፈጠሩ ሽኩቻዎችና ንግድ ደንብን አክብሮ የመጓዝ ችግሮች ያጠቋቸዋል፡፡

ይህ ብቻ ሳይሆን አንዳንዶች ንግድ ምክር ቤቱን መጠቀሚያ ለማድረግ የሚሸርቡት ሴራ ንግድ ምክር ቤቶች ቀዳሚውን ተግባራቸውን እንዲዘነጉ አድርጓል፡፡

በተለይ በአባሎቻቸው ፍላጎት ልክ አለመጓዛቸው በራሱ የነዚህ ተቋማት መገለጫ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ለንግድ ኅብረተሰቡ እንዲህ አደረጉ፣ ኢኮኖሚው እንዲያድግ ይህንን ሰሩ፣ ለውጭ ምንዛሪ ዕድገት በንግድ ምክር ቤቶቹ በኩል የቀረበው ሐሳብ እንዲህ ያለ ለውጥ አመጣ ሲባል አይሰማም፡፡

ይልቅዬ ወቅት ጠብቀው በምርጫና ከዚሁ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ተወዛገቡ የሚለው ዜና ጎልቶ ይወጣል፡፡ የእነዚህን ንግድ ምክር ቤቶች አመራር ለመቆጣጠር የሚደረግ ሽኩቻ ካለ አንድ ችግር መኖሩን ያሳያል፡፡ ዋናው ሥራ እየተሠራ ያለመሆኑንም ያሳብቃል፡፡

ይህ ተግዳሮት መከሰቱም ጥቂት የማይባሉ ነጋዴዎች እንዲያውቋቸው እያደረገ በመሆኑ ንግድ ምክር ቤቱን መጠቀሚያ ለማድረግ ለሚሹ ወገኖች ሠግርና ምላሽ እንዲሆንላቸው ዕድል ሰጥቷል ማለት ይቻላል፡፡  

እነዚህ ንግድ ምክር ቤቶች በዚህን ያህል ዕድሜያቸው የሠሩት ነገር የለም አይባልም፡፡ ብዙ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ በችግር ውስጥም አልፈዋል፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ስማቸውን የሚያስጠራ ይሄ ነው የሚባል ሥራ ሠርተዋል ማለት አይቻልም፡፡

ከዚህ ቀደም ያየናቸው አሳፋሪ ተግባራት ዛሬም መልክ ቀይረው እየተንፀባረቁ ናቸው፡፡ በተለይ እነዚህ ንግድ ምክር ቤቶች ወቅቱን ጠብቀው ምርጫ አለማድረጋቸውና እየሠሩ ያሉትን ሥራ ለአባሎቻቸው አለማሳወቃቸው ትልቅ ችግራቸው ነው፡፡

እንደ ኢትዮጵያና አዲስ አበባ ያሉ ንግድ ምክር ቤቶች ከሌሎች የአገሪቱ ንግድ ምክር ቤቶች በተሻለ ቁመና ላይ ያሉ ናቸው ቢባልም በተለይ ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት  ዓመታዊ ጉባዔያቸውን ጠብቀው አለማድረጋቸውና በየሁለት ዓመቱ ማካሄድ ያለባቸውን ምርጫ እንኳን ማድረግ ተስኗቸው አመራሮቹ ቦታውን የሙጥኝ ማለታቸው ለሌሎች የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶችም መጥፎ ምሳሌ እስከመሆን ደርሰዋል ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡

እነሱ ስላላደረጉ እኛም ማድረግ አይጠበቅብንም እስከማለት የደረሱ ሁሉ መኖራቸው የነገሩን ክብደት በደንብ ሊያሳይ ይችላል፡፡

ምክር ቤቶቹ በሕገ ደንባቸው መሠረት በየሁለት ዓመቱ ጠቅላላ ጉባዔ አድርገው ምርጫ ማካሄድ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን በየዓመቱም ጠቅላላ ጉባዔ ጠርተው ዓመታዊ ገቢያቸውንና ወጪያቸውንም ማሳወቅ እንዲሁም የኦዲተሮች ሪፖርት ማሰማት ሁሉ የግድ ነው፡፡ ይህ ሕግ ነው፡፡

ነገር ግን ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት እነዚህ ሕግጋት ተጥሰዋል፡፡ ይህ የሚያሳየው አንጋፋዎቹ የንግድ ምክር ቤቶች ለሕግ ተገዥ አለመሆናቸውን፣ የተወሰኑ ሰዎች የሚዘውሯቸውና የንግድ ኅብረተሰቡ ድምፅ የመሆን አቅማቸው የደከመ መሆኑን ያሳያል፡፡

ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ከሕግ ውጭ ጠቅላላ ጉባዔ አላደረጋችሁም፡፡ ምርጫም ማድረግ ሲገባችሁ አላደረጋችሁም ሲባሉ፣ ወቅታዊውን የአገር ሁኔታ ኮቪድ-19 እና አስቸኳይ ጊዜን እያሳበቡ እስካሁን መቆየታቸው በራሱ ችግራቸው ነው፡፡ ድርጊታቸው ከሕግና ከሕገ ደንብ ውጭ መሆኑን የተረዱ አይመስሉም፡፡

በእርግጥ ኮቪድና ወቅታዊ የአገሪቱ ሁኔታዎች ብዙ ነገሮችን ያስተጓጎለ ቢሆንም፣ ባለው አጋጣሚ ሕጋዊ አሠራሮችን በተቻለ መጠን መተግበር ይገባ ነበር፡፡

ለምሳሌ በሺዎች የሚቆጠሩ ተሰብሳቢዎች ያሉዋቸው ባንክና ኢንሹራንስ ኩብንያዎች በሕግ ተጠያቂ ስለሚሆኑ ጥንቃቄ አድርገው ጠቅላላ ጉባዔ ጠርተው ሪፖርት አቅርበዋል፡፡ በተመሳሳይ ብዙ ስብሰባዎችም ሲካሄዱ ዓይተናል፡፡

ራሳቸው ንግድ ምክር ቤቶቹ የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር ወይም የአድቮኬሲ ሥራዎችን ለመሥራት ስብሰባ እየጠሩ ውይይት እያደረጉ ቆይተዋል፡፡ ነገር ግን ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫ ሲነሳ እንዲህ ያለውን ስብሰባ ለማድረግ ወቅታዊ ጉዳይ፣ ኮቪድ-19 እና አስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ምክንያት ያደርጋሉ፡፡

ሌሎች ስብሰባዎችን ሕዝብ ሰብስበው ሲያደርጉ የእነሱን ጠቅላላ ጉባዔ ኮቪድ-19 እየመረጠ የሚያጠቃ ይመስል በሰበብ መቆየት ንግድ ምክር ቤትን ከሚያክል ተቋም አይጠበቅም፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ እንደ ቀድሞው የሚሞግት የምክር ቤት አባል መጥፋቱ ነገሩን የበለጠ አበላሽቶታል ማለት ይቻል፡፡ አሁን በተለይ በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ውስጥ አለ የተባለው ችግር ከመስመር እየወጣ ነው፡፡ አሁን ላይ ሪፎርም እየተደረገ ነው ቢባልም እንዲህ ዓይነቱ ዕርምጃ ምናልባት የዘገየውን የምርጫን ጊዜ በተመለከተ ጥያቄ እንዳይቀርብ የተደረገ ይመስላል፡፡

ንግድ ምክር ቤቶች እንዲህ የሚገለጹ መሆናቸው ያሳንሳቸዋል፡፡ ሌላው ቢቀር ዓመታዊ ሪፖርታቸውን አዘጋጅተው ለአባሎቻቸው ማሳወቅ ነበረባቸው፡፡ በተለይ በዚህ ወቅት ንግድ ምክር ቤቶች ያለባቸው ሚና ቀላል ስለማይሆን ይህንን ባገናዘበ መልኩ አጠቃላይ አሠራራቸውን ማስተካከል አለባቸው፡፡

የነበሩ ችግሮች እንዳይደገሙ ማድረግም ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ሕግ ያክብሩ፣ ከንቁሪያ ይውጡና በአስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔያቸውን ያካሂዱ፡፡ የንግዱ ኅብረተሰብም ማኅበሬን ይበል፡፡ ውስጣቸውንም ይመርምር፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት