Wednesday, February 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ዳያስፖራው በኢንቨስትመንት ዙሪያ የመከረበት መድረክ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጥሪ ወደ አገር የገቡ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የተለያዩ መድረኮች ተዘጋጅቶላቸው ሲወያዩ ሰንብተዋል፡፡ በተለይ በኢንቨስትመንት ዙሪያ የዳያስፖራውን አስተዋጽኦ በተመለከተ ከተዘጋጁ መድረኮች ውስጥ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ማክሰኞ ጥር 10 ቀን 2014 ዓ.ም. ያዘጋጀው ይገኝበታል፡፡

በዚህ መድረክ ላይ ዳያስፖራው በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ውስጥ እንዴት ይሳተፍ? የሚለው ቀዳሚ ሐሳብ ሲሆን፣ ኢንቨስት ለማድረግ አሉ የተባሉ ችግሮችና መፍትሔ ሊሆኑ የሚችሉ ሐሳቦች የተሰነዘሩበትም ነበር፡፡

ለአንድ አገር ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ደኅንነት መረጋገጥ ከሚጠቀሱ ጉዳዮች መካከል የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ የሚያደርገው እንቅስቃሴና የሚፈጥረው የሥራ ዕድል አንዱና ዋነኛው ነው የሚሉት የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ፣ ከዚህ አንፃር በተለይ የኢትዮጵያውያንና የትውልደ ኢትዮጵያውያን ሚናም ከፍተኛ መሆኑን ገልጻሉ፡፡

ዳያስፖራው በኢንቨስትመንት ዙሪያ የመከረበት መድረክ

ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በበርካታ የዓለማችን ክፍሎች የሚገኙ መሆናቸውን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቷ፣ በሚኖሩበት ሥፍራ ሁሉ የሚፈጥሩት ሀብት መልሶ ለእናት አገራቸው መጠነ ሰፊ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ የማይተካ ሚና እያበረከተ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በዙሪያቸው ላሉ አካላት ከሚልኩት የውጭ ምንዛሪ አንስቶ በአገር ላይ በሚፈጥሩት ኢንቨስትመንት ትልቅ ሚና እየተጫወቱ እንደሆነ እንደ ንግድ ምክር ቤት እንደሚገነዘቡ የገለጹት ፕሬዚዳንቷ፣ በተለያየ የትምህርት ደረጃና ሙያ በመሰማራት፣ ቴክኖሎጂን ወደ አገር በማስገባትና እንዲተዋወቅ በማድረግ እንዲሁም የአገልግሎት ዘርፉን በማሳደግ የኢኮኖሚው አለኝታ መሆናቸው ግነት እንደማይሆንም አመልክተዋል፡፡

ይሁን እንጂ ይህንን ትልቅ የዳያስፖራ ማኅበረሰብ በኢትዮጵያ ትርጉም ያለው ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ከተፈለገ በርካታ እግሮች መስተካከል እንደሚገባቸው በዕለቱ ከዳያስፖራው ማኅበረሰብ የተሰነዘረው አስተያየት ነው፡፡  

ዳያስፖራውና ጥያቄው

ከዕለቱ የውይይት መድረክ መገንዘብ እንደተቻለው፣ ዳያስፖራው በአገሩ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት አለው፡፡ ነገር ግን ይህንን ፍላጎት በተግባር ለመቀየር መስተካከል ያለባቸው ጉዳዮች ተነስተዋል፡፡

በዕለቱ አስተያየታቸውን ከሰጡ ዳያስፖራዎች መካከል ከኢትዮጵያ ከወጡ 40 ዓመታትን ያስቆጠሩት አቶ ግርማ መርጊያ አንዱ ናቸው፡፡ አሁን እየታየ ያለውን የዳያስፖራው ኅብረትና የአገር ፍቅር ስሜት የሚያስደስት መሆኑን ይገልጻሉ፡፡  ከውጭ ሲመጡ ‹‹እንኳን ወደ አገራችሁ በሰላም መጣችሁ›› መባሉ ትልቅ ነገር መሆኑንም ያስረዳሉ፡፡ በአሜሪካ በነበሩበት ወቅት ለአገራቸው የተጠየቁትን ድጋፍ ማድረጋቸውን የሚናገሩት አቶ ግርማ፣  ለግድብ፣ ለድርቁም መርዳታቸውን ነገር ግን ዳያስፖራው ሁሌ የሚታየው ከውጭ ምንዛሪ አቅም አንፃር እየመሰለ መምጣቱን ያስረዳሉ፡፡

ይህንንም ይገልጽልኛል ብለው በምሳሌነት ያነሱት፣ ‹‹እኔና ባለቤቴ 230 ሺሕ ዶላር አፓርትመንት ዩኒት ገዛን፡፡ ቤቱ እየተከራየ ገንዘቡን እናስቀምጣለን፡፡ ዩቲዩብ ላይ ባንኮች ሼር ይሸጣሉ የሚል ስለሰማሁ ይህንን ተከትዬ ሄጄ አንተ የሎ ካርድ ስላለህ መግዛት ትችላለህ ተብሎ በብር ሼር ገዛሁ፡፡ ሆኖም በኋላ ላይ የውጭ ዜግነት ያለው አይገዛም ተብሎ የገዛሁት አክሲዮን ተመላሽ ተደረገ›› ይላሉ፡፡

ዳያስፖራውን እናስተናግድ ሲባል እንዲህ ያሉ ነገሮች መስተካከል ይገባቸዋል በማለት ለምን ይህ እንደሆነ ጠይቀዋል፡፡ ‹‹እኛ ክልል የሌለን ኢትዮጵያውያኖች ምን እንሁን?›› በሚል ጥያቄ የጀመሩት ሌላው የዳያስፖራ አባል ደግሞ፣ በየክልሉ ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚገጥመው ችግር እንደሚያሳስባቸው አመልክተዋል፡፡

ኢትዮጵያ መታየት ያለባት እንደ አንድ መሆኑንም ገልጸው፣ ‹‹እኔ ካሊፎርኒያ ብኖር ነገ ሄጄ ጆርጂያ ልኖር እችላለሁ የሚጠይቀኝ የለም፡፡ ለምን መጣሽ የሚለን የለም፡፡ በአገራችን በተወለድንባት ኢትዮጵያ በየቦታው ማንነታችን መጠየቅ የለበትም፣ መሥራት ነው የምንፈልገው፤›› በማለት አለ ያሉትን ችግር ገልጸዋል፡፡  

ዳያስፖራዎች የሚጠበቅባቸውን ያህል ለምን ኢንቨስት አያደርጉም ከሚለው ጥያቄ ጋር ተያይዞ ሌላ አስተያየት ሰጪ ደግሞ ‹‹በአገር ውስጥ ገብተን ብንሠራ መጤና ከውጪ የሚባል አስተሳሰብ አለና እንዴት አድርገን ነው ንብረት እዚያ ላይ ማስፈር የምንችለው፣ እንዴትስ አድርገን ነው ይህንን ቢሮክራሲ ልንሻገር የምንችለው፡፡ እዚያ ላይ ንብረት አስፍረን ደግሞ ንብረታችን ሊወድም ይችላል፡፡ እያንዳንዱ ክልል የየራሱ ኢኮኖሚ ፖሊሲ አለው፡፡ እያንዳንዱ ክልል ደግሞ የራሱን ዘር ነው የሚፈልገው፡፡ እንደ አገር አንድ ወጥ የሆነ አሠራሮች ያስፈልጉናል›› ብለዋል፡፡

ውጭ ያለው ኅብረተሰብ ወደ አገር ውስጥ ገብቶ በተለየ ለመሥራት ፍላጎት ያለው ነው ያሉት እኚሁ አስተያየት ሰጪ፣ ችግሩ የአገር ውስጥ የፖለቲካ መዋቅር መሆኑን፣ መዋቅሩ እንደማይጋብዝ፣ ይህ ካልተስተካከለ አስቸጋሪ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

‹‹በደንብ ትቀበሉንና ለዘራፊ ትሰጡናላችሁ›› ያሉም አሉ፡፡ በተለይ ቢሮክራሲው በጣም አስቸጋሪ ነው ይላሉ፡፡ ይህ ብቻ አይደለም በጣም ሙስና መኖሩም ተነስቷል፡፡

እንዲህ ያሉ ሌሎች ችግሮች፣ ጥያቄዎችና አስተያየቶች፣ የመሠረተ ልማት ችግሮችም ተነስተዋል፡፡ የብዙዎቹ ሐሳብ መሥራት እንፈልጋለን ግን ቢሮክራሲውና ሙስናው መጥፋት አለበት የሚል ነው፡፡

የኮሚሽነሩ አስተያየትና ምላሽ

በዕለቱ የተሰጡ አስተያየቶችና የቀረቡ ጥያቄዎች ላይ በመድረኩ አጭር ቆይታ የነበራቸው አዲስ አበባ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር አቶ ግርማ ሰይፉ በአንዳንዶች አስተያየትና ጥያቄዎች ላይ ምላሽ ለመስጠት ሞክረዋል፡፡ ዳያስፖራው በኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት ሲያደርግ ሪስክ መሸከምም ይኖርበታል የሚለውን እምነታችን አንፀባርቀዋል፡፡

‹‹ዱይንግ ቢዝነስ ኢንዴክስን ስትመለከቱ ከ180 አገሮች ኢትዮጵያ 159ኛ ነች፣ ይህንን ቢዝነስ ኢንዴክስ ዓይቶ ኢትዮጵያ ኢንቨስት ላድርግ የሚል ሰው 158ቶቹ ጋር ከደሰረ በኋላ 159ኛ አገር ነው የሚመጣው፡፡ በዚህ ዓይነት ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት አግኝተን ኢትዮጵያን ካለችበት ችግር እናወጣታለን የሚል የአጭር ጊዜ ተስፋ የለም ማለት ነው›› ብለዋል፡፡

ዱይንግ ቢዝነስ ኢንዴክሱን የጋራ አድርጎ በመውሰድ መሥራት አንድ ትልቅ ነገር ይሆናል ያሉት አቶ ግርማ፣ ከቢሯቸው ያለውን ዱይንግ ቢዝነስ ኢንዴክስ ሊያስተካክሉ እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡

 መሬት አስተዳደርና ሌላ ሌላ ቦታ ያለውን እኔ ማስተካከል አልችልም ያሉት አቶ ግርማ፣ ሥራችን እነዚህን መግፋት ይሆናል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን አብረን እየሠራን እንቀጥላለን፡፡ እስከዚያው ድረስ ግን የማይንድ ኢንቨስተሮች በዱይንግ ቢዝነስ ኢንዴክስ የሚፈላሰፉ እንደተጠበቁ ሆነው፣ እኛ ግን አገሩን እንደሚወድ ኢትዮጵያዊ ትውልደ ኢትዮጵያ የልብ ኢንቨስተር መሆን ያስፈልገናል ብለዋል፡፡

እንደ አቶ ግርማ፣ የልብ ኢንቨስተሮች ዱይንግ ቢዝነስ ኢንዴክስን አያዩም፡፡ ኢንቨስት የሚያደርጉት ለአገርና ለወገን ይጠቅማል ወይ ብለው ያስባሉ፡፡ ሪስክ ይወስዳሉ፡፡ ማንኛውም ኢንቨስተር ሪስክ ወሳጅ ነው፡፡ ግን እነዚህ ኢንቨስተሮች ለአገራቸው ተጨማሪ ሪስክ ይወስዳሉ ማለት ነው፡፡ የሚወስዱት ሪስክ ለምሳሌ በአገራቸው ኢንሹራንስ ኩባንያ ካላቸው የኢንሹራንስ ኩባንያው የሚጨምርባቸውን ተጨማሪ ዓረቦን ለመክፈል ፈቃደኛ ይሆናሉ ማለት ነው፡፡ ካልሆነም ከራሳቸው አካውንት አውጥተው ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት ያደርጋሉ ማለት ነው፡፡ ‹‹የዚህ ዓይነት የልብ ኢንቨስተር ከሆናችሁ ኢትዮጵያ ትፈልጋችኋለች፣ እናንተም ኢትዮጵያን አለን የምትሏት በዚሁ መንገድ ነው›› ብለዋል፡፡

አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ሻሸመኔ ላይ ሆቴሉ ተቃጥሎበት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ  አዳማ ላይ ሆቴል ማስመረቁን ያስታወሱት አቶ ግርማ፣ የቢዝነስ ኢንዴክስ ስለማያውቅ ሳይሆን የኃይሌ ልብና ኢትዮጵያ የተሳሰሩ ስለሆነ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ዱይንግ ቢዝነስ ኢንዴክሱ ታይቶ አድካሚው ቢሮክራሲ ሲቀር ኢንቨስት ለማድረግ የሚመጣ ከሆነ አይሆንም ያሉ አቶ ግርማ፣ የዳያስፖራው ኢንቨስትመንት የልብ እንዲሆን ጠይቀዋል፡፡

‹‹አሁን ግን እዚህ ያላችሁ በሙሉ ትልቁን ሥራ ሠርታችኋል፡፡ አገራችሁ ችግር ላይ ነች፣ ልትሞት ነው፣ ኑና እዩኝ ስትል መጥታችሁ አይታችኋታል፡፡ አልሞትንም ተርፈናል፡፡ ተባብረን እንቢ ካልን ድህነትን ማሸነፍ እንችላለን ብዬ አምናለሁ›› ሲሉም ተደምጠዋል፡፡

ንግድ ምክር ቤቱ ከዳያስፖራው ጋር ሊሠራ የሚችለው ትልቅ ሥራ እንዳለ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከተለያዩ ዳያስፖራዎችን ማነጋገራቸውን፣ የኢንቨስትመንት ፍላጎት አለን ብለው የመጡ መኖራቸውን ያስታወሱን አቶ ግርማ፣ ‹‹እኔ ቢሮ መጥተው ምንድነው የምትደግፉን ይሉኛል፡፡ ለሁሉም የሰጠኋቸው መልስ ታክሲ አስቁማችሁ የት ነው የምንሄደው ትላላችሁ ወይ የሚል ነበር›› ብለዋል፡፡

አሁን የመጡት ብዙዎቹ ምንድነው የምትረዱን ይላሉ፡፡ ፕሮፖዛል የላቸውም፡፡ ከዳያስፖራ ኤጀንሲ ተባበሯቸው የሚል ደብዳቤ ይዘው ይመጣሉ፡፡ እኔ ቢሮ ስትመጡ ምንም ደብዳቤ አያስፈልግም፡፡ ስትመጡ ግን የምትፈልጉትን አውቃችሁ መምጣት አለባችሁ በማለትም፣ ቻምበር የዳያስፖራ ዴስክ አቋቁሞ በዚያ ዴስክ ምክርና መረጃ መስጠት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

አቶ ግርማ ሌላ የሰጡት አስተያየት ከሰላም ጋር በተያያዘ እየተፈጠረ ያለውን ችግር በተመለከተ ለቀረበ ጥያቄ ነው፡፡ ‹‹እኔ ልዋሽ አልችልም፡፡ ልነግርህ የምችለው ነገር እውነት ብቻ ነው፡፡ ላረጋግጥልህ የምችለው ሰላም የለም፡፡ ሰላምን ሁላችንም ተባብረን የምናመጣው ነው፡፡ ሁላችንም ሠርተን የምናረጋግጠው ነው፡፡ መንግሥት ብቻውን የሚያረጋግጠው አይደለም፡፡ ሪስክ ግን መውሰድ አለብን›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

እንደ ምሳሌ የራሳቸውን ገጠመኝም ሲገልጹ፣ ‹‹ተቃዋሚ ጎራ ውስጥ እያለሁ የዓባይ ግድብን ቦንድ ዕገዛ ነበር፡፡ ሌቦች እንደሚሰርቁ አውቅ ነበር፡፡ የተሰረቀው ተሰርቆ የተረፈው ተርፎ አሁን ያለንበት ደረጃ ደርሰናል፡፡ ሪስክ እንዳለ ተገንዝበን ልንሠራ ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

 መሠረተ ልማትን በተመለከተ ደግሞ አቶ ግርማ በአሁኑ ወቅት በፍጥነት እየሰራን ነው ይላሉ፡፡ በጣም ብዙ ፋብሪካዎች ከአቅማቸው 50 በመቶውን እንኳን እየሠሩ አለመሆኑን፣ ይህንን ከፍ ለማድረግ መሠራት እንዳለበት፣ ግን አሁንም እየተበጣጠሱ የሚሠሯቸው ሥራዎች እንዳሉ፣ አንዳንድ ቦታዎች ላይ በክላስተር በጋራ አንድ መሠረተ ልማት ለማስተካከል ዕቅድ አድርገው እየሠሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሌላው አስተያየት የሰጡበት ጉዳይ በቢሯቸው ለዳያስፖራውና ለሌላውም የሚሆን 200 የሚሆኑ የቢዝነስ ፕሮጀክቶች ተጠንተው እንዳሉና በሲዲ የሚሰጥ መሆኑን ነው፡፡ በጣም ከተንከባከባችሁንና ከደገፋችሁን በኋላ አሳልፋችሁ ለሌባ ትሰጡናላችሁ የሚለው ላይ ‹‹እኛ ቤት ጉቦ የሚቀበል ያለው እናንተ ሠፈር ጉቦ የሚሰጥ ስላለ ነው›› በማለት ችግሩ የንግድ ኅብረተሰቡም መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በቢሯቸው በኩል ችግሩን ለመቅረፍ ካሜራ እስከማስገጠም መድረሳቸውን ተናግረዋል፡፡

የአቶ ብርሃነ መዋ ምልከታ

በመድረኩ ላይ ሰፋ ያለ ገለጻና አስተያየት የሰጡት የቀድሞ የኢትዮጵያና የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃነ መዋ ናቸው፡፡ አቶ ብርሃነ በዕለቱ በንግድ ምክር ቤቱ በምክትል ዋና ጸሐፊው አቶ ሺበሺ ቤተ ማርያም የቀረበውን የንግድ ምክር ቤቱ እንቅስቃሴ የተመለከተ ገለጻ፣ በጣም ያስደሰታቸው መሆኑን በመጥቀስ ነበር የጀመሩት፡፡ 

ከሩቅ ሲያዩት ንግድ ምክር ቤቱ ጠንክሮ ይሠራል የሚል እምነት አልነበራቸውም፡፡ ሆኖም ንግድ ምክር ቤቱ ጠንካራ ጸሐፊ እንዳገኘ መገንዘባቸውን ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ትኩረት የሚያደርገው አዲስ አበባ ላየነው፣ ስለኢንቨስትመንት ስናወራ ግን፣ አጠቃላይ ኢትዮጵያን የሚመለከት ነው ያሉት አቶ ብርሃነ፣ ስለዚህ አዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ከመስመር ወጥቶ ሌሎቹን አካባቢዎች የሚያሳትፍበት ሥርዓት መፈጠር መቻል እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ አለበለዚያ የሚሰጠው አገልግሎት ቁንፅል እንደሚሆን አስገንዝበዋል፡፡

ሌላው ከታዘቧቸው የጠቀሱት ደግሞ፣ በፊትም ኢሕአዴግ በነበረ ጊዜ በተቻለ መጠን ንግድ ምክር ቤቱን ለመጫን ይፈልግ እንደነበር፣ አሁን አዲስ መንግሥት ከተቋቋመ በኋላ የታዘቡት ንግድ ምክር ቤትን እንደ አጋር አድርጎ አብሮ ከመሄድ ይልቅ፣ ግለሰብ ነጋዴዎችን እንደ አጋር አድርጎ የመሄድ ሁኔታ እንደሆነና ይህ ተቀባይነት እንደማይኖረው የገለጹበት ይገኝበታል፡፡

ይህንንም ሲያፍታቱ ከሽንኩርት ቸርቻሪ ጀምሮ እስከ ባለ ፋብሪካ ድረስ የሚወክለው የንግድ ምክር ቤቱ ስለሆነ፣ ነጋዴውም ራሱ በንግድ ምክር ቤቱ ላይ ኮንፊደንስ እንዲኖረው ማድረግ የሚቻለው ንግድ ምክር ቤቱ አለሁ ብሎ ድምፁን ሊያሰማ ሲችል በመሆኑ ነውም ይላሉ፡፡

አቶ ብርሃነ ዳያስፖራን በተመለከተ የሰነዘሩት ሐሳብም ነበር፡፡ ይህንንም ‹‹ከዛሬ 20 ዓመታት በፊት ቻምበር ኦፍ ኮሜርስና የኢትዮጵያ የግል ኢንዱስትሪዎች ማኅበር እያለሁኝ ኢንቨስት ለማድረግ የሚፈልጉና የሚመጡ በርካታ ዳያስፖራዎች ነበሩ፡፡ አቶ ውብሸት ወርቃለማው ያን ጊዜ ፕሬዚዳንት ነበሩና እሳቸው ጋር ይሄዳሉ፡፡ እሳቸው ብዙ ነገር ለመመለስ ሲቸገሩ ወደ እኔ ሰዎቹን ይመልሷቸዋል፡፡ ሰዎች ምን እንሥራ ብለው ነውና የሚጠይቁት ምን ሊሠሩ እንደሚችሉ ለማስረዳት እሞክራለሁ፤›› ብለዋል፡፡

‹‹አንድ ወር ወይም 15 ቀናት ቆይቶ ከዚያ ያልተለየ ጥያቄ ይዞ ይመጣልና በኋላ ምን እንሥራ ብለው ሲመጡ ጥያቄውን ቀየርኩና ምን ያህል ገንዘብ ይዘሃል ማለት ጀመርኩኝ፤›› የሚሉት አቶ ብርሃነ፣ እነሱ በፊት ከነበረው የኢትዮጵያ ሁኔታ 20 እና 30 ሺሕ ዶላር በጣም ትልቅ መሆኑን ነው የሚገምቱት፣ ያን ጊዜ ግን የመሬት ዋጋ እየናረ የኢንቨስትመንት ዋጋ እየጨመረ የሄደበት ሁኔታ ነበር፡፡ አሁንም እንደዚህ ያሉ ተመሳሳይ ጥያቄ እየጠየቁ እንደሆነ አንስተዋል፡፡ ስለዚህ ይህንን ሊመራ የሚችል ነገር በንግድ ምክር ቤቱ በኩል መዘጋጀት አለበት ብለዋል፡፡

እንደ አቶ ብርሃነ፣ ይህንንም ለማድረግ መጀመርያ ንግድ ምክር ቤቱ ተቋማዊ ችግሩን መፍታት አለበት፡፡ ችግሮችን ከፈታ በኋላ መረጃዎችን ተደራሽ ማድረግ አለበት፡፡ ለምሳሌ ከ25 ሺሕ እስከ 100 ሺሕ ዶላር ማውጣት የሚችሉ ሰዎች ይህንን ሥራ መሥራት ይችላሉ በማለት መረጃውን መስጠት ይኖርበታል፡፡

ከ200 ሺሕ እስከ 500 ሺሕ ዶላር ያላቸው ደግሞ እንዲህ ያለ ሥራ ላይ መሥራት ይችላሉ፡፡ በግለሰብ ደረጃ መሥራት የሚችሉት ደግሞ ይህንን መሥራት ይችላሉ፡፡ ከዚህ በላይ ያለውን ደግሞ በማኅበር በፒኤልሲ መሥራት ይችላሉ ተብሎ ፓኬጅ ቢዘጋጅ በጣም ጠቃሚ ይሆናል ብለዋል፡፡

‹‹እኔ ወክዬ የመጣሁት አንድ የፋርማሲዩቲካል ኩባንያ እዚህ ማምረት ፈልገን ነው፤›› ያሉት አቶ ብርሃነ፣ ለዚህ ኩባንያ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ለማግኘት ሒደት ላይ መሆናቸውን፣ እዚህ ለመድረስ ግን አሜሪካ ሆነው ሁለት ዓመት እንደፈጀ አመልክተዋል፡፡

ሁሉን አጥንቶ መረጃ የሚሰጥ አካል ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ አቶ ግርማም ይህንን ሐሳብ ተጋርተዋል፡፡ ንግድ ምክር ቤቱ ለዳያስፖራው የሚሆን መረጃ በመስጠት ሁነኛ ተቋም ነው ይላሉ፡፡

‹‹ከውጭ የሚመጣ ሁሉ ዕውቀት አለው ማለት አይደለም፤›› በማለት የጠቀሱት አቶ ብርሃነ፣ ገንዘብም ያን ያህል አለው ማለት አይደለም፡፡ ግን ገንዘቡን አጋጭቶ ብዙ መሥራት ይችላል ብለዋል፡፡ ይኼ ደግሞ ለሁላችንም የሚጠቅም ነገር ይሆናል፡፡ ከውጭ የመጣችሁ ደግሞ በግለሰብ ደረጃ ኢንቨስት ማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ በጋራ ሆናችሁ ኢንቨስት ማድረግን ማሰብ ይኖርባችኋል ብለዋል፡፡  በጣም ብሩህ ተስፋ ያለበት አገር ላይ ነው የመጣነው፡፡ እኔ በጣም ደስ ብሎኛል በማለት ሐሳባቸውን ቋጭተዋል፡፡

ወ/ሮ መሰንት በአቶ ብርሃነ ገለጻ፣ መደመማቸውንና ንግድ ምክር ቤታቸው ጠንካራ የሆኑ ቦርድ አባላት እንዳሉት ገልጸዋል፡፡ ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት በግራ በቀኝ ችግሮች ምክንያት ትንሽ መንቀሳቀስ እንዳልቻሉና ትንሽ ድክመት እንዳለ ማየታቸውን፣  አሁን አጠቃላይ ሪፎርም መደረጉን፣ ችግሮች እየተቀረፉ መሆኑንና መረጃን ማሠራጨት ላይ ድክመት እንደነበር አልሸሸጉም፡፡

መንግሥት ከተቋማት ጋር የሚያደርገው ግንኙነት ቀጣይነት እንዲኖረው ማድረግ አስፈላጊነት ላይ አስምረውበታል፡፡ ከግለሰቦች ጋር የሚያደርገው ግን ቀጣይነት የለውምና መንግሥት ከግለሰብ ነጋዴዎች ጋር ከሚያደርገው ግንኙነት ይልቅ ከተቋማት ጋር ያድርግ በማለት የአቶ ብርሃነን ሐሳብ ተጋርተዋል፡፡

ይህ ትልቅ ተቋም መንግሥትን ለመርዳት የሚያደርገው ጥረት በተቋም ደረጃ ቢሆን ቀጣይነት ይኖረዋል የሚለውን እምነታቸውንም አንፀባርቀዋል፡፡

ግንኙነቱ እንዴት ይቀጥል?

በዕለቱ ከተለያዩ አስተያየት ሰጪዎች ከተንፀባረቁ ሐሳቦች መካከል አንዱ አሁን ተጀመረው ግንኙነት እንዴት ይቀጥል የሚለው ነበር፡፡ ከዳያስፖራው ጋር የተፈጠረው ግንኙነት መቋረጥ የሌለበት መሆኑን ወ/ሮ መሠንበት ተናግረዋል፡፡

የመሬት ጉዳይን በተመለከተም ለመንግሥት ምክረ ሐሳብ ማቅረባቸውን አክለዋል፡፡ እንደ ኢትዮጵያዊ ኢንቨስት ለማድረግ በምንንቀሳቀስበት ጊዜ የተለያዩ ፖሊሲዎች በተለያዩ ክልሎች አሉና የፖለቲካ መዋቅሩ መስተካከል አለበት በሚሉ ጉዳዮች ላይ ለተነሱ ጥያቄዎች ወ/ሮ መሰንበት፣ የኢኮኖሚው ዕድገት በሚመጣበት ጊዜ ለውጡ ራሱ ይመጣል የሚል እምነታቸውን አንፀባርቀዋል፡፡

 ወደ ኢኮኖሚ በምንመጣበት ጊዜ ሁሉንም ጋብዞ ኢንቨስትመንትን ቀላል ማድረግ ዕድገት ያመጣል፡፡ ይህንን የምንረዳበት ሁኔታ ይመጣል፡፡ እየቀለለም ይሄዳል ይላሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ሁላችንም ተስፋ መቁረጥ የለብንም ያሉት ወ/ሮ መሰንበት፣ የትኛውም ኢትዮጵያዊ የትም ቦታ ሄዶ ቢሠራ ክልሉ ተጠቃሚ እንደሚሆን ማስገንዘብ ያስፈልጋል ይላሉ፡፡

የውጭ ዜግነት ያለው ኢትዮጵያዊ የባንክ አክሲዮን መግዛት ያለበት በውጭ ምንዛሪ መሆንን በተመለከተ እሳቸው አማራ ባንክ እያሉ የገጠማቸወን በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡ በወቅቱ ዳያስፖራ አክሲዮን መግዛት የሚችለው በውጭ ምንዛሪ ነው የሚለውን ያወቅነው አክሲዮን ከሸጡ በኋላ እንደሆነ፡፡ ይህ ሕግ ሊሻሻል ይችላል ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል፡፡ የንግድ ምክር ቤቱ የቦርድ አባል የሆኑ አቶ በቀለ ፀጋዬ በዕለቱ በአጠቃላይ የቢዝነስ እንቅስቃሴዎች ላይ ያላቸውን ሐሳብ ሰንዝረው መሆን አለበት ያሉትንም ሐሳብ አቅርበዋል፡፡

ከዚህ በላይ ግን ዳያስፖራው ማኅበረሰብ አለ ብሎ ላነሳቸው ችግሮች የሰጡት ምላሽ ነበር፡፡ እንደ እሳቸው ምልከታ፣ አንዳንድ ፖሊሲዎች ለዳያስፖራው አመቺ ያለመሆን ጉዳይ በሒደት እየተቃለሉ ይሄዳሉ፡፡ ባለፉት ሦስትና አራት የለውጥ ዓመታት ተረጋግቶ እንደዚህ ዓይነት ሥራ በመሥራት ላይ አልነበርንም ያሉት አቶ በቀለ፣ መንግሥት ህልውና ማስከበር ላይ ነበርና ያተኮረው እኛም ግፊት ለመፍጠር የሚያስችሉ ሁኔታዎች አልነበሩንም ወደፊት ይህ ሁኔታ ይሻሻላል የሚል እምነት አለ ብለዋል፡፡ የዳያስፖራው ኢንቨስትመንት ይዘት ምን መሆን አለበት? የሚለው ላይ አቶ በቀለ፣ ‹‹ብዙ የኢንቨስትመንት ካፒታል ከሌለ ውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሼር ኩባንያና በፒኤልሲ ደረጃ በጋራ የሚሠሩበት ሁኔታ ላይ ማተኮር ጠቃሚ ነው፤›› ይላሉ፡፡     

በተለይ ልጆቻቸው አገር ላይ እንዲሠሩ ማድረግ እንዲችሉ መግፋት ያስፈልጋል በማለትም፣ በጋራ ስንሠራ፣ ልዩነቶቻችንን አጥፍተን ኢትዮጵያን ማዕከል አድርገን ብዙ ነገር መለወጥ ይቻላል ብለዋል፡፡

በዕለቱ ከቀረቡ ጥያቄዎች የብሔራዊ ባንክን መመርያ በተመለከተ በሰጡት ምላሽ ደግሞ በንግድ ምክር ቤቱ በኩል አጀንዳ ተይዞ እየተሠራበት መሆኑን ነው፡፡ ከዳያስፖራዎች የሚገኝ ከፍተኛ ሀብት ኢኮኖሚውን የሚያነቃቃ በመሆኑና ለብዙ ሰዎችም እንጀራ ስለሚሆን ለእነሱ የሚሆን የንግድ ድጋፍ አገልግሎት ለመስጠት ንግድ ምክር ቤቱ ዝግጁ መሆኑን የገለጹት ወ/ሮ መሰንበት፣ የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤትና የዳያስፖራና ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ገለጻና ትውውቅም በርካታ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ፋይዳ አለው ብለው እንደሚያምኑ አክለዋል፡፡

የዚህ ግንኙነት መዳበርና ጠንካራ ትስስር  የአገራችንን የወደፊት ምጣኔ ሀብት ራዕይ ለማሳካት የተሻለ ዕድልና እርሾ ይሆናል ብለዋል፡፡

ዳያስፖራው በኢኮኖሚ ልማት ውስጥ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዲኖረው ምቹ ፖሊሲ እንዲኖር የበኩላቸውን ሚና እንደሚጫወቱ፣ በተለያዩ አገሮች ለሚኖሩ ዳያስፖራ ኢትዮጵውያን ወደ አገራቸው መምጣትም ሳያስፈልጋቸው ባሉበት ሆነው፣ ትርፋማ በሆነና ደኅንነቱ በተጠበቀ ኢንቨስትመንት ላይ የሚሰማሩበትን ዕድል የሚፈጥርላቸው ተመራጭ አሠራር እንዲኖር በርትተው እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

ዳያስፖራው እጅግ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ በውጭ አገሮች ባንኮች ውስጥ በቁጠባ መልክ ቢያስቀምጥም፣ ይህ ነው የሚባል ወለድ እያገኘበት እንዳልሆነ የሚታይ ነባራዊ ሀቅ መሆኑንም ጠቅሰው፣ በኢትዮጵያ ትርፋማ ሊያደርግ የሚችል የኢንቨስትመንት ዕድል መፍጠር ከተቻለ፣ ገንዘባቸውን ከባንክ አውጥተው በአገራቸው ኢንቨስት ሊያደርጉ የሚችሉ በርካታ የዳያስፖራ ባለሀብቶችን መሳብ ይቻላል ብለን እንደ ንግድ ምክር ቤት እናምናለን ብለዋል፡፡

ይህንን ውጤታማ ለማድረግ ዳያስፖራው በስፋት በሚኖርባቸው አገሮች ባሉ ኤምባሲዎችና ንግድ ምክር ቤቶች፣ እንዲሁም በአገር ቤት ካሉ ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት መሥራት አስፈላጊ እንደሆን ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች