Wednesday, March 29, 2023

የሰላም ተስፋና በአዋሳኝ አካባቢዎች የቀጠለው ጦርነት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

መንግሥት የመጀመርያውን የህልውና ዘመቻ መጠናቀቅ ማስታወቁ፣ በአንድ በኩል ከፍተኛ የሰላም ተስፋ የፈነጠቀ ቢሆንም፣ በሌላ በኩል ግርታ የፈጠረ ነበር፡፡ የአገር መከላከያ ሠራዊት ሕወሓትን በወረራ ከያዛቸው የአፋርና የአማራ አካባቢዎች ጠራርጎ የማስወጣቱ ዘመቻ ገፍቶ ትግራይ ክልል ወሰን ላይ ሲደርስ መጠናቀቁ ተሰምቷል፡፡ የሕወሓት ህልውና እስኪያከትም የሚቀጥል ይመስል የነበረው ይህ የሠራዊቱ ዘመቻ፣ ትግራይ ክልል ወሰን ላይ የመቆም ውሳኔ፣ የመጀመርያው ዙር የህልውና ዘመቻ መጠናቀቅ የተበሰረበት ነበር፡፡

በወቅቱ ሁኔታው ግርታና መደናገር የፈጠረባቸው ኢትዮጵያውያን በርካታ ቢሆኑም፣ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ግን ዕርምጃውን አዎንታዊ ተስፋ በሚያንፀባርቅ መንገድ ነበር የተቀበለው፡፡ መንግሥት ዘመቻውን ጋብ ማድረጉ ለሰላማዊ ንግግር በር ከፋች ሁኔታ መሆኑ፣ በቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት ጭምር ሲነገርለት ከርሟል፡፡ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ የአፍሪካ ኅብረትና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ዕርምጃው በጎ መሆኑን በይፋ ገልጸዋል፡፡ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ስለሰላም በጎ ተስፋውን በገለጸ ማግሥት ግን፣ የትግራይ ክልል ከአማራና ከአፋር ክልሎች ጋር በሚዋሰንባቸው አካባቢዎች የግጭትና የጦርነት ዜናዎች መሰማት ጀምረዋል፡፡

በተለይ ሦስቱ ክልሎች ለሚጋሯቸው የወሰን አካባቢዎች ቅርብ የሆኑ የመረጃ ምንጮች፣ አሁንም በአካባቢዎቹ ግጭቶች መቀጠላቸውን ይጠቁማሉ፡፡ ይህን ደግሞ የመንግሥትም ከፍተኛ አመራሮች እያረጋገጡት ናቸው፡፡ የጦሩ ከፍተኛ ባለሥልጣናትና የመንግሥት አመራሮች ሕወሓት ጦርነትና ትንኮሳ መቀጠሉን በተደጋጋሚ እየተናገሩት ነው፡፡ አንዳንዶቹ ንግግሮች ማስጠንቀቂያ አዘልና ዳግመኛ ጦርነቱ ሊጀምር የሚችልበት ዕድል መኖሩን ጭምር የሚያስረግጡ ናቸው፡፡

የአገር መከላከያ ሠራዊት ምክትል ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ፣ ጦርነቱ አለመጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡ ለብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያው በሰጡት ቃለ መጠይቅ፣ ‹‹ጦርነቱ የሚጠናቀቀው ፀረ ሰላምና ፀረ ኢትዮጵያ የሆነው የሕወሓት ኃይል ከእነ አካቴው ሲደመሰስ ነው፤›› ሲሉ ጄኔራል አበባው ተናግረዋል፡፡ እሳቸው ይህን ከመናገራቸው ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ ለሕወሓቶች ጠንከር ያለ ማስጠንቀቂያ አዘል መግለጫ ሰጥተው ነበር፡፡ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፣ ‹‹ሕወሓቶች ስህተት መሥራታቸውን ከቀጠሉና በኢትዮጵያ ላይ ዳግም ትንኮሳ ከፈጸሙ፣ ያን ጊዜ መጨረሻቸው ይሆናል፤›› በማለት ነበር ለሕወሓት ማስጠንቀቂያ የሰጡት፡፡

ሁለቱ የሠራዊት ከፍተኛ አዛዦች ብቻም ሳይሆኑ ጦርነቱ አለማብቃቱንና ሕወሓት ጥቃት መፈጸሙን ከቀጠለ፣ መንግሥት ከባድ አፀፋ ሊወስድ እንደሚችል ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ መንግሥት የሕወሓት ኃይልን ትግራይ ገብቶ የመደምሰስ ዘመቻ ያልከፈተው ከዚህ ቀደም ከነበረው ሁኔታ ልምድ በመውሰድ ተገቢ ያልሆነ ዋጋ ላለመክፈልና ለትግራይ ሕዝብ ወደ ሰላም እንዲመጣ ተጨማሪ ዕድል ለመስጠት መሆኑን በተደጋጋሚ ገልጿል፡፡

መንግሥት ይህን ቢልም የሕወሓት ኃይል ዳግመኛ ጥቃት ከከፈተ በአፀፋው ዘመቻውን ለመቀጠል እንደሚገደድ ከመናገር ተቆጥቦ ግን አያውቅም፡፡ አሁን በተጨባጭ በመሬት ላይ መለስተኛ ጦርነትና ግጭት መኖሩን የአካባቢዎቹ ምንጮች ያረጋግጣሉ፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ ወደ ከባድ ደም መፋሰስ የሚያስከትል ጦርነት እንዳይሸጋገር የሚያሠጋ መሆኑ ይነገራል፡፡

በወልዲያ ከተማ ነዋሪ የሆነውና ትኩስ ግጭት የሚካሄድባቸውን የወሰን አካባቢዎች በቅርበት የሚከታተለው ወጣት ቴዎድሮስ አያሌው፣ ጦርነቱ አለመቆሙንና ግጭቱ መቀጠሉን ይናገራል፡፡ ራሱን የማኅበረሰብ አንቂ የሚለውና የሕወሓት ኃይል ለአምስት ወራት ወልዲያን በወረረበት ወቅት በከተማዋ ወጣቱን የማስተባበር ሥራ ሲያከናውን የቆየው ቴዎድሮስ፣ በራያም ሆነ በዋግ ህምራ ግንባር የሕወሓት ጥቃት ተጠናክሮ መቀጠሉን ነው የተናገረው፡፡

በራያ በኩል የገና በዓል ዕለት የሕወሓት ኃይል ጥቃት ከፍቶ ከአላማጣ በ26 እና 27 ኪሎ ሜትር፣ ከቆቦ ደግሞ በ15 ኪሎ ሜትር አማካይ በሆነ ርቀት ላይ የሚገኙትን የዋጃና ጥሙጋ አካባቢዎችን ዳግም እንደተቆጣጠረ ቴዎድሮስ ያስረዳል፡፡ ሕወሓት በዋግ ህምራ በኩልም ወረራውን በመግፋት ሁለት ወረዳዎችን መቆጣጠሩን ይገልጻል፡፡ ቆቦ ከተማ አሁን በአሥር ኪሎ ሜትሮች ርቀት በሕወሓት ኃይል መከበቧንም የወልዲያው ወጣት ለሪፖርተር አስረድቷል፡፡

‹‹በቅርብ ሰሞን ከአላማጣ ከተማ ብዙ አሰቃቂ ዜና እየሰማን ነው፡፡ ሕወሓቶች በተለየ ሁኔታ የአማራ ተወላጆችን እየለዩ በማሰርና ወዳልታወቀ ቦታዎች እየወሰዱ መሆናቸውን፣ አምልጠው ወደ ወልዲያ ከመጡ ሰዎች አረጋግጫለሁ፡፡ በአላማጣና በአካባቢው ብዙዎች ሞተዋል ወይም የደረሱበት አይታወቅም፡፡ በአካባቢው ከ500 በላይ ወጣቶችን ማፈሳቸውንና ያለው ሁኔታ አስቸጋሪ መሆኑን አረጋግጫለሁ፤›› ሲል ነው ወጣት ቴዎድሮስ የሚናገረው፡፡ 

ቴዎድሮስ ሲቀጥልም ሕወሓት ዳግም ግጭትና ወረራ በከፈተባቸው የወሰን አካባቢዎች የነዋሪዎች ሁኔታ በአስከፊ ደረጃ ላይ ነው ይላል፡፡ በእነዚህ ትኩስ ግጭት ባሉባቸው ግንባሮች ደጋግሞ የመዘዋወር ዕድል እንደገጠመውና ሁኔታዎችን በአካል ተገኝቶ መመልከት መቻሉንም ያስረዳል፡፡

በእነዚህ ግጭቶች ሲሳተፉ የተማረኩ የሕወሓት ወታደሮችን ማግኘቱንና ከብዙዎቹ ጋርም በቅርበት መነጋገሩን፣ ‹‹ብዙዎቹ ወደ ግጭቱ ለምን እንደገቡ ስጠይቃቸው የሚነግሩኝ ነገር ተገደን ነው የሚል ነው፡፡ ብዙዎቹ የራሳቸውን ወይም የቤተሰባቸውን ሕይወት ለማትረፍ ሲሉ ተገደው የሕወሓትን ጦር እንደሚቀላቀሉ ነው የገለጹልኝ፤›› ብሏል፡፡

‹‹የትግራይ ሕዝብ ምርጫ ለሌለው የግዳጅ ሕይወት ተትቷል›› ሲል ይናገራል፡፡ ‹‹ትግራይ አልተገነጠለችም፣ ነፃም አገር አይደለችም፡፡ ትግራይ አሁንም ቢሆን የኢትዮጵያ አካል ናት፡፡ በዚህ የተነሳ የኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ ሁላችንም አቅማችንን በማስተባበር የትግራይ ሕዝብን ነፃ የማውጣት ከባድ ኃላፊነት አለብን፡፡ የማያባራው የሕወሓት ጠብ ጫሪነትና ጦርነት ለትግራይ ሕዝብ፣ ለአማራ፣ ለአፋርም ሆነ ለኢትዮጵያ በእኩል ደረጃ አደጋ የሚደቅን ሥጋት ነው፤›› በማለት ነው ቴዎድሮስ አስተያየቱን ያጠቃለለው፡፡

ሌላው አስተያየት ሰጪ በወልቃይት ግንባር በአሁኑ ወቅት ያለውን ሁኔታ በቅርበት የሚከታተለው ጸሐፊና የፖለቲካ ተንታኝ ሙሉዓለም ገብረ መድኅን በበኩሉ፣ ‹‹ሰላም በአካባቢው በዘላቂነት የሚሰፍነው የወልቃይት ጉዳይ በሕጋዊ መንገድ ሲፈታ ብቻ ነው፤›› በማለት ይናገራል፡፡ ጦርነቱ ቆሟል ስለተባለ ብቻ የአካባቢው ሰላም ዋስትና አለማግኘቱን የሚያስረዳው ሙሉዓለም፣ የወልቃይት አማራ የማንነት ጥያቄ መከበር የአካባቢውን ችግር እንደሚፈታው ያስረዳል፡፡

መቀመጫውን ጎንደር ያደረገው ሙሉዓለም በወልቃይት ስለሚካሄደው ጦርነት በቅርበት እንደሚያውቅና ባደረጋቸው የተለያዩ ጉዞዎች ሁኔታውን መመልከት መቻሉን ይናገራል፡፡ ‹‹ሕወሓት አሁን በሱዳን በኩል መተላለፊያ ኮሪደር ለማስከፈት ከባድ ጦርነት ጀምሯል፡፡ በተከዜ በኩልና በወልቃይት ግንባር በሞርታርና በመድፍ የታገዘ ጦርነት ከፍቷል፡፡ ወደ ኤርትራ ጭምር የመድፍ ጥቃት ሰንዝሯል፤›› በማለት የሚናገረው ሙሉዓለም፣ ሕወሓት ከጠብ ጫሪ ባህሪው እንደማይታቀብ ነው የሚገልጸው፡፡

‹‹ቡድኑ ግጭት ካልቀሰቀሰና ጦርነት ካላደረገ መኖር አይችልም፡፡ ከራሱ እወክለዋለሁ ከሚለው ሕዝብ ጭምር የቅቡልነት ጥያቄ እንዳይነሳበት፣ ሌሎች ችግሮችን ለመሸፋፈን ሲል ጦርነት መክፈትን እንደ ዋነኛ ስትራቴጂው ይከተላል፤›› ሲል የሚገልጸው ሙሉዓለም፣ አሁን በወልቃይት በኩል የሚካሄደው ግጭትም ሆነ የወልቃይት ጥያቄ ሌላ ቀጣናዊ የሆነ የጂኦ ፖለቲካ ቀውስ እንዳይፈጥር እንደሚያሠጋው ያስረዳል፡፡

‹‹ሕወሓት ያለ ግጭት መኖር አይችልም፡፡ አሁን በተለይ በየመን፣ በሊቢያ፣ በሶሪያና በሌሎች አገሮች የግጭት አዙሪት ለማትረፍ ሲራወጡ የሚታዩ ዓለም አቀፍ የግጭት ትርፍ ፈላጊ ኃይሎች ከሕወሓት ጀርባ ለመሠለፍ ሲያሰፈስፉ ይታያሉ፡፡ ግጭቱ በዚሁ ከቀጠለ በውጭ ጣልቃ ገቦች እየታገዘ አድማሱ እየሰፋ ከሄደ በወልቃይት ግንባር የሚታየው ግጭት ቀጣናዊ የጂኦ ፖለቲካ ቀውስ የማይሆንበት ምክንያት የለም፤›› ሲል ነው ሙሉዓለም የሁኔታ ትንተና የሚያቀርበው፡፡

በአጠቃላይ እስካሁን በተካሄደው ጦርነት ሕወሓት ከ400 ሺሕ የሚበልጥ ሠራዊት መስዋዕት አድርጓል ተብሎ እንደሚገመት የሚጠቅሰው ሙሉዓለም፣ ይህ ሁሉ ውድመት ከደረሰ በኋላም በትግራይ ክልል ተጨማሪ 100 ሺዎችን ለመገበር የጦር ድግስ እንዳለ መረጃ መኖሩን ይገልጻል፡፡

ለአካባቢው ቅርበት አለን የሚሉ ወገኖች ብቻ ሳይሆኑ፣ በትግራይና በአጎራባች ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የሚታይ ግጭት መኖሩን የክልል ባለሥልጣናት ጭምር አረጋግጠዋል፡፡ በወዲያኛው ሳምንት የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አወል አርባ በኦፊሴላዊ የፌስቡክ ገጻቸው ባወጡት መግለጫ፣ የሕወሓት ትንኮሳ መቀጠሉን አስረድተዋል፡፡ አቶ አወል ለትግራይ አዋሳኝ በሆኑ በኪልባቲና በአብአላ አካባቢዎች ሕወሓት በአፋር ላይ ጦርነት ከፍቷል ብለዋል፡፡ አቶ አወል እንደሚሉት፣ ሕወሓት ይህን  የአፋር ዘር ማጥፋት ዘመቻውን ከገፋበት ጠንካራ የአፀፋ ዕርምጃ ክልላቸው ለመውሰድ ይገደዳል፡፡

በትግራይና በአጎራባች ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ግጭት ወይም የግጭት ሥጋት እንዳጠላ መቀጠሉን፣ ከሕወሓት በኩል የሚወጡ መረጃዎችም ያረጋግጣሉ፡፡ የአገር መከላከያ ሠራዊት የመጀመርያ ዙር የህልውና ዘመቻው እንደተናቀቀ መንግሥት ባወጀ ማግሥት፣ የሕወሓት ከፍተኛ አመራሮች ጦራቸውን ከተቆጣጠራቸው የአማራና የአፋር ክልሎች በማስወጣት ወደ ትግራይ የመለሱት በሌላ ግንባር ለሌላ  ዙር ጦርነት ለመዘጋጀት መሆኑን የሚያረጋግጥ ንግግር ሲያሰሙ ተደምጠዋል፡፡ ይህም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሰላም ተስፋ አለ ቢልም፣ በሕወሓት በኩል ግን በተጨባጭ በጦርነቱ የመግፋት ፍላጎት መኖሩን አመላካች ነው፡፡

ስለዚህና ስለቀጠለው ግጭት ሪፖርተር ያነጋገራቸው የቀድሞ የሕወሓት አባል የነበሩት አቶ ሊላይ ኃይለ ማርያም፣ ሕወሓት በሕይወት እስካለ ድረስ በአካባቢውም ሆነ በመላው ኢትዮጵያ ሰላም ለማስፈን እንደማይቻል ነው የሚናገሩት፡፡

‹‹ከ1967 ዓ.ም. ጀምሮ ከሕወሓት ጋር ኖሬያለሁ፡፡ እነዚህ ሰዎች በውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ግጭቶችን በሰላም የመፍታት ጥበብ ኖሯቸው አይቼ አላውቅም፡፡ ሕወሓት በደም የሰከረና በግጭት የሚኖር ኃይል ነው፤›› ሲሉ ነው አቶ ሊላይ የሕወሓትን  ባህሪ ያስረዱት፡፡

አቶ ሊላይ እንደሚናገሩት ከሆነ የአየር ድብደባ ቀጥሏል፣ የእግረኛና የከባድ መሣሪያ ውጊያዎችም በመካሄድ ላይ ናቸው፡፡ ትግራይ ከአፋርና ከአማራ ክልሎች ጋር በሚዋሰናቸው አካባቢዎች ትኩስ ግጭት መኖሩን በተጨባጭ እንደሚያውቁም አቶ ሊላይ ያስረዳሉ፡፡

‹‹ኢትዮጵያ ሕወሓት እስካለ ድረስ ሰላም አታገኝም፡፡ የትግራይ ሕዝብም ቢሆን ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ጋር ተባብሮ ሕወሓትን ከማስወገድ ውጪ ምርጫ የለውም፡፡ የትግራይን ሕዝብና ትግራይን ነፃ ለማውጣት ሁሉም ሊተባበር ይገባል፤›› የሚሉት አቶ ሊላይ፣ ለአካባቢውም ሆነ ለኢትዮጵያ ሰላም መፍትሔው የሕወሓት መወገድ ነው ይላሉ፡፡

በቅርቡ የኢትዮጵያ መንግሥት የወሰደው የመጀመርያው የህልውና ዘመቻን የማጠናቀቅ ዕርምጃ፣ ከዓመት በላይ ያስቆጠረውን ሦስት ክልሎችን ያዳረሰውን የትግራይ ጦርነት በሰላም ለመቋጨት በር የሚከፍት አጋጣሚ እንደሆነ ሲገለጽ ሰንብቷል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ የሰላም ተስፋ ብልጭ ባለ ማግስት ትኩስ ግጭትና ጦርነት በአንዳንድ አዋሳኝ አካባቢዎች መስፋፋቱ እየተነገረ ነው፡፡

ይህ ሁኔታ ደግሞ የትግራይ ጦርነት ለማክተም ገና ብዙ መንገድ እንደሚቀረው አመላካች ሆኖ ነው የታየው፡፡ ሰሞኑን በብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያው ቃለ መጠይቃቸው የተደመጠው ጄኔራል አበባው በሰጡት አስተያየትም ቢሆን፣ በወሰን አካባቢዎች የሚታየው ግጭት ወደ ከፍተኛ ጦርነት ሊሸጋገር የሚችልበት ዕድል መኖሩን የሚያረጋግጥ ነው፡፡

‹‹የመጀመርያውን ዙር የህልውና ዘመቻ አጠናቀናል፡፡ የመጀመርያ ዙር ስንል ደግሞ ቀጣይ ዙር ዘመቻ ይኖረናል ማለታችን ነው፤›› በማለት ነው የተናገሩት ጄኔራል አበባው፡፡ ይህ ደግሞ ግጭቱ ወደ ከባድ ጦርነት የሚያድግበት ዕድል መኖሩን ጠቋሚ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -