Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልጥንታዊ የከተማ ገጽታን የሚያስታውሱ ሥፍራዎች ደኅንነት እስከምን?

ጥንታዊ የከተማ ገጽታን የሚያስታውሱ ሥፍራዎች ደኅንነት እስከምን?

ቀን:

ታሪካዊ ይዘት እንዳላቸው በቀዬው የተገኙ ሁሉ ምስክር ናቸው፡፡ የቤት አሠራራቸው፣ የመንገድ፣ የቀለም ቅብና አኗኗራቸው ያለፈውን መስተጋብር የሚያሳዩ ናቸው፡፡

በአዲስ አበባ ሕዝባዊ አኗኗርን ከሚያሳዩ ክፍለ ከተሞች መካከል አራዳ ክፍለ ከተማ አንዱ ነው፡፡ ዶሮ ማነቂያ፣ እሪ በከንቱ፣ ራስ መኰንን ድልድይ ሰፈሮችና ሌሎችም ታሪካዊና ትውፊታዊ አካባቢዎች ከሆኑት ይጠቀሳሉ፡፡ በተለይም የራስ መኰንን ድልድይን ተንተርሶ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አምስተኛ በር በሚያስኬደው የልዕልት ተናኘ ወርቅ ኃይለሥላሴ መንገድ ግራና ቀኝ የሚገኙት ከጥንታዊ የከተማዋ ድምቀቶች ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

 ከራስ መኰንን ድልድይ ወደ አፍንጮ በር የሚያስወጣው መሄጃ ያሉ አንዳንድ ቤቶች ዕድሜ ጠገብና በታሪክ የሚጠቀሱ አባቶች የኖሩባቸው ናቸው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ከእነዚህ ቤቶች መካከል አንዱ የፊታውራሪ ተሠራ ረታ ነው፡፡ እኚህ አርበኛ በጣሊያን ወረራ ወቅት ለፈጸሟቸው የጀግንነት ተግባራት በቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ የተሸለሙትን ቤት ታሪክ ያወሳል፡፡

መዲናዋ የራስ መኰንን ድልድይን በመሥራት ንጉሡ ለአባታቸው ማስታወሻነት መሰየማቸው፣ ከድልድዩ ገባ ብሎ ወደ አፍንጮ በር በሚወስደው መንገድ በስተቀኝ ላይ የተፈጥሮ ውኃ ምንጭ አናት ላይ የአባታቸውን ሐውልት ለታሪክ ተቀምጧል፡፡

ከምንጩ አለፍ ሲባል ደግሞ ፒያሳና ስድስት ኪሎን የሚያገናኘው ንጉሡ ያሠሩት ሰባ ደረጃ አለፍ ብሎ ያለውን መሬት ለፊታውራሪ ተሠራ ረታ መሸለማቸውን ‹‹ዳጉ›› የሥዕል ዓውደ ርዕይ መክፈቻ ላይ የመድረክ አጋፋሪው አቶ ሚፍታህ ዘለቀ ገልጸዋል፡፡

ፊታውራሪው በሥፍራው ከሠሯቸው በርካታ ቤቶች መካከል የኖሩበት የአሁኑ ጉራምዓይኔ የሥነ ጥበብ ማዕከል  አንዱ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ሚፍታህ፣ በዚህ ታሪካዊ ሥፍራ ከሁለት አሠርታት በላይ ሠዓሊያን እየሠሩበትና ለመኖሪያ ቤትነት እየተጠቀሙበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የፊታውራሪ ተሠራ ረታ መኖሪያ ቤት በ1936 ዓ.ም. የተገነባ ሲሆን፣ ዘንድሮ 78 ዓመት ይሆነዋል፡፡ ነገር ግን ይህ የአዲስ አበባ ነባር ቤት ከወንዞች ዳርቻ ልማት ጋር በተያያዘ ካለፉት ዓመታት ወዲህ የመፍረስ አደጋ አንዣቦበታል፡፡ በሥፍራው የተጋረጠውን አደጋ የሥነ ጥበብ ማዕከሉን ቤተሰቦች ‹‹ዳጉ›› (ውይይት) ማድረግ እንዳለበት፣ ጉዳዩም ከቤት ጋር ብቻ ሳይሆን ከአካባቢያዊ ታሪካዊነት ጋር ተያይዞ ዘርፈ ብዙ መነቃቃት እንዲፈጠር በማዕከሉ የሚሠሩ ሠዓሊያን ጥረታቸውን ቀጥለዋል፡፡

ማዕከሉ የምድር ቤት ያለው ሲሆን፣ በቤቱ ውስጥ ከሚሠሩት ሠዓሊያን ባሻገር ሌሎች የኪነ ጥበብ ዘርፎች ማለትም ገጣሚያን፣ ጸሐፊያን፣ ሙዚቀኞችን የቴአትርና የፊልም ባለሙያዎች፣ አርክቴክቶችና ሌሎች የጥበብ ባለሙያ የሆኑትን ያካተተ ‹‹የአዲስ አበባ የሥነ ጥበብ ጎዳና›› ለማድረግ ‹‹ዳጉ›› (ውይይት ምክክር) እንዲጀመር የመነሻ ሐሳብ መቅረቡን አቶ ሚፍታሕ አብራርተዋል፡፡

በማዕከሉ ለሁለት አሠርታት የኖረው ሠዓሊ ለይኩን ናሁሠናይ እንደተናገረው፣ የቤቱን ታሪካዊነትና ጥንታዊነት በተጨማሪ ሠዓሊያን ወደ ሥዕል ሥራ ሲገቡ መንደርደሪያቸው የሚያደርጉት እንደ ፊታአውራሪ ተሠራ ረታ ያሉ መኖሪያ ቤቶች ዓይነት ነው፡፡

መንደሮቹ የሕይወት፣ ታሪክ፣ ጥበብ፣ ዕውቀት መገኛ መሆናቸውን የጠቆመው ሠዓሊ ለይኩን፣ የዓለም አገሮች ላይ የጥበብ መንደሮች እንዳሉ ሁሉ በኢትዮጵያ ራስ መኰንን ድልድይ አካባቢን የሥነ ጥበብ መንደር ማድረግ ቢቻል የከተማዋ ታሪካዊ ገጽታ የሚመጣ መሆኑን ያስረዳል፡፡

የሥነ ጥበብ ሥፍራ ቢሆን ይበልጥ ተመራጭ መሆኑን የገለጸው ሠዓሊው፣ ሥዕል፣ ሙዚቃ፣ ግጥምና ሌሎችም የሥነ ጥበብ ዓይነቶችን በማከል የሚታይና የሚጎበኝ ሥፍራ ማድረግ እንደሚቻል ሐሳቡን ያጋራል፡፡

‹‹የንሥሐ አባቱ ስለአካባቢው ሲገልጹለት፣ ‹እውነትም ገዳም ውስጥ እየኖርክ ነው፤›› እንዳሉት፣ የገለጸው ሠዓሊው፣ ‹‹ናስ አርት ገዳም›› በማለት ለረዥም ጊዜያት በስያሜው እንዲጠቀሙበት ያደረጋቸው የቤቱ ስፋት፣ ወንዝ ዳር መሆኑ፣ በዛፎች የመከበቡ፣ የተመስጦ ሥፍራ በመሆኑ እንደሆነ አውስቷል፡፡

ተመስጦ ከመንፈሳዊ (ከቤተ እምነት) ሥፍራዎች በተጨማሪ የጥበብ ሰዎች ማለትም የሠዓሊዎች፣ ሙዚቀኞችና ገጣሚዎች የሚጠቀሙበት ሲሆን፣ የራስ መኰንን ድልድይ አካባቢ ለተመስጦ የተቸሩ ናቸው ሲል ያብራራል፡፡

የጉራምዓይኔ የሥነ ጥበብ ማዕከል ሕፃናት ሥዕል የሚማሩበት፣ መጽሐፍ የሚያነቡበት፣ ስለ ሥነ ጥበብ ምክክር የሚደረግበትና የአገር ውስጥና የውጭ እንግዶች ሥፍራውን የሚጎበኙበት መሆኑን ሠዓሊው ያብራራል፡፡

ረዥም ዓመታት የኖረው የፊታአውራሪ ቤት ታሪካዊ እንደሚያደርገው  የሥፍራውን አስፈላጊነት ያስረዳል፡፡

የወንዞች ዳርቻ ፕሮጀክት ከፒያሳ ወደ ስድስት ኪሎ መውጫ መንገድ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ይፈርሳል የሚባል ጭምጭምታዎች እንዳሉ፣ ቤቱ ከፕሮጀክቱ ጋር የሚተሳሰርበት መንገድ ቢኖር መልካም መሆኑን ሠዓሊው ይጠቁማል፡፡

አካባቢው ገብረ ክርስቶስ ደስታ፣ መስፍን ሀብተ ማርያም የኖሩበት ሥፍራ መሆኑን የገለጸው ሠዓሊው፣ ሁሉንም አዲስ አድርጎ ከመገንባት ይልቅ ያለፈውን ከአሁኑ ጋር ማስተሳሰር የሚቻልበት ሁኔታ ቢመቻች ይላል፡፡

ማዕከሉ የወንዞች ዳርቻ ፕሮጀክት አካል ማድረግ ቢቻል፣ ማዕከሉ ብቻ ሳይሆን አጠገቡ የሚገኙ ቤቶችም የዚሁ አካል ለማድረግ ቢሞከርም የተሻለና ታሪካዊ ገጽታ ያለው ሥፍራ ማድረግ እንደሚቻልም ያስረዳል፡፡ እነዚህ ጥንታዊ ሥፍራዎችን በሙዚቃ፣ በግጥም፣ በሥዕልና በድርሰት የተሞካሹ መሆኑን ያስረዳው ሠዓሊው፣ ሙዚቀኛ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) የሙዚቃ አስታውሷል፡፡

ከመኰንን ድልድይ ከእንጨት ፎቁ በላይ

ሲመሽ እንገናኝ

መጣሁ አንቺን ብዬ ሳይደክመኝ ዕርምጃው

በሰባ ደረጃው…

ሠዓሊ ለይኩን እንደተናገረው፣ የቀድሞ የአካባቢውን ወጣቶች ትውስታ በዛሬው እንዲቃኙት ዕድል የሚከፍት ሥፍራ ነው፡፡ ሙዚቀኞች በዚሁ መልኩ ታሪካዊና ጥንታዊ ሥፍራዎች ሲያሞካሹት ሠዓሊያን ደግሞ አካባቢው ያለውን ጥንታዊነትን በሥዕሎቻቸው ያሳዩታል፡፡

የጉራማዓይኔ የሥነ ጥበብ ማዕከል ካለበት ቤት በተጨማሪ የሥፍራውን ታሪካዊነት ይበልጥ በሚያጎሉ ሥዕሎች፣ ሙዚቃ፣ ግጥምና ሌሎችንም የሥነ ጥበብ ዓይነቶች በማከል ለሕዝብ ክፍት የማድረግ ትልም እንዳላቸው ይገልጻሉ፡፡

ነገር ግን በወንዞች ዳርቻ ልማት ከ70 እና ከ80 ዓመት በላይ የሆናቸው ጥንታዊ ቤቶች ከፈረሱ ሥፍራውን እናጠናዋለን የሚል ሥጋት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

ዓርብ ጥር 6 ቀን 2014 ዓ.ም. በጉራምዓይኔ የሥነ ጥበብ ማዕከል ‹‹ዳጉ›› የተሰኘ የሥዕል ዓውደ ርዕዩ መከፈቱ ይታወሳል፡፡ ዓውደ ርዕዩ ከርዕሱ ጀምሮ በዕለቱ ስለአካባቢው መወያየት፣ መነጋገር፣ መረጃ መቀየርና ታሪክን የማሳወቅ ሐሳብ ያዘለ መሆኑን ሪፖርተር በዕለቱ ተገኝቶ ቅኝት አድርጓል፡፡

በዕለቱ የአለ የሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ሠዓሊ አገኘሁ አዳነና የአዲስ አበባ ከተማ ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ምክትል ኃላፊ አቶ ሠርፀ ፍሬ ስብሐት ተገኝተዋል፡፡

አቶ ሠርፀ እንደተናገሩት፣ በሥዕል ዓውደ ርዕይ መገኘት ለቢሮ የተሰጠውን ትልቅ ዋጋ የሚያሳይ ነው፡፡ ከግለሰብ ተጠሪነት በላይ የአዲስ አበባ ባህል ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ስለተከበረ፣ ዋጋ ስለተሰጠው ማዕከሉን ያመሰገኑት አቶ ሠርፀ፣ በመደበኛው ጊዜ ያሉ ውጣ ውረዶች የሚያዩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የከተማ አስተሳሰብ ላይ የዕይታ ጥበባት ዋጋ የት መቀመጥ እንዳለበት፣ ምን ደረጃ ድረስ መድረስ እንዳለበት ጥቂት ሞዴል እንቅስቃሴዎች እየታዩ መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

በከተማ የልማት እንቅስቃሴ ምክንያት የሚገጥመው ችግሮች መኖራቸውን፣ ነገር ግን በሀዳራዊ (በሚያድረው) ምክንያት ማኅደሩ ክብር ያገኛል ብለዋል፡፡

በኪነ ሕንፃና በባለ ታሪኩ ምክንያት ቤቱን ቅርስ የማድረግ እንቅስቃሴ በቶሎ ቢጀመር፣ ቀጥሎ የሚመጣውን ነገር መቋቋም ያስችላል ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ባህል ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ውስጥ የከተማዋ ቅርሶች በሙሉ እንደሚመዘግቡ የገለጹት አቶ ሠርፅ፣ የቅርሶቹንም ደኅንነት እንደሚቆጣጠሩ ተናግረዋል፡፡

ታሪካዊ ቤቱ የተያዘበት ሁኔታ ለሥነ ጥበብ ምቹ መሆኑን፣ ሁሉም የታሪክና የቅርስ ቦታዎች መካነ ጥበብ እንዲሆኑ ለማድረግ ግፊት እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ እንደዚህ ያሉ ቤቶችን ሙዚየም፣ ጋለሪና የጥበብ ሰዎች መኖሪያ ጭምር የማድረግ ትልም እንዳላቸውና ቢሮዋቸውም ይኼንን ለማሳካት ጥረት እንደሚያደርግ ቃል ገብተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

‹‹ደስታ›› የተባለችው አማርኛ ተናጋሪ ሮቦት በሳይንስ ሙዚየም

‹‹እንደ ሮቦት ዋነኛው አገልግሎቴ ውስብስብ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና አሠራሮችን...