Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበጥምቀት በዓል በበጎ አድራጎት የጎሉት ወጣቶች

በጥምቀት በዓል በበጎ አድራጎት የጎሉት ወጣቶች

ቀን:

በጎ አድራጎትን ከበጎ ፈቃድ ጋር አያይዘው የተነሱት ወጣቶች ከጥር 10 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ የክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ተከብሮ የዋለውን የከተራ፣ የጥምቀትና የቃና ዘገሊላ በዓላት ላይ ከፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር በሰላም ተከብሮ እንዲውል አድርገዋል፡፡

በሳሪስ፣ በሃና ማርያም፣ በጀሞ፣ በላፍቶና በሌሎች አካባቢዎች የጥምቀት በዓል አከባበር ሁኔታን እንደቃነው የወጣቶች ሁለገብ ተግባር ጎልቶ ታይቷል፡፡

የርኆቦት መንፈሳዊ ማኅበር ሰብሳቢ አቶ ሳሙኤል ወንደሰን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በየዓመቱ የሚከበረው የጥምቀት በዓል ላይ ቅድመ ዝግጅት በማድረግና ታቦታቱ የሚያርፉበት ቦታዎችን በማስዋብ ማኅበሩ ጉልህ ሚና ተጫውቷል፡፡

ማኅበሩ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ የታቦት ማደሪያ ቦታዎችን በየዓመቱ እንደ አዲስ በመጠገን እያገለገለ እንደሚገኝ የገለጹት ሰብሳቢው ዘንድሮ ብቻ 500 ሺሕ ብር ማውጣታቸውን አስረድተዋል፡፡

ዘንድሮ የፀጥታ ችግር እንዳይከሰት ከተለያዩ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ጋር ተጣምረው መሥራታቸውን፣ ይኼም አንዳንድ ጊዜ የሚነሱ ጥቃቅን ችግሮችን ለመታደግ እንዳስቻላቸው አክለው ገልጸዋል፡፡

ማኅበሩ በተለያዩ ገዳሞች ላይ ለሚገኙት መነኮሳት የአልባሳትና ምግብ ነክ ግብዓቶችን በመሰብሰብ ተደራሽ ማድረጉን አብራርተዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ከሃና ማርያም ቤተ ክርስቲያን ጋር በመተባበር ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚውሉ ምግብና ምግብ ነክ ነገሮችን በመሰብሰብ ተደራሽ ማድረጋቸውን ያስታወሱት አቶ ሳሙኤል፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወደ ኢትዮጵያ በገባ ጊዜ ወረዳዎችና የእምነት ተቋሞች ላይ በመሄድ የእጅ መታጠቢያና ሌሎች ቁሳቁሶችን መደገፍ መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡

ማኅበሩ ከተመሠረተ 13 ዓመታት ማስቆጠሩን ገልጸው፣ ከተመሠረተ ጊዜ አንስቶ ከየአባላቱ ሀምሳ ሀምሳ ብር፣ ከተማሪዎች ደግሞ ሃያ ሃያ ብር እንዲያዋጡ በማድረግ ለተቸገሩ ወገኖች እየደረሱ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በ58 እና በላፍቶ አካባቢ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ወገኖች በየወሩ አስቤዛ እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን፣ ከዚያም አልፎ በየዓመት በዓላቱ ለነዳያን በማብላት አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

ማኅበሩ በቀጣይ በተለያዩ በጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ላይ ለመሳተፍና ከመንግሥት ጎን ለመቆም  ዝግጁ መሆኑን፣ አገራዊ ጉዳዮች ላይም ወጣቶች በመሳተፍ በጎ ተግባር ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

በበዓላቱ ላይ በርካታ በማኅበራት የተደራጁና በየአካባቢውና በየአጥቢያው የተሰባሰቡ ወጣቶች በዓሉ ውበቱና ሥርዓቱ ተጠብቆ በሰላም እንዲጠናቀቅ ከሳምነት ላላነሰ ጊዜ ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡

በየዓመቱ ጥር 11 ቀን የሚከበረውን የጥምቀት በዓል አስመልክቶ የፌዴራል የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል ባወጣው መግለጫም፣ የጋራ ግብረ ኃይሉ ከማኅበረሰቡ ጋር ተቀናጅቶ በመሥራቱ በዓሉ ያለምንም የፀጥታ ሥጋትና ችግር አዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተሞችን ጨምሮ በሁሉም አካባቢዎች በሰላም ተከብሮ መጠናቀቁን ገልጿል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤና ሌሎች የክልል አመራሮችም በአገሪቱ በተለያዩ ክፍሎች ላይ ከፀጥታ ኃይል ጎን በመቆም ለበዓሉ አከባበር ትልቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ወጣቶች ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በዓለም አቀፍ የፌስቲቫሎች መድበል ‹‹የአፍሪካ ኤጲፍኒያ›› (The African Epiphany) እየተባለ በዓለም የክብረ በዓላት ድርሳን ላይ በየጊዜው የሚተዋወቀው የጥምቀት በዓል በዩኔስኮ የማይዳሰስ ወካይ ቅርስነት መመዝገቡ ይታወቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...