Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየአንድ ጤና መርሕን አስገዳጅነት የሚጠይቁት ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎች

የአንድ ጤና መርሕን አስገዳጅነት የሚጠይቁት ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎች

ቀን:

በሽታዎች በአብዛኛው የሚተላለፉት ከእንስሳት ወደ ሰው ነው፡፡ አንዳንድ በሽታዎች ደግሞ ከሰው ወደ እንስሳት ይተላለፋሉ፡፡ የበሽታ አምጪ ተዋህሳት በአካባቢ ውስጥ የሚራቡ በመሆኑም የአካባቢ ሁኔታዎችም ለበሽታ መተላለፍ አስተዋጽኦ አላቸው፡፡ እነዚህ በሽታዎች ባህሪያቸው እንዲቀያየር፣ ከቁጥጥር ውጭ እንዲሆኑና የጤናውን ዘርፍ እንዲፈትኑ ምክንያት ሆነዋል፡፡

የሰው ልጆች ሕይወት ከእንስሳት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው፡፡ ከቤት እንስሳት ጋር አብሮ መኖር፣ ለምግብና ለግብርና የሚውሉትን መጠቀም፣ ለመዝናናት አስቦ በየጥብቅ ቦታው በመሄድ የዱር እንስሳትን ማየትና አደን የሰው ልጆች የሕይወት አንድ ክፍል ናቸው፡፡ ይህ ሲሆን ግን እንስሳቱ ምን ያህል ለሰው ልጆች የጤና ጠንቅ ሊሆኑ እንደሚችሉ በተለይም በግለሰብና በቤተሰብ ደረጃ ያለው ግንዛቤ አናሳ ነው፡፡

በመሆኑም በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካቶች ቤት ውስጥ ከሚያሳድጓቸውና አብረዋቸው ከሚኖሩት አሊያም በአካባቢያቸው ከሚገኙ እንስሳትና አዕዋፋት በርካታ በሽታዎችን ይሸምታሉ፡፡ በዓለም የተከሰቱ አቪያን ፍሉ፣ ስፓኒሽ ፍሉ፣ ኢንፍሉዌንዛ፣ ኢቦላ፣ ኮቪድ-19 እና ሌሎች ወረርሽኞች እንዲሁም ለሰው ልጆች የጤና ጠንቅ የሆኑ ባክቴሪያዎችና ኢንፌክሽኖች አብዛኞቹ መነሻቸው እንስሳት ናቸው፡፡

- Advertisement -

የአንድ ጤና መርሕን አስገዳጅነት የሚጠይቁት ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎች

የጤና ሚኒስትሯ ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) ይህንን አነጋገር ይጋሩታል፡፡ እንደ ሚኒስትሯ አነጋገር፣ በየጊዜው የሚከሰቱት አዳዲስና ብቅ ብቅ የሚሉ የእንስሳት በሽታዎች እንዲሁም በሽታዎችን ለመፈወስ የሚያገለግሉ መድኃኒቶችን የሚቋቋሙ ረቂቅ የበሽታ አምጪ ተዋህሲያን መከሰት የጤና ሥጋቶች ከሆኑ ውለው አድረዋል፡፡

የግብርና የአስተራረስ ልምድ መለወጥ ብሎም በየጊዜው እየጨመረ የመጣው የምግብ ደኅንነት ጉዳይም አሳሳቢ ከሆኑት ሥጋቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ስለሆነም በሰው ልጆች፣ በእንስሳት ብሎም በአካባቢ የሚከሰቱ የጤና ችግሮች ተናባቢነትና ተመጋጋቢነት ያላቸው በመሆኑ ችግሮቹም የጋራ ናቸው፡፡

ከዚህ አንፃር በሁሉም ደረጃ ላይ የሚገኙ የተለያዩ ሙያዎችና የተለያዩ ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ለሰው ልጆች፣ ለእንስሳት ብሎም ለአካባቢ ደኅንነት በጋራ ተባብረው የሚተገብሩት የሰውን፣ የእንስሳትንና የአካባቢ ጤና የሚያስተሳስረውና ችግሩን ለመቅረፍ ያግዛል የተባለው ‹‹የአንድ ጤና መርሕ›› ሥርዓትን መከተል ወሳኝ ነው ተብሏል፡፡

ይህ ዓይነቱ መርሕ የዓለም አቀፉን የጤና ደኅንነትና መመርያ ለመተግበር ዘርፈ ብዙ ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ተናበው፣ ተቀናጅተው፣ ተባብረውና ተግባብተው መሥራትን እንደሚጠይቅ  ሊያ (ዶ/ር)  ተናግረዋል፡፡

‹‹አሁን ባለንበት ዘመን የአንድ ጤና መርሕን በውዴታ ብቻ ሳይሆን የግድ ልንተገብረው የሚገባ እጅግ ቁልፍና አስፈላጊ የሆነበት ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡ ሁላችሁም እንደምታውቁ በአሁኑ ወቅት የዓለምን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እጅግ ካሽመደመደው የኮቪድ-19 በሽታ ተፅዕኖና ጠባሳን የቃኘን ከሆነ ይህ መርሕ እጅግ አስፈላጊና ውጤታማ መሆኑን ልንገነዘበው እንችላለን፤›› ብለዋል፡፡

እንደ ሊያ (ዶ/ር)  አባባል የብሔራዊ አንድ ጤና አስተባባሪ ኮሚቴ በ2008 ዓ.ም. ተቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ ኮሚቴው ሲቋቋም የሚመለከታቸው ሴክተር መሥሪያ ቤቶች በጋራ ተሰባስበው ከመከሩበት በኋላ ግልጽ የሆነ የሥራ መመርያ በጋራ የማስፈጸሚያ ሰነፍ ተዘጋጅቶላቸዋል፡፡

ይህም ሰነድ ልዩ ልዩ የሚኒስቴሮች፣ ተቋማትና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ በጋራና በቅንጅት ተባብረውና ተናበው ብሎም ተጋግዘው በሰው ልጆችና በእንስሳት እንዲሁም በአካባቢያችን ተመጋጋቢነት የተነሳ የሚከሰቱ የጤና ችግሮችን ለመከላከል፣ ከተከሰቱም በፍጥነት ለመለየትና ምላሽ ለመስጠት የሚቻልበትን አቅም የሚያጎለብት ነው፡፡

የብሔራዊ አንድ ጤና አስተባባሪ ኮሚቴ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ‹‹አንድ ጤና›› በአሁን ጊዜ የሰው ልጅን የሚገዳደረውን ትልቁን የጤና ችግር በመረዳት አበረታች የሆኑ በርካታ ሥራዎችን በብቃት እንዳከናወነም ገልጸዋል፡፡

ለሰው ልጆች ገዳይ የሆኑ እንደ ዕብድ ውሻ በሽታ ብሎም ወረርሽኝና ተላላፊ የሆኑ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ የኅብረተሰብ የጤና ችግሮች የሆኑትን እንደ ኮቪድ-19ና ሌሎች ወርሽኞችና በሽታዎችን በተመለከተ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት የሚችለው ‹‹የአንድ ጤና መርሕን›› መተግበር ሲቻል ብቻ እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡

አሁን ከተከሰተው ገዳይ ወረርሽኝ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የተማረው መሰል ዓለም አቀፋዊም ሆነ አገራዊ የጤና ችግሮች ሲከሰቱ ምላሽ ልንሰጥባቸውና ወደፊትም ከተከሰቱ ልንከላከላቸው የምንችለው ሁሉም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና ሁሉም ሴክተር ተቋማት የአንድ ጤና መርሕን በማንገብ ሲንቀሳቀሱ ብቻ መሆኑን ሚኒስትሯ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ከአኅጉራችን በከፍተኛ ደረጃ በኮቪድ-19 ከተጠቁ አገሮች መካከል ኢትዮጵያ  አንዷ መሆኗን ጠቅሰው፣ የእንስሳት በሽታዎችን ለመከላከል እንደተረባረብነው ሁሉ ኮቪድ-19 በሽታንም ለመከላከል ይቻል ዘንድ ሁሉም ሴክተር መሥሪያ ቤቶች በጋራና በቅንጅት መንፈስ እንዲንቀሳቀሱ እንዲሁም በ2022 ዓ.ም. የዕብድ ውሻ በሽታን ከኢትዮጵያ ለማስወገድ እንዲቻል ውጤታማ ያሉትን ዕገዛ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የጤና ሚኒስቴርም አገራዊ የሆኑ ከብሔራዊ የጤና ደኅንነት ሥራዎች ላይ አልተገደቡም፡፡ ስለሆነም እንደ የውሻ በሽታ፣ አባ ሠንጋ፣ ብሩስሎስስ፣ የቆላ ፊቨር፣ የወፎች ጉንፋን በሽታ የመሳሰሉትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ይቻል ዘንድ እየሠራ ነው ብለዋል፡፡

 አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ለሆኑ የጤና ችግሮች ምላሽ ለመስጠት የሚችል የአንድ ጤና አስተባባሪ ሴክሬታሪያት በአስቸኳይ እንዲቋቋም የበኩሉን አስተዋጽኦ ያደርጋል፣ ለዚህም ዕውን መሆን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት ለመሥራት ቁርጠኛ ነው ሲሉም አክዋል፡፡

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታና የእንስሳት ጤና ዓለም አቀፍ ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር)ከሰው ወደ እንስሳ፣ ከእንስሳ ወደ ሰው የሚተላለፉት በሽታዎችን የጤና ሚኒስቴር፣ ግብርና ሚኒስቴርና የዱር እንስሳት ልማትና የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣናት በተናጠል ሲከላከሉ፣ ሲቆጣጠሩና ከተገኘም ምላሽ ሲሰጡ መቆየታቸውን ገልጸው አሁን ግን በተናጠል ከመሥራት ተላቅቀው በጋራና በቅንጅት እየተንቀሳቀሱ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የጋራ ስትራቴጂ በመቅረፅና ቅንጅት በተሞላበት አካሄድ መንቀሳቀስ ከጀመሩ አራት ዓመታት እንደሆናቸው፣ በእነዚህም ዓመታት ውስጥ አመርቂና ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው ውጤቶችን ማስመዝገብ እንደቻሉ ከተመዘገቡት ውጤቶች መካከል ከ360,000 በላይ ለሚሆኑ ውሾች ባለፈው ዓመት የተሰጠው የዕብድ ውሻ በሽታ መከላከያ ክትባት እንደሚገኝበት አመልክተዋል፡፡

ክትባቱ የተከናወነው በአዳማ፣ በአርባ ምንጭ፣ በሐዋሳ፣ በድሬዳዋና በአሶሳ ሲሆን፣ በቅርቡም በባህር ዳር፣ ጎንደርና ጋምቤላ ከተሞች ለሚገኙ ውሾች ተመሳሳይ ክትባት የሚሰጥ መሆኑን ፍቅሩ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

የክትባቱን ሥራ ለማከናወን የሚያስችለው የፋይናንስ አቅም የተሸፈነው በባለድርሻ አካላቱ ሲሆን፣ ዩኔስኮ በተባበበሩት መንግሥታት የእርሻና የግብርና ድርጅት (ፋኦ)፣ የጤና ድርጅቶች የቴክኒክ ድጋፍ በመስጠት ዕገዛ ማድረጋቸውን አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ፣ ኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ዓይነትና ብርቅዬ የዱር እንስሳት ሀብት ቢኖራትም በሕዝብ ቁጥር መጨመር፣ በተለያዩ ውስጣዊ ጣልቃ ገብነት የተነሳ ሀብቱ እጅግ በከፋ አሥጊ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ባለሥልጣኑ የብሔራዊ አንድ ጤና ስትሪንግ ኮሚቴ አባል እንደመሆኑ መጠን ለአንድ ጤና ተነሳሽነት ዓላማ ዕውን መሆን ንቁ ተሳትፎ፣ ትብብርና ዕገዛ ከማድረግ እንደማይቆጠቡ ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል የሰዎች የእንስሳትና የአካባቢ ጤናን ማስተባበር ላይ ትኩረት ያደረገ ዓለም አቀፍ ‹‹የአንድ ጤና ቀን›› ጥር 10 ቀን 2014 ዓ.ም. ታስቦ ውሏል፡፡

‹‹የሰው ልጆችና የእንስሳት ጤንነት ብሎም የአካባቢያችን ደኅንነት ማግኘትና ማቀናጀት አንዱን በጠበቅን ቁጥር ሌሎችንም ለመጠበቅና ለመከላከል ዕገዛ እናደርጋለን፤›› በሚል መሪ ቃል ቀኑ በኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የስብሰባ አዳራሽ ታስቦ በዋለበት ሥነ ሥርዓት ላይ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የአንድ ጤና መርሕን ባጠናከረ መልኩ ለማከናወን የሚያስችላቸውን ሰነድ በፊርማቸው አፅድቀውታል፡፡

በዓለም የሰው ልጆች የጤና ጠንቅ ተብለው ከተለዩ ከ1,415 በሽታዎች ውስጥ 60 በመቶ ያህሉ መነሻቸው እንስሳት እንደሆኑ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል፡፡ በዓለም በየዓመቱ የ2.2 ሚሊዮን ሰዎች ሕይወት የሚቀጠፈውም ከእንስሳት ወደ ሰው በሚተላለፉ 13 ቀዳሚ በሽታዎች ነው፡፡

በኢትዮጵያ ከ43 በላይ ከእንስሳ ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎች በሳይንሳዊ መንገድ ተለይተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ደረጃ የኅብረተሰብ ጤና ሥጋት ናቸው ከተባሉት በሽታዎችም ቅድሚያ ተሰጥቶ እየተሠራ ያለው በአምስቱ ማለትም የዕብድ ውሻ በሽታ፣ አባ ሠንጋ፣ ብሩስሎሲስ፣ ሪፍት ቫሊ ፊቨር (የስምጥ ሸለቆ ትኩሳት) እና ሃይሊ ፓቶጄኒክ አቪያን ኢንፍሉዌንዛ ላይ ነው፡፡ ነገር ግን የበሽታው ብዛትና አሳሳቢነት ከዚህ በላይ መሆኑን በብሩክ ኢትዮጵያ የእንስሳት ደኅንነትና ጥበቃ ባለሙያ አቶ ፀጋዬ ነጋሽ ከዚህ ቀደም ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...