Thursday, July 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትብሔራዊ ቡድኑ ከትልልቅ ቡድኖች ጋር የወዳጅት ጨዋታ አለማድረጉ  ጎድቶታል ተባለ

ብሔራዊ ቡድኑ ከትልልቅ ቡድኖች ጋር የወዳጅት ጨዋታ አለማድረጉ  ጎድቶታል ተባለ

ቀን:

በካሜሩን አስተናጋጅነት እየተካሄደ ከሚገኘው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በምድብ ማጣሪያው የተሰናበተው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ)፣ ከትልልቅ ብሔራዊ ቡድኖች ጋር በታሰበው ልክ የወዳጅነት ጨዋታ አለማድረጉ የቡድኑ ትልቁ ክፍተት እንደነበር ዋና አሠልጣኙ ተናገሩ፡፡ የዋሊያዎቹ ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ በካሜሩን የነበራቸውን ቆይታ አስመልክቶ ማክሰኞ ጥር 17 ቀን 2014 ዓ.ም. ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

የፌዴሬሽኑ ዋና ጸሐፊ አቶ ባህሩ ጥላሁንና የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሠልጣኙ ማክሰኞ በፌዴሬሽኑ የመሰብሰቢያ አዳራሽ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የተጨዋቾች ምርጫና ሒደት እንዲሁም በጉዞ ወቅት የኮቪድ ወረርሽኝን ጨምሮ በተጨዋቾች ጉዳት ምክንያት ያጋጠሙ ችግሮች፣ ብሔራዊ ቡድኑ ከዋናው ውድድር በፊት ማድረግ የነበረበት የወዳጅነት ጨዋታና ከዚሁ ጋር ተያይዞ በገጠሙት ተግዳሮቶችና በሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ካሜሩን የገባው ከሁሉም ብሔራዊ ቡድኖች ቀድሞ ነው፡፡ ቀደም ሲል ለዚህ ምክንያት ተብሎ በአሠልጣኙም ሆነ በብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የተነገረው፣ እንደ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድኑ ሁሉ ወደ ካሜሩን ቀድመው ከሚመጡ ብሔራዊ ቡድኖች ጋር ማለትም ከሱዳን፣ ከሞሮኮና ዚምባቡዌ እንዲሁም ቀደም ሲል በነበረው ዕቅድ ውስጥ ባይካተቱም በጋዜጣዊ መግለጫው ዕለት እንደተነገረው ኢኳቶሪያል ጊኒና ጋቦን  ብሔራዊ ቡድኖች ጋር የአቋም መፈተሻ የወዳጅነት ጨዋታ ማድረግ ይቻል ዘንድ ያለመ እንደነበር ነው፡፡

የፌዴሬሽኑ ዋና ጸሐፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን ይህን አስመልክቶ ሲያብራሩ፣ ቡድኑ ወደ ካሜሩን ለማቅናት ከመወሰኑ አስቀድሞ ዕቅዱ በሳውዲ ዓረቢያ ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ ሲባል ከሚመለከታቸው ጋር መግባባት ላይ ተደርሶ ሳለ፣ በኮቪድ ምክንያት የሳውዲ ዓረቢያ መንግሥት ክልከላ ካደረገባቸው አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ በመሆኗ የታቀደው ቅድመ ዝግጅት ሳይሳካ መቅረቱን ተናግረው፣ የካሜሩኑ ሁለተኛው አማራጭ ስለመሆኑ ጭምር አስረድተዋል፡፡

የወዳጅነት ጨዋታውን አስመልክቶ ዋና ጸሐፊው፣ የካሜሩኑ የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ከመጀመሩ ከ45 ቀን በፊት በዕቅድ ከተያዙት አገሮች ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ማድረግ እንዲቻል በኤጀንት ጭምር ግንኙነት ተደርጎ የነበረ ቢሆንም፣ ከሱዳን ብሔራዊ ቡድን ውጪ ኢኳቶሪያል ጊኒና ጋቦንን ጨምሮ ጥረት እንደተደረገ ተናግረዋል፡፡ ይሁንና ቀደም ሲል በዕቅዳችን ከተያዙት ግን የሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን ዘግይቶ ካሜሩን በመግባቱ፣ የዚምባቡዌ ብሔራዊ ቡድን እንደዚሁ ውሳኔውን ሊያሳውቅ ባለመቻሉ የተነሳ የወዳጅነት ጨዋታው በታሰበው ልክ ሊደረግ እንዳልቻለ፣ ይህ ደግሞ ብሔራዊ ቡድኑ ዕቅዱን እንዳያሳካ ስለማድረጉ ጭምር አስረድተዋል፡፡

የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ በበኩላቸው፣ ብሔራዊ ቡድኑ በኮቪድ ምክንያት የገጠመው ችግር እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ወደ ካሜሩን ቀደም ተብሎ ለመግባት ሲወሰን አንዱና መሠረታዊ ነገር በእቅዱ መሠረት የተባሉትን የወዳጅነት ጨዋታዎችን ለማድረግና ከአየር ፀባዩ ጋር ለመላመድ ሲባል ነበር፡፡ ይሁንና በዋናነት የወዳጅነት ጨዋታውን በተባለው ልክ ከትልልቆቹ ብሔራዊ ቡድኖች ጋር ማድረግ አለመቻሉ፣ ከዚህም በላይ ቡድኑ ከኬፕ ቨርዴ ጋር ባደረገው የመጀመርያው ጨዋታ የተከላካዩ ያሬድ ባዬ በቀይ ካርድ መውጣት ጨዋታውን ባሰቡት ልክ መቀጠል እንዳይችል ትልቅ ሚና እንደነበረው ተናግረዋል፡፡

አሠልጣኙ በዋናነት ቡድናቸው የጎደለውን አስረግጠው ሲናገሩ፣ ውድድሩን በሚመጥን ደረጃ ከትልልቅ ቡድኖች ጋር የወዳጅት ጨዋታ ማድረግ አለመቻሉ እንደጎዳው ነው፡፡ በዚህ ጉድለት ምክንያት ቡድናቸው ክፍተቶቹን ከጨዋታ ጨዋታ ለማስተካከል የተጓዘበትን የጨዋታ ሒደትና ውጤቱን ጭምር አስረድተዋል፡፡

አሠልጣኙ ለዚህም ከኬፕ ቨርዴ፣ ከካሜሩንና ከቡርኪና ፋሶ ጋር ባደረጓቸው ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ቡድናቸው ያሳየውን የሜዳ ላይ እንቅስቃሴና የኳስ ቁጥጥር በማሳያነት ይጠቅሳሉ፡፡ እንደ አሠልጣኙ ከሆነ የቡድናቸው የፊት መስመር ተጨዋቾች ያገኟቸውን ጎል የማግባት ዕድሎች የካሜሩኑ ቪሴንት አቡበክር፣ የቡርኪና ፋሶው በርናንድ ትራዎሬና የአልጀሪያው ማህሬዝና ሌሎችም ቢያገኟቸው ምን ያህል ጥቅም ላይ እንደሚያውሏቸው፣ ይህ ደግሞ በተጨዋቾቹ ተሰጥኦ ብቻ ሳይሆን በትልልቅ ጨዋታዎች ላይ ከሚያዳብሩት ልምድ የሚገኝ ስለመሆኑ ጭምር ተናግረዋል፡፡

አሠልጣኙ በካሜሩን ዝግጅታቸው በታሰበው ልክ የወዳጅነት ጨዋታ አለማድረጋቸው በውድድሩ ወቅት ለመተግበር ባቀዱት አደረጃጀት ላይ ችግር እንደፈጠረባቸው ጭምር ከመግለጽ አልሸሸጉም፡፡ አሠልጣኙ ከወዳጅት ጨዋታ ጥቅም ጋር ተያይዞ ሲናገሩ፣ ‹‹የጎረቤት ዑጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ሁላችሁም እንደምታወቁት ለአፍሪካ ዋንጫ አላለፈም፡፡ ይሁንና በአሁኑ ወቅት ለሚቀጥለው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ይረዳው ዘንድ ከተለያዩ የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ብሔራዊ ቡድኖች ጋር  የወዳጅት ጨዋታዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡ እኛስ በዚህ ልክ ለብሔራዊ ቡድናችን ትኩረት እየሰጠን ነውን?›› በማለት ይጠይቃሉ፡፡

በመጨረሻም ከአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሥራ ውል ጋር ተያይዞ ለዋና ጸሐፊው ጥያቄ ቀርቦላቸው የሰጡት ምላሽ፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ከአሠልጣኝ ኮንትራት ጋር በተያያዘ በአሁኑ ወቅት ምንም ዓይነት ውሳኔ ላይ አለመድረሱን ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...