Tuesday, November 29, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ኪንና ባህልከግማሽ ምዕት ዓመት በላይ ያስቆጠረው የማዘጋጃ ቤት ሕንፃ እድሳት

  ከግማሽ ምዕት ዓመት በላይ ያስቆጠረው የማዘጋጃ ቤት ሕንፃ እድሳት

  ቀን:

  በአዲስ አበባ ከተማ ከግማሽ ምዕት ዓመታት በላይ ባስቆጠሩ ታሪካዊ ሕንፃዎች ውስጥ በጉልህ ይነሳል፡፡ በ1950ዎቹ መጀመርያ በከንቲባዎቹ በነብላታ ትርፌ ሹምዬ፣ ደጃዝማች ዘውዴ ገብረ ሥላሴ (ዶ/ር) ዘመን ግንባታው በመጀመር፣ በቢትወደድ ዘውዴ ገብረ ሕይወት ዘመን በ1957 ዓ.ም. ተጠናቆ ለሕዝብ ክፍት መደረጉን ታሪክ ያነሳዋል፡፡

  በአራዳ ክፍለ ከተማ እንብርት ላይ ከሚገኙ ሕንፃዎች ውስጥ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ያስቀለሱት የማዘጋጃ ቤት ሕንፃ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ነው፡፡ በሕንፃው መሀል ሆነው አዲስ አበባን በሁሉም ማዕዘናት ለመቃኘት አመቺ ተደርጎ ተሠርቷል፡፡ ለእይታ አመቺ ከመሆኑ ባሻገር ቸርችል ጎዳና ተንተርሶ ወደ ታች የተንዥረገገው የአስፓልት መንገድ ለመቃኘትም የማዘጋጃ ቤቱ ሕንፃ አገነባብ አመቺ ያደርገዋል፡፡ ይህ ታሪካዊ ሕንፃ አሁንም የፒያሳን ውበት ከሚያጎሉት ሕንፃዎች ቀዳሚ መሆኑን ብዙዎች ያወሩለታል፡፡

  ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ‹‹ለመናገሻቸው፣ ለሕዝባቸው፣ ለማኅበራዊ ኑሮው፣ ለኢኮኖሚውና ለባህሉ ዕድገት አማካይ የአገልግሎት ቤት ይሆን ዘንድ ፈቅደው›› ያሠሩትን ይህን ሕንፃ በሠላሳ አራተኛው ዘመነ መንግሥታቸው (1957 ዓ.ም.) መርቀው መክፈታቸው ታሪክ ያስረዳል። ለረዥም ጊዜ የከተማዋን ማኅበራዊና ሌሎች አገልግሎቶች ሲሰጥበት የቆየው ይኼ ሕንፃ እድሳት ሳይደረግለት ቆይቷል፡፡

  ከግንቦት 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ዕድሳት ሲደረግለት የቆየው የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ሕንፃ በከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት ጥር 15 ቀን 2014 ዓ.ም. ተመርቋል።

  ሕንፃው ከ57 ዓመታት በኋላ ነባር ገጽታውን ሳይለቅ፣ ከ1.5 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ዕድሳት እንደተደረገለት በሥነ ሥርዓቱ ላይ ተነግሯል።

  የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እንደተናገሩት፣ ሕንፃው አዳዲስና ደረጃቸውን የጠበቁ አገልግሎቶችን በውስጡ አካትቷል፡፡ የሕፃናት መዋያ፣ ቤተ መጻሕፍት፣ የሥልጠናና የምርምር ክፍሎች፣ ክሊኒክ፣ የቴአትር አዳራሽ፣ የስብሰባ አዳራሾች፣ የመኪና ማቆሚያ፣ አረንጓዴ ሥፍራዎችና የከተማ ግብርና ናሙናዎች ይገኙበታል።

  ከጥር 16 ቀን ጀምሮ ለሕዝብ ክፍት እንደሚደረግና መጎብኘት እንደሚቻል አሳውቀዋል። የአሁኑንና የወደፊቱን ድልድይ ሆኖ የሚያገናኝ መሆኑን የገለጹት ከንቲባዋ፣ የትውልድ ቅብብሎሽ የታየበት፣ ኢትዮጵያን የመውደድና ለኢትዮጵያ የመሥራት ቁም ነገሮችንም የታየበት ነው ብለዋል።

  ‹‹የምንመርቀው ሕንፃ ብቻ አይደለም፡፡ ቅርስና የአገራችን ሀብት ነው፡፡ ታሪካዊ እሴቱን በመጠበቅ ዘመኑን በዋጀ አሠራር የተገነባ ነው፤›› ያሉት ከንቲባ አዳነች ናቸው፡፡ ታሪካዊውን የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ሕንፃ ከ57 ዓመታት በኋላ ነባሩን እሴትና እይታ ሳይለቅ በአዲስ ወዝና ጥራት ዘመናዊነትን በማላበስ መሠራቱንም አክለዋል።

  ሕንፃው ለከተማው ቅርስ መሆኑን፣ ትውልድ የሚጠብቀው ዘመን ተሸጋጋሪ ሀብት መሆኑን ሳይገልጹ አላለፉም። በዚህ ታሪካዊ ሥራ ለተሳተፉ ባለሙያዎች፣ ተቋራጮች፣ አማካሪዎች፣ አመራሮችና ሠራተኞች ምሥጋናቸውን አቅርበዋል።

  የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት በ1957 ዓ.ም. የተጠናቀቀው በቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የአሁኑ የአፍሪካ ኅብረት) በተመሠረተ በሁለት ዓመቱ ነው፡፡

  ማዘጋጃ ቤቱ ለረዥም ጊዜ ያልታደሰ በመሆኑ በርካታ ክፍሎች በቂ ብርሃንና አየር ያልነበራቸው የተበላሹና የማይሠሩ መፀዳጃ ክፍሎችም ለተገልጋይና ለሠራተኞች አመቺ እንዳልነበሩ ተገልጿል፡፡ በእድሳቱ የነበሩ ችግሮቹ መቀረፋቸውን ዓለም አቀፍ ደረጃን የሚያሟሉና ለአካል ጉዳተኞች አመቺ መሆኑንም ከንቲባዋ ተናግረዋል፡፡

  ታድሶ ለምርቃት የበቃው ሕንፃው የማማከሩን ሥራ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት፣ ገንቢው መቀመጫውን ዱባይ ያደረገው አሌን ፊት አውት ኮንስትራክሽን ነው፡፡

  የአዲስ አበባ ትልልቅ ፕሮጀክቶች አካል የሆነው የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ዕድሳት፣ ከመስቀል አደባባይና ከአብርሆት ቤተ መጻሕፍት ቀጥሎ ለሕዝብ ክፍት በመሆን ሦስተኛው ፕሮጀክት መሆኑ ተገልጿል፡፡

  የአዲስ አበባ ሜጋ ፕሮጀክቶች ሥራ አስኪያጅ ዳባ ቱንካ (ኢንጂነር) እንደተናገሩት፣ ማዘጋጃ ቤቱ ታሪካዊ ይዘቱን ሳይለቅ በልዩ ሁኔታ የታደሰ ነው፡፡ ከ800 በላይ ሰዎችን ማስተናገድ የሚችል መሆኑን፣ ከአዲስ አበባ ታሪካዊ ፕሮጀክቶች ተርታ አንዱ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡  

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በችግር የተተበተበው የሲሚንቶ አቅርቦት

  ሲሚንቶን እንደ ግብዓት ተጠቅሞ ቤት ማደስ፣ መገንባት፣ የመቃብር ሐውልት...

  ‹‹የናይል ዓባይ መንፈስ›› በሜልቦርን

  አውስትራሊያ ስሟ ሲነሳ ቀድሞ የሚመጣው በተለይ በቀደመው ዘመን የባህር...

  ‹‹ልብሴን ለእህቴ››

  ለሰው ልጅ መኖር መሠረታዊ ፍላጎት ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ ልብስ...

  የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የምርመራ ውጤት እስከምን?

  በፍቅር አበበ የትምህርት ጥራትን፣ ውጤታማነትንና ሥነ ምግባርን ማረጋገጥ ዓላማ አድርጎ...