በደስታ ሄሊሶ
ከጥቂት ዓመታት በፊት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ባወጡት ‹‹የኦሮሞና የአማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ›› የተሰኘ መጽሐፋቸው ላይ ተመርኩዞ ከንዑስ ብሔር (ጎሳ) እና የጋራ ብሔራዊ አንድነት ጋር የተያያዘ ክርክር ተነስቶ ነበር፡፡ አማሮችና ኦሮሞዎች የጋራ የዘር ምንጭ እንዳላቸውና ‘ኢትዮጵያ’ የሚለውም ቃል ‘ኢትዮጲስ’ ከሚል ቃል የተገኘ ሲሆን፣ ይህም ቃል የእነዚህ የሁለቱ ሕዝቦች የዘር ምንጭ አንድ እንደሆነ የሚገልጽ እንጂ፣ የጥንት ግሪካውያን የፈጠሩት እንዳልሆነ መጽሐፉ ይጠቁማል። ክርክሩ በጊዜው በጣም የተጋጋለና ከፍተኛ ስሜት የተቀላቀለበት ነበር። አሁንም ጉዳዩ ዕልባት ያገኘ አይመስለኝም። በዚህ አጭር መጣጥፍ ከጋራ የብሔራዊ አንድነት ጋር በተያያዘ የጠቀመውን ያህል እንዲጠቅም የራሴን ሐሳቦች በማጋራት ለሙግቱ የራሴን አስተዋጽኦ ማድረግ እሻለሁ።
የማቀርበው ሐሳብ በጣም ቀላል ነው ‹‹ኢትዮጵያ አንድ ናት ኢትዮጵያውያንም እህትማማቾችና ወንድማማቾች ናቸው። ነገር ግን እንዲህ ያለ ቀላል የሚመስል ድምዳሜ ላይ ለመድረስ አንድ ሰው ሊቀበለው የሚገባው ነገር ቢኖር ኢትዮጵያ እንደ አገር ፖለቲካዊ ሥሪት መሆኗንና ኢትዮጵያዊነትም የአስተሳሰብ ውጤት መሆኑን ነው። ኢትዮጵያ እንደ አገር የተሠራችው የተለያዩ ማንነቶችና ባህሎች የሕዝብ ቡድኖችን አንድ በሚያደርጉ ልዩ ልዩ ተምኔቶችና ልዩነቶችን ሊሻገሩ በሚችሉ ማኅበረሰባዊ መሠረቶች ላይ ነው። ይህ ነው አሁን ኢትዮጵያ ብለን በምንጠራት አገረ ግዛት ሥር የጋራ ብሔራዊ ማንነት ያስገኘልን። ይህም ማንነት የተገነባው በብዙ ትውልዶች ሲሆን፣ የተጠናከረውም ለሁሉ የጋራ በሆነ የኢትዮጵያዊነት ትርክት ጥላ ሥር ነው።
ብዙ ጊዜ ይህ ትረካ በሆሜር የሥነ ግጥም ዓይነተኛ ሥራና በሄሮዶቶስ ሥነ ጽሑፎች ውስጥ ከሚጠቀሰው ኢትዮጲስ (Aithiopis) ጋር ይገናኛል። የግሪኩም መጽሐፍ ቅዱስ ለዕብራይስጡ ኩሽ የሚለውን ቃል ኢትዮጲስ በሚለው ይተረጉማል፡፡ ቃሉም ታችኛውን የደቡባዊ የዓለም ክፍል የሚወክል ሆኖ ጥቅም ላይ ውሏል። ይሁን እንጂ ኩሽ ወይም ኢትዮጲስ የሚሉት የተለመዱ አገላለጾች ዛሬ የምናውቃትን ኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ አይወክሉም። ብሉይ ኪዳን ኩሽ በማለት የሚገልጸው ምድር ኑቢያንና የዓረብን ሰላጤ ያካተተ ሊሆን ይችላል። ቀደምት ጸሐፍት ኩሽ በሚለው ምትክ ኢትዮጲስ የሚለውን ቃል መጠቀማቸውም የግድ ይኼን ላይፃረር ይችላል። ለግሪኮቹ ኢትዮጲስ ማለት ‹‹በፀሐያማ ምድር የሚኖር ጥቁር ዝርያ ያለው ሕዝብ መገኛ የሆነ ሩቅ አገር›› ሲሆን፣ የቃሉም ትርጉም ኢትዮጵያውያን ከግሪኮች ተለይተው የሚታወቁበት መለያ የሆነ ‹‹በፀሐይ የጠየመ›› መልክ ያላቸው እንደሆኑ የሚገልጽ ይመስላል። ግሪኮቹ እንዴት እዚህ ስያሜና ማብራሪያ ላይ ሊደርሱ እንደቻሉ እርግጡን መናገር አንችልም። ሆኖም አንድ ስም ለአንድ ሕዝብ የሚሰጠው ያን ሕዝብ ከመልክዓ ምድራዊ መገኛ፣ ከሃይማኖታዊ አዝማሚያ፣ ከማኅበራዊ ሥረ መሠረትና ከቆዳ ቀለም አኳያ ለመግለጽ እንደሆነ እናውቃለን። ስለዚህ ጥንታውያኑ ግሪኮች ‹‹ኢትዮጲስ›› የሚለውን ስያሜ የሰጡትም ከዚህ አኳያ ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ ከዘመነ ሆሜር እስከ ሮማ አገዛዝ ጊዜ ድረስ ይህ ኢትዮጲስ የሚለው ስም የትኞቹን በአሁኗ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙትን የሕዝብ ቡድኖች እንዳቀፈ በትክክል ለማወቅ ያስቸግራል።
ይሁን እንጂ ግሪኮቹ ጥንታዊቷን ኢትዮጵያ (ኢትዮጲስ) የሚገልጿት በወጉ የተደራጀ ሠራዊት ያላትና አክብሮት የተቸራት አገረ መንግሥት አድርገው ነው። ጥንታውያን ኢትዮጵያውያንንም የገለጿቸው ነፃነትና ፍትሕ ወዳድ ሕዝብ አድርገው ነው። አይሁዳዊው የታሪክ ጸሐፊ ጆሲፈስ፣ Jewish Antiquities በተሰኘው ድርሳኑ ኢትዮጵያውያንን የገለጸበት መንገድም አስደናቂ ነው። ጆሲፈስ ኢትዮጵያ የማይናቅ ወታደራዊ ኃይል ያላት ጉልህና ነፃ አገር እንደነበረች፣ ታርቢስ የተባለች ውብ ኢትዮጵያዊት ልዕልት ሙሴን እንዳገባች፣ እንዲሁም ተደናቂዋና ብልኋ ንግሥተ ሳባ የግብፅና የኢትዮጵያ ንግሥት እንደነበረች ያትታል። በተለይ ጆሲፈስ ስለንግሥተ ሳባ ያወሳው ታሪክ በዓረቦችና በሌሎች ዘንድ በአያሌው ማስፋፊያ ታክሎበታል። በ14ኛ ክፍለ ዘመኑ የኢትዮጵያው ሰነድ ክብረ ነገሥት ደግሞ የበለጠ ማስፋፊያ ተጨምሮበታል። እነዚህ ማስፋፊያዎች የሚሉትን ከተከተልን የየመን፣ የግብፅ፣ የኢትዮጵያ፣ ወዘተ ሰዎች ንግሥተ ሳባን የእኛ ንግሥት ናት ሊሉ ይችላሉ።
እንግዲያው ኢትዮጲስ ወይም ሳባ የትኞቹን ግዛቶች ወይም ወሰኖች ያካተተ ነው? የዘመናችንን ኢትዮጵያ ፖለቲካዊና መልክዓ ምድራዊ ወሰን ብቻ የሚወክል ነው ማለት አንችልም። እርግጠኛ መሆን የሚንችለው ግን ጥንታዊቷ ኢትዮጵያ ከአሁኗ ኢትዮጵያ በግዛት ወሰን እጅግ ትልቅ የነበረች መሆኗን ነው። ጥንታዊት ኢትዮጵያ የኬንያን አንዳንድ ክፍሎች ያካትት ነበር ብሎ የሚሟገት ኬንያዊ ገጥሞኝ ያውቃል። በሱዳን፣ በየመን፣ በሶማሊያ፣ በጂቡቲና በግብፅ ተመሳሳይ ሙግት የሚያቀርቡ ይገኛሉ። ከዚህ ሁሉ በመነሳት የአሁኗ ኢትዮጵያ ምድርና ሕዝብና ሌሎችም ለምሳሌ በአፍሪካ ቀንድ፣ በኑቢያና በዓረብ ሰላጤ የሚኖሩ ሕዝቦች የጥንታዊቷ ኩሽ፣ ሳባ ወይም ኢትዮጲስ አካል እንደነበሩ መገመት ይቻላል። ይህ ከሆነ የአሁኗ ኢትዮጵያ የጥንታዊቷን ኩሽ፣ ሳባ ወይም ኢትዮጲስ ስምና ማንነት ተሸክማ የሚትኖር ናት ማለት ነው።
ከዚህ ሁሉ ተነስተን የአሁኑን ታሪክ ስናይ ኢትዮጵያ የተሰኘች አገረ መንግሥት ደጋግማ ስትፈጠር፣ ደጋግማ ስትበየን የኖረች ፕሮጀክት ነች። ኢትዮጵያ እንደ አገረ መንግሥት የተጓዘችውን ታሪካዊ ጉዞ ያጠኑ ሰዎች፣ አክሱም ኃያል መንግሥት በነበረበት ጊዜ እንኳ በሹሞችና በሡልጣኖች የሚተዳደሩ የተበታተኑ መንግሥታት እንደነበሩ ይረዳሉ። እነዚያ የተበታተኑ መንግሥታት በግድም ይሁን በውድ፣ በጦርነትም ይሁን በሰላም በሰሜኑ ክርስቲያናዊ መንግሥት ሥር መተዳደር ጀመሩ። በመቀጠል ከ16ኛው እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን የአገረ መንግሥት ግንባታው ቅርፅ እየያዘ ቢሄድም ልዩ ልዩ የፖለቲካ፣ የሃይማኖት፣ የኢኮኖሚና የመስፋፋት ግቦችን ባነገቡ ቡድኖች ተከታታይና አስከፊ ውጊያዎች ምክንያት ሒደቱ ክፉኛ ፈተና ደርሶበታል። በአጭሩ ዛሬ የምናውቃት ኢትዮጵያ የፖለቲካ፣ የሃይማኖትና የኢኮኖሚ ፍጭት መነሻ ሆኖ ደጋግማ ስትፈጠር፣ ደጋግማ ስትበየን በመኖር ውጣ ውረድ ውስጥ ያለፈች ነች።
በመሆኑም ኢትዮጵያ የተፈጠረችው በዋነኝነት በደም አፋሳሽ ውጊያዎች፣ በፖለቲካ ብልጣ ብልጥነት፣ በሃይማኖት በጭቆናና አስገዳጅነት፣ እንዲሁም አንዳንድ የሐሳብ መርሆዎችን በግድ በመጫን ነው ብሎ የሚሟገት ሰው ተሳስተሃል ሊባል አይችልም። ይህ ዓይነት ታሪካዊ ሒደት በተለየ ሁኔታ ኢትዮጵያን ብቻ የገጠማት አይደለም። ጀርመን፣ ብሪታንያ፣ አሜሪካ፣ ወዘተ በተመሳሳይ ሒደት ውስጥ አልፈዋል። የኢትዮጵያ ዓውድ የተለየ ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም ኢትዮጵያ እንደ አገረ መንግሥት ደጋግማ የተፈጠረችበት ሒደት በዓለም ላይ የሚገኙ የትኛውም አገረ መንግሥታት ከተፈጠሩበት ሒደት የሚለይ አይደለም። ለአንድ ሹም፣ ሡልጣን ወይም ንጉሥ ከሚገብሩ የተበታተኑ መንግሥታት በንጉሠ ነገሥት ሥር ወዳሉ ጠቅላይ ግዛቶች፣ ከዚያም በፕሬዚዳንት ሥር ወዳሉ ክፍላተ አገሮች፣ በመቀጠልም በጠቅላይ ሚኒስትር ሥር ወዳሉ ክልሎች ተሸጋግረናል። ቀጣዩ ትውልድ እንዴት ያለ የአስተዳደር ዘዬ ይዞ እንደሚመጣ የሚያውቀው አንድዬ ብቻ ነው። ይህ ሁሉ የሚያሳየው ‹‹የአገረ መንግሥት›› ጽንሰ ሐሳብ እንዲህ ነው ተብሎ ተወስኖ በድንጋይ ተጽፎ የተቀመጠ አለመሆኑን ነው።
ፕሮፌሰር ክዋሜ አንቶኒ አፒያ ‹‹በስህተት የተወሰዱ ማንነቶች›› (‘Mistaken Identities’) በሚል ርዕስ ከሃይማኖት መግለጫ፣ ከአገር ከቀለምና ከባህል ጋር በማያያዝ እ.ኤ.አ. በ2016 በቢቢሲ ባቀረበው ትምህርት የብሔራዊ ሉዓላዊነት ጽንሰ ሐሳብ ‹‹አስኳሉ ተያያዥነት የሚጎድለው›› እንደሆነ፣ ፖለቲካዊ አንድነት ቀድሞውኑ ዋስትና በተሰጠው ብሔራዊ የጋራ ገጽታ ወይም ማንነት ላይ የተመሠረተ እንዳልሆነና አገር ደጋግማ የምትበየን ፖለቲካዊ ህዋስ እንደሆነች ይሞግታል። እኔም ከአፒያ ጋር እስማማለሁ። የኢትዮጵያ አንድ አገረ መንግሥትነት ቀዳሚ ብሔራዊ የጋራ ገጽታ ወይም ማንነት ላይ የተመረኮዘ ሳይሆን፣ ቀደም ሲል ተበታትነው የነበሩና በከፊልም ሆነ ሙሉ በሙሉ በራሳቸው ይተዳደሩ የነበሩ ቡድኖች የተለየ ማንነታቸውን ሳያጠፉ ልዩነቶቻቸውን ግን የሚያልፉ አንድ የሚያደርጓቸውን ተምኔቶችና ትርክቶች በመቀበላቸው ላይ የተመሠረተ ነው። እንዲህ በማድረጋቸው እነዚህ ቡድኖች ራሳቸውን ከጋራ ታሪካዊና ባህላዊ እሴቶች እንዲሁም መሻቶች ጋር አቆራኝተዋል፡፡ ብሔራዊ ንቃተ ህሊናን አዳብረዋል፣ ብሎም በጋራ የኢትዮጵያዊነት ትርክት ሥር ላለ የጋራ ብሔራዊና ፖለቲካዊ ማንነት ራሳቸውን ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ የፖለቲካዊና የብሔራዊ ማንነት የግንባታ ሒደት ውጤት ከሆነች ኢትዮጵያዊነት ደግሞ ከተለያየ ጎሳ የሆኑና የተለያየ ባህልና ሃይማኖታዊ አመለካከት ያላቸውን ሕዝቦች አንድ የሚያደርግ ሁሉን አቀፍ የሆነ የአስተሳሰብ ይዞታ ወይም ትርክት (Metanarrative) ነው። በኢትዮጵያ ‹‹ታሪክ›› እና ‹‹ልማዶች›› የተቃኘ የአዕምሮ ሁናቴ (State of Mind) ነው። ኢትዮጵያዊነት በማኅበራዊው አስተሳሰብ ውስጥ እጅግ በጥልቀት የተገመደ ከመሆኑ የተነሳ ሳያስቡት ከራስ ጋር የሚዋሀድ ነገር ነው። ለአገር ያለ ጥልቅ ስሜት፣ ከአገርና ከሕዝብ ጋር ያለም ጥብቅ ቁርኝት ነው። ይህንን የአገር ፍቅር ብለን እንገልጸዋለን። ይህ ጥልቅ ስሜት ለምሳሌ በሙዚቃ፣ በሥነ ጥበብ፣ በስፖርትና በብሔራዊ መዝሙር ይቀጣጠላል፡፡ አንድ ለሚያደርጉን ትዕምርቶች ያለን መሰጠትም ይታደሳል። በአመክንዮ ልጓም ካልተያዘ፣ ለአገር ያለን ስሜት አንዳንዴ ምክንያታዊነትን እየጣሰ አደገኛ እስከ መሆን ሊደርስ ይችላል። ይህን ስሜት ለሰው በሚገባው መንገድ ዘርዝሮ ማብራራት ቢቸግርም እውነታው ግን ለማንም ሰው ግልጽ ነው።
ለምሳሌ በብሪታንያ፣ ‹‹ቢቢሲ ፕሮምስ›› የተሰኘ የሙዚቃ ኮንሰርት በየዓመቱ ይዘጋጃል። የሚካሄደው በማዕከላዊ ለንደን በሚገኘው የሮያል አልበርት አዳራሽ ነው። በኮንሰርቱ የመጨረሻ ምሽት ከሚዘመሩት መዝሙሮች አንዱ ‹‹እንግሊዝን የተስፋና የክብር ምድር›› ሲል ይገልጻታል። ሌላው በሰፊው የሚታወቀው መዝሙር ደግሞ ብሪታንያ ግዥ (Rule Britannia) የሚለው ነው። ብዙ ጎበዛዝት የብሪታንያን ሰንደቅ ዓላማ ተከናንበው እነዚህን መዝሙሮች በሚያስደንቅ ተነሳሽነት ዓይናቸው ዕንባ እያቀረረ ይዘምሯቸዋል። መዝሙሮቹ የሚያወሱት የዓለምን አንድ ሦስተኛ በቅኝ ትገዛ ስለነበረችው፣ በዚያም ታሪኳ ስለሚያፍሩባት ብሪታንያ ነው፡፡ ይህቺ ብሪታንያ እነዚህ ወጣቶች ከሚያውቋትና ከሚኖሩባት ከአሁኗ ዘመን ብሪታንያ ጋር ያላት ተያያዥነት እጅግ አናሳ ነው። ያም ሆኖ ግን የብሪታንያ ዜግነት ስሜታቸውን የሚቆሰቁስና ለብሪታንያ ያላቸውን የፍቅር ስሜት የሚያቀጣጥለውን መዝሙር በዕንባ ይዘምራሉ። ይህንን ስሜት በምክንያት ማብራራት ባይቻልም ስሜቱ ለልማትም ይሁን ለጥፋት በየትኛውም አገር መኖሩ ግን እውነት ነው።
እንዲሁ ኢትዮጵያዊነት እንዲህ ነው ተብሎ የማይገለጽ፣ በአዕምሯችን ጓዳ የተቀረፀና በስሜት የሚቀጣጠል ነገር ነው። በጋራ ምድር ላይ የሚኖሩና እግዚአብሔር የሰጣቸውን በረከቶች በአንድነት የሚጠቀሙ ከሰማንያ በላይ ብሔረሰቦች ወይም የሕዝብ ቡድኖች የሚጋሩት በአንድ የሚያስተሳስር ትርክት ነው። በተጨማሪም እነዚህ ቡድኖች በፈቃደኝነት የጋራ እሴቶችን ይጋራሉ፣ የጋራ ባህላዊ ውርስንና መገለጫዎችን ያዳብራሉ፣ እንዲሁም አንድ የሚያደርጉ ትዕምርቶችን ይይዛሉ። በዚህ ሒደት አብላጫዎቹ ይህችን ኢትዮጵያ የተሰኘች አገር ዕውቅና ሊሰጡና ሊወዱ ችለዋል። የጋራ ትርክት የጋራ ማንነትን ፈጥሯል። ከዚህም የተነሳ በምሳሌ መግለጽ ካስፈለገ የአንድ እናት ልጆች ወይም እህትማማቾችና ወንድማማቾች ሆነዋል። በእርግጥ እንደ ማንኛውም እህትማማቾችና ወንድማማቾች የቤተሰብ ፍጭት ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ፡፡ ይህም አንዳንዴ ጤና ቢስና የሞት ሽታ ያዘለ ሊሆን ይችላል። ያም ሆኖ የኢትዮጵያዊነትን ትምህርት ጠብቀው አገራቸውን ሊወዱ ይችላሉ። ኢትዮጵያውያን በገቢር የሚወዱት የኢትዮጵያን መልክዓ ምድራዊ ውበት ወይም በሥርዓቶችና ሕጎች ላይ የተመሠረተውን ያን ‹የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፓብሊክ› የተባለ ፖለቲካዊ ፈትል ብቻ አይደለም። ከሁሉም በላይ የሚወዱት ታሪካዊ ዕጣ ፈንታቸው ኢትዮጵያ ከተሰኘችው አገር ጋር በአንድ ላይ የተገመደውን ሴቶችና ወንዶች ነው። በርካታ ሴቶችና ወንዶች በዓድዋም ይሁን በባድሜ፣ በጋሸናም ይሁን በጭፍራ ራሳቸውን መስዋዕት ያደረጉት እነዚህ እህቶቻቸውና ወንድሞቻቸው በሰላም እንዲኖሩ ነው። ሲሰውም ‹ለትግሬ፣ ለአማራ፣ ለኦሮሞ ወይም ለአፋር ብዬ ነው የሚሰዋው’ እንዳላሉ እርግጠኛ ነኝ። የተሰውት ኢትዮጵያ የምትባል አገር እንድትኖር ነው።
ስለሆነም በኢትዮጵያ የሚገኙ የተወሰኑ ቡድኖች (ለምሳሌ አማራና ኦሮሞ) የጋራ ምንጭና ማንነት እንዳላቸው ለማረጋገጥ መፍጨርጨር ሌሎችን የሚያገል ብቻ ሳይሆን ፋይዳ ቢስ አካሄድ ነው። እንዲህ ያለው ትርክት የማይጠቅም ከመሆኑም ባሻገር፣ ራሳቸውን በአንድ አገረ መንግሥት ሥር ያዋቀሩ የልዩ ልዩ ቡድኖችን አንድነት አሊያም አንድ የሆኑ ልዩ ልዩ ቡድኖችን ብዝኃነት የሚረብሽና ለአምባጓሮ ምክንያት ሊሆን የሚችል በመሆኑ አደገኛም ጭምር ነው። ጆርጅ ሳንታናያ ‹‹ከታሪክ የማይማሩ፣ ታሪክን እንዲደግሙ ተረግመዋል›› እንዳሉት፣ ገንቢ ያልሆነን ታሪክ ለመድገም መሻት የለብንም። ላለፉት ሁለት ሺሕ ዓመታት ኢትዮጵያ ተቆጥሮ የማይዘለቅ አስቃቂ ፍዳ አሳልፋለች። ከእነዚህ ፍዳዎች ልንማር ያስፈልጋል እንጂ፣ አስተሳሰባችን ልክ እንደሆነ ለማሳየት ወይም ለርዕዮተ ዓለማችን ስኬት ስንል እነዚያን ለፍዳችን ምክንያት የሆኑትን ነገሮች ልንደግማቸው አይገባም። ጤናማ በሆነ መልኩ ብዝኃነታችንን ተቀብለን፣ ማንነታችንን የሚገልጹ ቋንቋዎቻችንና ባህሎቻችንንም ጤናማ በሆነ መንገድ እያከበርን ሁሉን አቀፍ በሆነ ትርክት ሥር በመሆን በአንድነት ‹‹ኢትዮጵያ አንድ ናት፣ ኢትዮጵያውያንም ሁሉ እህትማማቾችና ወንድማማቾች ናቸው!›› ብለን ልናውጅ ይገባል።
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡.