በአገር አቀፍ ደረጃ ብሔራዊ ምክክር ለማድረግ የሚረዳ ኮሚሽን ለመመሥረት በቅርቡ አዋጅ መፅደቁ ይታወሳል፡፡ ኮሚሽኑን የሚመሩ ኮሚሽነሮችን ለመሰየም የዕጩዎች ጥቆማ ቀነ ገደብም ተጠናቋል፡፡ የተለያዩ ፖለቲካዊ ዓላማዎችና ሐሳቦች ያሏቸው ፖለቲከኞችና የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ በብሔራዊ ጉዳዮች ላይ የሚኖሯቸውን ልዩነቶች በመያዝ በሠለጠነ መንገድ ለመነጋገርና ለመግባባት ምክክሩ አስፈላጊ ነው፡፡ ሒደቱ ሕዝባዊ አካታችነቱ ሲጠበቅ ደግሞ፣ ለማመን የሚያዳግት አዎንታዊ ውጤት ይገኝበታል፡፡ ይህ እንዲሳካ ግን ዴሞክራሲያዊ ባህል መላበስ ይገባል፡፡ ዴሞክራቶች በሌሉበት ስለዴሞክራሲ መነጋገር አዳጋች ነውና፡፡ ዴሞክራሲ በሰረፀባቸው አገሮች ውስጥ ከግጭት ይልቅ ውይይት፣ ከመጠላለፍ ይልቅ ክርክር፣ ከሐሜትና ከአሉባልታ ይልቅ ድርድር ትልቅ ቦታ ይሰጣቸዋል፡፡ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች ዋስትና የሚኖራቸው በዚህ መንገድ መጓዝ ሲቻል ነው፡፡ ብዙዎቹ የሠለጠኑ አገሮች ዴሞክራሲንና የሰብዓዊ መብት ጥበቃን የውጭ ፖሊሲያቸው ማዕከላዊ ነጥብ የሚያደርጉዋቸው፣ የሰው ልጆች ነፃነት ማረጋገጫ መሣሪያዎች በመሆናቸው ነው፡፡ ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ ምድር ሊሰርፅ የሚችለው መብትን በመጠቀም መነጋገር ሲለመድ ነው፡፡ በዴሞክራሲ የሚመራ አገር ሰላማዊ፣ አፈናን የማይቀበል፣ የዜጎችን መብት የሚያስከብር፣ የመደራጀት መብት የሚፈቅድ፣ ሰብዓዊ ቀውሶችንና ግጭቶችን የሚያስወግድና የአገርን ብሔራዊ ክብር የሚጠብቅ ነው፡፡
በኢትዮጵያ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ውጥኖች ከተጀመሩ ግማሽ ክፍለ ዘመን ቢያስቆጥሩም፣ አሁንም ሒደቱ እጅግ አስቸጋሪና ውጣ ውረድ የተሞላበት ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ብሔራዊ ምክክር ለማድረግ አስቻይ ሁኔታ ለመፍጠር፣ አሁንም መተማመን ስለሌለ ቅድመ ሁኔታዎችን የማስቀደም ምልክቶች እየታዩ ነው፡፡ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ደም በፈሰሰባት አገር ውስጥ፣ ሰላምና መረጋጋት አምጥቶ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ዛሬም እንቅፋት አለ፡፡ ብሔራዊ ጉዳዮችን ማዕከል በማድረግ ልዩነቶችን ከማጥበብ ይልቅ፣ ማዶ ለማዶ እየተያዩ ጣት መቀሳሰር አልቆመም፡፡ በሰላማዊ መንገድ በሕዝብ ተሳትፎ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት እንደሚቻል እየታወቀ፣ ከዚያ በተቃራኒ የግለሰቦችና የቡድኖች ፍትጊያ ለሰላም ጋሬጣ እየሆነ ነው፡፡ ልዩነት በተፈጠረ ቁጥር ገዥው ፓርቲና ተፎካካሪዎቹ መፋጠጣቸው የተለመደ በመሆኑ፣ በሰላማዊ መንገድ መፈታት ያለባቸው ጉዳዮች ወደ ግጭትና ትርምስ ያመራሉ፡፡ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ያለው ልምድና ፍላጎት በጣም አናሳ ስለሆነ፣ ጎራ ለይቶ ለመተናነቅ ማድባት ሊገላገሉት ያልቻለ በሽታ ነው፡፡ አሉባልታ፣ ሐሜት፣ አሽሙር፣ ስድብና አላስፈላጊ ድርጊቶች ከፖለቲከኞች አልፈው ወደ ዜጎች እየተዛመቱ፣ መብትን ተጠቅሞ በሥርዓት መኖር አልተቻለም፡፡
ፖለቲከኞች ገና ከመነሻው በሰላማዊ መንገድ መነጋገር ቢለማመዱ ኖሮ ይህ ሁሉ ችግር አይፈጠርም ነበር፡፡ ምክንያቱም ማንኛውም ልዩነት በምክክር ማዕቀፍ ውስጥ ተከባብሮ መሄድ ይችላልና፡፡ ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን ለማቋቋም ጥረት ከተጀመረ ወዲህ ያለው ሒደት ሲታይ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ሥር የሰደደው ያለ መተማመን መንፈስ በገሃድ እየታየ ነው፡፡ ከኮሚሽነሮች ጥቆማ እስከ ምክክሩ ዓለም አቀፋዊ መስፈርት ማሟላት ድረስ ያለው እንቅስቃሴ፣ በምክክር እንዲከናወን ለማድረግ የሚታየው ዳተኝነት ብዙ የሚናገረው አለው፡፡ ለምክክሩ ጅማሮ ማማር መነጋገር ለምን አይፈለግም? የአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር ታሪክ ጠላትነትን እንጂ ወዳጅነትን ስለማያበረታታ፣ በእያንዳንዱ ብሔራዊ ጉዳይ ላይ ለመነጋገር አልተቻለም፡፡ አሁን ግን ከዚያ ድባቴ ውስጥ በመውጣት ለብሔራዊ ምክክሩ ጅማሮ ስኬት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይህ አስተዋፅኦ ለተወሰኑ ቡድኖች ወይም ግለሰቦች የሚተው ሳይሆን፣ ለኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ሲባል ግዴታ እንደሆነ መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከጨለማ ወደ ብርሃን የምትሸጋገረው ዜጎች መብታቸውን ሲጠቀሙ ነው፡፡
ብሔራዊ ምክክር በጠላትነት እየተያዩ የመጠፋፋት ስሜትና ፍላጎትን ለመቀነስና ለማስወገድ ይረዳል፡፡ ብሔራዊ ምክክሩ ሕዝቡ ውስጥ በስፋት እየተዳረሰ ሁሉን አቀፍ ውይይቶችን ማድረግ ሲለመድ፣ እንደ በፊቱ ጀርባ እየተሰጣጡ በነገር መፈላለግ ወይም እርስ በርስ ለመፋጀት ቀላል ሰበብ አይኖርም፡፡ ‹‹ልዩነት ለዘለዓለም ይኑር›› በሚባለው የዴሞክራሲያዊነት መርህ መሠረት፣ የተለየ ሐሳብን ማክበርና መከራከር ብሔራዊ ልማድ ይሆናል፡፡ ሥልጣነ መንበሩ ላይ የተቀመጠው ኃይል እንዳሻው ፈላጭ ቆራጭ እንዳይሆን፣ ብሔራዊ ምክክሩ እንደ ልጓም የማገልገል ዕድሉ ይሰፋል፡፡ ‹‹ሥልጣን በራሱ ዕውቀት ነው›› ብለው የሚያስቡ ጭምር እንዲጠነቀቁ ያግዛል፡፡ በተለይ ሴቶችና ወጣቶች በብሔራዊ ምክክሩ ውስጥ የሰፋ ሚና ሲኖራቸው፣ ጉልበት አምላኪዎችና መሰሎቻቸው ከሕገወጥ ድርጊቶቻቸው ይታቀባሉ፡፡ ብሔራዊ ምክክሩ ሁሉን አካታች ሆኖ ለአገር ዘርፈ ብዙ ችግሮች መፍትሔ የሚገኝበት መደላድል እንዲሆን፣ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች በሙሉ ተሳትፏቸው እንዳይገታ መበርታት አለባቸው፡፡ በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው እንግዳ የማይሆንበት ሥርዓት የሚፈጠረው፣ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ መብትን ተጠቅሞ ተሳትፎን ማሳደግ ሲቻል ነው፡፡ ከዚህ ውጪ መብትን በችሮታ ለማግኘት መሞከር በራስ ላይ መቀለድ ነው፡፡
የዴሞክራሲ ጽንሰ ሐሳብ ተግባራዊ በሆነባቸው አገሮች ዜጐች በነፃነት የፈለጉትን የመምረጥ መብት ስላላቸው፣ ተመራጮች ለሕዝብ ያላቸው ከበሬታ ከምንም ነገር በላይ የላቀ ነው፡፡ ነገር ግን ለመድበለ ፓርቲ ሥርዓትና ለሕግ የበላይነት ዋጋ በማይሰጥባቸው አገሮች ደግሞ ግጭቶች ስለሚፈጠሩ ለአምባገነንነት በር ይከፈታል፡፡ ይህ የሚሆነው ደግሞ ለአገር የማያስቡ፣ ተቀናቃኞችን ከፖለቲካ ምኅዳሩ ሲያገሉና አንዱን ወገን በሌላው ላይ በብሔርና በእምነት ተከልለው ሲያነሳሱ ነው፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነት በጎደለው ሥርዓት ውስጥ ዴሞክራሲ ከማበብ ይልቅ የሚጫጫው፣ ፖለቲከኞች የዴሞክራሲን መሠረታዊ ሐሳብ እያጣመሙ በመተርጎም ወደ ተቃራኒ አቅጣጫ ስለሚገፉት ነው፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ልዕልና ሲባል በአገር ጉዳይ ተሳትፎ አይገደብ፡፡ ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ ከ115 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ይኖርባታል ተብሎ በሚገመትባት ኢትዮጵያ ውስጥ፣ በርካታ ፍላጎቶች መኖራቸው መዘንጋት የለበትም፡፡ እነዚህን ፍላጎቶች አግባብቶና አማክሎ መሄድ የሚቻለው ዴሞክራሲን በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ማስቀጠል ሲቻል ነው፡፡ ዴሞክራሲ የዜጎች በነፃነት የመምረጥ መብት ነው፡፡ ዴሞክራሲ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ነው፡፡ ዴሞክራሲ የመቃወምና የመደገፍ መብት ነው፡፡ ዴሞክራሲ ዜጐች በእኩልነት የሚስተናገዱበት መብት ነው፡፡ ዴሞክራሲ ሰብዓዊ መብቶች የሚከበሩበት ነው፡፡ ዴሞክራሲ የሕግ የበላይነት የሚሰፍንበት ነው፡፡
በእርግጥ ዴሞክራሲ በሒደት የሚያድግና የሚያብብ ቢሆንም፣ በሕዝብ የነቃና የጎላ ተሳትፎ ነው ተግባራዊ የሚሆነው፡፡ ዴሞክራሲ የተጓደለበት ማኅበረሰብ አየር እንደተነፈገ ስለሚቆጠር፣ ያለ ዴሞክራሲ የትም መድረስ አይቻልም፡፡ በኢትዮጵያ ዴሞክራሲ የተሟላ ሥርዓት መሆን የሚችለው፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ በቀጥታም ሆነ በትክክለኛ ተወካዮቹ አማካይነት በአገሩ ጉዳይ መነጋገር ሲችል ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ብሔራዊ ምክክሩን የሚያስተናግደውን ኮሚሽን የሚመሩ ሰዎች የሕዝብ አመኔታና ተቀባይነት ሲኖራቸው ነው፡፡ ከትምህርት ዝግጅት፣ ከሥራ ልምድ፣ ከሥነ ምግባርና መሰል ተፈላጊ መስፈርቶች በተጨማሪ የአገር ፍቅር ያላቸው ሰዎች አስፈላጊ ናቸው፡፡ ራሳቸውን ከአገር ጥቅምና ህልውና በታች የሚያዩ፣ ሰዎችን በሰብዓዊ ፍጡርነት እንጂ በማንነትና በሌሎች ልዩነቶች የማያስተናግዱ፣ በኢትዮጵያ ሁሉንም ወገኖች ሊያግባባ የሚችል ሥርዓት እንዲገነባ ፅኑ ፍላጎት ያላቸው፣ ለዚህም ስኬት ሲሉ በፈቃደኝነት ኃላፊነት ለመረከብ ዝግጁ የሆኑ ሰዎች ያስፈልጋሉ፡፡ በአገር ጉዳይ ‹‹ገለልተኛ የሆነ/ች›› የሚባል መስፈርት ፈፅሞ መቅረብ ስለሌለበት፣ አገራቸውን ለማገልገል ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎች የሚጠበቅባቸው ለሕግና ለህሊናቸው ታማኝ መሆን ብቻ ነው፡፡ ለብሔራዊ ምክክር የሚደረገው ዝግጅት ሁሉን አካታች መሆን የሚችለው፣ መብትን በአግባቡ ለመገልገል ቁርጠኝነት ሲኖር ነው!