Sunday, October 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ፋብሪካዎች ለመስኖ ግድብ ፕሮጀክቶች 802 ሺሕ ኩንታል ሲሚንቶ በአስቸኳይ እንዲያቀርቡ ታዘዙ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በቆላማው የአገሪቱ ክፍሎች የሚደረጉ የመስኖ ግድብ ግንባታዎች የገጠማቸውን የሲሚንቶ እጥረት ለመፍታትና በፍጥነት እንዲጠናቀቁ ለማድረግ፣ ለፕሮጀክቶቹ የሦስት ወራት የሲሚንቶ ምርት ፍላጎት 802,972 ኩንታል ሲሚንቶ በአስቸኳይ እንዲቀርብ ታዘዘ።

በዚህም መሠረት ሁሉም ሲሚንቶ ፋብሪካዎች ቅድሚያ ሰጥተው የተገለጸውን መጠን የሲሚንቶ ምርት የጥር ወርን ጨምሮ ለሦስት ወራት የመስኖ ግድብ ግንባታዎቹን ለሚያከናውኑ ሥራ ተቋራጮች፣ በቀጥታ እንዲሸጡ የማዕድን ሚኒስቴር ሰኞ ጥር 16 ቀን 2014 ዓ.ም. ማሳሰቢያ ሰጥቷል። 

በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እየተገነቡ የሚገኙ 19 የመስኖ ግድብ ፕሮጀክቶች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ ለማድረግ፣ ከጥር ጀምሮ እስከ መጋቢት ድረስ የሚያስፈልጋቸውን የሲሚንቶ ፍጆታ ሁሉም የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ቅድሚያ በመስጠት ፕሮጀክቶቹን ለሚያከናውኑ ኮንትራክተሮች በቀጥታ ከፋብሪካ ሽያጭ እንዲፈጽሙላቸው መወሰኑን፣ የማዕድን ሚኒስትሩ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) ለሲሚንቶ አምራቾች ዘርፍ ማኅበር በጻፉት ደብዳቤ አሳስበዋል። 

ሚኒስትሩ በጻፉት ደብዳቤ በአገሪቱ 19 የመስኖ ግድብ ግንባታዎች የሚያከናውኑ ኮንትራክተሮችን ማንነትን፣ እንዲሁም እያንዳንዱ ኮንትራክተር ከጥር ወር ጀምሮ እስከ መጋቢት ወር ድረስ የሚያስፈልገውን የእያንዳንዱን ወር የሲሚንቶ ፍላጎት በመጥቀስ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በዚሁ መሠረት እንዲያስተናግዷቸው አሳስበዋል።

የማዕድን ሚኒስትሩ ይህንን ማሳሰቢያ የሰጡት ከመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር በቀረበ ጥያቄ መሠረት ሲሆንሚኒስትሩ በቀረበው ጥያቄ ዙሪያም ከመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትሯ አይሻ መሐመድ (ኢንጂነር) ጋር በመሆን ከሲሚንቶ አምራቾች ጋር ጥር 16 ቀን ተወያይተዋል።

ይህንንም ተከትሎ የማዕድን ሚኒስትሩ፣ ‹‹በቆላማው የአገሪቱ ክፍሎች የሚደረጉ የመስኖ ግድብ ግንባታዎች የገጠማቸውን የሲሚንቶ እጥረትን በተመለከተ ጥር 16 ቀን 2014 ዓም ከመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትሯ አይሻ መሐመድ (ኢንጂነር) ጋር በመሆን፣ ከሲሚንቶ አምራቾች ጋር ውይይት አድርገናል፡፡ የመስኖ ግድብ ግንባታዎች እንዳይቆራረጡና በተገቢው ፍጥነት እንዲጠናቀቁ ለማስቻል ግንባታውን የሚያከናውኑ ተቋራጮች ሲሚንቶ በቀጥታ ከፋብሪካዎች እንዲወስዱ ማድረግ በሚቻልበት ላይከአምራቾቹ ጋር መግባባት ላይ ደርሰናል፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የሲሚንቶ ምርት አቅርቦትና ፍላጎት ባለመመጣጠኑ በምርቱ ላይ ከፍተኛ የዋጋ ንረት እየተስተዋለ ሲሆን፣ 19 የመስኖ ግድብ ፕሮጀክቶች በቅድሚያ እንዲቀርብ መወሰኑ በገበያው ላይ የሚታየውን የዋጋ ንረት ሊያባብሰው እንደሚችል ሥጋት ፈጥሯል። 

የመስኖ ግድብ ፕሮጀክቶችን ለሚያከናውኑት ኮንትራክተሮች የሦስት ወራት የሲሚንቶ ፍላጎት ቅድሚያ ተሰጥቶ እንዲሸጥ የተባለው የሲሚንቶ ምርት ለታለመለት ዓላማ መዋሉን፣ የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ሚኒስቴር እንደሚከታተልና እንዲሚያረጋግጥ የማዕድን ሚኒስትሩ በጻፉት ደብዳቤ ላይ ግልባጭ አድርገዋል።

19 የመስኖ ግንባታ ፕሮጀክቶች የሦስት ወራት የሲሚንቶ ምርት ፍላጎት ቅድሚያ እንዲሰጥ መባሉ የፕሮጀክቶቹ በፍጥነት መጠናቀቅ ከሚኖረው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ አንፃር ተገቢ ቢሆንምየሲሚንቶ ንግድ ሥርዓት ላይ ያለው አሻጥርና ውስብስብ አሠራር ምክንያታዊ ያልሆነ ከፍተኛ የዋጋ ንረት እያስከተለ እንደሆነ ይነገራል።

የማዕድን ሚኒስቴርም ይህንን ችግር ለመቅረፍ በጥናት ላይ የተመሠረተ የመፍትሔ ዕርምጃ መውሰድ መጀመሩን፣ ሪፖርተር ከሚኒስቴሩ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ከሲሚንቶ አከፋፋዮች (ኤጀንቶች) ጋር በመሠረቱት ጤናማ ያልሆነ የንግድ ግንኙነት ወደፊት ለሚያመርቱት የሲሚንቶ ምርት ክፍያ ተቀብለው የሽያጭ ውል የሚገቡመሆኑ፣ በጥናት ከተለዩት ችግሮች መካከል ለአብነት የሚጠቀስ እንደሆነ የማዕድን ሚኒስቴር ይገልጻል። 

የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው አራት የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ብቻ ክፍያ ተቀብለው፣ ያላቀረቡት ውዝፍ የሲሚንቶ ምርት ዕዳ ከ2.6 ሚሊዮን ቶን በላይ ነው። 

የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ቀድመው ገንዘብ የተቀበሉበት 2.6 ሚሊዮን ቶን በላይ ውዝፍ የሲሚንቶ ዕዳ ያለባቸውመሆኑ ሌሎች ተጠቃሚዎች የሲሚንቶ ምርት ለማግኘት ረዥም ጊዜ እንደሚወስድባቸው፣ ጤናማ ያልሆነው ይህ የንግድ ግንኙነትም ለሲሚንቶ ምርት ዋጋ መናር ቀጥተኛ ተፅዕኖ እያሳረፈ እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል። 

በዚህም ምክንያት የማዕድን ሚኒስቴር ከሁለት ሳምንት በፊት ለሲሚንቶ አምራቾች ጥብቅ ማሳሰቢያ ሰጥቷል። 

ሚኒስቴሩ የሰጠው ማሳሳቢያም ሁሉም የሲሚንቶ አምራች ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው በማምረት፣ ውዝፍ የሲሚንቶ ሽያጭ ዕዳቸውን ከምርታቸው ጋር በማመሳከር እንዲያስተካክሉ የሚል ነው። 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች