Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናምርጫ ቦርድ የተሳተፈበት የኢትዮጵያ ፌዴራል ጠበቆች ማኅበር ተመሠረተ

ምርጫ ቦርድ የተሳተፈበት የኢትዮጵያ ፌዴራል ጠበቆች ማኅበር ተመሠረተ

ቀን:

  • ባለፉት 80 ዓመታት ያልታየና ሁሉንም የሕግ ባለሙያዎች ያስደመመ ተብሏል

ላለፉት 80 ዓመታት ማለትም ዘመናዊ የፍርድ ቤት ውሎና ሙግት ከተጀመረበት ከ1934 ዓ.ም. ጀምሮ ያልታየና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ልምዱን ያካፈለበት፣ ‹‹የኢትዮጵያ የፌዴራል ጠበቆች ማኅበር›› ጉባዔና ምሥረታ ጥር 15 ቀን 2014 ዓ.ም. ተካሄደ፡፡

የፌዴራል የጥብቅና ፈቃድ አገልግሎት አሰጣጥና አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1249/2013 አንቀጽ 57(1) ድንጋጌ መሠረት ተግባራዊ በተደረገው ጉባዔ፣ የረዥም ጊዜ የዳኝነት ልምድ ያላቸው ወ/ሮ ስንዱ ዓለሙ ፕሬዚዳንት ሆነው ሲመረጡ፣ ወጣቱ የሕግ ባለሙያ አቶ ቴዎድሮስ ጌታቸው ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ተመርጠዋል፡፡

በተሰጠው ሚስጥራዊ የድምፅ አሰጣጥ ሒደት በተቀራረበ ድምፅ አንገት ለአንገት ተያይዘው የተመረጡ ሰባት የማኅበሩ ሥራ አስፈጻሚ አባላት ደግሞ ወ/ሮ ሒሩት መሰለ፣ አቶ ፊልጶስ ዓይናለም፣ አቶ ሊቁ ወርቁ፣ አቶ ዮሴፍ አዕምሮ፣ ሆሳና ነጋሽ፣ ወ/ሮ ትደነቂያለሽ ተስፋና አቶ ሰለሞን ዕምሩ ናቸው፡፡

ዘመናዊ የፍርድ ቤት ሒደትና ሙግት ከተጀመረበት 1934 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ ሁኔታዎች የሕግ ባለሙያዎች የሙግት ሥራቸውን ሲያካሂዱ ከመቆየታቸው ባለፈ፣ ሁሉንም ባለሙያዎች በሕግ አስገዳጅነት አባል ያደረገ የጠበቆች ማኅበር ተመሥርቶ እንደማያውቅ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሙያው ባለቤቶች ተናግረዋል፡፡

ታሪካዊና ላለፉት 80 ዓመታት ታይቶ በማያውቅ ሁኔታ፣ ዴሞክራሲያዊ ሒደትን በተከተለ ሚስጥራዊ የድምፅ አሰጣጥ ሒደት የተካሄደው፣ ‹‹የኢትዮጵያ የፌዴራል ጠበቆች ማኅበር›› ምሥረታና ጠቅላላ ጉባዔ ሴት ጠበቆችንም ያሳተፈ ነበር፡፡

በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲታደሙበት ‹‹አየሁ›› የማይለው የኢንተር ሌግዠሪ ሆቴል ከአፍ እስከ ገደፉ ጢም ብሎ ሲታይ፣ አንድ የሙያ ማኅበር ለማቋቋምና ጠቅላላ ጉባዔ ለማካሄድ የተገኙ ባለሙያዎች የታደሙበት ስብሰባ ሳይሆን፣ በመንግሥት ጥብቅ ማሳሰቢያ የተጠሩና መቅረትም ከባድ ቅጣት እንደሚያስወስድ ተነግሮት የተሰበሰበ ሕዝብ ይመስል እንደነበረ አስተያየታቸውን የሰጡ ባለሙያዎች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ጉባዔው የተጠራው ከስድስት ወራት በፊት በፀደቀው የፌዴራል የጥብቅና አገልግሎት ፈቃድ አሰጣጥና አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1249/2013 አንቀጽ 57(1) ድንጋጌ መሠረት በፍትሕ ሚኒስቴር አማካይነት ሲሆን፣ የፌዴራል ጥብቅና የወሰደ በመላው የኢትዮጵያ ክልሎች የሚገኙ የሕግ ባለሙያዎችን በአባልነት የሚያካትት ነው፡፡

አንድ የጥብቅና ፈቃድ ያወጣ የሕግ ባለሙያ ተመዘገበም ወይም አልተመዘገበም፣ ‹‹የኢትዮጵያ ፌዴራል ጠበቆች ማኅበር›› አባል መሆን ግዴታው እንደሆነ በአዋጁ ከመደንገጉም በተጨማሪ፣ የሕግ ባለሙያዎችም በጉጉት ይጠብቁት ስለነበር በዕለቱ ጥር 15 ቀን 2014 ዓ.ም. በጉባዔው የታደሙ አባላት ከ1,600 በላይ እንደነበሩ ታውቋል፡፡

ወ/ሮ ስንዱ ዓለሙና አቶ ቴዎድሮስ ጌታቸው

በዕለቱ በክብር እንግድነት የተገኙት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሰለሞን አረዳ ባደረጉት ንግግር፣ ‹‹የዳኝነት ሥርዓቱን ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት፣ ፍርድ ቤቶቹ አብረው ይሠራሉ፤›› ብለዋል፡፡ ማኅበሩ የዳኝነት ነፃነትን ማስጠበቅ፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ማከናወንና የዳኝነት አካሉ ከማንኛውም አካል ጫና ሲደርስበት የተቃውሞ ድምፁን በማሰማት፣ ለዳኝነት ነፃነት መከበር ሕጋዊ ዕርምጃዎችን በመውሰድ ቁርጠኝነቱን ሊያሳይ እንደሚገባም አቶ ሰለሞን አሳስበዋል፡፡

በማኅበሩ መቋቋምና በታሪኩ የመጀመርያ በሆነው የጠቅላላ ጉባዔ ሒደትና ምርጫ የተሰማቸውን ደስታ በመግለጽ ንግግር ያደረጉት ደግሞ፣ የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ሲሆኑ፣ ‹‹ማኅበሩ የተጣለበትን ኃላፊነት በብቃት በመወጣት፣ የጥብቅና ሙያ የተከበረ ሙያ እንዲሆን፣ በብቃታቸውና በሥነ ምግባራቸው ስመ ጥር የሆኑ ጠበቆች እንዲበዙና ጎልተው እንዲወጡ፣ የሚመሩት ተቋም በቅርበት አብሮ ለመሥራት ፈቃደኛና ዝግጁ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የፌዴራል ጠበቆች ማኅበር ጉባዔ ላይ ከ40 ዓመታት በላይ አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩ ባለሙያዎች የታደሙ ሲሆን፣ በክልሎች (ከትግራይ ክልል በስተቀር) የሚገኙ የጠበቆች ማኅበራት ተወካዮች፣ የክልሎች የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንቶችና ጠቅላይ ዓቃቤያነ ሕግ ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡

የሕግ አገልግሎት ሥራ በነበረበት የሚቀጥል ስላልሆነና የጥብቅና ፈቃድ ሲታደስም ክፍያ ብቻ በመክፈል የሚታደስ ባለመሆኑ፣ በጥብቅና ሙያ ላይ ለተሰማሩ ከ1,500 በላይ ባለሙያዎች ሥልጠና መስጠቱም ታውቋል፡፡

በአጠቃላይ ጉባዔው ከ98 በመቶ በላይ ወንዶች የታደሙበት ቢሆንም፣ በጣት የሚቆጠሩ ሴት ጠበቆች መሀል የማኅበሩ ፕሬዚዳነት ሴት ሆነው በመመረጣቸው፣ ሴት ጠበቆች ደስታቸውን ገልጸዋል፡፡

ምርጫው የተሻለና ለሌሎችም ተቋማት ምሳሌ እንዲሆን በማሰብ፣ ስለምርጫ ሒደቱ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ልምዱን ማካፈሉንና ባለሙያዎች መድቦ የተሳካ ምርጫ እንዲሆን ከፍተኛ ዕገዛ ማድረጉን በምክትል ፕሬዚዳንትነት የተመረጡት ወጣቱ ጠበቃ አቶ ቴዎድሮስ ተናግረዋል፡፡ የጉባዔውን ጠቅላላ ወጪ በአዋጁ በተደነገገው መሠረት ፍትሕ ሚኒስቴር መሸፈኑም ታውቋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...