Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበብሔራዊ ምክክሩ ላይ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት እንዳይኖር ተጠየቀ

በብሔራዊ ምክክሩ ላይ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት እንዳይኖር ተጠየቀ

ቀን:

የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን አዋጅ ታኅሳስ 20 ቀን 2014 ዓ.ም. ከፀደቀ በኋላ፣ በቅርቡ ኮሚሽነሮች ይመረጡለታል ተብሎ በሚጠበቀው አገራዊ ምክክር ኮሚሽንም ሆነ ሒደቱ ላይ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት እንዳይኖር ተጠየቀ፡፡

የጉድ ገቨርናንስ አፍሪካ-ምሥራቅ አፍሪካ (Good Governance AfricaEastern Africa) የተሰኘው መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋም፣ ‹‹ምርጫ 2013 እና የድል ኃላፊነት›› በሚል ርዕስ አንጋፋ ምሁራን የተገኙበት ውይይት ጥር 19 ቀን 2014 ዓ.ም. አካሂዷል፡፡ ለውይይቱ መነሻ የሚሆኑ ጽሑፎች የአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ መምህራን በሆኑት ዮናስ አሽኔ (ዶ/ር) እና ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል፡፡

በውይይቱ ላይ የተገኙት ጎምቱው የታሪክ ተመራማሪ ባህሩ ዘውዱ (ኤመረተስ ፕሮፌሰር) በበኩላቸው፣ ብሔራዊ ምክክሩ ሙሉ ለሙሉ ከመንግሥት ጣልቃ ገብነት ነፃ መሆን እንዳለበትና በሒደቱ ውስጥም መንግሥት እጁን የሚያስገባ ከሆነ ምክክሩ የመበላሸት አዝማሚያ እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ብሔራዊ ምክክሩ የብዙኃን ተሳትፎ ሊኖረው እንደሚገባና የልሂቃን ተሳትፎ አስፈላጊ ቢሆንም፣ ውሳኔ የመስጠት ሒደቱ በብዙኃኑ እጅ ላይ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል፡፡  

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

‹‹በብሔራዊ ምክክሩ የሚሳተፉ በሙሉ በኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት የሚያምኑ መሆን አለባቸው፤›› ብለዋል፡፡ የታሪክ ተመራማሪው ይህንን ሲያብራሩም፣ ኢትዮጵያን የማፍረስ አጀንዳ መቅረት እንዳለበት ተናግረው፣ ከዚህም በተጨማሪ ተሳታፊዎች በአመፅ የሚደረግ ትግልን የተው መሆን እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡

ባህሩ (ኤመረተስ ፕሮፌሰር) የምክክሩ ተሳታፊዎች በሰላማዊ ትግል፣ በክርክርና በሐሳብ የበላይነት ማሸነፍን የሚቀበሉ የመሆናቸውን ጉዳይ ያሰመሩበት ሲሆን፣ ‹Liberation Front› (የነፃነት ግንባር) የሚባል ነገር መቅረት አለበት፡፡ እስከ መቼ በግንባር ስንፋጭ እንኖራለን?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

በውይይቱ ላይ ሐሳባቸውን ያካፈሉት ተሳታፊ የብሔራዊ መግባባት ሒደቱ እየሄደበት ያለው ፍጥነት አሳሳቢ እንደሆነ ገልጸው፣ ‹‹በመንግሥት የሚመራ መሆኑም እምነትን ያጎድላል፤›› ብለዋል፡፡

በጥቅምት 2013 ዓ.ም. ተጀምሮ እስካሁን መቋጫ ያላገኘው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ርዕዮተ ዓለማዊ (Ideological) መሠረት የሌለውና በባህሪውም ከጦርነት ይበልጥ ጥፋትና አመፅን ያስተናገደ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በዓለም ላይ የሚደረጉና ምክንያታዊ መሠረት ላይ የሚቆሙ ጦርነት ወይም አመፃዎች፣ አብዮት ያመጣቸው ወይም ቅኝ ግዛትን ጥሎ ነፃነትን ለመጎናፀፍ አልያም ማኅበራዊ ንቅናቄን ተከትለው የሚመጡ ቢሆኑም፣ ከተጀመረ አንድ ዓመት ያለፈው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ግን ከእነዚህ ዓይነት መሠረቶች አንዱንም መነሻ ያላደረገና የመሪዎች ሕዝበኝነት (Populism) ያመጣው መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

‹‹ከግጭት ወደ ውይይት፡- አገራዊ መግባባትን የመፍጠር አስፈላጊነት፣ ሒደትና ታሳቢዎች›› በሚል ርዕስ የውይይት መነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፋዊ ግንኙነት መምህር ዮናስ አሽኔ (ዶ/ር)፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት ሲታዩ የነበሩ ግጭት፣ መፈናቀልና ግድያዎች በአገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ኢሰብዓዊ ሁኔታዎች እንዲታዩ ማድረጋቸውን አስረድተዋል፡፡ አሁን እየተደረገ ያለው ጦርነትም ቢሆን በባህሪው ከጦርነት ያለፈ፣ ብዛት ያለውና በቡድን የሚደረግ አስገድዶ መድፈር የመሳሰሉ ኢሰብዓዊ ድርጊቶች ጎልተው የታዩበት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

እንደ ዮናስ (ዶ/ር) ገለጻ፣ ጦርነቱ አሁን ከተቀሰቀሰበት ምክንያት የዘለሉና በአገሪቱ ዘመናዊ ሥርዓተ መንግሥት ግንባታ ላይ የተፈጠሩ ቁስሎችም የወለዱት ነው፡፡ በ1960ዎቹ ከነበረው የተማሪዎች ንቅናቄ የመጡ ውርሶችም ለዚሁ ጦርነት መንስዔ ሆነዋል ብለዋል፡፡

ጽሑፍ አቅራቢው ጎምቱውን የታሪክ ተመራማሪ ባህሩ (ኤመረተስ ፕሮፌሰር) ጠቅሰው የተማሪዎች ንቅናቄ፣ ለውጥ ወይም ፍላጎትን ፅንፍ በያዘና አመፅ በተሞላበት መንገድ ማምጣት በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ባህል እንዲሆን ማድረጉን አብራርተዋል፡፡

ከተማሪዎች እንቅስቃሴ ውስጥ የወጡትና ኋላ ኢሕአዴግን መሥርተው ሥልጣንን የያዙት አካላትም በሥልጣን ዘመናቸው አመፅን እንደ ፖለቲካዊ መሣሪያ ሲጠቀሙ መቆየታቸውን ያስረዱት ዮናስ (ዶ/ር)፣ ከዚህም ባሻገር ኢሕአዴግ በውስጡ መከፋፈል የነበረው መሆኑ ሥርዓቱ ‹‹እንዲበሰብስ›› (Decay) ሚና እንደነበረው ተናግረዋል፡፡ ይሁንና ‹‹የበሰበሰው›› ሥርዓትን ከመውደቅ ይልቅ ገው ፓርቲ እየመራ ለውጥ ወደ የሚያመጣበት አካሄድ (Transition by Transformation) መለወጡን ገልጸዋል፡፡ ይህ ሒደት አዲሱ ለውጥ የቀድሞውን ሥርዓት ችግሮች እንዲሸከምና በዚህም ምክንያት ጦርነት ውስጥ እንዲገባ ማድረጉን ዮናስ (ዶ/ር) በጽሑፋቸው አብራርተዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ አገሪቱ ውስጥ ትርክት ላይ የተመሠረተ አመፅ (Discursive Violence) እንዳለና ከትርክቶቹ ውስጥም ቀዳሚው የጭቆና ትርክት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በዚህም የተነሳ በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ሁሉም አካላት የ‹‹ተጨቁኛለሁ›› ሥነ ልቦናን መያዛቸውን ተናግረው፣ ‹‹ከሕወሓት እስከ አብን ማኒፌስቶ የተጠቂነት ሐሳብን የያዙ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡ ይህም በአገሪቱ ታሪክ ውስጥ ዋነኛው ጨቋኝ አገረ መንግሥቱ ሆኖ ሳለ አንዱ ሌላኛውን በጨቋኝነት እንዲፈርጅ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

ዮናስ (ዶ/ር) በፖለቲካዊ ምክክር በእነዚህ ችግሮች ሥጋት የወደቀውን የአገረ መንግሥቱን ህልውናና የሕዝቦችን አንድነት ላይ የተደቀነውን ችግር  እንደሚፈታ አስረድተዋል፡፡ በዚሁ መንገድ ግጭትን አስቁሞ ችግርን ከሥር መሠረቱ ለማከም እንደሚቻልም ገልጸዋል፡፡

በመፍትሔነት የተቀመጠው ምክክር ሲደረግ ‹‹የቄሳርን ለቄሳር›› በሚል አካሄድ መሆን እንዳለበት የጠቆሙት ዮናስ (ዶ/ር)፣ ሥልጣን ላይ ባሉት አካላት ተነስቶ ወደ ለኅብረተሰቡ የተረፈውን ግጭት ወደ መነሻው መመለስ እንደሚገባ አብራርተዋል፡፡ ለዚህም እስካሁን ብዙ ሰዎች ሞተውና ተጎድተው ቢሆንም የተረፉትን እያሰቡ መጓዝ እንደሚጠይቅ አክለዋል፡፡

ከዚህ ሁሉ በፊት ግን የጥይትን ድምፅ ፀጥ ማሰኘትና ፅንፈኛ የሆነ የፖለቲካ አመለካከትን ትጥቅ ማስፈታት እንደሚያስፈልግ ዮናስ (ዶ/ር) ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...