Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየምዕራባዊያን ጣልቃ ገብነት ዓለም አቀፍ ሕጎችንና መርሆዎችን የጣሰ መሆኑ ተገለጸ

የምዕራባዊያን ጣልቃ ገብነት ዓለም አቀፍ ሕጎችንና መርሆዎችን የጣሰ መሆኑ ተገለጸ

ቀን:

ምዕራባዊያን አገሮች በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ የሚያደርጉት ጣልቃ ገብነት ዓለም አቀፍ ሕጎችንና መርሆዎችን የጣሰ መሆኑ ተገለጸ፡፡

ባለፈው ሳምንት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሸራተን አዲስ ባዘጋጀው የፓናል የውይይት መድረክ ላይ ጥናታዊ ጽሑፎችን ያቀረቡ ምሁራን እንደገለጹት ምዕራባዊያኑ በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ጫና ለመቋቋም አገሪቱ የውስጥ ችግሯን መፍታትና አንድነቷን ማጠናከር ይገባታል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎችና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሚናቸውን አገራዊ ፋይዳ ያላቸው የፖሊሲ ምክረ ሐሳቦችንና ቴክኖሎጂዎችን ወደ ማመንጨት ማሸጋገር እንዳለባቸውም በውይይቱ ወቅት ተገልጿል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ደኤታ ወ/ሮ ሁሪያ ዓሊን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ታዋቂ ምሁራን የተካፈሉበትን የፓናል ውይይት የከፈቱት፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጣሰው ወልደ ሐና (ፕሮፌሰር)፣ የምዕራባዊያኑን ኢትዮጵያን የመጉዳት ሴራ በዝርዝር አብራርተዋል፡፡ የሕወሓት ኃይልን፣ ‹‹ምዕራባዊያኑ ለክፉ ቀን ብለው ያበቀሉትና ያዘጋጁት የአገር ማፍረሻ ኃይል ነው፤›› ሲሉ የገለጹት ጣሰው (ፕሮፌሰር)፣ ይህ ኃይል በምዕራባውያኑ እየታገዘ በአገሪቱ ላይ ያደረሰውን ጥፋት መላው ዓለም እንዳየው አስረድተዋል፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ የአገሪቱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ምሁራኖቻቸው አገር በጭንቅ ውስጥ በምትገባበት ወቅት ብቻ ሳይሆን፣ በሰላም ጊዜም ሚናቸው ከፍ ያሉ ሐሳቦችን ወደ ማመንጨት ማሸጋገር እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

መንግሥት ከእነዚህ መሰል የምሁራን ውይይት መድረኮች የሚገኙ ሐሳቦችን የመጠቀም መብት እንዳለው ያስረዱት ጣሰው (ፕሮፌሰር)፣ ይሁን እንጂ በየመድረኩ የሚፈልቁ ሐሳቦችን እንደወረደ ሳይሆን፣ የበለጠ የማሻሻልና በተጨባጭ የፖሊሲ ሐሳቦች አስደግፎ በማዳበር ሊጠቀም ይገባል ብለዋል፡፡ ‹‹ሐሳቦች ቴክኖሎጂ ጭምር ናቸው፤›› ሲሉ የተናገሩት ጣሰው (ፕሮፌሰር)፣ የሚጠቅመውን ለይቶ መውሰድና መጠቀም የመንግሥት ኃላፊነት ነው ብለዋል፡፡ 

በውይይቱ ላይ ንግግር ያደረጉና ለ36 ዓመታት በዲፕሎማትነት ያገለገሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲ (አምባሳደር)፣ ኢትዮጵያ ያላትን ዓለም አቀፍ ገድል በጥልቀት አብራርተዋል፡፡ ‹‹በዓድዋ ድል፣ የአፍሪካ ኅብረትን በመመሥረትም ሆነ የፓን አፍሪካን እንቅስቃሴ በማቀንቀን በኩል ኢትዮጵያ ብዙ ዓለም አቀፍ ገድሎች ያላት አገር ናት፤›› ያሉት ዲና (አምባሳደር)፣ ‹‹ይህን ሀብት ምን ያህል እንጠቀመዋለን?›› ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ‹‹እኛ ዘለግ ያለ የነፃነት ታሪክ ቢኖረንም፣ ሌሎች አፍሪካዊያንና ጥቁር ሕዝቦችም ዝም ብለው በነጮች ሲገዙ አልኖሩም፣ ከተገዥነት ለመላቀቅ ታግለዋል፣ ብዙ ጀግኖችም አፍርተዋል፤›› ሲሉ የገለጹት ዲና (አምባሳደር)፣ እነዚህን ትግሎቻቸውንና ጀግኖቻቸውን ከእኛ እኩል ስናደንቅና በአፍሪካዊ ወንድማማችነት ስሜት ከጎናቸው ስንቆም ነው የአፍሪካዊያን አንድነት የሚጠናከረው ብለዋል፡፡

የውይይት መድረኩ የመጀመሪያው ጥናታዊ ጽሑፍ አቅራቢ አንጋፋው የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ካሳሁን ብርሃኑ (ፕሮፌሰር)፣ የምዕራባዊያንን ጣልቃ ገብነት ታሪክ በሰፊው አቅርበዋል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1675 የዌስትፋሪያ ስምምነት ጀምሮ ምዕራባዊያኑ እርስ በእርሳቸው መዋጋት ሲሰለቻቸው፣ ሌሎችን አስገብሮ ለመኖር ተማምለው በመላው ዓለም ለወረራ መሰማራታቸውን አውስተዋል፡፡ ይህ የአውሮፓዊያኑ የውጭ ጣልቃ ገብነት እ.ኤ.አ. በ1815 በቬና ኮንፍረንስ፣ እንዲሁም በበርሊን ጉባዔ በፖሊሲ መልክ ተቀርፆ የሚተገበር መሆኑን የገለጹት ምሁሩ፣ ይህም ቅኝ ገዥነትና ተገዥነትን መውለዱን አስረድተዋል፡፡

‹‹ኢትዮጵያ በታሪኳ ከውጭ ጣልቃ ገቦች ተላቃ አታውቅም፤›› ሲሉ የተናገሩት ካሳሁን (ፕሮፌሰር)፣ በአክሱም ዘመነ መንግሥት በቤዛንታይኖችና በፐርሺያኖች የኃይል ቁርቁስ ኢትዮጵያ ወደቦቿን ጭምር መስዋዕት ያደረገችበት ጣልቃ ገብነት ገጥሟት ነበር ብለዋል፡፡ በ16ኛው ክፍለ ዘመን በፖርቹጋሎችና በቱርኮች ፍጥጫ ኢትዮጵያ ደም አፋሳሽ የጣልቃ ገብነት ግጭት ማስተናገዷን የጠቀሱት ፕሮፌሰሩ፣ ይኸው የውጭ ጫናም ከቅኝ ግዛት መስፋፋት ጋር ተያይዞ እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡

አያይዘውም የአሜሪካኖችን በኢትዮጵያ ላይ የሚካሄድ ጣልቃ ገብነት ያነሱት ካሳሁን (ፕሮፌሰር)፣ የዴሞክራቶች ተፅዕኖ በኢትዮጵያ ጥሩ የታሪክ ሪከርድ የሌለው መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በብዙ የታሪክ አጋጣሚዎች ኢትዮጵያ በአሜሪካኖች ጣልቃ ገብነት መስዋዕት ስትከፍል መኖሯን ጠቁመው፣ ‹‹የታላቁ ህዳሴ ግድብ ጉዳይን ወደ አሜሪካ ለምን ይዘን እንደሄድን ሁሌም ሳስበው ግር ይለኛል፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ጋዳፊ የተመታውና ሊቢያ ለመበታተን የተጋለጠችው የኑክሌር ተቋማቱን ካስፈተሸ በኋላ ነበር፡፡ የኢራቁ ሳዳም ሁሴን የወደቀውም የኬሚካል መሣሪያውን ላስፈትሽ ካለ በኋላ ነው፤›› ሲሉ ሁለቱን አገሮች በምሳሌነት ያነሱት ካሳሁን (ፕሮፌሰር)፣ ‹‹እኛም ለምዕራባዊያኑ ሸብረክ ካልን ያበቃልናል፤›› ብለዋል፡፡

በምዕራባዊያኑ ጣልቃ ገብነት የተቆሰቆሰው አፍሪካዊ ስሜትና የአንድነት መንፈስ ዛሬ በአንዳንድ አጀንዳ ወርዋሪዎች መፈተኑን ገልጸዋል፡፡ መንግሥት ውስጡን ያፅዳ ሲሉ የተናገሩት ምሁሩ፣ ‹‹አጀንዳ የሚሰጡንና የሚከፋፍሉን ኃይሎች ለምዕራባዊያን ባርነት ሳይገብሩን በፊት፣ አንድነትንና ውስጣዊ ጥንካሬን ማጠናከር አስፈላጊ ነው፤›› የሚል ምክረ ሐሳባቸውንም አክለዋል፡፡

ዓለም አቀፍ ሕጎችና የምዕራባዊያንን ጣልቃ ገብነት የሚገመግም ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት የሕግ ምሁር ጌታቸው አሰፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የአገሮች ሉዓላዊነት የሚከበርባቸውንና የሚጣስባቸውን ምክንያቶች በሰፊው አስረድተዋል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተር ላይ በሕግ ካልሆነ በስተቀር የአገሮች ሉዓላዊነት መጣስ እንደሌለበት በግልጽ መቀመጡን፣ ይህም በተለያዩ የዓለም አቀፍ ሕጎች መደገፉን አስረድተዋል፡፡ ሆኖም የዓለም መንግሥታት ማኅበር ዳኝነት በጥቂት አገሮች ስብስብ (በፀጥታው ምክር ቤት) እንደሚበየን ያስረዱት ጌታቸው (ዶ/ር)፣ የዚህ ተቋም ውሳኔም ይግባኝ የሌለውና ሚዛኑ የሚጠበቅበት መንገድም ያልተመቻቸ መሆኑን በጎጂነት ጠቅሰውታል፡፡

‹‹በቅርቡ የምዕራባዊያን አገሮች በኢትዮጵያ ጉዳይ ሙሉ ለሙሉ ተነክረው፣ የአገር ውስጥ ወሰናችሁን ጭምር ያለኛ ፈቃድ መቀየር አትችሉም ሲሉ ታይተዋል፤›› ያሉት ጌታቸው (ዶ/ር)፣ የምዕራባዊያኑ የጣልቃ ገብነት አካሄድ መገለጫ ብዙ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻው፣ የባለሥልጣናትን ስም ማጥፋት፣ ወታደራዊ ዛቻ፣ ማዕቀብ፣ ተቋማዊ ጫና፣ ዓለም አቀፍ ተቋማትን መገልገያ ማድረግ ሁሉ የምዕራባዊያኑ የጣልቃ ገብነት አካሄዶች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ ይህን መሰል ጣልቃ ገብነትን መመከት የሚቻለው ደግሞ ውስጣዊ ጥንካሬን ከመፍጠር በተጨማሪ፣ ዓለም አቀፍ ውሳኔ ሰጪነትን በማሳደግ፣ እንዲሁም ዘርፈ ብዙ ትብብሮችን ከሌሎች አገሮች ጋር በመፍጠር ጭምር መሆኑን አሳስበዋል፡፡

ሌላው ጥናት አቅራቢ የኢኮኖሚ ምሁሩ ዓለማየሁ ገዳ (ፕሮፌሰር) በበኩላቸው፣ ‹‹ጣልቃ ገብነት የሚቀለው በኢኮኖሚ ደሃ ሲኮን ነው፤›› ሲሉ ነበር ማብራሪያቸውን የጀመሩት፡፡ የኢትዮጵያ ድህነትና ኋላቀርነት ዋና መጠቂያ እንደሆነ ያስረዱት ዓለማየሁ (ፕሮፌሰር)፣ የኢኮኖሚ ዕድገትን ሲፈታተኑ የነበሩ ችግሮችን በስፋት አስረድተዋል፡፡ ‹‹የዋጋ ንረት ዋናው የኢኮኖሚያችን ችግር ነው፣ የወረደ ምርትና ምርታማነትም ሌላው ፈተና ነው፣ ብርን የማርከስና የማተም ፖሊሲም ዋና ማነቆ ነው፤›› ብለው፣ ነጋዴዎች ያላቸው የሞኖፖሊ ጡንቻ ወይም የግብይት ሥርዓቱ መበላሸትም ሌላው የኢኮኖሚ ፈተና እንደነበር አስረድተዋል፡፡

‹‹እነዚህ ሁሉ ችግሮች የተጫኑት ኢኮኖሚ ይዘን ወደ ጦርነት ገብተናል፤›› ካሉ በኋላ፣ ‹‹ከዚህ ጦርነት ተላቆ በኢኮኖሚ ለማገገም ግን መንግሥት እየተዘጋጀ አይመስለኝም፤›› ሲሉ ያሳስበኛል ያሉትን ጉዳይ ገልጸዋል፡፡

ከጦርነት በኋላ ያለው መልሶ የመገንባት ሥራ ከባድ መሆኑን ብዙ መረጃዎችን ማጣቀሻ በማድረግ ገልጸው፣ ‹‹በብዙ አገሮች እስከ 30 ዓመት ሊፈጅ ይችላል፣ ሩዋንዳን ብናይ 14 ዓመታት ነው በእግሯ ለመቆም የፈጀባት፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ‹‹አሁን የገባንበት ጦርነት ከፍተኛ የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት የሚያስከትል ከባድ ቀውስ ነው፤›› ያሉት ምሁሩ፣ ከዚህ ለመውጣት ያስፈልጋሉ ያሉዋቸው ምክረ ሐሳቦችም አያይዘው አቅርበዋል፡፡

‹‹የኢኮኖሚ ቅደም ተከተል መለየት (ተቋማትን የማደስ ሥራ ሌላ ጊዜ ስለሚደርስ ተወት ማድረግ)፣ የዋጋ ማስተካከያ ማድረግ፣ የመልሶ ግንባታ (ኮንስትራክሽን) ቦንድ መሸጥ፣ የፋይናንስ ተቋማት አስገዳጅ የቦንድ ሽያጭ እንዲያደርጉ ማድረግ፣ የማዕድን ኤክስፖርት ላይ ቀድሞ ቀብድ (ክፍያ) መውሰድ…›› በማለት ከጦርነቱ ለመውጣት ሊወሰዱ ይገባል የሚሏቸውን ምክሮች ዓለማየሁ (ፕሮፌሰር) አቅርበዋል፡፡       

የፍልስፍና ምሁሩ ዳኛቸው አሰፋ (ዶ/ር) የመሩት ይህ የፓናል ውይይት በዓይነቱ ከፍ ባለ ደረጃ የፖሊሲ ምክረ ሐሳቦች የፈለቁበት መሆኑ ከተሳታፊዎቹ ተነግሮለታል፡፡ የአይሲቲ (ዲጂታል) ቴክኖሎጂ ጣልቃ ገብነት ጉዳይ ጭምር ተነስቶ ተመክሮበታል፡፡ በዲጂታል ቴክኖሎጂው ዘርፍ አገሪቱ የገጠማት የጣልቃ ገብነት ውጊያም ከባድ መሆኑን፣ እሱንም መመከት እንደሚገባ ሐሳቦች ተንሸራሽረዋል፡፡ በዳያስፖራው በኩል ሊደረግ የሚገባው የተጠናከረ ትግል መቀጠል እንደሚገባውና ጥሩ ውጤቶች የተገኘበት መሆኑ ተሰምሮበታል፡፡ የመድረክ መሪው ዳኛቸው (ዶ/ር)፣ የዩኒቨርሲቲዎች ሚና እንዲህ ያሉ መድረኮችን በብዛት ማስተናገድ መሆኑን አተኩረው አስረድተዋል፡፡ አንጋፋው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ይህን መሰል መድረክ በማሰናዳቱ እንደመነሻ ተመሥግኖበታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...