ግብፅ ጥገኝነት የጠየቁ ኤርትራዊያንን መረጃዎቻቸውንና ፍላጎቶቻቸውን ሳትገመግም ማባረሯን ሂውማን ራይትስ ዎች አስታወቀ፡፡
ግብፅ ሕፃናትን ጨምሮ 24 ኤርትራውያን ጥገኝነት ጠያቂዎችን ከአገሯ ያስወጣች ሲሆን፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ውሳኔውን ተቃውመዋል። በጥቅምትና በኅዳር ወራትም ከግብፅ ከተባረሩ 15 ኤርትራውያን ውስጥ ስምንት ያህሉ የደረሱበት እንዳልታወቀም ገልጸዋል።
የሂዩማን ራይትስ ዎች የመካከለኛው ምሥራቅና የሰሜን አፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር ጆ ስቶርክ ‹‹ግብፅ ኤርትራዊያን ስደቶችን በማባራረ ለእንግልትና ለሥቃይ እየዳረገች ነው፤›› በማለት፣ ‹‹የጥገኝነት ሒደቶችን ሙሉ በሙሉ እንዲያገኙ መፍቀድ አለባት፤›› ብለዋል። የግብፅ ባለሥልጣናትም የሕፃናትን እስር በአስቸኳይ ማቆም አለባቸው ሲሉ አክለዋል።
ሂዩማን ራይትስ ዎች በግብፅ ዘጠኝ ጥገኝነት ጠያቂዎች ለወራት በዘለቀ እስራት እንደቆዩና በከባድ ሁኔታ ውስጥ ማለፋቸውን ሪፖርት አድርጓል። ከታሳሪዎቹ መካከልም ሦስቱ ሴቶች፣ ሁለት ወንዶችና አራቱ ሕፃናት መሆናቸውን በሪፖርቱ አመላክቷል።
የግብፅ ባለሥልጣናት እስረኞቹን በሚመለከት ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ኤጀንሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ አለመስጠታቸውንም ድርጅቱ ገልጿል።
በግብፅ የሚገኘው የስደተኞች መድረክ እ.ኤ.አ. በ2021 በአስዋንና በቀይ ባህር ግዛት ውስጥ በሚገኙ ፖሊስ ጣቢያዎች የታሰሩ 55 ኤርትራውያንን መመዝገቡን አስታውቋል።
ግብፅ ምንም እንኳን የዓለም አቀፉ የስደተኞች መብት ጥበቃና የአፍሪካ የስደተኞች መብት ጥበቃ ስምምነቶችን ብትፈርምም፣ ነገር ግን በስደተኞች ላይ እያደረሰችው ያለው ግፍ ተቀባይነት የሌለው ነው ሲል ድርጅቱ አክሏል።
እ.ኤ.አ. በኅዳር 2021 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ኤጀንሲ ባወጣው መረጃ መሠረት፣ ግብፅ 21 ሺሕ የሚሆኑ የተመዘገቡ ኤርትራውያን ጥገኝነት ጠያቂዎችንና ስደተኞችን አስተናግዳለች፡፡
ግብፅ ከ270,000 በላይ የተመዘገቡ ጥገኝነት ጠያቂዎችንና ከ65 አገሮች የመጡ ስደተኞችን መቀበሏ ይነገራል፡፡ አብዛኞቹ ከሶሪያ የመጡ ሲሆኑ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኤርትራ፣ ኢትዮጵያ፣ የመንና ሶማሊያ ተከታዮቹ መሆናቸው ተመልክቷል፡፡