በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት በ1991 ዓ.ም. ያበሩት የነበረው የጦር ጀት ተመትቶ ሲወድቅ በፓራሹት ወርደው በኤርትራ ወርደው ከተማረኩ በኋላ የት እንደደረሱ ሳይታወቅ ደብዛቸው ለጠፋው የአንጋፋው ፖለቲከኛ በየነ ጴጥሮስ (ፕሮፌሰር) ታናሽ ወንድም የኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ መታሰቢያ ሐውልት በሆሳዕና ከተማ ተሠርቶ ዛሬ እሑድ ጥር 22 ቀን 2014 ዓ.ም. እንደሚመረቅ ታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ አየር ኃይል ውስጥ በነበሩበት ወቅት በሠሩት ታላቅ ገድል በብዙዎች ዘንድ የብሔራዊ ጀግና ተምሳሌት ተደርገው የሚቆጠሩት ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ፣ በተለይም በ1969 ዓ.ም. በተካሄደው የኢትዮ–ሶማሊያ ጦርነት ሚግ 23 የተባለች ጀት በማብረርና ሞቃዲሾ ድረስ በመዝለቅ በዚያድ ባሬ ወታደራዊ ጦር ሠፈር ላይ ያደረሱት ተደጋጋሚ ጥቃት አንቱ አስብሏቸዋል።
በ1977 ዓም. ከሻዕቢያ ጋር በናቅፋ ግንባር እየተዋጉ በነበሩበት ወቅት አውሮፕላናቸው ተመትቶ ሲወድቅ፣ ኮሎኔሉም በሻዕቢያ ተማርከው እስረኛ ሆኑ፡፡
የደርግ መንግሥት በ1983 ዓ.ም. ከወደቀ በኋላ ኮሎኔል በዛብህ ተይዘው ከነበረበት ኤርትራ ወደ አገራቸው ተመልሰው ነበር፡፡ ኮሎኔል በዛብህ ኢትዮጵያና ኤርትራ በ1990 ዓ.ም. ወደ ጦርነት ሲያመሩ በድጋሚ የጦር አውሮፕላን አብራሪ በመሆን ጦርነቱ ላይ ዘምተዋል፡፡
ወደ ኤርትራ ምድር ዘልቀው ከገቡ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ተዋጊዎች አንዱ የነበሩት ኮሎኔሉ፣ የሚያበሩትን አውሮፕላን በጣም ዝቅ አድርገው በኤርትራ ጦር ላይ ጥቃት እየሰነዘሩ በነበረበት ወቅት የሚያበሩት ጀት ተመቶ መውደቁን ታሪክ ሰንዶታል፡፡
ኮሎኔሉ በዚሁ ጦርነት ወቅት ያበሩት የነበረው ጀት ሲከሰከስ በፓራሹት ዘለው መውረድ የቻሉ ሲሆን ለሁለተኛ ጊዜ በሻዕቢያ እጅ ገብተዋል።
በኋላም የሁለቱ አገሮች ጦርነት እንደተጠናቀቀ ኢትዮጵያና ኤርትራ የጦር ምርኮኞቻቸውን ሲቀያየሩ ኮሎኔሉ ግን ወደ አገራቸው ሳይመለሱ ቀርተዋል፡፡
በ1972 ዓ.ም. ‹የላቀ የጦር ሜዳ ጀብዱ ሜዳይ› ተሸላሚ የሆኑት ኮለኔሉ፣ ‹‹እኛ ብንሞት ሌላ ሰው ይተካል፣ መተኪያ የሌላት ኢትዮጵያ ከሞተች ግን ተተኪው ትውልድ ስለሚሞት ዋጋ አይኖረውም፡፡ የአገርን ሉዓላዊነት በአስተማማኝነት መጠበቅ ቆራጥነትና ልበ ሙሉነትን ይጠይቃል፤›› ሲሉ በሕይወት በነበሩበት ጊዜ ከተናገሩት የማይረሳ ሆኖ በብዙዎች ዘንድ ይታወሳሉ።
‹‹የሰማዩ አርበኛ›› በሚል የሚሞካሹት ኮሎኔሉ ለበርካታ ጊዜያት የሞት ዜናቸው ካሉበት ኤርትራ ቢሰማም፣ እስካሁንም ድረስ ግን ትክክለኛ መረጃውን ማረጋገጥ አልተቻለም። የታላቅ ጀብዱ ባለቤት የሆኑትን ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ፣ በሆሳዕና ከተማ አሥር ወራትን የፈጀ ሐውልት ሲገነባ ቆይቶ ዛሬ ለምርቃት በቅቷል፡፡