ግብርና ሚኒስቴር በአንድ ቢሊዮን ብር ወጪ የፀረ ተባይ መድኃኒቶች መፈተሻ ላቦራቶሪ ሊገነባ መሆኑን አስታወቀ።
ላቦራቶሪው ከውጭ የሚመጡም ሆነ በአገር ውስጥ የሚመረቱ ፀረ ተባይ መድኃኒቶች ለሰው ጤና፣ እንዲሁም ለአካባቢ የሚኖራቸውን ጎጂነት ፍተሻ ለማድረግ የሚያገለግል መሆኑን፣ በግብርና ሚኒስቴር የዕፀዋት ጤናና ጥራት ቁጥጥር ዋና ዳይሬክተር አቶ ግርማ በቀለ ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት ከውጭ የሚመጡ ፀረ ተባይ መድኃኒቶች ፍተሻ የሚደረግላቸው ከሚመጡበት አገር መሆኑን፣ ፍተሻው ከሚመጡበት አገር የሚደረግና የጥራት ማረጋገጫውን በወረቀት ብቻ ይዘው በመቅረብ የሚሠራ መሆኑን አስረድተዋል።
በአገር ውስጥ ለሚመረቱት ፀረ ተባይ መድኃኒቶች ደግሞ ሚኒስቴሩ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ በግብርና ኮሌጆች፣ በግብርና ምርምር ተቋማትና ዕውቅና ባላቸው የግል ተመራማሪ ተቋማት፣ እንዲሁም በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በሚገኙ ላቦራቶሪዎች የጥራት ፍተሻው እንደሚደረግ አቶ ግርማ አብራርተዋል።
ላቦራቶሪው በአገር ውስጥ ባለመገንባቱ በተለይ ከውጭ የሚመጡ ፀረ ተባይ መድኃኒቶችን የፍተሻ ውጤት ተዓማኒነቱ ላይ ጥያቄ ማስነሳቱን ጠቅሰው፣ ገና ከመግባቱ በፊትም ሆነ በሥራ ላይ ባለበት ወቅት አስፈላጊውን ምርመራ ለማድረግ አለመቻሉን ገልጸዋል።
ላቦራቶሪውን በሚቀጥሉት አንድ ዓመት ተኩል ጊዜያት ገንብቶ ለማጠናቀቅ መታቀዱን ጠቁመው፣ ግንባታው በአንድ ቢሊዮን ብር አቃቂ ቃሊቲ አካባቢ እንደሚከናወን ተናግረዋል። የላቦራቶሪ መሣሪያዎቹን ለማሟላት ደግሞ በተለይ ከጂአይዜድና ከግብርና ልማት ፕሮጀክት ጋር በመተባበር ለማሟላት እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል።
በሌላ በኩል ግብርና ሚኒስቴር የፀረ ተባይ መድኃኒቶች ምዝገባና ማስመጣትን ለመቆጣጠር የሚሆን መመርያ ማዘጋጀቱን ገልጸው፣ መመርያው በተለይ ከውጭ የሚመጡ ፀረ ተባይ መድኃኒቶችን በሚሸጡና አምራቹን በሚወክሉ አካላት መካከል ያለውን ልዩነት በግልጽ የተቀመጠበት መሆኑን አስረድተዋል።
የፀረ ተባይ ምዝገባና ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 674/2002 ከአሥር ዓመታት በላይ የቆየ ቢሆንም፣ አዋጁ ግልጽ በሆነ መመርያ ተግባራዊ ባለመደረጉ በተለይ በፀረ ተባይ ምዝገባና ማስመጣት በኩል ከፍተኝ ክፍተት እንደነበር አቶ ግርማ ገልጸዋል። በመሆኑም አዋጁን መሠረት አድርጎ አዲስ በተዘጋጀው መመርያ ላይ የፀረ ተባይ አስመዝጋቢው፣ ከፀረ ተባይ ነጋዴው ጋር ያለውን ልዩነትና መብት በግልጽ አስቀምጧል ብለዋል።