Monday, March 20, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየኢትዮጵያ ሊግ አክሲዮን ማኅበር አዲስ የኮቪድ-19 መመርያ ይፋ አደረገ

የኢትዮጵያ ሊግ አክሲዮን ማኅበር አዲስ የኮቪድ-19 መመርያ ይፋ አደረገ

ቀን:

ክለቦች የኮቪድ-19 ምርምራ ውጤትን ሲያስቀይሩ እንደነበር ተጠቁሟል

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የሕክምና ክፍል፣ ከኮቪድ-19 ምርመራ ጋር ተያይዞ አዲስ መመርያ ማውጣቱን አስታወቀ፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በካሜሩን አፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎውን ተከትሎ ተቋርጦ የነበረው የቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ ከዓርብ ጥር 20 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በድሬዳዋ ቀጥሏል፡፡ 

ከአሥረኛ ሳምንት ጅምሮ በድሬዳዋ ከተማ የሚከናወነውን የፕሪሚየር ሊግ መርሐ ግብር ተከትሎ የሕክምና ክፍሉ ሐሙስ ጥር 19 ቀን ድሬዳዋ ከከተሙት ክለቦች ጋር መምከሩን ሊግ ካምፓኒው አስታውቋል፡፡  የሕክምና ክፍሉ የኮቪድ-19 ምርመራን በአንድ ማዕከል ብቻ እንዲደረግ በወሰነውና ክለቦች በተሰማሙት መሠረት ከሁለተኛው የውድድር ሳምንት ጅምሮ በሐዋሳ ከተማ በተከናወኑት የፕሪሚየር ሊግ ውድድሮች ላይ ተግባራዊ የሆኑትን መመርያዎች አሻሽሎ ማቅረቡን ገልጿል፡፡

መመርያው፣ በተለይም ከመርሐ ግብር አያያዝና ከክፍያ ጋር የተያያዙትን ጨምሮ ሌሎች በሐዋሳ የተከሰቱትን መለስተኛ ችግሮች ለመቅረፍ የሚረዳ እንደሆነ የአክሲዮን ማኅበሩ የምርመራ ክፍል ለክለቦች ባቀረበው ጥናት ላይ አብራርቷል፡፡ 

በመመርያው መሠረትም የሕክምና ክፍሉ፣ የክለቦችን ሥነ ሥርዓት ኃላፊነትና ግዴታ ዝርዝር ይፋ አድርጓል፡፡ በዚህም ምርመራ የሚያደርጉ ቡድኖች ጨዋታ ከሚያደርጉበት 48 ሰዓታት በፊት መሆን እንዳለበት፣ ወደ መልበሻ ክፍል ወይም ወደ ሜዳ የሚገባ ማንኛውም ቡድን አባል መመርመር እንዳለበት እንዲሁም ከአንድ ጨዋታ በፊት የሚደረገው ምርመራ አንድ ጊዜ ብቻ እንደሚሆን ያትታል፡፡

የምርመራ ውጤት በአንድ ሰዓት ውስጥ እንዲታወቅ፣ ኮቪድ-19 የተገኘበት ተጫዋች ዳግም ምርመራ የሚያደርገው ለቀጣይ ጨዋታ ቡድኑ ምርመራ ሲያደርግ እንደሆነና ምርመራው በሚደረግበት ቀን ቦታና ሰዓት ያልተገኘ ወይም ክፍያ ባልተጠናቀቀና ሪፖርት በተደረገበት ክለብ ላይ በዲሲፕሊን መመርያው መሠረት ቅጣት እንደሚጣልበት ያስቀምጣል፡፡

ከዚህም ባሻገር የአክሲዮን ማኅበሩ የሕክምና ክፍል ግዴታና ኃላፊነት በመመርያው የተካተተ ሲሆን፣ የመመርመሪያ ቁሳቁሶችን ማቅረብ፣ ምርመራ የሚያካሂዱ ባለሙያዎችን ማዘጋጀት፣ የክለብ ተጫዋቾችንና በውድድሩ ላይ የሚሳተፉ አባላትን ምርመራ ማካሄድ፣ የምርመራ ውጤት መጠበቅ እንዲሁም ጨዋታው ከመደረጉ 75 ደቂቃ በፊት በኮቪድ-19 የተጠቁ አባላትን ለጨዋታ አመራሮች ማሳወቅ የሚለው ተዘርዝሯል፡፡

መመርያው የክለቦችን ኃላፊነትና ግዴታ በዝርዝር ያስቀመጠ ሲሆን፣ ክለቦች የቡድን አባላትን ቴሴራና መታወቂያ ይዘው እንዲቀርቡ ማድረግ፣ ምርመራውን ያላደረገ ማንኛውም የቡድን አባል ወደ ስታዲየም እንዳይገባ ማድረግ፣ የምርመራ ክፍያ መፈጸም እንዲሁም የቡድኑ አባላት በሁሉም ቦታዎች የኮቪድ-19 ፕሮቶኮልን እንዲተገብሩ ማስገደድ የሚለው በዋነኛነት ተቀምጧል፡፡

ክለቦች ከኮቪድ-19 ምርመራ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ቅሬታዎች እየተነሳባቸው  ሲሆን፣ በተለይ የምርመራ ውጤትን በገንዘብ የማስቀየር ሒደት በዋነኝነት ይጠቀሳል፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በአርባ ምንጭ በነበረው ጠቅላላ መደበኛ ጉባዔ ላይ ተሳታፊ ክለቦች ተጫዋቾቻቸው በኮቪድ-19 ሲያዙ፣ የቡድን መሪዎች ከሕክምና ባለሙያ ጋር በመሆን ውጤትን ማስቀየር እየተለመደ መምጣቱን አንስተዋል፡፡

እንደ አስተያየት ሲጪዎቹ ከሆነ፣ ተጫዋች፣ ቡድን መሪና አሠልጣኝ በጋራ በመመሳጠር ይኼንን ተግባር እንደሚከውኑ ተጠቁሟል፡፡ በተለይ ክለቦቹ ወሳኝ ተጫዋች በኮቪድ-19 መያዙ ከታወቀ፣ የምርመራ ውጤቱን ለማስቀየር እንደ ግዴታ ተደርጎ እየተወሰደና አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን እየተነገረ ይገኛል፡፡

በሌላ በኩል በአንድ ክለብ ውስጥ ከአምስት በላይ ተጫዋቾች በኮቪድ-19 ሊገኝባቸው የሚችልበት አጋጣሚ እንዳለ የተገለጸ ሲሆን፣ ተጫዋቾቹ ማረፍ ሲገባቸው አንድ ቦታ ተስባስበው ከመታየታቸውም ባሻገር፣ አንድ ክፍል ለሁለት የሚጋሩበት አጋጣሚ እንዳለም ተጠቁሟል፡፡

ፕሪሚየር ሊጉ ዘጠኝ ሳምንቶች ያስተናገደው የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ዕድሉ ለቀጣዩ ባለተረኛ ድሬዳዋ ከተማ አስተላልፏል፡፡ ከአሥረኛ ሳምንት በኋላ ያሉትን ጨዋታዎች የማስተናገድ ዕድል የነበረው አዳማ ከተማ የነበረ ቢሆንም፣ የስታዲየሞቹ ለውድድር ዝግጁ ያለመሆናቸውን ተከትሎ፣ ዕድሉ ለድሬዳዋ ተስጥቷል፡፡

ድሬዳዋ ከተማ ከ10ኛ እስከ 15ኛ ሳምንት ድረስ ያሉትን ጨዋታዎች ለማስተናገድ ዕድሉን ከተረከበች በኋላ ክለቦች ቀደም ብለው ወደ ከተማዋ ማምራታቸው ይታወሳል፡፡ ዓርብ ጥር 20 ቀን 2014 ዓ.ም. መርሐ ግብር መሠረት ኢትዮጵያ ቡና ከሐዋሳ እንዲሁም ሲዳማ ቡና ከባህር ዳር ከተማ ባደረጉት ጨዋታ ተጀምሯል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ዜጎች የተፈተኑበት የኑሮ ውድነት

በኢትዮጵያ በየጊዜው እየተባባሰ የመጣው የኑሮ ውድነት የበርካታ ዜጎችን አቅም...

በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች የሚደረጉ ድጋፎች ዘላቂነት እንዲኖራቸው ተጠየቀ

በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች የሚደረጉ ድጋፎች ዘላቂነት እንዲኖራቸውና በተቀናጀ መልኩ...

ወደ ኋላ የቀረው የሠራተኞች ደኅንነት አጠባበቅ

በአበበ ፍቅር ለሠራተኞች የሚሰጠው የደኅንነት ትኩረት አናሳ በመሆኑ በርካታ ዜጎች...