የደቡብ አሜሪካዋ ኮስታሪካ ዘንድሮ ለምታስተናግደው ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች ሴቶች የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ማጣሪያውን እያደረገ የሚገኘው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን፣ የፊታችን ዓርብ ጥር 27 ቀን 2014 ዓ.ም. ከታንዛኒያ አቻው ጋር በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የሚያደርጉት የመልስ ጨዋታ ይጠበቃል፡፡ ታንዛኒያ ባለፈው እሑድ በሜዳው ባደረገው ጨዋታ ኢትዮጵያን 1 ለ 0 በሆነ ጠባብ ውጤት ማሸነፉ ይታወሳል፡፡
በአሠልጣኝ ፍሬው ኃይለ ገብርኤል የሚሠለጥነው ብሔራዊ ቡድኑ፣ እስካሁን ባደረጋቸው አራት የደርሶ መልስ የማጣሪያ ጨዋታዎች በታንዛኒያ አቻው ከደረሰበት ሽንፈት በስተቀር ሦስቱን የደርሶ መልስ ጨዋታዎች በአሸናፊነት አጠናቋል፡፡
የመልሱን ጨዋታ ውጤቱን መገልበጥ የሚችል ከሆነ፣ ምናልባትም ለኮስታሪካው ከ20 ዓመት በታች የሴቶች የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ወደ መጨረሻው ምዕራፍ ይሸጋገራል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የቡድኑን ዝግጅት አስመልክቶ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳስታወቀው ከሆነ፣ ቡድኑ ከታንዛኒያ እንደተመለሰ ከአንድ ቀን ዕረፍት በኋላ በካፍ የልህቀት ማዕከል ልምምዱን አጠናክሮ እንደቀጠለ ይገኛል፡፡ ምክንያቱም ቡድኑ እስካሁን ባደረጋቸው ሦስት ማጣሪያ የደርሶ መልስ ጨዋታዎች ላይ በፍፁም ብልጫ ተጋጣሚዎቹን በሰፊ ውጤት ማሸነፍ የቻለው ጠንካራ ዝግጅት በማድረጉ እንደሆነና ውጤቱም የጠንካራ ዝግጅት ነጸብራቅ በመሆኑ ነው ብሏል፡፡