በንጉሥ ወዳጅነው
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የካቢኔ አባሎቻቸውን ይዘው ወደ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ቦታ በመውረድ፣ የመቶ ቀናት የሥራ ግምገማዎችን ማድረጋቸውን ከቀናት በፊት ሰምተናል፡፡ ይህ ከስድስተኛው ዙር ምርጫ በኋላ የተመሠረተው አዲሱ መንግሥት የሦስት ወራት ከአሥር ቀናት ግምገማ ምንም እንኳን በጦርነት ኢኮኖሚ በምትዋከብ አገር ውስጥ የተካሄደ ቢሆንም፣ በርካታ ጉዳዮች እንደሚነሱበት ጥርጥር የለውም፡፡ ሕዝብ እንዲሰማቸው የሚደረጉት ጭብጦችም የተወሰኑ መሆናቸውን መገመት አይከብድም፡፡
በዚህ ጽሑፍ ለማንሳት የምሞክረው ግን በብልሽትና የሥርዓት ንቅዘት ሕዝብ ያማረረው ኢሕአዴግን የተካውን ብልፅግናን የሚመለከት ነው፡፡ ምንም እንኳን ሥርዓቱ እንደ እንጉዳይ ድንገት የበቀለ ድርጅት ባይሆንም፣ በተሃድሶም ይሁን በ‹‹ሪፎርም›› መንፈስ ተፀይፎት የመጣውን ሙስናና ብልሹ አስተዳደር እንዴት እየታገለው መሆኑን ለመቃኘት ይሞከራል፡፡
በተለይ ባለፈው ጊዜ ውይይት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደጋግመው እንዳነሱት፣ በፍትሕና ፀጥታ መዋቅሩ፣ ከፍተኛ ሕዝብና የመንግሥት ሀብት በሚንቀሳቀስባቸው ሴክተሮችና መሰል አገልግሎት ሰጪዎች አካባቢ ያልተገባ የጥቅም ፍላጎት አሁንም እንዳልቆመ በግልጽ ማንሳታቸው ነገሩን መለስ ብሎ መፈተሽ አስፈልጓል፡፡ እውነት የለውጥ ኃይሉ እንዲህ ያሉ የከፉ ችግሮችን ከመቅረፍስ በላይ ምን ኃላፊነት አለበትና ችላ ይባላል?
እንደ እውነቱ ከሆነ ሙስናና የሥርዓት ንቅዘት በመላው ዓለም አገሮች ውስጥ አለ፡፡ የአንዳንዶቹም ዋነኛ የሥርዓት ብልሽት ማሳያ፣ ወይም ሥልጣንን ያላግባብ በመጠቀም የጥቂቶችን አጋባሽነት የሚያረጋግጥ በሽታ ቢሆንም፣ የአስከፊነቱ ደረጃ ይለያያል እንጂ ሙስና የሌለበት አገር አይኖርም፡፡ ምንም ያህል ይህን እውነት መረዳት ቢቻልም፣ ግን እኛን በመሰሉ አገሮች ‹‹ሙስና ይኖር›› ብሎ መተው አይቻልም፡፡ እንዲኖርም ሊፈቀድለት አይገባም፡፡
ለአብነት ያህል በዴሞክራሲ ረገድ በጣም የተሻለ መንግሥትና ሥርዓት እንዳላቸው የሚነገርላቸው እንደ ዴንማርክ፣ ኒውዚላንድ፣ ፊንላንድ፣ ስዊድን፣ ኖርዌይ፣ ስዊዘርላንድ፣ ሲንጋፖር፣ ኔዘርላንድ፣ ካናዳና አውስትራሊያ የመሳሰሉ አገሮች በሙስና በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ተብለው የተፈረጁ ናቸው፡፡ ‹‹ሙስና የለባቸውም›› ግን አልተባለም፡፡ ‹‹ሙስና አለባቸው ግን የሙስናው ደረጃ ዝቅተኛ ነው›› ማለት ብቻ ነው፡፡ አርዓያዎቻችን መሆን ያለባቸው እነዚህ አገሮች ሊሆኑ ይገባል፡፡
እስካሁን እንደ ‹‹ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል፣ ኮርፖሬሽን ሬቲንግና ዴሞክራሲ ኢንዴክስ›› የመሳሰሉት ዓለም አቀፍ የሙስናና የዴሞክራሲ ደረጃ አውጪ ድርጅቶች፣ በመረጃ ላይ የተመሠረተ ዘገባ ይፋ እንደሚያደርጉ ይታወቃል፡፡ በእነዚህ አካላት ዕይታ ከጥቂት ዓመታት በፊት የወጣ አንድ መረጃም አለ፡፡ የ150 አገሮች ጥናትን መሠረት አድርጎ በቀረበው መረጃ በሙሰኝነት ለአፍሪካ አገሮች ከተሰጣቸው ደረጃ ናሚቢያና ሩዋንዳ 41ኛና 40ኛ ደረጃ ሲያገኙ፣ ደቡብ አፍሪካ 52ኛ ደረጃ ሴኔጋል 54ኛ፣ አግኝተዋል፡፡
በዚህ ጥናት መሠረት ከ150 አገሮች መካከል ለኢትዮጵያ 86ኛ ደረጃ ተሰጥቷል (ምናልባት ይህ ደረጃ ኢሕአዴግ በተሃድሶ መድረኩ የደረሰበትንም ሆነ፣ ሕዝቡ ክፉኛ እያዘነበት የነበረውንና በኋላም መንግሥት ጉሮሮውን የተያዘበትን የለውጥ ፍላጎትና ተያያዡን መረጃ እንዳላካተተ ግልጽ ነው)፡፡ በወቅቱ በከፍተኛ የሙስናና የሥርዓታዊ ዘረፋ ደረጃ የሚታሙት የአፍሪካ አገሮች ሶማሊያ፣ ኤርትራና ሱዳን ነበሩ፡፡ ከአራት ዓመታት ወዲህ መረጃው ሊቀያየር ቢችልም አሁንም ሙስና የአገራችን ሥጋት መሆኑ አልቀረም፡፡
ትናንትም ሆነ ዛሬ አገራችን ከሙስናም በላይ የምትታማው ግን በዴሞክራሲ ሰንጠረዥ ደረጃ ነው፡፡ የመልካም አስተዳደር ዕጦትና ሙስና የዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ጉድለት ዋነኛ ማሳያዎች ቢሆኑም፣ ዴሞክራሲ ሌሎች በርካታ ዘውጎችም ስላሉት ከ150 አገሮች በዴሞክራሲ ደረጃ 121ኛ ላይ መገኘታችን የወደቅንበት ቁልቁለት ምን ያህል ጭቃ እንደያዘው የሚያመለክት ነበር፡፡ በእርግጥ በኋላ የአሁኑ የለውጥ አመራር በታሰበው ልክ ባይሄድበትም፣ የጀማመራቸው ማሻሻያዎች ገጽታችንን ቀና አድርጎት እንደነበር መካድ አይቻልም፡፡
ዓለም ኢትዮጵያን ከሙስና ይልቅ በኢሕአዴግ ጊዜ በፀረ ዴሞክራሲ (ዘዴኛና አስመሳይ በሆነ ዴሞክራሲ) እንደሚያውቃት ግልጽ ነበር፡፡ ወይም ‹‹ከፍተኛ ሙስና አለባት›› ብሎ ከማመን ይልቅ፣ በጽንፈኛና በጥላቻ ፖለቲካ የተሰነከለ የዴሞክራሲ ጉዞ ላይ መገተራችንን ይሳለቅበት እንደነበር አይዘነጋም፡፡ አሁንም ብልጭ ካለ የተስፋ ብርሃን በኋላ የችግሩን ሥረ መሠረት ቸል ብሎ ዘር ማጥፋት፣ አምባገነንነት እያለ ሥርዓቱን ማጥቆሩ ባይቆምም፡፡ ቢያንስ መልካም አስተዳደርን በተሻለ ግልጽነትና ተጠያቂነት መገንባት ያስፈልጋል፡፡
ወደ ነጥባችን ስመለስ በታዳጊ አገሮች የሙስና ደረጃን ስንመለከት ከተሞች ከገጠር በበለጠ ለጥገኝነት የታጋለጡ ናቸው፡፡ በእኛም አገር እንደሚታየው በሥርዓትና በሕግ ካልተመራ በተለይ የከተሞች መሬት እንደ ማዕድን ነው፡፡ ቀስ በቀስ ተጠቅልሎ በጥቂቶች እጅ የመግባት ዕድሉ በጣም ሰፊ ከመሆኑ ባሻገር፣ ቢሮክራሲው እንደ ሕዝብ ሀብት በጥንቃቄ ካልጠበቀው የጥገኝነት መፈልፈያ መሆኑም የሚታይ ነው፡፡ እዚህ ላይ ብልፅግናም ቢሆን ከኢሕአዴግ መሻሉ የሚረጋገጥበትን ተግባር ካልጀመረ ከኃጢያቱ መፅዳት አይችልም፡፡
በሌላ በኩል ዛሬም ቢሆን በከተማ አስተዳደሮች አገልግሎት ሰጪ ተቋማቱ ለአድሎአዊ አሠራርና ዜጋን ማማረር የቀረቡ መሆናቸው ብርቱ ትግል የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡ በእርግጥ በአንድ በኩል በአንድ ላይ ታጭቆ የሠፈረ ሕዝብ ፍላጎት፣ በሌላ በኩል ከከተሞችና ከገጠር የሚፈልስ ሕዝብ የመሳብ ኃይል ስላላቸው ተገልጋይ መብዛቱ አይቀሬ ነው፡፡ ይህን ተግዳሮት መቅረፍ የሚቻለው ግን በፍትሐዊና በሚዛናዊ አሠራር፣ በጠንካራ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነትና ትግል ነው፡፡
የመንግሥትን ብቃትና አቅም መጎልበትም ያስፈልጋል፡፡ በእርግጥ የፈጻሚው የዕውቀትና የክህሎት ውስንነት ብሎም ጠባቂነት በአንድ ጊዜ ሊቀረፍ አይችልም፡፡ እንዲያውም መዋቅሩን አዳዲስና ጀማሪ ፈጻሚና አመራር ሲሞላው መደነባበሩ በእጥፍ ሳይጨምር አይቀርም፡፡ ይህን ለማስተካከል የሚያስችል ተከታታይ ዕርምት እንዳይወስድ ደግሞ መንግሥት በሌላ ቀውስ ውስጥ መጠመዱ አይካድም፡፡ ወደፊትስ ምን ይደረግ ብሎ መነሳት ግን ግድ ይላል፡፡ ከመንግሥታዊ አገልግሎት አንፃር የአስተዳደር፣ የፍትሕና የፀጥታ አገልግሎትን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ሕዝቡን እየተሳተፉ፣ በሥነ ምግባር መምራት ካልተቻለ ዋነኛ የብልሽት ምንጮች መሆናቸውን መጠራጠር አዳጋች ነው፡፡ እዚህ ላይ በተለይ በዋና መዲናችን ቢሮክራሲውን ለማስተካከል ስንት እየተደከመ፣ ተግባሩ ሽንፍላ የማጠብ ያህል ከብዶ ያለው ለምንድነው ማለት ተገቢነት ይኖረዋል፡፡
ሰው በመለዋወጥ ብቻ የማይፈቱ የሥርዓት ማስተካከያና ቁርጠኝነት የሚሹ ዕርምጃዎችንም ቸል ማለት አይገባም፡፡ ሕዝቡንም በፀረ ሙስና ትግሉ ላይ በላቀ ደረጃ ማሳተፍ ጠቃሚ ነው፡፡ ብልሽቶቹ ከግለሰብ ወደ ተቋም እንዳይቀየሩ ቁርጠኛ ትግል ሊያብብ ይጋባል፡፡
በመሠረቱ ሙስና የትም ቢሆን ሁለት ዓይነት ነው፡፡ ግለሰባዊና ሥርዓታዊ (Individual and Systemic Corruption) በአፍሪካ ደረጃ እንደ ኬንያ፣ ዛየር፣ ኮንጎ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን፣ ግብፅ፣ ሊቢያ፣ ናይጄሪያ… ያሉ አገሮች ውስጥ ያለው ሙስና ሥርዓታዊ (Systemic) መሆኑን ነው መረጃዎች የሚያስረዱት፡፡
ይህም ከላይ እስከ ታች ያሉ ባለ ሥልጣናት በየደረጃው የሚገኙ ሹመኞችና ሠራተኞቻቸው ጭምር እከሌ ከእከሌ ሳይባል በሙስና የተዘፈቁበት ጊዜ ብዙ እንደነበር ያሳያል፡፡ ብዙዎቹ የዚህ ችግር ሰለባዎች የራሴ የሚሏቸውን ሰዎች፣ ቡድኖችና ድርጅቶች በልዩ ሁኔታ በመጥቀም ሙስናን የፖለቲካ መሣሪያ እስከ ማድረግ ድረስ ይሄዳሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ የእኛም ሁኔታ ወደዚህ ዓይነቱ ገጽታ የመሄድ ዝንባሌ ሲያሳይ የሚደነግጡ ሰዎች መብዛታቸው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ሙስና በሚሞዳሞዱ በርከት ያሉ ፈጻሚዎችና አመራሮች ያለ ከልካይ ከተፈጸመ ውጤቱ አገር መበተን ነው፡፡ ሙሰኝነት በአዋጅ የተፈቀደና በሕግ የማያስጠይቅ እስኪመስል ድረስ ፍጥጥና ግጥጥ ብሎ የሚካሄድባቸው ሌሎች አገሮችም አሉ፡፡ በባለሥልጣኑ ዙሪያ የተኮለኮሉ ሁሉ የዘረፋው ተጠቃሚና ምንደኛ በመሆን የሚታወቁበት፣ ተጠያቂነት የላላበት፣ ሕጋዊ የፖለቲካ ሥርዓት መኖሩም የሚረሳበት፣ ፀረ ዴሞክራሲያዊ አገሮች መጨረሻቸው ውድቀት ቢሆንም፣ የሙስና መቀፍቀፊያና የሕዝብ ምሬት ማሳያ ሆነው አሉ፡፡ ከወደቁት አገሮች መማር ያስፈልጋል፡፡
በእኛ አገር ዓይናችንን ጨፍነን እዚህ ደረጃ ላይ እንደርሳለን ባይባልም፣ ከወዲሁ መገራት ያለባቸው የአሠራር ክፍተቶች እንዳሉ ግን መካድ አይቻልም፡፡ እውነት ለመናገር ግን ትናንትም ሆነ ዛሬ የእኛ አገርና መሰል ታዳጊ አገሮችን እየፈተነ ያለው ሙስና በዋናነት ግለሰባዊ ሙስና (Individual Corruption) መሆኑ ላይ ልንጠራጠር አንችልም፡፡
እንደ ኢትዮጵያ በመርህ ደረጃ ወይም ሕጎቻችን ሙስናን አይፈቅዱም፡፡ በጀት ስረቅ፣ ሕዝብን ያላግባብ በዝብዝ ብሎ በድፍረት የሚናገር መሪም አልነበረም፣ አሁንም የለም፡፡ ስለሆነም እንደ ሕዝብ ሙሰኞችን በንቃት ለመፋለም ‹‹አቤት›› ብንልና ብናጋልጥ ሕጋዊ ዕርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ እንችላለን፡፡ የተሻለ ውጤትም ማምጣት ይቻላል፡፡ ለዚህ ግን የመገናኛ ብዙኃንን የግልጽነት ባህል ማዳበር፣ የፍትሕ አካላትንና የፀረ ሙስና ተቋማትን የጠያቂነት አቅም ማዳበር ግድ ይላል፡፡
እንደ ሕዝብ ግን በተጨባጭ ተጋፍጠን ወንጀልን በማጋለጣችን ጉዳያችን አይፈጸም ይሆናል፡፡ በኔትወርክና በጥቅም በተሳሰሩ ኃይሎች የበቀል ዕርምጃ ይደርስብናል፣ ወይም እገሌን ባጋልጠው እከሌ የሚባለው ዘመዱ (የአካባቢው ሰው) ስለሆነ ይከፋል የሚል ፍርኃት እንደሚኖርብንም አይካድም፡፡ በዚህ ላይ በብሔርና በመንደር መጠባበቁ ቀላል እንዳልሆነ አይካድም፡፡ ግን ከደፈርን በተለይም ከተባበርን ሙሰኞችን ማሳፈር፣ ብሎም በሕግ መጠየቅ ይቻላል፡፡ ውስን ናቸው እንጂ የቻሉ ብርቱዎችም አሉ፡፡
ይህን የሕዝብና የዜጎችን በሙስና ያለመሸነፍ ትግል የሚያነሳሳው ግን ሥርዓቱ መሆን አለበት፡፡ የፌዴራል፣ የክልል መንግሥታትና ከተማ አስተዳደሮች የተናጠልም የጋራም ኃላፊነታቸውን መወጣትም ግድ ይላቸዋል፡፡ ብልፅግና ራሱም ቢሆን ከኢሕአዴግ ውድቀት ትምህርት ወስዶ ምርር ያለ ሕዝባዊ የፀረ ሙስና ትግል እንዲደረግ ይፈልግ ይሆን? የሚለው የብዙዎች ሥጋት ግን ከሚመለከተው አካል የተግባር ምላሽ ይፈልጋል፡፡ ሌላው ቀርቶ የባለሥልጣናቱ የሀብት ምዝገባ ሒደት ምን ላይ ነው የቆመው? ዋና ዋና የለውጡ መሪዎቹና የሕዝብ አደራ የተሸከሙ አካላት ሀብትስ ስለምን ለአብነት አይቀርብም? ብሎ መጠየቅ ግድ ይላል፡፡
ዛሬም እንደ ትናንቱ ምንም እንኳን ጉቦ ሲቀበሉ በዓይናችን ባናይም፣ የአሉባልታውንም ያህል አንዳንዱ ላይ በቂ ማስረጃ ባይኖረንም፣ የመንግሥት ሹመኞችና አንዳንድ ሠራተኞች ከገቢያቸው ጋር በማይመጣጠን ሁኔታ ሕይወታቸው መለወጡን እንታዘባለን፡፡ ቤታቸው ተገንብቶ፣ በውድ ውድ የቤት ዕቃዎች ተሞልቶ፣ እንደ ልብ ተበልቶና ተጠጥቶና ተዝናንቶ ልጆችን ውድ ትምህርት ቤት አስገብቶ፣ መኪና ተገዝቶ ሲታይ ‹‹ከየት አመጡ›› ብሎ መጠየቅ እንደ ነውር ሊቆጠር አይገባም፡፡ መበረታት ነው ያለበት፡፡ የብልፅግና አዲሱ ትውልድ ማስረፅ ያለበትም ይህን አስተምህሮ ሊሆን ይገባል፡፡
ላይጠቀሙበትና ይዟቸው ሊጠፋ ትናንት በመዲናችን አዲስ አበባ ከትልልቅ ሕንፃዎች ጀርባ የሚነሱ ብዙ ስሞች እንደነበሩ መዘንጋት አይቻልም፡፡ በአጭር ጊዜ በኮንትሮባንድ፣ ከቀረጥ ነፃና የመሬት ወረራ ቁንጮ ባለሀብት መሆን የጀመሩ ጥገኞች አገር የሚጠፋ የዕብሪት ድርጊት ውስጥ የገቡት በወቅቱ ተቆጪና ቀጪ ሕዝብና መንግሥት በማጣታቸው እንደነበር ለአፍታም መርሳት ሞኝነት ነው፡፡ አሁን ደግሞ ብቅ ብቅ ካሉ አንዳንድ ዋልጌዎች ጋር በእንጭጩ መቆራረጥ መለመድ ይኖርበታል፡፡
ለዚህ ደግሞ መዲናችንን ጨምሮ በብዙዎቹ ትልልቅ ከተሞች ዛሬም ቢሆን በቀላሉ የመሬት ካርታ በማውጣት፣ ግብር በመሰብሰብና በቅሬታ ምላሽ፣ በግንባታ ፈቃድ፣ በዕድሳትና በኮንትራት፣ በማዕድን ማውጣት ሥራ፣ በወንጀል ምርመራ… መሰል መስኮች ላይ ያለውን እንግልትና አሻጥር መፈተሽ ግድ ይላል፡፡ እውነተኛ የሕዝብ ተቆርቋሪነት ካለም ሕዝብን እያሳተፉ የግልጽነትና ተጠያቂነት ሥርዓቶችን ማጠናከር ይበጃል፡፡
ተደጋግሞ በተጨባጭ እንደታየው ከበፊት አንስቶ ጉቦ የለመደ ሠራተኛ ገንዘብ ይዞ ላልመጣ ሰው ጉዳዩን ሊፈጽምለት አይችልም፡፡ አበሳጭቶ፣ አመላልሶና አማርሮ በማንገላታት ዜግነቱን እንዲጠላ ያደርገዋል፡፡ ሕዝብ በመንግሥት ላይ እንዲማረር ይገፋዋል፡፡ መረጃ ቢኖረው እንኳን ማስረጃ አምጣ እያለ እንደ ውኃ ቀጂ ያመላልሰዋል፡፡ የሕዝብና የመንግሥት መረጃን ቀድሞ እያወጣ ያስፈራራዋል፡፡
ይህም ተገልጋዩ ሳይወድ በግድ በእጅ መንሻ ለመኖር ያስገድደዋል (ይህን ዛሬም በገቢ መሥሪያ ቤቶች በተለይ ኦዲተሮች፣ በፍትሕና በፖሊስ አንዳንድ አካላት፣ በመሬትና በማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት… አካባቢ እንደሚጋፈጡ የሚናገሩት ብዙ ናቸው፡፡ ራሳቸው የመንግሥት አካላትም በቅርቡ ግምገማ እንዳነሱት አድምጠናል)፡፡ አሁን መጠየቅ ያለበት ችግሩን አዳምጦ ለመፍታት የሚረባረብ ራሱን የቻለ ጠንካራ ተቋምስ አለን ወይ? የሚለው ጥያቄና የመንግሥታዊ ቁርጠኝነት ጉዳይ ነው፡፡
በቀጣይም ዋነኛው መፍትሔ መንግሥት ከወዲሁ ሕዝቡን ማታገል፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱን ማጠናከርና ተጠያቂነትን ማስፈን እንደሆነ ተገንዝቦ ካልዘመተበት ችግሩ ሊቀረፍ አይችልም፡፡ እውነት ለመናገር እስካሁንም ቢሆን በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ በሙስና ጉዳይ ላይ ዝም ያለ አልነበረም፡፡ መሪዎቻችን ይናገራሉ፡፡ ጋዜጦቻችን ይጽፋሉ፣ ሬዲዮና ቴሌቪዥኑ ያወግዛሉ፣ የሃይማኖት አባቶች ይመክራሉ፡፡ ዞሮ ዞሮ ውኃ ቢወቅጡት እንቦጭ እየሆነ መሻሻሉ በተፈለገው መጠን ማምጣት ለምን አልተቻለም ብሎ መፈተሽ ወቅቱ የሚጠይቀው ወሳኝ ተግባር ሆኖ ይገኛል፡፡
እዚህ ላይ ለልጆቻችን የተሻለች አገር ከማስረከብ፣ ትውልዱን በሥነ ምግባርና በሞራል ከማስተማር ጀምሮ፣ ሙሰኛን የዘረፈውን የሕዝብ ሀብት ወደ መንግሥት በማስመለስ ማስተማር ያስፈልጋል፡፡ የቅደም ተከተል ጉዳይ ሆኖ እንደሆን እንጂ፣ በየትኛውም ደረጃ የሚገኝ ባለሀብት ወይም ባለሥልጣን ቢሆን በሕግ የበላይነት መርህ እንዲመራ፣ ዴሞክራሲያዊነትን በማስፋት (የሐሳብ ነፃነት፣ የመደራጀት፣ የሕግ የበላይነት፣…) የሙስናን ሥሩን መንቀል ባይቻል እንኳን በእርግጠኝነት ማዳከም ይቻላል፡፡ ከተበረታም መሆኑ አይቀርም፡፡
ቢያንስ ከለውጡ ወዲህ በክልሎችም ሆነ በፌዴራል ደረጃ ጠቅላይ ዓቃቢያነ ሕግና የፀረ ሙስና ኮሚሽኖችም በመንግሥት ተቋማት ውስጥ የሚካሄዱ ምንም ዓይነት ብልሽቶችንና ሙስናዎችን ለመከላከልና ለመቀነስ፣ ከመቼውም ጊዜ በላይ መትጋት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በእርግጥ የትኛውም ምሁርና የምርምር ሰነድ ሙስናን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚያስወግድ ተዓምራዊ ቀመር (Magic Formula) ሊኖረው አይችልም፡፡ ሕዝብና መንግሥት በጋራ ከተረባረቡ ግን ሊያዳክሙት ይችላሉ፡፡ በየዘርፉ የሞቀና ጠንካራ ትግል መለመድም አለበት፡፡ ያኔ ለውጡ በሙሉ እግሩ ይቆማል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡