በጌታቸው አስፋው
የሥራ ቅጥር፣ የሥራ ዋጋ፣ የሥራ ገበያ፣ የሠራተኛ ፍላጎት፣ የሠራተኛ አቅርቦት፣ የሥራ አጥነት ሁኔታ፣ የማክሮ ኢኮኖሚክስ ጥናት መስክ ነው ወይስ የማይክሮ ኢኮኖሚክስ ጥናት መስክ ነው በሚል ጉዳይ ላይ ኢኮኖሚስቶች በሐሳብ ይከፋፈላሉ፡፡ በአጠቃላይ አነጋገር ገበያና የዋጋ አወሳሰን ሥርዓት የማይክሮ ኢኮኖሚክስ የጥናት መስክ ሲሆን፣ ሥራ አጥነትን የመሰለ ሕዝባዊ ጉዳይ ደግሞ ከዝርዝር የገበያ ጥናት ይልቅ፣ የጥቅል የማክሮ ኢኮኖሚና የመንግሥት ፖሊሲ ጉዳይ ነው፡፡ ለመኖር መሥራት ስለሚያስፈልግም ሥራ ማግኘትና ማጣት የኑሮ ደረጃን አመልካች ነው፡፡ የዋጋ ንረት አመልካች የኑሮ ደረጃ አመልካች አካል ስለሆነም፣ ከአገራዊ የዋጋ አመልካች ጎን እያንዳንዱ ሰው የየራሱን ኑሮ መመርመር አለበት፡፡
ይህችን ሰሞን ጨምሮ የጠቅላይ ስታትስቲክስ ባለሥልጣን የዋጋ ንረት አመልካቾችን መረጃ ካወጣ በኋላ በርካታ ጋዜጠኞች ደውለውልኛል፡፡ ምክንያቱ ምንድንው መፍትሔውስ ይሉኛል፡፡ ካቻምና የጠየቁኝን ዓምናም መልሰው ጠይቀውኛል፡፡ ዓምና የጠየቁኝንም ዘንድሮም መልሰው ጠይቀውኛል፡፡ ዘንድሮ የጠየቁኝንም ለከርሞ መልሰው እንደሚጠይቁኝ እገምታለሁ፡፡ ስለዋጋ ንረትና አለካኩ፣ ምክንያቱ፣ ውጤቱ ምን ያህል አሳስቧቸው ወይም አድማጭ እንደሚረዳቸው ተገንዝበው፣ የመፍትሔው አካል ማን ሊሆን እንደሚችል አውቀው እንደሚጠይቁኝ አላውቅም፡፡ የእኔ መልስም ምን ያህል እንዳረካቸው አላውቅም፡፡
ዋጋ የሌለው ነገር የለም፡፡ ዋጋው የማይጨምር ነገርም የለም፡፡ ዋጋው የማይቀንስ ነገርም የለም፡፡ ከጊዜ ጋር ብዙ ነገሮች ይቀያየራሉ፡፡ ብር የሌሎችን ሸቀጦች ዋጋ ይተምናል፡፡ በቀድሞ ጊዜ አሞሌ ጨውና ጠገራ ብርም የሌሎችን ሸቀጦች ዋጋ መተመኛ መሣሪያ ሆነው አገልግለዋል፡፡ የብር የራሱም ዋጋ በሌሎች ሸቀጦች ዋጋ ይተመናል፡፡
ለምሳሌ ከአምስት ዓመት በፊት በአሥር ብር ሦስት ራስ በቆሎ እሸት ይገዛ ነበር፡፡ የሦስት ራስ በቆሎ እሸት ዋጋ አሥር ብር ነበር፡፡ የብርን ዋጋ ስንለካ የአሥር ብር ዋጋ ሦስት ራስ በቆሎ እሸት ነበር፡፡ ዘንድሮ የአንድ ራስ በቆሎ ዋጋ አሥር ብር ሆነ፡፡ ስለሆነም የአሥር ብር ዋጋ አንድ ራስ በቆሎ እሸት በመሆን፣ የብሩ ዋጋ ከአምስት ዓመት በፊት ከነበረበት ዋጋ ተቀይሯል፡፡
ደርግ ሥልጣን ሲለቅ የአንድ ኪሎ ቡና ዋጋ ሦስት ብር ነበር፡፡ ያኔ የሦስት ብር ዋጋ አንድ ኪሎ ግራም ቡና ነበር፡፡ ዛሬ የአንድ ኪሎ ግራም ቡና ዋጋ ሦስት መቶ ብር ሲሆን፣ የሦስት መቶ ብር ዋጋ አንድ ኪሎ ግራም ቡና ሆነ፡፡ በ1990ዎቹ ከሉካንዳ ቤት አንድ ኪሎ ሥጋ በአሥር ብር ይገዛ ነበር፡፡ ያኔ የአሥር ብር ዋጋ አንድ ኪሎ ሥጋ ነበር፡፡ ዛሬ በሉካንዳ ቤት አንድ ኪሎ ሥጋ በአማካይ አምስት መቶ ብር ያወጣል፡፡ የአምስት መቶ ብር ዋጋ አንድ ኪሎ ሥጋ ነው ማለት ነው፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት አንድ እንቁላል ሁለት ብር ያወጣ ነበር፡፡ ያኔ የሁለት ብር ዋጋ አንድ እንቁላል ነበር፡፡ ዛሬ የአንድ እንቁላል ዋጋ ስምንት ብር ሲደርስ፣ የስምንት ብር ዋጋ አንድ እንቁላል ነው፡፡
ሥራ የሚሠራ እያንዳንዱ ሰውም የገበያ ዋጋ አለው፡፡ ዋጋቸው የሚጨምርም ዋጋቸው የሚቀንስም ሰዎች አሉ፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት አምስት ሺሕ ብር ደመወዝ ያገኝ የነበረ ሰው በጊዜው የአንድ ኩንታል ጤፍ ዋጋ ሁለት ሺሕ አምስት መቶ ብር ሒሳብ፣ የሰውየው የወር የሥራ ዋጋ ሁለት ኩንታል ጤፍ ነበር፡፡ ዛሬ ያንኑ ደመወዝ የሚያገኝ ሰው የወር የሥራ ዋጋው አንድ ኩንታል ጤፍ ነው፡፡ በሌሎች ሸቀጦች መለኪያነትም የራሱን ዋጋ ሊያውቅ ይችላል፡፡ ይህን ሳያውቅ ለኢኮኖሚስት እንኳ ትርጉማቸው ግራ በሚያጋባ አገራዊ የዋጋ ንረት አመልካቾች ዕድገት የዘንድሮው ከዓምና ጋር ሲነፃፀር ከኢኮኖሚስት ሰማሁ በማለት ቁንፅል ጥያቄ ጠይቆ ቁንፅል መልስ አግኝቶ ለሕዝብ ቁንፅል መረጃ ለመስጠት ጋዜጠኛው ይደክማል፡፡ ኢኮኖሚክሱ በትክክል ያልገባው ሰውም የራሱን ዋጋ ሳያውቅ የሌላውን ዋጋ ለማወቅ ይሻል፡፡
የዓምናውን ከዘንድሮ በዕድገት መጣኝ ማወዳደር በየዓመቱ ከዓምናው ጋር ሲነፃፀር የሚል ዘገባ ለሚዲያ ፍጆታ ብቻ ብሎ ማቅረብና የኢኮኖሚ ባለሙያ ላልሆነ ሰው መንገር ጥቅሙ ለእኔ በግሌ እየቀነሰብኝ መጥቷል፡፡ እያንዳንዱ ሰው ኑሮው ጉሮሮው ስለሆነ ነገር አይወቅ ማለቴ አይደለም፡፡ በተቃራኒው ማወቅ አለበት ማለቴ ነው፡፡ ሲያውቅ ግን ምንን እንደሚያውቅ አውቆ ነው እንጂ ማወቅ ያለበት፣ እንዲያው ዝም ብሎ ቁጥር ከቁጥር መበላለጡን ብቻ ማወቅ ብዙ አይጠቅመውም የሚል እምነት ስላለኝ ነው፡፡ በጠቅላይ ስታትስቲክስ ባለሥልጣን ጥናት መሠረት የሚቀርብ መረጃን ሙሉ ትርጉም ለመረዳት፣ በቅድሚያ አገራዊ የዋጋ ንረት አመልካች ለአገርም ለራስም ምን ትርጉም እንዳለው ጽንሰ ሐሳቡን መረዳት ያስፈልጋል ብዬ አምናለሁ፡፡
አገራዊ የዋጋ ንረት አመልካችና የኑሮ ደረጃ ተቃራኒ የሆኑ ነገሮች ናቸው፡፡ የዋጋ ንረት አመልካች ሲጨምር የሕዝብ የኑሮ ደረጃ ይቀንሳል፡፡ በግለሰቦች የአንዳንዱ የኑሮ ደረጃ መቀነስና መጨመሩን ግን ራሱ የራሱን ለክቶ ነው የሚያውቀው፡፡ ባለፉት አምስት፣ አሥር፣ ሃያና ሰላሳ ዓመታት እያንዳንዱ ሰው የራሱ ዋጋ ምን ያህል እንደጨመረ ወይም እንደቀነሰ፣ ይህን ተከትሎም የኑሮ ደረጃው ምን ያህል እንደጨመረ ወይም እንደቀነሰ ራሱ የራሱን ለክቶ ወይም ገምቶ ሊያውቅ ይችላል፡፡
የአትራፊዎች ዋጋ በሚሊዮኖች ሊቆጠር ስለሚችል፣ እነሱን ትቼ በደመወዝ ተከፋይነት በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛው ማማ ላይ የደረሱትን ባለ አንድ መቶ ሃምሳ ሺሕ ብር የወር ደመወዝተኞች የባንኮች ሥራ አስኪያጆችን፣ በብርም ሆነ በሌሎች ሸቀጦች ዋጋ ተመን ምን ያህል እንደሚያወጡ መለካት እንችላለን፡፡ ደርግ ሥልጣን ሲለቅ አንድ ሺሕ አምስት መቶ ብር ደመወዝ የነበረው የባንክ ሥራ አስኪያጅ፣ በያኔው አንድ መቶ ሃምሳ ብር የአንድ ኩንታል ጤፍ ዋጋ በወር ደመወዙ ዋጋው አሥር ኩንታል ጤፍ ነበር፡፡ አሁን መቶ ሃምሳ ሺሕ ብር ሲያገኝ በአምስት ሺሕ ብር የኩንታል ጤፍ ዋጋ የሥራ አስኪያጁ የወር ዋጋ ሰላሳ ኩንታል ጤፍ ነው፣ የኑሮ ደረጃው አድጓል፡፡
በተቃራኒው ደርግ ሥልጣን ሲለቅ የወር ደመወዙ አንድ ሺሕ አምስት መቶ ብር የነበረ ሚኒስትር በጊዜው አንድ መቶ ሃምሳ ብር የኩንታል ጤፍ ዋጋ የተለካ፣ የወር ዋጋው አሥር ኩንታል ጤፍ ነበር፡፡ አሁን አንድ ሚኒስትር አስራ አምስት ሺሕ ብር የወር ደመወዝ ቢያገኝ፣ በአምስት ሺሕ ብር የአንድ ኩንታል ጤፍ ዋጋ ሲለካ የሚኒስትሩ የወር ዋጋ ሦስት ኩንታል ጤፍ ነው፡፡ በሌሎች ሸቀጦች ዋጋ መለኪያነትም የራሱን የግል የኑሮ ደረጃ በተመሳሳይ ሁኔታ መለካት ይችላል፡፡
እያንዳንዱ ሰው የወር ዋጋውን በብር ብቻ ሳይሆን በቃሪያ፣ በሎሚ፣ በሽንኩርት፣ በጥራጥሬ፣ ወዘተ በእያንዳንዱ ሸቀጥ ዋጋ መለኪያም ሊለካ፣ የወር አስቤዛውን መጠን በቅርጫት ውስጥ ከቶ ዋጋ አውጥቶለት ሊለካ፣ ከዓመት ዓመት ልዩነቱን ሊያወዳድር፣ የዋጋውንና የኑሮ ደረጃውን መውጣትና መውረድ ሊያመዛዝንም ይችላል፡፡ መጠኑ ከመጣኙ የበለጠ ትርጉም ቢሰጥም፣ የዓምናው መቶ ቢሆን የዘንድሮው መቶ ስንት ሆነ ብሎ በመጣኝ አስልቶ ለራሱ የዋጋ ንረት አመልካች ሊያወጣ ይችላል፡፡
ሆኖም ከዓመታዊ የዋጋ ንረት ንፅፅሩ በላይ ከፍ ብዬ የጠቀስኩት የሰውን ዋጋ፣ የኑሮ ደረጃውን በዕቃዎች ዋጋ መጠን መለካቱ በግልና በሚያስተዳድራቸው ቤተሰብ የኑሮ ደረጃው ምን ያህል እንዳሻቀበ ወይም እንዳቆለቆለ ይነግረዋል፡፡
በቴክኖሎጂ ዕድገትና በምርታማነት መጨመር የዓለም ሕዝብ የወር የሥራ ዋጋ እያደር ይጨምራል፡፡ ይህም በነፍስ ወከፍ አገራዊ ገቢ መረጃ ማደግ መገለጫነት የተረጋገጠ ነው፡፡ የኢትዮጵያዊ የሥራ ዋጋና የኑሮ ደረጃ እንደ ኤሊ ጉዞ በጣም የተንቀረፈፈ ነው፡፡ ከሃምሳ ዓመት በፊት ቅኝ ተገዥ የነበሩ ጎረቤቶቻችን ነፍስ ወከፍ ገቢያቸው ሁለትና ሦስት ሺሕ ዶላር ከገባ ዓመታትና ወራት አስቆጥሯል፡፡ የእኛ ነፍስ ወከፍ ገቢ አንድ ሺሕ ዶላር ገባ ብለን የምንደሰተው ገና ዛሬ ነው፡፡ ይህስ ቢሆን በትክክል ተለክቷል ወይ? እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በዓመት ሃምሳ ሺሕ ብር ነፍስ ወከፍ ገቢ አለው ወይ? የገጠሩና የከተሜው ሕዝባችን የገቢ ክፍፍልስ ፍትሐዊ ነው ወይ? በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙና በተነፃፃሪነት በከፍተና የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሕዝቦች የገቢ ክፍፍልስ ፍትሐዊ ነው ወይ? ከአገራዊ ነፍስ ወከፍ ገቢ ጎን ለጎን ማወቅና መረዳት የሚገባን ነገሮች ናቸው፡፡
በየዓመቱ የኤክስፖርት ሸቀጦቻችን ዋጋ ለዓለም ሕዝብ ሲቀንስ፣ የኢምፖርት ሸቀጦቻቸው ዋጋ ለእኛ እየጨመረ ነው፡፡ ቡናውን ቆልተን ስላልሸጥነው ነው፣ ቆዳውን በጫማ መልክ አዘጋጅተን ባለመላካችን ነው እንላለን፡፡ ነገሩ የቡናና የጫማ ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ በአገር ውስጥ በሚሸጡትም፣ በውጭ በሚሸጡትም ምርቶቻችን ምን ያህል ቴክኖሎጂ ሰርፆና ምርታማነት ተዋህዶ ለውጪው ዓለም ሕዝብ ጠቃሚ ዕቃ ሆኖ በዓለም አቀፍ ገበያ ውስጥ ሊሸጥ የሚችል ሆኗል የሚለው ነው ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነታችንን የሚወስነው፡፡ በቴክኖሎጂም ሆነ በምርታማነት የእያንዳንዱ የዓለም ሕዝብ የሥራ ዋጋ ወደ ላይ ሲወጣ የእኛ የሥራ ዋጋ ወደ ታች እየወረደ እንደሆነ፣ ኤክስፖርቶቻችንና ኢምፖርቶቻችን ምስክር ናቸው፡፡
ሰሞኑን አንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ ከፍቼ የተመለከትሁትና የሰማሁት ነገር እጅግ ገርሞኛል፡፡ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በአንድ አዳራሽ ተሰብስበው የእምነት ሰባኪው ስልካችሁን በእጃችሁ ያዙ ብሎ ይፀልይላቸውና ስንት ብር በስልካችሁ ገባላችሁ ይላቸዋል፡፡ የራሳቸው የሥራ ዋጋ ሳይኖራቸው የሰውን የሥራ ዋጋ በነፃ ሊወስዱ የፈለጉ ሰዎች በአዳራሽ ተሰብስበው፣ በግላጭ በየተራ እየተነሱ ይህን ያህል ገባልኝ ይላሉ፡፡ እንዴት እንደዚህ በአምላክ ይቀለዳል? እንዴት እንደዚህ በክርስቶስ ይቀለዳል፡፡ የምድሩን ቀልዳችንን እንዴት ወደ ሰማያዊ ቀልድ እንወስደዋለን፡፡
ከዳያስፖራ ከዓለም ባንክ ከአውሮፓ ኅብረት ከዚህ አገር ከዚያ አገር ይህን ያህል ዕርዳታና ድጋፍ ብድር ተገኘ እየተባለ ሲነገር እንሰማለን፡፡ ለመሆኑ ይህ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ስንት ሰው ያውቃል፡፡ ኢኮኖሚያዊ ትርጉሙ ምን እንደሆነ ልንገራችሁ የሌሎች አገር ሕዝቦች ከሥራ ዋጋቸው ቀንሰው የቆጠቡትን እኛ እየተረዳንና እየተበደርን እየበላን ነው፡፡ ቴክኖሎጂ የሚሰርፀውና ምርታማነት የሚዳብረው በሁለት መንገድ ብቻ ነው፡፡ አንዱ ጥሬ የተፈጥሮ ሀብትን ወደ የተመረተ ካፒታልነት በመቀየርና ሁለተኛው የጉልበት ሥራ የሚሠራው ሰው ቁሳዊ ቴክኖሎጂውን ተጠቅሞ ማምረት እንዲችል፣ በሙያና በክህሎት የላቀ ደረጃ ላይ ሲደርስ ነው፡፡ ዓለም ስለየገበያ ኢኮኖሚ እየተነጋገረ ባለበት ጊዜ እኛ በተፈጥሮ ሀብት ሽሚያ እየተጨቃጨቅን የትም አንደርስም፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡