Monday, March 4, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትስለመነጋገር እስኪ እንነጋገር

ስለመነጋገር እስኪ እንነጋገር

ቀን:

በገነት ዓለሙ

ዴሞክራሲ መብቶችና ነፃነቶች የሚሠሩበት የሕዝብ አስተዳደር ነው፡፡ ሰብዓዊ መብቶችንና ነፃነቶችን መኗኗሪ ያደረገ ሥርዓት ነው፡፡ እነዚህ መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች በተፈጥሮ የተገኙ፣ ሰው በመሆናችን ብቻ የተጎናፀፍናቸው፣ ማንም የማይሰጣቸው፣ የማይነፍጋቸው ናቸው ማለት ዛሬ የትም ቦታ፣ መብቶቹና ነፃነቶቹ ለስም ጌጥ፣ ለወግ ያህልም ሆነ ለፍጆታ፣ ወይም እንደ ነገሩና የምርና የእውነት ይሠራሉ በሚባሉበት አገርና አኅጉር ሁሉ የሚነበነብ የሁሉም ሥልጣኔ የ‹‹ጥበብ›› መጀመርያ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ይህንን የሚክድ ‹ሥልጣኔ› የለም፣ ያለዚህ ቅድመ ሁኔታ የሚጀመር ዴሞክራሲ የለም፡፡

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ፣ በተለይም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኅዳር 22 ቀን 1943 ዓ.ም. በቁጥር 390(5) ስለኤርትራ የሰጠው ውሳኔን መነሻ አድርጎ፣ ይህንንም ኢትዮጵያ የፌዴራል አዋጅ ብላ መስከረም 1 ቀን 1945 ዓ.ም. ካፀደቀችው በኋላና ይኼው የፌዴራል አዋጅ ከ1923 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት ጋር የአገር የበላይ ሕግ ከሆነ ወዲህ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ከዚህ ሁነት በኋላ በኢትዮጵያ የፀደቁት ሕገ መንግሥቶች፣ መብቶችንና ነፃነቶችን በሕግ/በወረቀት በመደርደርና በመዘርዘር ረገድ ብዙ የሚነቀፍና የሚያደናቅፍ ችግር ስለነበራቸው አይደለም፡፡ ዴሞክራሲ ሊረጋገጥ የሚችለው በእነዚህ መብቶችና ነፃነቶች፣ እንዲሁም መቻቻል ውስጥ መኗኗርን መሠረት ማስያዝ ሲቻልና ችግር ሲመጣም በሰላማዊ፣ በሕጋዊና በዴሞክራሲያዊ መንገዶች ለመፍታትና ውጤቱንም ለመቀበል የሚያበቃ ሥርዓት ሲገነባ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ዴሞክራሲ የመብትና የነፃነት ሁኔታን፣ እንዲሁም ለዚህ የሚደረገውን ትግል ከዘመን ዘመን፣ ከለውጥ ለውጥ (በየጊዜው በተደረጉ የለውጥ የትግል ዘመኖች) ሰቅዞ ያቆየውና ድል ሲያሳጣው የኖረው ከቡድንም ሆነ ከግለሰብ ቁጥጥር የተላቀቀ ወገናዊ ያልሆነ ተቋም መገንባት ባለመቻሉ ነው፡፡ መንግሥታዊ ሥልጣን ከሕዝብ ድምፅ፣ ከሕዝብ ሿሚነትና ጠያቂነት ጋር እንዳይገናኝ ያደረገው፣ ሥልጣን ላይ ያለው አካል በሕዝብ ድምፅ የሚወጣና የሚወርድበት ሥርዓት የውኃ ሽታ ሆኖ የቆየው፣ የሕዝብና የመንግሥት ፍቅር የሚባል ነገር የጠፋው፣ የአገሪቱና የሕዝቧ ሰላምና ልማትም ከአደጋ አልወጣ ያለው፣ የመንግሥት አውታራት ወገናዊነት፣ ቡድናዊነት፣ ፓርቲያዊነት፣ የእነሱም ባለቤትነት ታማኝነትና አገልጋይነት ስላለ፣ ስለነበር፣ ስላልተቋረጠና ስላልቀረ ነው፡፡ ይህ ዋናውና አገር እየለፋበት፣ እየተጋደለለት፣ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ (መጋቢት 2010 ዓ.ም. በኋላ) ዒላማው አድርጎ የተነሳለት፣ ነገር ግን አደጋ፣ ጥቃትና ክህደት የደረሰበት ትግል ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

መንግሥታዊ አውታራትን ከቡድን ታማኝነትና ወገናዊነት ለማላቀቅ፣ አምባገነንነትንና የፓርቲም ሆነ የሌላ (የግለሰብ ሆነ የቡድን/የድርጅት) ወገናዊነትን እንዲያገለግሉ፣ የእነሱ ሀብትና ጉልበት ብቻ እንዲሆኑ የተቀረፁና የተቀናበሩ አውታራት ለሕግና ለሕዝብ ብቻ ታምነው እንዲሠሩ ለማድረግ (እነሆ) ከአራት ዓመት ወዲህ አዲስ የተጀመረውን ትግል፣ ለውጥና ሽግግር ከሁሉም በላይ የተገዳደረው ደግሞ የኢትዮጵያን ዴሞክራቶችና ታጋዮች የተጠናወተው ንግግርን፣ ዴሞክራሲያዊ ንግግርን አላውቅ ያለ፣ በአጠቃላይ ንግግር አይገባኝም ብሎ የተፈጸመ፣ ከ‹‹እኔ ብቻ ልክ››፣ ‹‹እኔ ያልኩት ካልሆነ አገር ይፈርሳል›› የሚነሳ ተጋዳይነት ሞቼ እገኛለሁ ባይነት ነው፡፡

መነጋገርን አለማወቅ፣ ንግግርን ውይይትን አላውቅም፣ አላውቅላችሁም ብሎ ለዴሞክራሲ መዋደቅ ብሎ ነገርና ችግር፣ ዛሬ ዛሬ በተለይም ‹‹ሕዝበኛ›› መሪዎችን ሥልጣን ላይ ሰቅሎ መከራ ማየትን የመሰለ ዕዳ አሜሪካንን ጨምሮ ባደጉ አገሮች ያመጣው ጣጣ ከተከሰተ በኋላ፣ የእኛ ብቻ ችግር አይደለም፡፡ እነ አሜሪካንም ዛሬ እንደ ኮቪድና ከኮቪድ በላይ ወጥሮ የያዛቸው ሕመም ነው ሲባል እንሰማለን፡፡ በእነሱና በእኛ መካከል ያለው መነጋገር ላይ የመደናቆርና ንግግርን አላውቅም የማለት ችግር ግን ልዩነት አለው፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ልዩነት አለው ይባላል፡፡ እነሱ ጋ ከዚህ ቀደም ነበር፣ እኛ ጋ ጨርሶ የሚታወቅ አይደለም፣ አይታወቅም፡፡ እነሱን ያቃታቸው የነበራቸውን፣ የጠፋባቸውን፣ የት እንደሄደባቸው የማያውቁትን የመነጋገር ጥበብ ፈልጎ ማግኘት ነው፡፡ ፈልጎ የማግኘት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን መፈለግ መጀመር፣ የመፈለግን አስፈላጊነት ገና አልተረዱም ይባላል፡፡ የእኛ ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ‹‹ያልፈጠረብን››ን ነገር ገና የመፈለግ ነገር ነው፡፡ ልብ ብሎ ለሚመለከተው የሚገርም ነገር አለው፡፡ ንግግርን፣ የንግግርን አስፈላጊነት፣ የንግግር አስፈላጊነት ብቻ ሳይሆን፣ የንግግርን ጥበብ ሳያውቁ ለዴሞክራሲ እታገላለሁ ማለት ገና ከመነሻው ፉርሽ መሆን ነው፡፡ ሳይጀምሩ መክሸፍ ነው፡፡

መነሻዬ ላይ ዴሞክራሲ መብቶችና ነፃነቶች የሚሠሩበት፣ መኗኗሪያ የሚሆኑበት የሕዝብ አስተዳደር ነው ብያለሁ፡፡ ይህንን የመሰለ የአገሪቱን ሕዝቦች ድምፅ ሰጥተው የገለጹትን ፍላጎት ልዕልና መወከል የሰመረለት ዴሞክራሲና ሪፐብሊክ ለማደራጀት ሕገ መንግሥቱ ዋስትናና መተማመኛ የሰጠባቸው መብቶች ሲሠሩ፣ የሕዝብ መኗኗሪያ ሲሆኑ፣ ከስም ጌጥ ይልቅ ህልውና አግኝተው ሲላወሱ፣ ሕዝብን ከእነ ሁለመናቸው ሲያላውሱና ሊያንቀሳቅሱ ማየት አለብን፡፡ በእርግጥ ይህንን ለማረጋገጥ የመንግሥት አደረጃጀትና የአውታራቱ ባህርይ ገለልተኛ ሆኖ መቀረፅ አለበት፡፡ እንዲያ ባለም ሆነ፣ እሱኑ በመሰለ ሥርዓት ውስጥ ሳይቀር መነጋገርን አላውቅም ማለት ካለ፣ ዴሞክራሲያችን ‹‹ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ›› ነው፡፡

የንግግርና ሐሳብን የመግለጽ ነፃነትን ምሳሌ አድርገን ጉዳዩን እንመልከተው፡፡ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የአንቀጽ 29 ድንጋጌ የአመለካከትና ሐሳብን በነፃ የመያዝና የመግለጽ መበትና ነፃነትን ይደነግጋል፡፡ ማናቸውም ሰው ያለ ምንም ጣልቃ ገብነት የመሰለውን አመለካከት ለመያዝ ይችላል ይላል፡፡ እንዲሁም ማናቸውም ሰው ያለ ምንም ጣልቃ ገብነት ሐሳቡን የመግለጽ ነፃነት አለው ብሎ ይደነግጋል፡፡ በተለይም ይህንን ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት ይዘት ትርጉምና ዳር ድንበር ሲገልጽ፣ ይህ ነፃነት በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጪ ወሰን ሳይደረግበት፣ በቃልም ሆነ በጽሑፍ ወይም በኅትመት በሥነ ጥበብ መልክ ወይም በመረጠው በማናቸውም የማሠራጫ ዘዴ ማንኛውንም ዓይነት መረጃና ሐሳብ የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሠራጨት ነፃነቶችን ያካትታል ይላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የአመለካከትና ሐሳብን በነፃ የመያዝና የመግለጽ መብትና ነፃነት እንደሌሎቹ የሕገ መንግሥቱ መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች አፈጻጸምና አተረጓጎም ኢትዮጵያ ከፈረመቻቸውና ካፀደቀቻቸው የአገሪቱ ሕግ አካልም ከሆኑ ዓለም አቀፋዊ የሰብዓዊ መብቶችና ነፃነቶች ሕጎች ስምምነቶችና ሰነዶች ጋር መጣጣም አለበት፡፡

በዚህ ሕግና ይህ ሕግ፣ ሕገ መንግሥታዊ መተማመኛና ዋስትና በሚሰጠው ነፃነትና መብት መሠረት እያንዳንዳችን የመሰለንን አመለካከት ለዚያውም ያለ ምንም ጣልቃ ገብነት መያዝ መብታችን ነው፡፡ ይህ የማንኛወም ሰው መብትና ነፃነት ነው፡፡ የኢትዮጵያውያን ብቻ አይደለም፡፡ ሕገ መንግሥታችንና ‹‹ዴሞክራሲ››ያችን ይህንን ያህል ከግለሰብ ደረጃ የሚጀምርና ከዚያ የሚነሳ የተለያየ አመለካከት የመጫር፣ የመፅነስ፣ የመያዝ መብትና ነፃነት ያረጋግጣል፡፡

ሰዎች ደግሞ በ‹‹ማኅበር›› አብረን የምንኖር ፍጡራን ነንና በአኗኗራችንና በኑሮ ጥቅማችን ውስጥ በመደብም ሆነ በሌላ ጉዳይ በመለያየታችንና በመገናኘታችን ልክ የሚወሰን የአመለካከትና የፍላጎት ተመሳሳይነት፣ እንዲሁም ልዩነት አለ፡፡ እያንዳንዱ ሰው ‹‹ያለ ምንም ጣልቃ ገብነት›› የመሰለውን አመለካከት ከመያዝ መብቱ ይነሳና ሰዎች በአመዛኙ በኑሮ ጥቅም በመገናኘታቸው ልክ የሚወሰን (በአጠባ፣ በአፈና፣ በጥዝጠዛ ከሚጫን አቋም ውጪ) የአመለካከትና የፍላጎት ተመሳሳይነት ይፈጥራሉ፡፡ በአንድ ሰፊና መሠረታዊ ተመሳሳይነት ውስጥም፣ በጋራ መደባቸው ወይም የኑሮ ጥቅማቸው ውስጥ ካለ የጥቅም ሠፈር የሚመነጭ ልዩነት ይመጣል፡፡ ፓርቲዎችም እነዚህን ተመሳሳይነቶችና ልዩነቶች አደራጅተው፣ ፈርጀው፣ የተለያዩ ፍላጎቶችንና ዓላማዎችን ደርድረው፣ ሰድረውና ዘርዝረው በየፀበላቸው፣ ‹‹በሥፍራና በቦታ›› አገናኝተው ለተባሉት ለእነዚህ ፍላጎቶች ስም አውጥተው፣ የፖለቲካ ቀለም ሰጥተው፣ ዓርማ አበጅተው ለትልቁ የአገር ‹‹ጨዋታ›› ወይም ‹‹ግጥሚያ›› ይዘጋጃሉ፣ ያዘጋጃሉ፡፡ ፓርቲዎች ይህን ያደርጋሉ ስል ነገሩን ለማስረዳት ያህል ጉዳዩን አቅልሎ ለማሳየት እንጂ፣ ፓርቲዎች በ‹‹አመለካከት›› የተገናኙ ሰዎች በመደራጀት መብታቸው የሚያቋቁሙዋቸው ‹‹የመሰለውን አመለካከት›› የመያዝ መብት ያላቸው ሰዎች ፍጡር ናቸው፡፡

ከሕገ መንግሥቱ ውስጥ አንድ ሌላ ድንጋጌ ልውሰድና ጉዳዬን ቀጥዬ ላስረዳ፡፡ አንቀጽ 56 የፖለቲካ ሥልጣን እንዴትና ማን እንደሚይዝ ከተገለጸባቸው/ከተደነገገባቸው መካከል አንዱ ነው፡፡ ‹‹በምክር ቤቱ አብላጫ መቀመጫ ያገኘ የፖለቲካ ድርጅት ወይም ጣምራ ድርጅቶች የፌዴራሉን መንግሥት የሕግ አስፈጻሚ አካል ያደራጃል/ያደራጃሉ፣ ይመራል/ይመራሉ›› ይላል፡፡ ይህ የፖለቲካ ሥልጣን ድንጋጌ ራሱ በውስጠ ታዋቂነት ብቻ ሳይሆን በግልጽ እንደሚያሳየው፣ ሕገ መንግሥታዊ የሥልጣን አያያዝ ፍጥርጥርም እንደሚያስረዳው የመንግሥት ሥልጣን የመያዝ የዜጎች ፍላጎት ለፈለጉት ማንኛቸውም ዓላማ ከመደራጀት፣ ፓርቲ/የፖለቲካ ድርጅት ከማቋቋም መብት ይነሳል፣ ወይም ይህን ቅድመ ሁኔታ ያደርጋል፡፡ የመደራጀት መብትም በገዛ ራሱ የመሰለውን አመለካከት መብትና ነፃነት ይፈልጋል፡፡ የትኛውም ፓርቲ ይሁን የድምፅ ብልጫ አግኝቶ፣ የሕዝብን ፈቃድ ረትቶ፣ ፍላጎቱን ውሳኔ ማድረግ የሚያስችል የጨዋታ ሕግ ይጠይቃል፡፡ በአንድ ወይም በሌላ ፓርቲና በዚያ ፓርቲ መስመር የመመራት፣ የማመን ነገር የተለያዩ ሐሳቦች መኖራቸውን ከመቀበል፣ ከእነዚህ የተለያዩ ሐሳቦች ጋር ውድድር ገጥሞ ሐሳብን በሐሳብ ረትቶ ሰፊ ተቀባይነትም አግኝቶ፣ ይህንንም በሕዝብ ነፃ ድምፅ በምርጫ የማረጋገጥ ግዳጅን አስፈላጊ ያደርጋል፡፡

አገራችን ውስጥ ይህ ባህል ገና የለም፡፡ ይፋና የጓዳ የፖለቲካ መድረካችንም ሆኑ ግንኙነቶቻችን ዥንጉርጉር ሐሳቦችን በማፍራትና ከመካፈል ጋር ብዙ አይተዋወቁም፡፡ ይህ ችግር፣ ይህ ደዌ የሚጀመረው ፖለቲካዊ ባልሆኑ ግንኙነታችንም ነው፡፡ ከፖለቲካ በመለስ ባሉ ጉዳዮችም ከራሳችን የተለየ ሐሳብ ለመስማት ቻይነት የለንም፡፡ የሠፈር፣ የሥራ ቦታ ጓደኝነታችን፣ ጉድኝታችን ይህንን መከላከል ወይም መሸሽ እንዲችል ተደርጎ የተደራጀ ነው፡፡ ድንገት ሐሳባችን ሲተች ኩርፊያን፣ ሐሜትን፣ ንቀትን፣ መሠሪነትን መሣሪያ ከማድረግ ‹‹ነውር››› አልወጣንም፡፡ ይህን የጥንት የጠዋቱን ነውር ዛሬም ለዴሞክራሲ እንዋደቃለን፣ ዴሞክራቶች ነን በምንልበት ወቅት አላነወርነውም፡፡

አንድ ሐሳብ ብቻ ማለት ያለ እኔ ሐሳብ፣ ያለ እኔ መሪነት ባይነት በእኛ አገር በኃይለ ሥላሴ፣ በደርግ፣ በኢሕአዴግም ጊዜ እንደታየው፣ በሌሎች አገሮችም እንደተመሰከረው የአምባገነንነት መሰንቆ፣ የፈላጭ ቆራጭነት መዝሙር ነው፡፡ ለዚህ መሰንቆና መዝሙር መማረክ፣ የአገር ዕጣን ከብቸኛ ሐሳብና ገዥነት ጋር አጣብቆ ማየት ለፈላጭ ቆራጭነትና ለአድራጊ ፈጣሪነት እጅ መስጠት ነው፡፡ በአማራጭ የለሽ ሐሳብ ውስጥ መኖር ራሱ እስረኝነት ነው፡፡ ሌሎች ሐሳቦችን ብቻ ሳይሆን የሐሳብ ነፃነትን ራሱን ይነጥቃል፡፡ የአዕምሮ ጠያቂነትን ይሰልባል፡፡ በዝምታና በአጨብጫቢነት ሰብዕናን ያደቅቃል፣ ያስጨርሳል፡፡ ዝም ባይነትን፣ የሩቅ አደግዳጊ መሆን የሚመጣው ነፍስን በማስመሰል ሥለት እንድትገዘገዝና ሽባ እንድትሆን የሚያደርገው፣ ከሽባነትም አልፎ የመንግሥትና የአለቃ ንብረት እንድትሆን የሚያበቃት፣ ‹‹የመሰለውን አመለካከት›› የመያዝ መብትን፣ ያመኑበትን ፊት ለፊት ተናግሮ የመኖር ክብረን የሚገፈን፣ የዝምታ፣ የምንተዳዬና የማረጥረጥ ኑሮ መዋጣችንን በውጤትነት የሚያስከትለው ‹‹ያለ እኔ ሐሳብ›› ብሎ የሚጀምረው አኗኗራችን ነው፡፡ ዕጣን ከብቸኛ ሐሳብ ጋር አጣብቆ የሚያየው ኑሯችን ነው፡፡

ከዚህ የተለየ ኑሮ አለ፡፡ በሐሳብ ብዙነት ውስጥ የሚባል ሕይወት፣ ባህልና ኑሮ አለ፡፡ በሐሳብ ብዙነት ውስጥ መኖር በራሱ ወዲህና ወዲያ ያፈናፍናል፡፡ በሐሳብ ብዙነት ውስጥ መኖር ነፃነት ነው፡፡ የማንኛችንም ሐሳብ፣ ‹‹ያለ ምንም ጣልቃ ገብነት የመሰለውን አመለካከት የመያዝ›› የማንኛውንም ሰው መብትና ነፃነት ዕውን ያደርጋል፣ ያንንም የማንኛውንም ሰው ሐሳብ እንዲወጣና ከሌሎች ጋር እየተመዛዘነ እንዲኖር/እንዲያገለግል ይፈቅዳል፡፡ የተለያዩ ሐሳቦች መመዛዘንም አዕምሮን ያሠራል፣ ያበለፅጋል፡፡ ይህን የመሰለ አሠራርና አካሄድ ማለትም ለሐሳብ ብዙነት ደጋፊ ማብዛት በአጠባ፣ በፕሮፓጋንዳ፣ በጥርነፋ የተሠሩ አዕምሮዎችን ብዛት ይቀንሳል፣ ነፃነትን ያቀርባል፣ የአምባገነንነትን ዕድሜ ያሳጥራል፡፡

የማንንም ሰው የመሰለውን አመለካከት የመያዝ ሐሳቡን ያለ ፍርኃት የመግለጽ መብትና ነፃነት ሕይወት እንስጠው፣ መነጋገር እንጀምር፣ የመነጋገርን ጥበብና ሚስጥር እንወቅበት፣ በሐሳብ ብዙነት ውስጥ መኖር የሚባል የማናውቀው ዓለም አለ ማለት፣ ዝም ብሎ ብዙ ሐሳብ በሚንሸራሸርበት ሁኔታ ውስጥ መኖር ያዋጣል እያሉ መስበክ ሳይሆን፣ ፈላጭ ቆራጭነት፣ አድራጊ ፈጣሪነት ከሚወደው ፀበኝነት፣ ኩርፊያና መፈራራት ወጥተን መነጋገር እንጀምር፣ አንዳችን ሌላችንን ለማጥመቅ ሳንከጅል ከአቋማችን ውስጥ የሚያስማማንን እንፈልግ፣ የሚያስማማንን በማጥበቅና ልዩነታችንን በማክበር መቀራረባችንን እናበርክት፣ እናልማ ማለት ነው፡፡

ሐሳብን በነፃ የመያዝና የመግለጽ ሕገ መንግሥታዊ መብትና ነፃነት አለን ብለናል፡፡ የተለየ ሐሳብ መያዝ መብትና ነፃነት መሆኑን መቀበል አለመቻልና ከሚጣሉ አስተሳሰቦች ጋር ተቻችሎ የመኖር ባህል ከቤት፣ ከጓደኝነት ጀምሮ እንዲጎለብት ከማድረግ፣ ሐሳብን በሐሳብ ከመፎካከር ይልቅ ጠልቶ ማስጠላትን ‹‹ሙያ›› እና ‹‹ትዳር›› ማድረግ ከዴሞክራትነት ጋር አይገናኝም፡፡ ከዴሞክራሲ ጋር አያስተዋውቅም፡፡ የእኔ ሐሳብ ብቻ ይሰማ፣ ልክ ማለት ወደ ማኅበር፣ ዕድር፣ ዕቁብ፣ ፓርቲ፣ መንግሥት ከፍ ሲል የተለየ ‹ባላንጣ› ሐሳብን በሐሳብ አሸንፋለሁ ማለት አያውቅም፣ በሸር ወደ መገላገል ይሄዳል፡፡ ይህ ደግሞ ሁሉንም አስተሳሰብና የሥልጣን ፍላጎት ጭምር በውድድር ወደሚያስተናብረው ወደ ዴሞክራሲ የሚወስደውን መንገድ ይዘጋል፡፡ የአቋሞች ብዙነትና ፀብ/ጥል የለሽ ውድድር የሚባል ነገር ውሸት ይሆናል፡፡

አገራችን ውስጥ የጋራ መግባቢያ የቸገራቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ አንዳንዶችን በምሳሌነት ለመጥቀስ ያህል (ከዚያ በላይ አሟጦ መዘርዘር ራሱ የጋራ መግባቢያ የቸገረው ሌላው ጉዳይ ነው!)፣ የኢትዮጵያ ታሪክ ጉዳይ ብሎ መጀመር ይቻላል፡፡ የቡድንና የግለሰብ መብቶች ነገር ሌላውና ከታሪክም ጋር መያያዙ የማይቀር አገራዊ መግባባት የቸገረው ዋና ጉዳያችን ነው፡፡ እዚህ ጉዳይ ውስጥ የጋራ መግባባትን ቀርቶ መነጋገርን (እንደያዝኩት ያለ በጽሑፍ መናገርን ጭምር) የሚያስፈራራና የሚያስደነግጥ ገደል የሠራ ልዩነት አለ፡፡ የግለሰብ መብቶች የሁሉም ነገር መፍቻ ተደርጎ የሚወሰደውን ያህል፣ የብሔር/ብሔረሰብ ጥያቄ ዋናው የአገር ቅራኔ መፈታት የሁሉም የአገር ችግር መፈታት ነው ማለትም አለ፡፡ ኢትዮጵያ ባለብዙ ብሔረሰቦች መሆኗን ተቀብሎ ይህንን እውነት ከአገራዊ ትስስር ጋር የሚያግባባ፣ አብሮ መኖርን የመፈቃቀድ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ ከዚያም በላይ የህልውና ጥያቄ አድርጎ የሚያሠፍን ዴሞክራሲያዊ አመለካከት ይዞ ወደ ሕዝብ መቅረብ ለንግግርና ለምክክር ዝግጁ መሆን አሁንም ገና ከአደጋ የፀዳ፣ ከንግግር በላይ ያልሆነ አጀንዳ አልሆነም፡፡ እነዚህ ጉዳዮች ለምሳሌ፣ ከእነ ግትልትል ተከታይ ወይም ከእነሱ የሚፈልቁ ሌሎች ጥያቄዎች ጋር ደጋፊዎቻቸውንና ተቃዋሚዎቻቸውን በጥላቻ ስሜት እየመረዙ፣ አዕምሮና ማኅበራዊ ግንኙነቶችን እየከታተፉ፣ ጭፍን ጥቃትንና መበቃቀልን ያስከተሉ ከሩብ ምዕተ ዓመት በላይ ዕድሜ ያገኙ የአገር ሕመሞች ናቸው፡፡

የሰንደቅ ዓላማችንን ጉዳይ እዚህ ዝርዝር ውስጥ እንዲገባ ማድረግ አስቸጋሪ አይደለም ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ነገር ግን መነጋገሪያ መሆን ያለበት፣ እስካሁን ድረስ ግን ከሌሎች መካከል መነጋገርን አላውቅበትም ያለ፣ ከንግግር በላይ ነን ብሎ ያወጀ ጉዳይ ሆኖ ኖሯል፡፡

የ‹‹ማንነት›› ጉዳይም መግባባት የቸገረው የአገራችን ሕመም ነው፡፡ ይህን ጉዳይ እዚህ ያነሳሁት ከላይ ከተጠቀሰው የግለሰብ/ቡድን መብት ርዕሰ ጉዳይ ወጥቶ ራሱን የቻለ አጀንዳ ይሆናል/አይሆንም የሚል ብይን ውስጥ ልገባ ፈልጌ ሳይሆን፣ ለእሱም ቢሆን መፍትሔና መድኃኒት የምናገኝለት የንግግርን ጥበብ የሚያውቅ የመነጋገሪያ ጉዳይ ስናደርገው ነው ለማለት ነው፡፡

እና በሐሳቦች፣ በአመለካከቶች፣ በአቋሞ ብዙነትና ፀብ የለሽ ሰላማዊ ውድድር ያለበት ባህል ለመተዋወቅ መነጋገር እንጀምር፡፡ መነጋገር ማለት ተመሳሳይ ሐሳብና አመለካከት ውስጥ እናውራ፣ እንነጋገር ማለት አይደለም፡፡ የተቃረኑ ግንዛቤዎችንና ትርጓሜዎችን እየተደማመጥን ሐሳብ እንለዋወጥ፣ እንዲህ ያለ አዲስ ‹‹አገር›› ውስጥ እንግባ ነው፡፡ በውስጣችን በተለያየ መልክና ልክ ነትበው የሚንቀዋለሉ ሐሳቦች፣ የፓርቲ ቲፎዞነት፣ የሚተናነቁን የፍጥጫ አቋሞች፣ የሾኬ የውይይት ሥልቶች የመሳሰሉ በሽታዎች አሉብን፡፡ እነዚህን ወደ ጎን ብሎ በክፍት አዕምሮና በአዲስ ሙሽት የተለየ ሐሳብ መስማት፣ ነገሮችን በማስረጃ እየመዘኑ ለመቀበል እንዘጋጅ፡፡ እዚህ ውስጥ ያለፍንባቸውን ስህተቶችና ጥፋቶች በጥሞና ማስተዋል፣ ከእኔ ሐሳብ ውጪ ሌላ አማራጭ የለም ባይነቱን እርግፍ አድርጎ መተው፣ የተለየና የሚቃረን ሐሳብን የማቅረብ የሌላውን መብትና ነፃነት ማክበር ብቻ ሳይሆን ጥቅሜ ብሎ ማድመጥ፣ መከራከር፣ ሳይቀየሙ፣ ቂም ሳይዙ መለያየትን ወግ ማድረግ ማለት ነገር ሁሉ አለበት፡፡

መነጋገር ከቻልን፣ መነጋገርን ካወቅንበት ‹‹አንድ ነው ደማችን››ም፣ ‹‹ልዩነታችን ውበታችን ነው›› ከሚል የነተበ ነገር ወጥተን መፍትሔ መፈለግን፣ ከልዩነት ጋር መኖርን፣ የተለያየ ሐሳብ መያዝ በሐሳብ ‹‹መለያየት ሞት›› አለመሆኑን፣ እንዲያውም እንዲህ ዓይነት ሕይወት ውስጥ በልዩነት እየኖሩ ማሸነፍን እንማራለን፡፡   

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...