Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የቡና ሕገወጥ ንግድ እንዳይስፋፋ በምርት ገበያ ላይ የተፈጠረው ብዥታ ይጥራ!

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ከሰሞኑ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዙሪያ ተናገሩ የተባለው ነገር አስደማሚም፣ አስገራሚም ከሆነባቸው ሰዎች መካከል አንዱ ነኝ፡፡

ብዙዎቻችንን ያነጋገረው በተለይም በምርት ገበያ ውስጥ ያሉ ተዋንያኖችን ትኩረት የሳበውን ንግግር የከተከበሩ አቶ ሽመልስ የተናገሩት የአዳማ ኅብረት ሥራ ማኅበራትን በተመለለከተ በተዘጋጀ መድረክ ላይ ነው፡፡

ይህ ንግግራቸው በግርድፉ የክልሉ ገበሬዎችና አምራቾች በደንብ እንዲሠሩ በማድረግ ገበሬዎቹ እኩል ተጠቃሚ መሆን እንደሚገባቸው አመልክተው፣ ነገር ግን የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የሚባል ዘራፊ ድርጅት ተቋቁሞብን ተጠቃሚ መሆን ስላልተቻለ፣ ማኅበራትና ገበሬዎች ከዚህ በኋላ ለምርት ገበያው አትሽጡ የሚል አንደምታ ያለው ንግግር ማድረጋቸው ይበልጡኑ አርሶ አደሮችን ጥቅም ያሳጣ እንደሆን እንጂ አያከብርም፡፡

ይህ መልዕክት በተለይ ቡና አምራቾችንና ማኅበራትን የተመለከተ ቢሆንም፣ መልዕክቱ ከክልሉ ወደ ምርት ገበያው የሚገቡ ምርቶችንም የሚያጠቃልል እንደሆነ ይታመናል፡፡

ከዚህ ንግግራቸው በኋላ ደግሞ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ከክልሉ ቡና አምራች ማኅበራትና አቅራቢዎች ወደ ኢትዮጵያ ምርት ገበያ የሚገባው የቡና መጠን በእጅጉ ቀንሷል፡፡

ወትሮ ግብይታቸውን በምርት ገበያው ይፈጽሙ ከነበሩ አቅራቢዎች የአቶ ሽመልስን ቆንጠጥ ያለ ‹‹ቡናችሁን ለምርት ገበያ አታቅርቡ›› የሚለውን መልዕክት የተቀበሉ እጃቸውን ሰብስበዋል፡፡ በፈለጉት መንገድ ቡናቸውን እየሸጡ ነው፣ ወይም እየላኩ ነው፡፡

 ያልተጠበቀ ነው የተባለው ንግግርና ይህንኑ ተከትሎ ቡና አቅራቢዎች ቡናቸውን ወደ ምርት ገበያው ያለማስገባታቸው ደግሞ ድንጋጤ ፈጥሯል፡፡ ጉዳዩንም በጥብቅ ይዘው እስከ ላይ አቤት ያሉበት መሆኑ እየተሰማ ነው፡፡

ነገር ግን በዚህ ጉዳይ ምርት ገበያው ምንም ነገር ከመተንፈስ መቆጠቡን የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን መረጃ ለማግኘት ያደረጉት ሙከራ አለመሳካቱ ምስክር ነው፡፡ ንግግሩ ያስከተለው ተፅዕኖ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የብዙዎቻችንን አዕምሮ የያዘው ግን አንድን በአዋጅና በሕግ የተቋቋመ ተቋም እንዲህ ባለ በአደባባይ ንግግር መቀልበስ ይቻላል ወይ? የሚለው ነው፡፡

የአንድ ክልል ፕሬዚዳንት በፌዴራል ደረጃ የሚሠራበትን አሠራር ወደ ጎን ትተው ቡና አቅራቢዎች ‹‹ለዚህ ሽጡ››፣ ለዚያ አትሽጡ›› ማለትስ ይችላሉ ወይ? የሚለው ጥያቄ ምን ዓይነት መልስ እንደሚሰጠው ግራ ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዘራፊ ከሆነ፣ ይህንኑ በመረጃ በማቅረብ ከድርጊቱ እንዲታቀብ ወይም ዘራፊ ከሆነ በሕግ ሊዳኝ ይችላል፡፡

እንዲያውም ድርጊቱ ሕገወጥ ከሆነ ምርት ገበያውን መዝጋትና የተሻለ የሚባለውን አሠራር ማስፈን ይቻላል፡፡ በእርግጥ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ እጅግ የበዙ ችግሮች ያሉበት ስለመሆኑ ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ ምርት ገበያው ከተቋቋመ አሥር ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፣ በዚህ የአገልግሎት ዘመኑ ሕጋዊና ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት እንዲሰፍን አስችሏል የሚሉ ወገኖች እንዳሉ ሁሉ፣ ከዚህ ተቃራኒው የቆሙም አሉ፡፡

ምርት ገበያው የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ በአግባቡ እንዳይሳለጥ እንቅፋት መሆኑንም ይገልጻሉ፡፡ ተቋሙ ባይኖር ከዚህም በላይ ይሠራ ነበር የሚለው ይህ አመለካከት ዛሬ ብቻ ሳይሆን ምርት ገበያው ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በተደጋጋሚ የሚነገር ነው፡፡ የአቶ ሽመልስ ከንግግራቸውና ይህንን ሐሳብ ከልብ የሚቀበሉ ወገኖች ምርት ገበያው ዘራፊና አላስፈላጊ መሆኑን ያምናሉ፡፡

  ተቋሙ ፍፁም የጠራ ሥራ እየሠራ ነው ብሎ ለመናገር አይቻልም፡፡ የምርት ገበያው አሠራር ያልተመቻቸው ወገኖች በአደባባይ የቃል አዋጅ አውጀው ይህ የቃል አዋጅ ተቀባይነት ያገኘ ያስመሰለውም ወይም የሆነው ከዚህ ጋር ሊያያዝ ይችላል፡፡ ለዚህም ነው ብዙዎቹ ከሰሞኑ ለአሥር ዓመታት ሲገበያዩበት ከነበረው የምርት ገበያ እጃቸውን እንዲሰበስቡ የሆነው፡፡

ስለዚህ የምርት ገበያው አሠራርን የተመለከተ የተለያየ አመለካከት ቢኖርም፣ ችግሩን ፈትሾ በሕግ አግባብ መፍትሔ መፈለግ እየተቻለ በደፈናው ከምርት ገበያው ጋር አትሥሩ ማለት ትልቅ ስህተት ሊሆን ይችላል፡፡

ምርት ገበያው አላስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ በሕግ እንደተቋቋመ በሕግ ማፍረስ ወይም ደግሞ ቡናን ብቻ የሚያገበያይ ለብቻው ተነጥሎ የሚሠራ ሌላ ተቋም ማድረግ ይቻላል፡፡ ይህንን ለማድረግ ግን ሕጋዊ አሠራርን መከተል ያስፈልጋል፡፡

እንዲህ ዓይነት አመለካከት ሲንፀባረቅ ደግሞ ጎን ለጎን አማራጭም መቅረብ ይኖርበታል፡፡ በተለይ የንግድና የኢኮኖሚ ጉዳዮች እንደ ፖለቲካው ዝም ብሎ ስሜት የሚገለጽበት አይደለም፡፡ ሒሳብ አለው፡፡ በተለይም የቡና ገበያ በአገር ውስጥ በልዩ ሁኔታ ቁጥጥር እየተደረገበት የሚሠራና በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ዓለም አቀፋዊ ንግድ ጋር የተሳሰረ በመሆኑ ተወደደም ተጠላ ዓለም አቀፋዊ ስምምነቶች የሚገዙት ነው፡፡

ስለዚህ ዛሬ እንደ ዋዛ እንዲህ አታድርጉ በሚል የሚወሰድ ዕርምጃ በኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ገበያ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳድር ይችላል፡፡ አጠቃላይ የቡና ገበያው ወጥ የሆነ አሠራር እንዳይኖረው ሊያደርግና ችግር ሊፈጥር የሚችል መሆኑንም መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በተለይ ጥሮና ግሮ ቡና የሚያለማውን ገበሬ በእርግጥም ተጠቃሚ እንዳይሆን አድርጎ ከሆነ፣ ለወጪ ንግዱ እንቅፋት ከሆነና ምዝበራና ብልሹ አሠራር የሠፈነበት ሆኖ ከተገኘ ከአቶ ሽመልስ ጎን እቆማለሁ፡፡ ምክንያቱም ለፍቶ አዳሪውን የሚጎዳ አሠራር ካሰፈነ ማናችንም አንቀበለውም፡፡

ምርት ገበያው ሲቋቋም ዘመናዊ ግብይትን ከማስፈን ባሻገር፣ አምራቾችን ተጠቃሚ የማድረግ ዓላማ አለኝ የሚል ነውና ባለፉት አሥርና አሥራ አንድ ዓመታት እንደተባለው በዋናነት መጠቀም ያለበትን አምራች ካልጠቀመ አንዱን ዓላማውን ስቷል ማለት ነው፡፡

ለአገር ኢኮኖሚ እንቅፋት መሆኑ ከተረጋገጠም አያስፈልገንም፡፡ ምናልባትም አቶ ሽመልስ እንዲህ ምርር ብለው የተናገሩት በቂ መረጃ ይዘው ሊሆንም ይችላል፡፡ ነገር ግን ችግሩ ካለ፣ ችግሩ የሚፈታው በዚህ መንገድ ነው ወይ? የሚለው ጉዳይ በእጅጉ ያሳስባል፡፡

ምርት ገበያው አሉበት የተባሉት ችግሮች ብዙ ሊሆኑ ቢችሉም፣ አለበት ከተባሉ ችግሮቹ ባሻገር ለአገር ጠቃሚ የሆኑ አሠራሮች እንዳሉት መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ምርት በአግባቡ በማዕከል እንዲሸጥ፣ ሻጭና ገዥ በሕጋዊ መንገድ እንዲገበያዩ ማድረግ፣ በዚህም ሕጋዊ ግብይት የመንግሥት ታክስ በአግባቡ እንዲከፈል የሚያስችል አሠራር አለው፡፡

እንዲህ ያሉ አሠራሮች ከተፈተኑ ደግሞ ሕገወጥ አሠራር ሊሰፍን አይችልም ወይ? ኮንትሮባንድ እንዲስፋፋ አያደርግም ወይ? በመሆኑም ምርት ገበያው የግብይት ሥርዓቱ ፀር መሆኑ ከተረጋገጠ የተሻለ አሠራር መዘርጋቱ የግድ ይላል፡፡

ይህም በዘመቻ ሳይሆን በሕግ መሆን ይኖርበታልና አጠቃላይ የወጪ ንግድ ግብይትና አሠራሩን የሚያጠነክር የተሻለ አሠራር ሳይዘረጋ ችግርም ቢኖረው ነባሩን አሠራር የሚያፈርስ ነገር እንዲህ ባለ መንገድ መናገር ተገቢ ይሆናል ተብሎ አይታመንም፡፡

ስለዚህ የኦሮሚያ ክልል ቡና አምራቾችና አቅራቢዎች የአቶ ሽመልስን ንግግር ተቀብለው በምርት ገበያው መገበያየት ካልቻሉ ሌሎችስ ይህንን መንገድ ላለመከተላቸው ምን መተማመኛ ይኖራል፡፡ ስለዚህ ይህ ጉዳይ በደንብ ሊፈተሽ ይገባል፡፡ አጠቃላይ የግብይት ሥርዓት ውስጥ ችግር እንዳያስከትል በአግባቡ መታየትና የሚመለከተው አካል ሁሉ ተመልክቶ ተገቢውን ውሳኔ ማሳለፉና የተፈጠረውን ብዥታ ማጥራት ይኖርባቸዋል፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት