Friday, March 24, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አዋሽ ኢንሹራንስ በግማሽ በጀት ዓመት ከ857 ሚሊዮን ብር በላይ የዓረቦን ገቢ ማሰባሰቡን ገለጸ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

አዋሽ ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር በ2014 ግማሽ የበጀት ዓመት ከ857 ሚሊዮን ብር በላይ ዓረቦን ገቢ ማሰባሰብ መቻሉን ገለጸ፡፡

ኩባንያው በሒሳብ ዓመቱ ከግል የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከፍተኛ የሚባለውን ዓረቦን ገቢ ማግኘቱን፣ በግማሽ ሒሳብ ዓመት ውስጥ ካሰባሰበው ዓረቦን ገቢ ውስጥ 618 ሚሊዮን ብሩ ሕይወት ነክ ካልሆነ የመድን ሽፋን የተገኘና  ቀሪው 218 ሚሊዮን ብሩ ከሕይወት መድን ዘርፉ የተሰባሰበ ዓረቦን ገቢ መሆኑን አመልክቷል፡፡

በግማሽ ዓመቱ የኩባንያው የሥራ አፈጻጸም ዙሪያ ያነጋገርናቸው የአዋሽ ኢንሹራንስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጉዲሳ ለገሠ እንደገለጹት፣ ኩባንያቸው ከሁለቱም የኢንሹራንስ ዘርፎች ያገኘው ገቢ ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ብልጫ አለው፡፡

ኩባንያው ባለፈው ዓመት በሙሉ የበጀት ዓመቱ ከሁለቱም ዘርፎች ያገኘው የዓረቦን ገቢ 1.28 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ በ2014 በስድስት ወራት ያገኘው 857 ሚሊዮን ብር ከፍተኛ የሚባል የዓረቦን ብር ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚችልም ጠቁሟል፡፡ ሕይወት ነክ ካልሆነው የመድን ዘርፍ ያገኘው የዓረቦን ገቢ የ24 በመቶ ብልጫ ያለው መሆኑንም አቶ ጉዲሳ ገልጸዋል፡፡

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ በተለይ ዘንድሮ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የዓረቦን ገቢ ከፍ ያለ ነው፡፡ ለዚህም በዋናነት እየተጠቀሰ ያለው ከተሽከርካሪ የመድን ሽፋን የኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ ያገኙት ገቢ ከፍ ማለቱ ነው፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት የተሽከርካሪዎች ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመሩ ነው፡፡

አንድ ያነጋገርናቸው የኢንሹራንስ ባለሙያ እንደገለጹልንም፣ ሁሉም የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከጠቅላላ የዓረቦን ገበያቸው ውስጥ ከ60 በመቶ እስከ 70 በመቶ የሚሆነውን ከሞተር ኢንሹራንስ ዓረቦን ወይም ከተሽከርካሪዎች የመድን ሽፋን የሚሰበስቡ በመሆኑ የተሽከርካሪዎች ዋጋ መጨመር የዓረቦን ገቢያቸውን ማሳደጉ የማይቀር መሆኑን ነው፡፡

አሁንም የአብዛኛዎቹ ኩባንያዎች የዓረቦን ገቢ ዕድገት ከዚሁ የተሽከርካሪ ዋጋ ጭማሪ ጋር የተያዘ እንደሚሆንም ጠቁመዋል፡፡ ይሁን እንጂ የተሽከርካሪዎች ዋጋ ጭማሪ የዓረቦን ገቢያቸውን ከፍ ሊያደርግ ቢችልም፣ የኩባንያዎቹ ወጪ በዚያው ልክ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን ይጠቁማሉ፡፡

 የኩባንያዎቹ ወጪ ከፍ ማለቱንና ወደፊትም እንደሚጨምር የገለጹት ባለሙያው፣ ለዚህም በዋናነት የሚጠቅሱት የተሽከርካሪዎች የመለዋወጫ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ነው፡፡ የዋጋ ጭማሪው ደግሞ ከዚህ ቀደም እንደሚታወቀው በተወሰነ ደረጃ ሳይሆን ከእጥፍ በላይ አንዳንድ ዕቃዎችም ካለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ዋጋቸው አንፃር ሲታይ ሦስትና አራት እጅ የዋጋ ጭማሪ በማሳየታቸው ጉዳት በደረሰ ቁጥር ኩባንያዎቹ ለካሳ ክፍያ የሚያውሉትን ገንዘብ በእጅጉ እንዲጨምር እያደረገው ነውም ይላሉ፡፡

ስለዚህ የዓረቦን ዕድገቱ ቢኖርም የተሽከርካሪዎች መለዋወጫና ከዋጋ ንረት ጋር ተያይዞ የተደረጉ ጭማሪዎች ኩባንያዎቹ የመድን ሽፋን ለሰጡት ንብረት በተለይ ተሽከርካሪ የሚያወጡት ወጪ ከፍተኛ እንዲሆን እያደረገው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

አቶ ጉዲሳም በተለይ የተሽከርካሪ የመለዋወጫ ዕቃዎች ዋጋና አሁን እየታየ ያለው የዋጋ ንረት ለኢንሹራንስ ኩባንያዎች የጉዳት ካሳ ክፍያን በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር እያደረገ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም በተለይ ለተሽከርካሪዎች ጉዳት የሚከፈለውን የጉዳት ካሳ እንዲጨምር እያደረገ ያለው ይኸው የመለዋወጫ ዋጋ ጭማሪ እንደሆነም አቶ ጉዲሳ ገልጸዋል፡፡

አዋሽ ኢንሹራንስ በ2013 የበጀት ዓመት ከታክስ በፊት 290.3 ሚሊዮን ብር ያተረፈ ሲሆን፣ በዚሁ በጀት ዓመት ለመጀመርያ ጊዜ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ዓረቦን ያሰባሰበ የግል ኩባንያ ለመሆን ያስቻለውን የ1.28 ቢሊዮን ብር የዓረቦን ገቢ ማግኘቱንም መግለጹ ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች