Tuesday, March 5, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ባንኮች የደንበኞቻቸውን ዝርዝር መረጃ የመያዣ ጊዜና የታዩ ክፍተቶች

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ በሥራ ላይ ከሚገኙ 20 ባንኮች ውስጥ የቁጠባ ሒሳብ የከፈቱ ደንበኞች ቁጥር ከ66 ሚሊዮን በላይ ደርሷል፡፡ ይህ ቁጥር በአንድ ባንክ ሁለትም ሦስትም አካውንት ያላቸውንም የሚያጠቃልል ነው፡፡ ይህንን ያህል ቁጥር የደረሱ የባንክ ደንበኞችን የተሟላ መረጃ መያዝ አስፈላጊነት ታኖበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከስድስት ወራት በፊት አንድ መመርያ አውጥቷል፡፡

መመርያው ባንኮች የደንበኞቻቸውን ዝርዝር መረጃ በሚገባ በማጣራትና በማደራጀት በመረጃ ቋት ውስጥ መያዝ እንደሚገባቸው የሚያስገድድ ነው፡፡ ይህ ድንጋጌ መተግበር የሚገባው በስድስት ወራት ውስጥ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የባንክ ደንበኞች ሁሉ በመመርያው መሠረት የሚጠበቅባቸውን መረጃ ደንበኛ ለሆኑበት ባንክ በአካል ቀርበው መስጠትና የተዘጋጀውን ፎርም መሙላት ይኖርባቸዋል፡፡

በመመርያው ድንጋጌ መሠረት የደንበኞችን መረጃ የመቀበልና የማደራጀት ሥራ የተቀመጠለት የጊዜ ገደብ የሚጠናቀቀው የካቲት 20 ቀን 2014 ዓ.ም. ነው፡፡

ባንኮች በዚሁ መመርያ መሠረት ይህንን አገልግሎት የሚሰጥ ክፍል አደራጅተው የደንበኞቻቸውን መረጃዎች እያሰባሰቡ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያወጣውን ይህንን መመርያ ተከትለው ደንበኞቻቸው ወደ ባንክ ቀርበው የተጠየቀውን መረጃ እንዲሰጡም በተለያዩ መንገዶች መልዕክት እያስተላለፉ ይገኛሉ፡፡

የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ገነነ ሩጋ፣ ይህንን መመርያ ለመተግበር በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃንና በሌሎች የመረጃ መቀበያ ዘዴዎች ደንበኞቻቸው የባንክ ደብተር ወደ ከፈቱበት ቅርንጫፍ ቀርበው በመመርያው የተጠቀሰውን መረጃዎች እንዲሞሉ እየተደረገ ነው ይላሉ፡፡ እስካሁን ባለው ሒደት በብዛት የባንክ አገልግሎት ለማግኘት ሲመጡ ይህንኑ መረጃ እንዲሞሉ የሚደረግ መሆኑንም አክለዋል፡፡

የዘመን ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ደረጀ ዘበነም የአቶ ገነነን ሐሳብ ተጋርተው ደንበኞቻቸውን መመርያውን ተከትለው እያስተናገዱ ነው፡፡ እስካሁን የመረጃ አሰባሰቡ በጥሩ ሁኔታ እየሄደላቸው ስለመሆኑም ይገልጻሉ፡፡

እንደ አቶ ደረጀ ገለጻ፣ ደንበኞች በግንባር ቀርበው መረጃውን እንዲሰጡ በሚዲያ ከማስነገር ባለፈ በስልክ ጭምር እየነገሩ መሆኑ ነው፡፡ በዚህ ሒደት አንዳንዶች በተደወለላቸው ስልክ የማይገኙ መሆኑን መገንዘብ ስለመቻላቸው እኚሁ የሥራ ኃላፊዎች ይገልጻሉ፡፡ ሆኖም እስካሁን ባለው ሒደት አብዛኛውን ደንበኞቻቸውን እያደረሱ መሆኑን በመግለጽ እስከተቀመጠው የጊዜ ገደብ ደረስ ይህንኑ እየሠሩ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡  

የኦሮሚያ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ተፈሪ መኮንንና አቶ ገነነም ብዙ ደንበኞች በመስተናገዳቸው በቀረው ጊዜ ቀሪዎቹን ደንበኞቻቸውን ለመድረስ ይቻላል የሚለውን እምነታቸውን አንፀባርቀዋል፡፡

ይሁን እንጂ ብዙዎቹ ባንኮች በአዲሱ መመርያ መሠረት ደንበኞቻቸውን ተቀብለው እያስተናገዱ ቢሆንም፣ አንዳንድ ደንበኞች በተለይ ወርኃዊና ዓመታዊ ገቢውን ከማሳወቅ ጋር ተያይዞ ተደጋጋሚ ጥያቄዎች የሚቀርቡላቸው መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ዓመታዊ ገቢያቸውን ለመገመት ያልቻሉም ይህንን መመርያ ለመፈጸም ፈራ ተባ ማለታቸውን የሚገልጹም አሉ፡፡

ሌሎች የሚጠየቁ መረጃዎች በአግባቡ ተሞልተው ውርኃዊና ዓመታዊ ገቢ ምን ያህል እንደሆነ በሚያመለክተው የመረጃ ሥፍራ ብዙዎች የሚቸገሩ ስለመሆኑም ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ ሆኖም ባንኮች ዕገዛ በማድረግና ማብራሪያ በመስጠት የገቢያቸውን መጠን እንዲሞሉ እየተደረገ እንደሚገኝ ካነጋገርናቸው የባንክ ኃላፊዎች ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ይህንን መመርያ ያወጣው የፋይናንስ ተቋማት ደንበኞቻቸውን ስለሚያውቁበት ሁኔታ በአገራቸው ብሔራዊ መታወቂያ ባለመኖሩ ከባንክ ሒሳብ መክፈት፣ ከገንዘብ መክፈልና ማስቀመጥ ጋር የተያያዙ በርካታ ችግሮች የሚታዩ መሆኑን በመግለጽ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በጥቁር ገበያና በሌሎች ሕገወጥ ተግባራት የተሰማሩ አካላትም ይህንኑ ክፍተት ሲጠቀሙበት የቆዩ በመሆኑ እንዲህ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ታልሞ የወጣ ነው፡፡

ችግሮችን በዘላቂነት ለመከላከል አዲስ የተጀመረው ብሔራዊ መታወቂያ ለዜጎች የመስጠት ሒደቱ እስኪደርስ የፋይናንስ ተቋማት ለደንኞቻቸው የተለየ የደንበኛ መለያ ቁጥር እንዲሰጡ ባንኮችን የሚያስገድድ መሆኑንም መመርያው ያመለክታል፡፡ በዚህ መለያ ቁጥር አማካይነት የአንድ ባንክ ደንበኛ በባንኩ የተለያዩ ቅርንጫፎች ብዙ ሒሳብ ቢኖረውም፣ እንደ አንድ ደንበኛ እንዲታወቅ ለማድረግ እንዲቻል ታስቦም የወጣው ይህ መመርያ ተፈጻሚ እንዲሆን የተሰጠው የስድስት ወራት ጊዜ የቀረው ከአንድ ወር ያነሰ ጊዜ ነው፡፡ ቀነ ገደቡ  ወደ ማለቁ ቢሆንም፣ አሁንም ተገቢውን መረጃ ለባንክ ያልሰጡ ደንበኞች ቁጥራቸው ቀላል እንደማይሆን ስለሚታመን ባንኮች ተከታታይ ማስታወቂያዎችን እያወጡ ነው፡፡

 በመመርያው መሠረት ባንክ ቀርበው ተገቢውን መረጃ ያለማሟላታቸውንና በአራት ባንኮች የቁጠባ ሒሳብ እንዳላቸው የገለጹት ተገልጋይ እስካሁን መረጃን አሟልተው ያልሰጡት ፎርሙ ላይ ወርሃዊና ዓመታዊ ገቢን መግለጽ ግዴታ ሆኖ በመቀመጡ ነው ይላሉ፡፡

እንደ እሳቸው ገለጻ፣ ችግራቸው ገቢን ማሳወቁ እንደ ግዴታ የተቀመጠ መሆኑ ሳይሆን፣ ከደመወዜ ሌላ ዓመታዊ ገቢዬን ይህን ያህል ነው በሚል በትክክል ማስቀመጥ ባለመቻላቸው ነው፡፡  

‹‹በአራቱም ባንኮች ውስጥ ባለ አክሲዮን ነኝ፤›› ያሉት እኚህ የተለያዩ ባንኮች ደንበኛ ባለአክሲዮን፣ ከእነዚህ ባንኮች የሚያገኙት ዓመታዊ የትርፍ ድርሻ በአካውንታቸው ሲገባ የቆየ ሲሆን፣ ነገር ግን እነዚህ ባንኮች በየዓመቱ የሚከፍሉት የትርፍ ክፍፍል መጠን ምን ያህል እንደሆነ ባላወቁበት ሁኔታ ዓመታዊ ገቢያቸውን ይህንን ያህል ነው ብዬ ለመግለጽ ስለተቸገሩ ፎርሙን መሙላት እንዳልቻሉ ይገልጻሉ፡፡  

‹‹ባንኮች ዓመታዊ የትርፍ ድርሻቸው ስለሚለያይ የሚገኘውን ዓመታዊ ትርፍ መጠን ምን ያህል እንደሆነ ሳላውቅ ገቢዬ ይኼን ያህል ነው ብሎ ለመሙላት በመቸገሬ በአንድ ባንክ ከአካውንቴ ላይ ብቻ የደመወዝ መጠኔን ገልጫለሁ፡፡ የሌሎቹን እስካሁን አልሞላሁም፤›› ይላሉ፡፡

እንዳነጋገርናቸው የሥራ ኃላፊዎች ከሆነ፣ እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥም ደንበኛው አማካይ ገቢውን አስቀምጦ ትክክለኛ ገቢው ቢታወቅ ማስተካከል የሚቻልበት ዕድል አለ፡፡ ይህ ጉዳይ ችግር አለው ብለው እንደሚያምኑ የሚገልጹት አቶ ደረጀ ደግሞ፣ የተለያዩ የገቢ ምንጫቸውን በማሥላት ገቢያቸውን ማስመዝገብ ይኖርባቸዋል ይላሉ፡፡ ባንኩ ዓመታዊ ገቢያቸውን ሊያጣራ የሚችልበት ሁኔታ የተገደበ ቢሆንም፣ ደንበኞቻቸውን የሚያስተናግዱት በሰጡት መረጃ መሠረት እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

ገቢውን ማሳወቅ ያለበት ደንበኛው ነው፡፡ ለጊዜው የተለየ ሊመጣበት የሚችል ነገር የለም፡፡ አንድ ወቅት ላይ ግን ከገቢው በላይ የሆነ ገንዘብ ተንቀሳቅሷል ተብሎ ቼክ ሲደረግ፣ እሱ ከመደበኛ ገቢው በላይ ሌላ ተጨማሪ ገቢ እንዳለው ማሳያውን ማቅረብ አለበት እንጂ የሚከለክለው ነገር የለም፡፡

መመርያው የሒሳቡ ባለቤት የሚታወቅ ሰው ነው ወይ? የሚለውን የሚመልስ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ደረጄ፣ ለምሳሌ አንድ ሰው አካውንት ከፍቶ ሲፈልግ በፎርጅድ መታወቂያ ሌላ ሰው ሆኖ ይገኛል፣ ስለዚህ እንዲህ ያለውን ነገር ለማፅዳት ተብሎ የተዘጋጀ ነው ይላሉ፡፡

ለተሰጠው መረጃ ኃላፊነቱን የሚወስደውም ደንበኛው መሆኑን ያመለከቱት አቶ ደረጄ፣ ዓመታዊ ገቢን አሥልቶ መረጃ መስጠት ግን ምንም ችግር የሌለውና ለሁሉም የሚጠቅም መሆኑንም አክለዋል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አሠራር በሌላው አገርም የሚተገበርና እየተሠራበት ያለ በመሆኑ፣ ደንበኞች ምንም ሥጋት ሊገባቸው እንደማገባም አመልክተዋል፡፡ በተለያዩ ባንኮች አካውንት ያላቸው ደንበኞችም የሚሰጡት መረጃ ተመሳሳይ መሆን እንደሚገባው አስረድተው፣ ይህ መመርያ ምንም ችግር የሌለው በመሆኑ የጊዜ ገደቡ ከማለቁ በፊት መረጃ መስጠት ጠቃሚ ነው ይላሉ፡፡   

ከዚህ ውጪ አንዴ የተሞላ መረጃ ዘለዓለም በቋሚነት የሚቀመጥ ሲሆን፣ ዓመታዊ ገቢው ሲቀንስና ሲጨምር ይህንኑ በማስታወቅ መረጃውን በየጊዜው ማስተካከል የሚቻልበት ዕድል ስለመኖሩ ከባንኩ የሥራ ኃላፊዎች ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ሆኖም በዚሁ መመርያ ውስጥ እንደተቀመጠው የአጠራጣሪ ግለሰብ ወይም ድርጅት መረጃ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክና ለፋይናንስ መረጃ ደኅንነት ማዕከል መተላለፍ እንዳለበት በፋይናንስ ተቋማት ላይ ግዴታ የተጣለ በመሆኑ በዚሁ መሠረት እየተሠራ ነው ተብሏል፡፡ ይህ መመርያ ተፈጻሚ የሚሆንባቸው የፋይናንስ ተቋማት የደንበኞቻቸውን ሁኔታና ታሪክ የሚከታተል አዲስ አደረጃጀትና ዘመናዊ የቴክሎጂ አሠራር እንዲዘረጉ የሚያስገድድ በመሆኑም ባንኮቹ በዚሁ መሠረት አደራጅተው እየሠሩ መሆኑ ታውቋል፡፡

ከባንክ የሥራ ኃላፊዎች መረዳት እንደሚቻለው፣ የባንክ ደንበኞች እስከተሰጠው የጊዜ ገደብ ድረስ በመመርያው መሠረት ማንነታቸውንና አጠቃላይ ገቢያቸውን፣ እንዲሁም ሌሎች በመመርያ በግዴታ የተቀመጡ መረጃ ካልሰጡ ከየካቲት 20 በኋላ ሒሳባቸውን ማንቀሳቀስ ይችላሉ? ወይስ አይችሉም? የሚለው ጥያቄ ላይ የተለያየ አመለካከት ይንፀባረቃል፡፡

እንደ አቶ ደረጀ ገለጻ፣ ከቀነ ገደቡ በኋላ አካውንቱ መንቀሳቀስ አይችልም ይላሉ፡፡ ከዚያ በኋላ ደንበኛው ሄዶ ነው የሚያስተካክለው፡፡ በመመርያው መሠረት ደንበኛው መጥቶ ፎርሙን ካልሞላ አካውንቱን መጠቀም አይችልም፡፡ ሆኖም ከየካቲት 20 በኋላ በዚህ መመርያ ዙሪያ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚሰጠውም ተጨማሪ ነገር ካለ በዚያው የሚታይ እንደሚሆንም ጠቁመዋል፡፡  

በአንድ ግለሰብ ወይም በድርጅት ስም የባንክ ሒሳብ ሲከፍት፣ ገንዘብ ለማስቀመጥ ሲያስፈልግ፣ ከሒሳብ ወደ ሒሳብ ገንዘብ ማስተላለፍ ሲፈለግ፣ ገንዘብ ከባንክ ለማውጣትም ሆነ ለማስቀመጥ ለሚጠየቁ መረጃዎች ሁሉም የፋይናንስ ተቋማት ተመሳሳይ ቅፅ እንዲጠቀሙ ያስገድዳል፡፡ ይህም በፋይናንስ ተቋማቱ ያለውን ወጣ ገባ አሠራር ያስቀራል ተብሎ ታምኖ እየተሠራበት ነው፡፡

የኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ደርቤ አስፋው፣ ይህ መመርያ በትክክል መተግበሩ አገራዊ ጠቀሜታ ይኖረዋል ይላሉ፡፡ ባንካቸውም ባለው አቅም ይህንን የደንበኞቹን መረጃ በማጠናከር ሥራ ላይ መጠመዱንም ገልጸዋል፡፡ ሥራው ግን ቀላል ያለመሆኑን ያስረዱት አቶ ደርቤ፣ ገቢን ከማሳወቅ በላይ አንድን ደንበኛ ትክክለኛነት ለመለየት የሚሠራው ሥራ ከባድ ነው፡፡ ለምሳሌ ‹አበበ› የሚለውን ስም አንዳንዱ ፊደሎችን በመቀያየር ይጠቀማል፡፡ ይህንን የማጣራት ሥራ ቀላል አይደለም፣ ያደክማል፡፡ መጨረሻ ላይ ግን እንዲህ ያለው የጠራ አሠራር በንፅህና ለመሥራትና ደንበኞችን ለይቶ አስፈላጊውን አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል ይላሉ፡፡ 

የወጡ ሕጎችን ያላከበረ፣ የሚያጠራጥር መረጃ የሰጠ፣ አጠራጣሪ ክፍያ የፈጸመ ግለሰብ ወይም ድርጀት ከፋይናንስ ተቋማት ማንኛውንም አገልግሎት እንዲያገኝ ለፋይናንስ ተቋማት ሥልጣን የተሰጠ በመሆኑ ደንበኞች መረጃቸውን ካልሰጡ ባንኮች ዕርምጃ እንደሚወስዱም ኃላፊነት የተሰጣቸውን መሆኑ ይታወቃል፡፡

ይህ መመርያ በዚህ መልኩ እንዲተገበር ካስገደዱ ምክንያቶች መካከል አንዱ የብሔራዊ መታወቂያ አለመኖር ነው፡፡

ዓርብ ጥር 20 ቀን 2014 ዓ.ም. ይፋ የሆነው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ በሙከራ ደረጃ ሊተገበር ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተገኘው መረጃም፣ በተለይ ባንኮች ደንበኞቻቸውን ለማወቅ የሚያስችላቸውን ዲጂታል የብሔራዊ መታወቂያ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል በሙከራ ደረጃ የሚጀመር መሆኑን ገልጿል፡፡

በብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያ ፕሮግራም ጽሕፈት ቤትና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መካከል በተደረሰ ስምምነት መሠረት ባንኩ ካለው ከፍተኛ የደንበኞች ቁጥር አንፃር ለሙከራ ትግበራ ሊመረጥ መቻሉ ታውቋል፡፡ ይህ ስምምነት ባንኩን ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የባንክ ኢንዱስትሪውን የሚጠቅም በመሆኑ አሁን ባንኮች በአስገዳጅነት የደንበኞችን ማንነት ለማወቅ እያደረጉ ያሉትን የመረጃ አሰባሰብ በማስቀረት በቀላሉ የደንበኞችን መረጃ ለማግኘት ያስችላል ተብሎ ታምኖበታል፡፡

በዕለቱ በተደረገው ስምምነት ላይ አቶ አቤ ሳኖ ባንኮች የደንበኞችን መረጃ በአግባቡ ለማግኘት ባለባቸው ችግር ምክንያት ደፍረው አገልግሎት ባለመስጠታቸው ለኪሳራ የተዳረጉበት ሁኔታ እንዳለ ጠቁመው፣ የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ በአገሪቱ መጀመሩ አጠቃላይ የባንክ ኢንዱስትሪውን አሠራር በመሠረታዊ ደረጃ እንደሚቀይርም ተናግረዋል፡፡

ከአቶ አቤ ገለጻ መረዳት እንደሚቻለው፣ ደንበኞችን በተገቢው ሁኔታ ማወቅ ሕገወጥ ተግባራትን ከመከላከል ባሻገር፣ በተለይ ባንኮች ከብድር አሰጣጥ ጋር ችግር ውስጥ እንዲወድቁ ያደርግ ነበር፡፡ የደንበኞችን መረጃ በአግባቡ አለማወቅ አስቸጋሪ ከመሆኑ አንፃር፣ በተለያዩ አካባቢዎች የተለያየ ማንነት ይዘው በሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች ሳቢያ ባንኮች ለኪሳራ ሲዳረጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡

በተለይ የብድር አገልግሎት ለመስጠት የደንበኞችን የተሟላ መረጃ ማግኘት ግድ ስለሚል ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ መተግበሩ አገልግሎቱን ለብዙኃን ማድረስ ያስችላል፡፡

እንደ አቶ ደርቤ ገለጻ፣ አሁን ባንኮች እንዲሠሩ የተገደዱትን ሥራ ለማቃለል ብቸኛው አማራጭ ብሔራዊ መታወቂያ ነው፡፡ የአገሪቱ ብሔራዊ መታወቂያ ቢኖር በዚያ መታወቂያ ሁሉንም ሰው በመለየት መሥራት ይቻል ነበር ብለዋል፡፡ አሁንም የኢንዱስትሪውን አገልግሎት የበለጠ ለማስፋት ከተፈለገ ብሔራዊ መታወቂያን መተግበር የግድ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ለዘለቄታውም አስፈላጊ ነገር እርሱ ነው ብለዋል፡፡

አቶ ደረጄም በዚህ ይስማማሉ፡፡ ይህን ለመተግበር ግን ብዙ ወጪና ድካም እንዳለውም ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች