Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየመፍትሔ ያለህ የሚለው የኩላሊት ሕመምተኞች እጥበት አገልግሎት

የመፍትሔ ያለህ የሚለው የኩላሊት ሕመምተኞች እጥበት አገልግሎት

ቀን:

ዓለምን እያሳሰቧት ካሉ ጉዳዮች መካከል የኩላሊት ሕመም በዋነኛነት ይጠቀሳል፡፡ በኢትዮጵያ የብዙዎች ሥጋት ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ ‹‹በእንቅርት ላይ…›› እንዲሉ ካለው የኑሮ ሁኔታ አንፃር ሕክምናው በቀላሉ የሚደፈር አይደለም፡፡ ብዙዎች በአቅም ማጣት ምክንያት በራቸውን ዘግተው የተቀመጡት ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡

በዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚገኘው የኩላሊት ሕመምተኞች እጥበት በጎ አድራጎት ድርጅትም በሕመሙ የተጠቁትን በከፊል በገንዘብ በማገዝና ቅድመ መከላከል ሥራ ላይም ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ ቢገኝም፣ የኩላሊት ሕሙማን ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ፈታኝ ሆኗል፡፡ ድጋፉን አጠናክሮ በመሥራት ላይም መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን፣ የሲቪክ ማኅበራትን፣ የሃይማኖት ተቋማትንና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ትብብርና ዕገዛ ይጠይቃል፡፡

አቶ ሰሎሞን አሰፋ የኩላሊት ሕመምተኞች እጥበት በጎ አድራጎት ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ እንደ ሥራ አስኪያጁ አነጋገር፣ ለዕገዛና ለትብብሩ ስኬታማነት በግዮን ሆቴል ቅጥር ግቢ በሚገኘው ዩኒቲ ፓርክ ጥር 26 ቀን 2014 ዓ.ም. ከጠዋቱ 3፡00 እስከ ምሽቱ 12፡00 ሰዓት ድረስ የሚቆይ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ይካሄዳል፡፡

- Advertisement -

አጋር አካላትና በጎ ፈቃደኞች በተጠቀሰው ቦታና ፕሮግራም ላይ ተገኝተው ከሁለት ብር ጀምሮ አቅም እስከፈቀደ ድረስ ድጋፋቸውን በማድረግ ለኩላሊት ሕሙማን አለኝታነታቸውን በተግባር እንዲያሳዩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከዚህም ሌላ ወጣቶች በየሠፈሮቻቸውና፣ በየትምህርት ቤቶቻቸው እየተደራጁ በገንዘብ ማሰባሰቡ ሥራ ላይ እንዲሳተፉ አቶ ሰሎሞን አሳስበው፣ በዚህ ዓይነት እንቅስቃሴ የሰበሰቡትን ገንዘብ በተወካዮቻቸው አማካይነት ለድርጅቱ ገቢ እንዲያደርጉና እንቅስቃሴውም ዘላቂነት እንዲኖረው ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

‹‹የዳያስፖራው ማኅበረሰብም የዲያሊሲስ ሕክምና መስጫ ማሽን በማቅረብ እንዲሁም የወደፊት ዕቅዳችን ላይ ድጋፍ እንዲያደርግልን ጥሪ ለማቅረብ እንወዳለን፤›› ብለዋል፡፡  

በድርጅቱ በኩል የሚቀርቡትን የኩላሊት ሕሙማንን እየተቀበለ የኩላሊት ንቅለ ተከላ አገልግሎት በነፃ ሲሰጥ የቆየው የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሕክምና ኮሌጅ፣ ማዕከሉ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሳቢያ አገልግሎቱን እስከዛሬ ድረስ አቋርጦ መቆየቱን የገለጹት ሥራ አስኪያጁ፣ አሁን ግን አገልግሎቱን በአስቸኳይ እንዲጀመር፣ ይህ ዓይነቱም አገልግሎት ለሕሙማኑ ዕፎይታና ተስፋ እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡

‹‹የኩላሊት ባንክ›› ለማቋቋም የሚያስችል ሰነድ በሕክምና ባለሙያዎች ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ከቀረበ ውሎ ማደሩን ገልጸው፣ ይኼው ሰነድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተላልፎ የሕግ ማዕቀፍ ወጥቶለት ለአገልግሎት እንዲቀርብ በመግለጫቸው ላይ አበክረው ጠይቀዋል፡፡

‹‹በኢትዮጵያ ወደ 400 ሺሕ የሚጠጉ የኩላሊት ሕሙማን እንዳሉ፣ ከዓለም ጤና ድርጅት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፤›› ያሉት አቶ ሰሎሞን ከተጠቀሱት ሕሙማን መካከል ዳያሊሲስ የሚያገኙት ከ3,100 እንደማይበልጡ፣ የተቀሩት ግን ወደ ፀበል በመመላለስና በቤታቸው ሆነው ጊዜቸውን በስቃይ እንደሚያሳልፉ አስረድተዋል፡፡

የኩላሊት ሕሙማንን አስመልክቶ በየትምህርት ቤቶች እየተገናኛችሁ ለተማሪዎች ያደረጋችሁት ቅስቀሳና ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ አለ ወይ ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ሰሎሞን ሲመልሱ፣ ‹‹ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ በደብዳቤ አሳውቀናል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ድምፅ አልባው ገዳይ›› እየተባለ የሚጠራውን ይህንን በሽታ በመከላከል ረገድ እየተንቀሳቀሰ ያለውን የኩላሊት ሕመምተኞች እጥበት በጎ አድራጎት ድርጅት በቀዳሚነት ያቋቋሙ አርባ ሁለት የኩላሊት ሕሙማን ሲሆኑ፣ እነዚህም መሥራቾች ዛሬ በሕይወት እንደሌሉ ከአቶ ሰሎሞን ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...