የኢትዮጵያ የግብይት ሥርዓት በተለይም የከተሞች ከጊዜ ወደ ጊዜ ይዘቱን እየቀየረና ገዥና ሻጭ የሚገናኙበትም መንገድ እየሰፋ ከመጣ ሰነባብቷል። አርሶ አደሩ ምርት ሲደርስለት፣ የተወሰነውን ለቀለቡ አስቀርቶ የተቀረውን ወደ ገበያ በማውጣት፣ ተጨማሪ ለቤት ፍጆታ የሚሆነውን ሸማምቶ የመግባት ልምድ አለው። አንዳንዱ አርሶ አደር ደግሞ ምርቱን በሥፍር አቅርቦ፣ ለቤት ውስጥ በሚፈልገው ፍጆታ ቀይሮ የሚገባበት ሒደት አለ።
ኑሮውን በከተማ ያደረገው ነዋሪ ወደ ገበያ ወጥቶ ባለው የገንዘብ መጠን በአካባቢው ባለ የገበያ አማራጭ ይሸማምታል፡፡ ምንም እንኳን በአብዛኛው የሚጠቀመውን የምግብ ፍጆታ አገር በቀል ምርት ቢሆንም፣ አልባሳትን ጨምሮ በርካታ ጥቃቅን ቁሳቁሶችን ከውጭ አገር የሚገባን ምርት መሸመት ያዘወትራል።
በተለይ ከቻይናና ምዕራብ አገሮች ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ምግብ ነክ ያልሆኑ ምርቶች የኢትዮጵያን ገበያ ከተቆጣጠሩ ሰነባብተዋል። ሆኖም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአገር ውስጥ የሚመረቱ አገር በቀል ምርቶች ብቅ ብቅ እያሉ ነው፡፡ በቅርቡ የአገር ጥሪን ተቀብለው ወደ አገር ቤት የገቡ ዳያስፖራዎችን ታሳቢ አድርጎ የአገር ውስጥ ምርት ለሸማቾች በስፋት እየቀረበ ይገኛል።
የተለያዩ የአገር ውስጥ ምርቶች በተለይ በበዓላት ወቅት በባዛሮች፣ በኤግዚቢሽኖች፣ እንዲሁም በተለያዩ ሥነ ሥርዓቶች ላይ መቅረብ ከጀመሩ ሰንብተዋል።
በቅርቡ መንግሥት ያቀረበውን ጥሪ ተከትሎ ወደ አገር ቤት የመጡትን ዳያስፖራዎች ታሳቢ በማድረግ ‹‹እኛው በእኛው›› የተሰኘ ባዛር ጥር 7 እና 8 ቀን 2014 ዓ.ም. በልባዊ አካዴሚ ተሰናድቶ ነበር። የተለያዩ አምራቾች ኢትዮጵያ ውስጥ የተመረቱ ምርቶችን ለዳያስፖራው እንዲሁም በአገር ውስጥ ላለው ኅብረተሰብ ለማስተዋወቅ ግብ አድርጎ ባዛሩን ማሰናዳቱን የልባዊ አካዴሚ ዳይሬክተር ፓኖስ አዛንድሪያስ (ፕሮፌሰር) አስረድተዋል።
በባዛሩ ከ47 በላይ የአገር ውስጥ አምራቾች የተካፈሉ ሲሆን፣ አልባሳት የቆዳ ውጤቶች፣ የሸክላ ውጤቶችና ጌጣጌጦች፣ የጥበብ ውጤቶች የቅባት ውጤቶች፣ መዓዛማ ዘይቶች እንዲሁም የሥዕል ዓውደ ርዕይ ቀርበዋል።
በባዛሩ በአገር ውስጥ የተመረተ መዓዛማ ዘይቶች (Essential Oil) ያቀረበችው ወ/ሮ ቃል ኪዳን ኃይለ ማርያም፣ ምርቶቿ ለፊት፣ ለፀጉር እንዲሁም ለማሳጅ አገልግሎት እንደሚውሉ ትናገራለች፡፡ ምርቱን ከሁለት ዓመት በፊት ማምረት የጀመረች ሲሆን፣ ከአገር ውስጥ ደንበኞች ባሻገር በቻይና ገበያ ደንበኞች አፍርታለች።
ምርቱ የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ደረጃውን ያሟላ ሲሆን፣ በዋነኛነት ነጭ ዕጣንና ከርቤ እንዲሁም ዳማከሴን ለግብዓትነት እንደሚጠቀሙ ገልጻለች፡፡
ምንም ዓይነት ኬሚካልን እንደማይጠቀሙ የምታስረዳው ወ/ሮ ቃል ኪዳን፣ በተለይ ምርቱ በውጭ አገር ተፈላጊነቱ መጨመሩን፣ የአገር ውስጥ ደንበኛ የግንዛቤ ችግር ቢኖርም፣ በሒደት የአገር ውስጥ ደንበኛ ቁጥርም እየጨመረ መምጣቱንም ለሪፖርተር አብራርታለች።
እንደ ፕሮፈሰር ፓኖስ አስተያየት፣ ባዛሩ የአገር ውስጥ ምርትን ከኅብረተሰቡ ጋር ለማዛመድና የአገሩን ምርት የመጠቀም ልምድ ለማዳበር ያግዛል፡፡
ከዚህም ባሻገር በልባዊ አካዴሚ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ የሚገኙ ተማሪዎች አፍሪካዊ የሆኑ የአገር ውስጥ ምርቶችን በመመልከት ፓን አፍሪካኒዝምን እንዲረዱ ይረዳቸው ዘንድ በማሰብ እንደተሰናዳ ይናገራሉ።
በተለያዩ ባዛሮች ላይ የአገር ውስጥ ምርቶች ሲቀርቡ ስለምርቶቹ ግንዛቤ እንዲኖር የማስረዳት ሒደቱ አብዛኛውን ጊዜ እንደሚወስድ የሚገልጹት አምራቾቹ፣ ኅብረተሰቡ በሒደትም ቢሆን በተለያዩ መንገዶች ግንዛቤ እየወሰደ እንደሆነ ያስረዳሉ።
በተለይ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ከተከሰተ በኋላ አብዛኛው ኅብረተሰብ ቤቱ በተቀመጠበት ወቅት የማኅበራዊ ሚዲያ ትስስርን በመጠቀም ግንዛቤ ማሳደጉን ደግሞ ቃል ኪዳን ተናግራለች፡፡
የቆዳ ውጤቶች በማምረት የተሰማሩም በባዛሩ የታደሙበት ነበር፡፡ የአገር ቤት የጥበብ ውጤቶችን ከቆዳ ጋር በማዋሃድ፣ የላፕቶፕ ቦርሳ፣ የካርድ ዋሌት፣ ጫማንና አልባሳት በባዛሩ ከቀረቡት ይጠቀሳሉ፡፡ የቆዳ ምርቶችን በበይነ መረብ በመታገዝ ለአሜሪካና ለአውሮፓ የማቅረብ ዕድል ያገኙም አሉ፡፡
ምንም እንኳን ግንዛቤ መፍጠሩ ፈታኝ ቢሆንም፣ አሁን ላይ የውጭ አገር እንዲሁም የአገር ውስጥ ደንበኛው እኩል ምርቶችን እየተጠቀሙ እንደሆነ ተሳታፊዎች ነግረውናል፡፡
በአንፃሩ የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪዎች ማኅበር የአውታር መረብ በመዘርጋት በቆዳና ቆዳ ውጤት ሻጮችና ገዥዎችን በማገናኘት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ አምራቾች ይናገራሉ።
ከአገር ወስጥ ምርቶች ጋር በተያያዘ በሸማቾች ላይ የሚስተዋለው የግንዛቤ እጥረት በቀዳሚነት ቢጠቀስም፣ መንግሥት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት አናሳ መሆን፣ ሥራው በታክስ ሥርዓት ውስጥ እንዲካተት ሕጋዊ መንገድ አለመኖሩና ለምርቱ ግብዓት የሚሆኑ ጥቃቅን ቁሳቁሶች በገበያው አለመኖራቸውን እንደ ችግር አንስተዋል፡፡
በልባዊ አካዴሚ ከነበረው ባዛር ጎን ለጎን የጥበብ ሥራዎች፣ የገበያ መርሐ ግብር፣ የግዕዝና የፓን አፍሪካ ሥልጠና፣ የፊልም እንዲሁም የሙዚቃ ድግሶችን ለተማሪዎችና ተሳታፊዎች ቀርቧል፡፡