Wednesday, February 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትዮ ቴሌኮም በ100 ወረዳዎች አገልግሎት እየሰጠ አለመሆኑን አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ቀጥተኛ ተፅዕኖ እንዳሳደረበትና የአፋር፣ የአማራ፣ የኦሮሚያና ሌሎች ክልሎችንም ጨምሮ 100 ወረዳዎች ውስጥ አገልግሎት እየሰጠ አለመሆኑን ኢትዮ ቴሌኮም አስታወቀ፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም የግማሽ በጀት ዓመት አፈጻጸሙን ሰኞ ጥር 23 ቀን 2014 ዓ.ም. ይፋ ባደረገበት ጊዜ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች ለአንድ ወር ያህል ሙሉ ለሙሉ የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጦ እንደነበር አስታውቋል፡፡ በኦሮሚያ ክልልም በከፊል አገልግሎት ተቋርጦ እንደነበር የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ታምሩ ተናግረዋል፡፡

ወ/ሪት ፍሬሕይወት ኢትዮ ቴሌኮም ጦርነቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይፈታል የሚል ግምት እንደነበር ተናግረው፣ ጦርነቱ ግን ከትግራይ ክልል አልፎ ወደ ሌሎች ክልሎች መዛመቱን አስታውሰዋል፡፡ በዚህም የተነሳ በቴሌኮም ኢንዱስትሪው ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ ማድረሱን አክለው ገልጸዋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም በግማሽ በጀት ዓመቱ 28 ቢሊዮን ብር ገቢ በማግኘት የዕቅዱን 86.6 ማሳካቱን አስታውቋል፡፡ ኩባንያው በስድስት ወር አፈጻጸሙ ያገኘው ገቢ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነፃፀር የ6.7 በመቶ ጭማሪ ቢያሳይም፣ በበጀት ዓመቱ የመጀመርያ ስድስት ወራት ለማግኘት ካቀደው 35 ቢሊዮን ብር አኳያ ዕቅዱ ላይ የ13.6 በመቶ ጉድለት አለ፡፡

ከጦርነቱ ጋር የተያያዙ ክስተቶች ባይኖሩ ኩባንያው 97.7 በመቶ የሚሆነውን ዕቅዱን ማሳካት ይችል እንደነበር የተናገሩት ወ/ሪት ፍሬሕይወት፣ ‹‹ከገጠመን ችግር አንፃርና በሙሉ አቅማችን ሳንንቀሳቀስ ይህንን ያህል ገቢ ማስገኘታችን በጣም ጥሩ ነው ስንል ገምግመነዋል፤›› ብለዋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም ካሉት ስምንት ሺሕ የሚደርሱ የሞባይል ጣቢያዎቹ ውስጥ በጦርነቱ ሳቢያ 3‚473 ያህሉ አገልግሎት አቋርጠው እንደነበረ፣ በስድስት ወራት አፈጻጸም ሪፖርቱ ላይ አስታውቋል፡፡ እንደ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ገለጻ፣ በሞባይል ጣብያዎቹ ላይ የደረሰው ጉዳት በኢትዮ ቴሌኮም አደረጃጀት መሠረት ካሉት 17 ሪጅኖች ውስጥ አሥሩ ላይ በቀጥታና በተዘዋዋሪ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ በተጨማሪም 34 የሽያጭ ማዕከሎች ላይ ሙሉ ለሙሉና በከፊል ጉዳት መድረሱ የተገለጸ ሲሆን፣ በታወሮችና በፋይበሮች የጥገና ጣቢያዎችና ሌሎች ንብረቶች ላይ ስርቆትና ጉዳት መድረሱን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ አብራርተዋል፡፡

በአጠቃላይም በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ በ320 መሠረተ ልማቶቹ ላይ ጉዳት መድረሱን ያስታወቀው ኢትዮ ቴሌኮም፣ ከዚህ ውስጥ 62 በመቶው በክልሎች፣ 38 በመቶው ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የተከሰተ መሆኑን ገልጿል፡፡ በግማሽ በጀት ዓመቱ ከደረሰው 320 ጥቃት ውስጥም 45 በመቶ ወይም 145 ጥቃቶች “ሆን ተብሎ” የተደረጉ መሆናቸው የተነገረ ሲሆን፣ ይህም “ሆን ተብሎ” የሚፈጸሙ ጥቃቶች ላይ የ26 በመቶ ጭማሪ እንዳለ አሳይቷል፡፡

ወ/ሪት ፍሬሕይወት ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ጋር ተያይዞ በተፈጠረው የአገልግሎት መቋረጥ ኩባንያው ከ3.6 ቢሊዮን ብር በላይ ማጣቱን አስረድተው፣ ጉዳት የደረሰባቸው ንብረቶች ዋጋና መልሶ ግንባታ ለማከናወን የወጣው ወጪ ደግሞ ከ328 ሚሊዮን ብር እንደሚልቅ ተናግረዋል፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም በጦርነቱ ሳቢያ በአጠቃላይ አራት ቢሊዮን ብር ያጣ መሆኑን፣ አሁን መግባት ባልቻለባቸው አከባቢዎች ለጥገና የሚወጣው ወጪ ይህንን አኃዝ እንደሚጨምረው ሥራ አስፈጻሚዋ አክለዋል፡፡

ኢትዮ በቴሌኮም በስድስት ወራት አፈጻጸሙ ያገኘው ገቢ፣ ዕቅዱ እንዲሳካ ባደረገው የአገልግሎት ተጠቃሚዎች ቁጥርን በዕቅዱ መሠረት መቶ በመቶ አሳድጓል፡፡ ኩባንያው የአገልግሎቶቹ ተጠቃሚዎች ቁጥር 60.8 ሚሊዮን እንደደረሰ ያስታወቀ ሲሆን፣ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነፃፀር የ20 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ገልጿል፡፡ የሞባይል ድምፅ ተጠቃሚዎች ቁጥር 58.7 ሚሊዮን መድረሱን፣ ካለፈው ዓመት አንፃር የ43 በመቶ የተጠቃሚ ጭማሪ መታየቱን የተናገሩት ወ/ሪት ፍሬሕይወት፣ የፊክስድ ብሮድባንድ ተጠቃሚዎች ቁጥር 443 ሺሕ መድረሱን አስታውቀዋል፡፡

ኩባንያው ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ያስተዋወቀውና የኤሌክትሮኒክ ገንዘብ ዝውውር አገልግሎት መስጫ የሆነው ቴሌ ብር፣ ተጠቃሚዎቹ 13.1 ሚሊዮን መድረሳቸው ታውቋል፡፡ አገልግሎቱ ይፋ ከተደረገ አንስቶም የ5.1 ቢሊዮን ብር ዝውውር እንደተደረገበት ተነግሯል፡፡ ወ/ሪት ፍሬሕይወት በዚህ ጊዜ ውስጥ በቴሌ ብር የተደረገው የዝውውር መጠን፣ ከሌሎች አገሮች ተሞክሮ ጋር ሲነፃፀር የፈጠነ ነው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ባለፉት ስድስት ወራት በቴሌብር አማካይነት አንድ መቶ ሺሕ ዶላር መገኘቱን ያስረዱት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፣ በቴሌ ብር የሀዋላ አግልገሎት ከሚሰጡ ተቋማት ጋር ትስስር እየተፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም በ136 ከተሞች ውስጥ መስጠት የጀመረውን የ4ጂ አገልግሎትን ጨምሮ፣ ባለፉት ዓመታት እያከናወነ ያላቸውን ማስፋፊያዎች በራሱ አቅም እየሸፈነ መሆኑን ወ/ሪት ፍሬሕይወት አስረድተዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ለተከናወኑ ፕሮጀክቶች የተወሰደ ብድርን ለመመለስ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ 2.3 ቢሊዮን ብር ክፍያ መፈጸሙን ገልጸዋል፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥም አንድ ቢሊዮን ዶላር ብድር መከፈሉን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ አክለዋል፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ኩባንያው የትርፍ ህዳጉን ለማሳዳግ በትንሽ ወጪ ብዙ ሥራ የሚሠራበትን አሠራር (Do 2 Save) እየተገበረ መሆኑን ያስታወቁ ሲሆን፣ በዚህ አሠራር መሠረት ባለፉት ስድስት ወራት 1.2 ቢሊዮን ብር ወጪ መቆጠብ መቻሉን አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች