Sunday, June 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትዮጵያ ለዓለም ገበያ በሽያጭ ያቀረበችው ቦንድ የተሻለ የግዥ አፈጻጸም ማሳየቱ ተገለጸ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ በ2007 ዓ.ም. በሽያጭ ለዓለም ገበያ ያቀረበቸው የአንድ ቢሊዮን ዶላር የብድር ቦንድ ከሦስት ወራት በፊት ከፍተኛ ማሽቆልቆል ከታየበት በኋላ፣ ካለፈው ሳምንት አንስቶ የተሻለ አፈጻጸም እንደታየበት ተገለጸ፡፡

ስቶን ሃርቦር ኢንቨስትመንት ፓርትነርስ›› የተሰኘው የኢንቨስትመንት አስተዳዳሪ ኩባንያ ባወጣው የታዳጊ አገሮች የብድር ቦንድ ሽያጭ ሳምንታዊ ደረጃ፣ የኢትዮጵያ ቦንድ የ9.7 በመቶ ጭማሪ በማሳየት የቀዳሚነት ደረጃን መያዙን ገልጿል፡፡ ከኢትዮጵያ ባሻገር ኢኳዶርና ጋና ቦንዳቸው የተሻለ አፈጻጸም ያሳየ ታዳጊ አገሮች መሆናቸውን ደግሞ፣ ግራሜርሲ የተሰኘው የታዳጊ አገሮችን ቦንድ ኢንቨስትመንት አስተዳዳሪ በድረ ገጹ አሥፍሯል፡፡

ብሉምበርግ ሚዲያ ግሩፕ ግሩፕ አደረግኩት ባለው ዳሰሳ፣ የኢትዮጵያ የቦንድ ሽያጭ ከ80 ታዳጊ አገሮች መካካል ቀዳሚው የሆነ አፈጻጸም እንዳሳየና ቦንዱ እ.ኤ.አ. ከጥር 26 ቀን 2022 ጀምሮ በዶላር ስድስት ሳንቲም እንደጨመረ አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ቦንድ ባለፈው እ.ኤ.አ. በ2021 ዓመት 28 በመቶ ቅናሽ በማሳየት ከኤልሳቫዶር ቀጥሎ ዝቅተኛ የሆነውን አፈጻጸም እንዳሳየ ብሉምበርግ የዘገበ ሲሆን፣ አሁን የታየው የገበያ መሻሻል መንግሥት ከጥቅምት 2014 ዓ.ም. አንስቶ የጣለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የማንሳት አዝማሚያ በማሳየቱ የመጣ ነው ብሏል፡፡

እንደ ስቶን ሃርቦር የኢንቨስትመንት አማካሪ አስተያየት ደግሞ ይህ ዓይነቱ መሻሻል የታየው በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ጦርነት ሁኔታ የመቀዛቀዝ ሁኔታ በማሳየቱ፣ የፖለቲካ እስረኞች በመፈታታቸውና መንግሥት ብሔራዊ ምክክር ለማድረግ በዝግጅት ላይ በመሆኑ እንደሆነ አስታውቋል፡፡

ኢትዮጵያ ለአሥር ዓመት በሚቆይ የክፍያ ጊዜ በ2007 ዓ.ም. ለዓለም ገበያ ያቀረበችው ይህ የብድር ቦንድ የአንድ ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያለው ሲሆን፣ ቦንዱን የገዙ ዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮች በየዓመቱ የ6.6 በመቶ ወለድ ያገኛሉ፡፡ በዚህም መሠረት ኢትዮጵያ እስከ እ.ኤ.አ. ጥር 2024 በየዓመቱ 66.2 ሚሊዮን ዶላር ለቦንዱ ገዥዎች ወለድ ትከፍላለች፡፡ ይኼ ቦንድ ኢትዮጵያ ለዓለም ገበያ ያቀረበችው ብቸኛ ቦንድ ሲሆን፣ ቦንዱን ለዓለም ገበያ ያቀረበችውም ጄፒ ሞርጋን በተሰኘው ኩባንያና በደች ባንክ ዕገዛ ነው፡፡

የኢኮኖሚ ባለሙያዎች እንደሚያስረዱት፣ አገሮች ይኼንን ዓይነት ቦንድ ለዓለም ገበያ የሚያቀርቡት በተለያዩ ጊዜያት ለሚያስጀምሯቸው ፕሮግራሞች ወይም ላለባቸው ብድር መክፈያ ፋይናንስ ለማግኘት ሊሆን ይችላል፡፡ አገሮች ይኼ ዓይነቱን ቦንድ ለዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮች ካቀረቡ በኋላ ቃል የገቡትን የወለድ መጠን ሲከፍሉ ይቆዩና የቦንዱ መክፈያ ጊዜ ሲጠናቀቅ ለቦንድ ገዥዎቹ ሙሉ ገንዘቡን ይመልሳሉ፡፡

የእንዲህ ዓይነቱ የቦንድ ሽያጭ መሻሻል ቦንድ አቅራቢ አገሮች ካላቸው የውስጥ ሰላምና ወቅታዊ ሁኔታ ጋር የሚያያዝ ሲሆን፣ አገሮች አለመረጋጋት ወይም የኢኮኖሚ መውደቅ ካጋጠማቸው፣ ‹‹የቦንዱ መክፈያ ጊዜ ሲደርስ ብድሩን አይከፍሉም›› የሚል ሥጋት ስለሚፈጠር የቦንዱ ሽያጭ ይቀንሳል፡፡

ሪፖርተር ያናገራቸው የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ አብዱልመናን መሐመድ፣ ‹‹የኢትዮጵያ የውስጥ ሁኔታ በቦንዱ ዋጋ ላይ በጣም ተፅዕኖ አለው፤› ብለው፣ የኢትዮጵያ የውስጥ ሁኔታ መሻሻል መንግሥት የቦንዱ መክፈያ ጊዜ ሲደርስ ዕዳውን ለመክፈል መተማመን እንደሚፈጥር አስረድተዋል፡፡

የኢኮኖሚ ባለሙያው፣ ‹‹የቅርቡ  የቦንዱ ዋጋ መጨመር የሚነግረን ነገር ቢኖር፣ የኢትዮጵያ የውስጥ ሁኔታ እየተሻሻለ መምጣቱን ነው። ለዚያም ኢንቨስተሮች ቦንዱን የመግዛት  ፍላጎታቸው ስለጨመረ ነው  የቦንዱ ዋጋ የጨመረው፤›› ብለዋል፡፡

ባለሙያው ከጥቂት ወራት በፊት ሕወሓት ወደ መሃል አገር እየገፋ በመምጣቱ የአገሪቱ ሁኔታ አሳሳቢ እንደነበረ አስታውሰው፣ በዚህም የኢትዮጵያ መንግሥት ቦንድ በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ገበያ ላይ ዋጋው በጣም ወርዶ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ በቅርብ ጊዜያት ውስጥም መንግሥት ሕወሓትን ገፍቶ ወደ ትግራይ ክልል በመመለሱና የአገሪቱ ሁኔታ በጣም መሻሻል በማሳየቱ፣ የቦንዱ ዋጋ ሊጨምር እንደቻለ ምልከታቸውን አጋርተዋል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው ሌላው የኢኮኖሚ ባለሙያ አቶ ዋሲሁን በላይ በበኩላቸው፣ የዓለም የገንዘብ ድርጅት (IMF) ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው የፀጥታ ሥጋት የተነሳ የ2022 ዓመታዊ የዕድገት ትንበያ ሪፖርቱ ውስጥ እንዳላካተተ አስታውሰው፣ የዓለም ባንክ በአንፃሩ ከቀናት በፊት ባወጣው ሪፖርት አገሪቱ ኢኮኖሚ አራት በመቶ ያድጋል የሚል ግምት ማስቀመጡን ተናግረዋል፡፡ ‹‹15 ወራት ጦርነት ውስጥ ላሳለፈና ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ኢኮኖሚያዊ ጫና ላላገገመ ኢኮኖሚ የአራት በመቶ ዕድገት ትንበያ ትልቅ ነው፤›› ብለው፣ ይኼ ትንበያ ለኢትዮጵያ መንግሥት የቦንድ ሽያጭ መጨመር አስተዋፅኦ ሊኖረው እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

ይኼንንና ሌሎች አገራዊ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ የሚያስገቡ ዓለም አቀፍ አሻሻጮችም፣ የኢትዮጵያ ሁኔታ ላይ ያለውን መሻሻል በመጥቀስ ኢንቨስተሮች ቦንዱን እንዲገዙ እንደሚወተውቱ አስረድተዋል፡፡

አቶ አብዱልመናን የቦንዱ ዋጋ መጨመር ኢንቨስተሮች የኢትዮጵያ መንግሥትን ቦንድ የመግዛት ፍላጎታቸው መጨመሩን እንደሚያመላክት ገልጸው፣ ስለአገሪቱ የመረጋጋት ሁኔታ በጎ ምሥል እንደሚሰጥ አስረድተዋል፡፡ ይኼም በአንፃሩ መንግሥት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እንዲስብ ወይም ከውጭ የግል አበዳሪዎች ለመበደር ቢፈልግ ጥሩ ሁኔታን እንደሚፈጥር አብራርተዋል፡፡

አቶ ዋሲሁንም በዚህ ሐሳብ የሚስማሙ ሲሆን፣ አበዳሪዎች ከማበደራቸው በፊት እንዲህ ዓይነት የኢኮኖሚ ጠቋሚዎችን ከግምት ውስጥ እንደሚያስገቡ አስረድተዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ቦንዱ ላይ የሚታየው የመግዛት ፍላጎት ከፍተኛ የሚሆን ከሆነ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ያቀረበው የብድር ወለድ መጠን ላይ ማሻሻያ ለማድረግ ዕድል እንደሚሰጠው ገልጸዋል፡፡

ይሁንና እንደ ኢኮኖሚ ባለሙያው ገለጻ፣ ይኼ የኢትዮጵያ መንግሥት ቦንድ ሽያጭ ጭማሪ ማሳየት የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ገጽታ ላይ ጥሩ ምሥል እንዲኖር ከማድረጉ በዘለለ በራሱ እንደ ስኬት መታየት የሚችል አይደለም፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች