ከተመሠረተ አንድ ክፍለ ዘመን ያስቆጠረው አንጋፋው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት፣ ለሦስት ዓመታት የኅትመት ቴክኖሎጂ ትምህርት ሲከታተሉ የነበሩና በዘርፉ በኢትዮጵያ ቀዳሚ ናቸው የተባሉትን ተማሪዎችን አስመረቀ፡፡
ድርጅቱ ከመስከረም 2014 ዓ.ም. ጀምሮ እያከበረ ባለው የ100ኛ ዓመት በዓሉ ማጠናቀቂያ ላይ ያስመረቃቸው እነዚህ 31 ተማሪዎች፣ ድርጅቱ ባቋቋመው የኅትመት ቴክኖሎጂ ኮሌጅ በደረጃ ሦስት ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ነበር፡፡ ተመራቂዎቹ ከወጣት እስከ ጎልማሳ ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፣ በዘርፉ የሚሰጥ ትምህርት ባለመኖሩ፣ የተፈጠረውን የሠለጠነ የሰው ኃይል እጥረት በመጠኑም ቢሆን ይቀርፋሉ ተብሎላቸዋል፡፡
የብርሃንና ሰላም የኅትመት ቴክኖሎጂ ኮሌጅ በ2007 ዓ.ም. የተቋቋመው በድርጅቱ ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞችን በማሠልጠን ብቃታቸውን ከፍ ለማድረግ እንደነበር የተናገሩት የኮሌጁ ዳይሬክተር አቶ መስፍን ካሳ፣ በ2008 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኤጀንሲ ፈቃድ በማግኘቱ ከድርጅቱ ውጪ ለሚመጡ ሥልጠና ፈላጊዎች አጫጫር ሥልጠናዎችን ሲሰጥ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡
ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮም በኅትመት ግራፊክስ አርት ከደረጃ አንድ እስከ ደረጃ ሦስት እንዲሁም በኅትመት፣ በግራፊክስ ዲዛይን አርትና በኅትመት ዋጋ ግመታ አጫጫር ሥልጠናዎች እየሰጠ መሆኑን፣ ኮሌጁ ከሚሰጠው ሥልጠና ባሻገር ለኅትመት ድርጅቶችና ዩኒቨርሲቲዎች የማማከርና የኅትመት መሣሪያ ጥገና ሥራ እንደሚሠራ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
በአገሪቱ ብቸኛው የህትመት ሞያ ብቃት ምዘና ማዕከል የሆነው ኮሌጁ አገልግሎት መስጠት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከ1,400 በላይ ሰዎችን ያሠለጠነ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ 530 ሠልጣኞች አሉት፡፡ ጥር 21 ቀን 2014 ዓ.ም. ባካሄደው ሥነ ሥርዓት ደግሞ ለአገሪቱና ለኮሌጁ የመጀመሪያ ናቸው የተባሉትን 31 የደረጃ ሦስት የኅትመት ቴክኖሎጂ ተማሪዎችን አስመርቋል፡፡
የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሽታሁን ዋለ በበኩላቸው፣ ዘርፉ ላይ ባለው የሰው እጥረት ምክንያት በደንበኞች ፍላጎት ልክ ጥራት ያለው የኅትመት አገልግሎት መስጠት ላይ ክፍተት እንደሚታይ ተናግረዋል፡፡ በአገር ደረጃም ለኅትመት ቴክኖሎጂ ትምህርት የተሰጠው ትኩረት ዝቅተኛ ለመሆኑ አንዱ ማሳያ፣ በአንዳቸውም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የኅትመት ቴክኖሎጂ ትምህርት አለመሰጠቱ ነው ብለዋል፡፡
ብርሃንና ሰላም ላለፉት 100 ዓመታት የአገሪቱን መደበኛና ሚስጥራዊ ኅትመት አገልግሎት ሲሸፍን መቆየቱን የተናገሩት አቶ ሽታሁን፣ ድርጅቱ ካስቆጠረው ዕድሜ አንፃር በቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ በአደረጃጀትና አሠራር በሚጠበቅበት ደረጃ ራሱን ባለማሳደጉ፣ የደንበኞቹን ፍላጎት ማሳካት ላይ ውስንነቶች እንዳሉበት አስታውቀዋል፡፡ በዚህም የተነሳ በአገር ውስጥና በድርጀቱ ሊታተሙ የሚችሉ በርካታ ኅትመቶች በውጭ አገር እንደሚታተሙ ጠቁመው፣ ይህም አገሪቱ ካላት ውስን የውጭ ምንዛሪ ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው ምንዛሪ በክፍያ እንዲወጣ ማድረጉን አስረድተዋል፡፡
እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ፣ ይኼንን ችግር ለመቅረፍ ድርጅቱ ጥናት በማስጠናትና አስፈላጊ ቴክኖሎጂዎችን በመለየት ዘመናዊ የማተሚያ ማሽን እንዲገዛና ረዥም ጊዜ አገልግሎት የሰጡ ማሽኖች እንዲተኩ፣ ዕቅድና በጀት ቀርቦ በመንግሥት መፅደቁን ተናግረዋል፡፡ ይሁንና ለግዥው የሚሆን የውጭ ምንዛሪ ባለመፈቀዱ ምክንያት የድርጅቱ ችግር ሊቀረፍ አለመቻሉን አክለዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር በአሁኑ ጊዜ ድርጅቱ የቀለም ኅትመት ለማተም ከፍተኛ ችግር ላይ እንደሚገኝ አቶ ሽታሁን ተናግረዋል፡፡
ዋና ሥራ አስፈጻሚው ድርጅቱ 100ኛ ዓመቱን ባከበረባቸው መርሐ ግብሮች ላይ ለተገኙ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጉዳዩ እንደተነሳ አስታውቀው፣ ችግሩ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ይፈታል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡
ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ከ1914 ዓ.ም. ጀምሮ ላለፉት አንድ መቶ ዓመታት ያለፈባቸውን ሒደቶች በሚመለከት የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይቶች ተካሂደዋል፡፡ የተገኙትን ግብዓቶችን በማካተትና የተሻሉ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በተለይ ወደ ውጭ ተልከው የሚታተሙ መጻሕፍትንና ሌሎች የኅትመት ውጤቶች በአገር ውስጥ ለመሥራት ጥረት እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡