Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ኅብረተሰቡ የሥጋ ደዌ ተጠቂነት ከሥራ እንደማያግድ እያየና እየተረዳ መጥቷል››

አቶ ከፍያለው በቀለ፣ የሥጋ ደዌ ተጠቂዎች ብሔራዊ ማኅበር ሊቀመንበር

የሥጋ ደዌ ተጠቂዎች ችግር ከጤና ባሻገር ዘርፈ ብዙ የሆነ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ሥነ ልቦናዊ ገጽታ አለው፡፡ ይህም ችግር በአንድ ምዕራፍ የሚወሰን ሳይሆን የመላው ኅብረተሰብ ብሎም የአገር ጉዳይ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ የችግሩን ምንጭ ከሥር መሠረቱ ለማድረቅና ተጠቂዎቹን በግንባር ቀደምትነት ለማሰለፍ ስለሥጋ ደዌና ስለተጠቂዎች ያለውን የተሳሳተ ግንዛቤ ለማሻሻልና ለመፍታታ የሥጋ ደዌ ተጠቂዎች ብሔራዊ ማኅበር ተቋቁሞ ወደ ሥራ ከገባ ከሁለት አሠርታት በላይ ሆኖታል፡፡ የማኅበሩም ሊቀመንበርም አቶ ከፍያለው በቀለ ሲሆኑ በማኅበሩ እንቅስቃሴና ተያያዥ በሆነ ሌሎች ጉዳዮች ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ በትኞቹ ክልሎች እንደሚንቀሳቀስና በዚህም እያበረከተ ያለውን አገልግሎት ቢያብራሩልን?

አቶ ከፍያለው፡- እያደገ በመጣው ፍላጎት የኢትዮጵያ ሥጋ ደዌ ተጠቂዎች ብሔራዊ ማኅበር በበርካታ አካባቢዎች፣ ማለትም በአማራ፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች፣ በሐረሪ፣ በሲዳማ ክልሎችና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 68 የአካባቢ ማኅበራትን በማደራጀት የሥጋ ደዌ ተጠቂዎችና ቤተሰቦቻቸው ላይ ሥር ሰዶ የሚገኘውን የተሳሳተ ግንዛቤ በማስተካከልና እንዲሁም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ እየሠራ ይገኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ግንዛቤን የማስተካከሉ እንቅስቃሴ በምን ላይ ያተኮረ ነው?

አቶ ከፍያለው፡- ግንዛቤን የማስተካከሉ እንቅስቃሴ ሥጋ ደዌ በእርግማን የሚመጣና በዘር የሚተላለፍ በሽታ ሳይሆን፣ ‹‹ማይኮሮ ባክትሬየም›› በሚባል በሽታ አምጪ ህዋስ የሚመጣ መሆኑን የሚያስረዳ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ ሥጋ ደዌ እንደማንኛውም በሽታ በሕክምና እንደሚድን፣ በተለይም በ1975 ዓ.ም. በተገኘው የጣምራ መድኃኒት (መልቲ ድራግ ቴራፒ) ሕክምና ከስድስት ወር እስከ አንድ ዓመት በሆነ ጊዜ ውስጥ የሥጋ ደዌን ማዳን እንደሚቻል በሚገልጽ መልኩ ለኅብረተሰቡ በተለያዩ ጊዜያት የተላለፈው መልዕክት የግንዛቤ ማስተካከሉ ሥራ አንዱ ክፍል መሆኑን መታወቅ ይኖርበታል፡፡

ሪፖርተር፡- የማኅበሩ ዓላማዎች ምንድናቸው?

አቶ ከፍያለው፡- ማኅበሩ አምስት ዓላማዎች አሉት፡፡ ከእነዚህም መካከል አንደኛው የሥጋ ደዌ ተጠቂዎችን መልስ ማቋቋምና የማኅበረሰብ ተሃድሶ መሥራት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ሥጋ ደዌ ስለሚከሰትበት ሁኔታ፣ ስለሚያደርሰው ጉዳትና ስለመከላከያው ትምህርታዊና የጤና ግንዛቤ ሥራዎችን መሥራት ናቸው፡፡ የሥጋ ደዌ ተጠቂዎችና ቤተሰቦቻቸው የሙያ ባለቤቶች እንዲሆኑና በገቢ ማስገኛ ሥራዎች እንዲሰማሩ ትምህርትና ሥልጠና መስጠት፣ በሥጋ ደዌ ዙሪያ ከሚሠሩ አካላት ጋር በመተባበር መሥራት፣ የአገሪቱን የረዥም ጊዜ የልማት አቅጣጫ መሠረት በማድረግ የሥጋ ደዌ ተጠቂዎች ራሳቸውን ለማቋቋም የሚያደርጉትን ጥረት ለማጠናከር የሚያስችሉ የአቅም ግንባታ ሥራዎችን ማከናወን በዓላማዎቹ ውስጥ የተካተቱ ነጥቦች ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ለገቢ ማስገኛ ተብሎ የተጀመረ የሕንፃ ግንባታ አለ፡፡ አሁን ምን ደረጃ ላይ ደርሷል?

አቶ ከፍያለው፡- ሕንፃው እየተገነባ ያለው በአዲስ አበባ ከተማ ጀሞ አካባቢ ሲሆን ባለ አምስት ወለል ነው፡፡ የሕንፃው ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ ሲሆን እስካሁንም የፈጀው እስከ 30 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ነው፡፡ ብዙ ክፍሎች ያሉት ሲሆን በማከራየት ገቢ ለማስገኘት ታስቦ የተጀመረ ነው፡፡ በዚህም ገቢ ማኅበሩ ራሱን ችሎና ከተረጂነት ተላቅቆ አባላቱንም ተጠቃሚ ያደርጋል በሚል ተስፋና እምነት ላይ ተመሥርቶ የተገነባ መሆኑንና ይህም ዕውን እንደሚሆን ከወዲሁ ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡ ማኅበሩ እስካሁን እየተንቀሳቀሰ ያለው በዋነኛነት ከተለያዩ የዓለም አቀፍና አጋር ድርጅቶች በሚያገኘው የገንዘብ ድጋፍ ነው፡፡ ድጋፉንም የሚያደርጉት በሥጋ ደዌ ላይ የሚሠሩ ‹‹ሳሳካዋ›› እና ‹‹ቲኤልኤምአይ›› የተባሉ የውጭ ድርጅቶች ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- በመላ ኢትዮጵያ ምን ያህል የሥጋ ደዌ ተጠቂዎች አሉ? ብሔራዊ ማኅበሩስ ለስንቱ ተደራሽ ሆኗል?

አቶ ከፍያለው፡- በአሁኑ ጊዜ በመላ ኢትዮጵያ ውስጥ ከ20 እስከ 30,000 የሚደርሱ የሥጋ ደዌ ተጠቂዎች እንዳሉ ይገመታል፡፡ ከእነዚህም መካከል ብሔራዊ ማኅበሩ ተደራሽ አድርጎ ያደራጃቸውና የልማት ተጠቂዎች ያደረጋቸው 15,000 የሥጋ ደዌ ተጠቂዎችን ብቻ ነው፡፡ ብሔራዊ ማኅበሩ በአፋር፣ በሶማሌ፣ በጋምቤላና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ተደራሽ አልሆነም፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት በአቅም ማነስ የተነሳ ነው፡፡ ወደፊት ግን በእነዚህ በተጠቀሱት ክልሎች ተደራሽ ለመሆን የሚያስችሉትን ዝግጅት አከናውኗል፡፡

ሪፖርተር፡- በማኅበሩ የታቀፉት የሥጋ ደዌ ተጠቂዎች በገቢ ማስገኛም ሆነ በሌላ ሥራ ራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ ማኅበሩ ያበረከተውን እንቅስቃሴ ቢያብራሩልን?

አቶ ከፍያለው፡- በዚህ በኩል ብሔራዊ ማኅበሩ በርካታ ሥራዎችን ሠርቷል፡፡ ካከናወናቸው ሥራዎች መካከልም የብድርና ቁጠባ አገግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ በከብት ዕርባታ፣ በማደለብና በወተትና በወተት ተዋጽኦ ላይ እንዲሠማሩ በማድረግ ራሳቸውን አስችሏቸዋል፡፡ የእህል ወፍጮ ቤትና የብሎኬት ማምረቻ እንዲያቋቁሙ የበኩሉን አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ ከዚህም ሌላ ቡና ቆልተውና ፈጭተው ለገበያ እንዲያቀርቡ ሁኔታዎችን አመቻችቶላቸዋል፡፡ ኅብረተሰቡ የሚመለከተው ሥጋ ደዌ ተጠቂ ሲባል ጎዳና ላይ ቁጭ ብሎ የሚለምን ብቻ ነው የሚመስለው፡፡ ነገር ግን ከላይ በዝርዝር የተጠቀሱ ተግባራትን ማከናወናቸውን ሲመለከት የሥጋ ደዌ ተጠቂነት ከሥራ እንደማያግድ እያየና እየተረዳ መጥቷል፡፡

ሪፖርተር፡- በሥጋ ደዌ ተጠቂዎች የተከናወኑ ልዩ ልዩ ዕደ ጥበባት አንድ ሰሞን ገበያ ወይም ገዥ አጥተው ችግር ተፈጥሮ ነበር፡፡ ይህ ጉዳይ አሁን ከምን ደረሰ?

አቶ ከፍያለው፡- በወቅቱ ከውጭ ሰዎች ሲመጡ በማኅበሩ የታቀፉ የሥጋ ደዌ ተጠቂዎች ያከናወኗቸው ልዩ ልዩ የእጅ ሥራዎች የሚሸጡበትን ቦታ ብሔራዊ ማኅበሩ ይመራቸው፣ ይጠቁማቸውና ያገናኛቸው ነበር፡፡ አሁን ግን በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ከውጭ የሚመጡት እየቀነሰ መጥቷል፡፡ በዚህም የተነሳ ገበያ ማጣታቸው ይታያል፡፡ ይህ ዓይነቱ ሁኔታ ደግሞ ይቀጥላል ብለን አናምንም፡፡ በእርግጥ እዚህ አዲስ አበባ ከተማ ላይ የእጅ ሥራ ቡድን አለ፡፡ ይህም ሁኔታ በየክልሉ እንዲኖር አድርገናል፡፡ የእጅ ሥራዎች ጠቀሜታ አላቸው፡፡ ከጠቀሜታዎችም መካከል አንደኛ ኅብረተሰቡን ለማስተማር ይረዳል፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ገቢ ማስገኛ ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- የሥጋ ደዌ ተጠቂዎችና ቤተሰቦቻቸው የሚደርስባቸውን መገለል ለማስቀረት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያወጣቸው መርሆዎችና ማስፈጸሚያ መመርያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ምን ያህል ተግባራዊ ሆነዋል ይላሉ?

አቶ ከፍያለው፡- በእርግጥ መሮሆዎቹና ማስፈጸሚያ መመርያዎቹ አስገዳጅ ሕግን እስካሁን ድረስ አላወጡም፡፡ ቢወጡ ኖሮ ሥጋ ደዌ ተጠቂዎችና ሌሎችም አካል ጉዳተኞች በጣም ጥሩ ዕድል ያገኙ ነበር፡፡ ጠቃሚም ነው፡፡ ሞራልም ይሰጣል፡፡ ለበለጠ ሥራ እንድንነሳሳ ያደርጋል፡፡ ብሐራዊ ማኅበሩ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማኅበራዊ ፌዴሬሽን አባል ስለሆነ ከፌዴሬሽኑ ጋር በመሆን አስገዳጅ ሕጎች እንዲወጡ የበኩሉን ጥረት እያደረገ ነው፡፡ ወደፊት ዕውን ይሆናሉ የሚል እምነትም አለን፡፡

ሪፖርተር፡- ስምምነቱን ኢትዮጵያ አልተቀበለችም እያሉኝ ነው?

አቶ ከፍያለው፡- ስምምነቱን ተቀብላለች ግን አስገዳጅ ሕጎቹን አላወጣችም፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ በየዓመቱ እየተከበረ ያለው የዓለም ሥጋ ደዌ ቀን ዓለም አቀፋዊ አጀማመርና ይዘት ምን እንደሚመስል ቢያብራሩልን?

አቶ ከፍያለው፡- የዓለም የሥጋ ደዌ ቀን መከበር የጀመረው በ1946 ዓ.ም. ነበር፡፡ መሥራቹም ፈረንሳዊው ፈዑል ፎልሮ ሲሆን ዓላማውም የሥጋ ደዌ ተጠቂዎች የነበሩበትን አሰቃቂ ሁኔታና የሰብዓዊ መብት መገፈፍን ለዓለም ሕዝብና መንግሥታት ለማሳወቅና ዕርምጃ እንዲወሰድ ተፅዕኖ ለማድረግ ነው፡፡ በወቅቱም አንግቦ የተነሳቸው ሰባት ዓላማዎች አሉ፡፡ ከዓላማዎቹም መካከል የሥጋ ደዌ ተጠቂዎች እንደ ሰዎች ሁሉ እንዲከበሩ፣ በነፃነት እንዲኖሩና እንደ ሌሎች ሰዎች በአግባቡ እንዲታከሙ፣ ለተጠቂዎች መረጃ ግንዛቤ ለማሰባሰብ፣ በመንከባከብና በማቋቋም በራሳቸው እንዲተማመኑ ለማድረግ የሚሉና ሌሎችም ይገኙባቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የዓለም የሥጋ ደዋ ቀን በኢትዮጵያ መከበር የጀመረው መቼ ነው?

አቶ ከፍያለው፡- የኢትዮጵያ ሥጋ ደዌ ተጠቂዎች ማኅበር ከተመሠረተ በኋላ በ1992 ዓ.ም. ከመንግሥትና ከሌሎች አጋሮች ጋር በመሆን ቀኑ ለመጀመርያ ጊዜ በብሔራዊ ደረጃ ዕውቅና አግኝቶ በአዲስ አበባ፣ በሐዋሳ፣ በባህር ዳር፣ በጅማ፣ በድሬዳዋ፣ በአዊ ዞን፣ በሻሸመኔ፣ በደሴ፣ በሐሮማያ፣ በትግራይና በጎንደር ሲከበር ቆይቷል፡፡ የዘንድሮው የዓለም አቀፍ የሥጋ ደዌ ቀን ‹‹የሥጋ  ደዌ በሽታን አንዘንጋው!!›› በሚል መሪ ቃል በብሔራዊ ደረጃ፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጥር 22 ቀን 2014 ዓ.ም. ተከብሮ ውሏል፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ በየዓመቱ የሚከበርበት ዓላማ ምንድነው?

አቶ ከፍያለው፡- የሥጋ ደዌ ተጠቂዎች የእኩል ዕድልና ተሳትፎ ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ ለማድረግ፣ በአግባቡ እንዲታከሙና መገለል ከሚያስከትልባቸው አካል ጉዳት እንዲጠበቁ ለማስቻል፣ ብዙ ሰዎች በሥጋ ደዌ ተጠቃዎች ዙሪያ ያላቸው አመለካከት ትክክለኛ ያልሆነና የተዛባ በመሆኑ፣ ይህን አመለካከት ለማረምና ለማስወገድ፣ የሥጋ ደዌ ተጠቂዎች ሁለንተናዊ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ለማድረግ ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለቀድሞ የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት የቆመው የብርጋዲየር ጄኔራል ለገሠ ፋውንዴሽን

የቀድሞ የኢትዮጵያ የጦር ሠራዊት አባላት ለአገራቸው የሕይወት መስዋዕትን ለመክፈል የወደዱ፣ ለአገራቸው ክብር ዘብ የቆሙና ውለታን የዋሉ ናቸው፡፡ እነኚህ የአገር ጌጦች በአገሪቱ በተከሰተው የሥርዓት ለውጥ...

ገደብና አፈጻጸም የሚሹ የአየር ሙቀት መጠንና የካርቦን ልቀት

የአየር ንብረት ቀውሱን ለመቋቋም የዓለም ከተሞች ከንቲባዎችን የሚያስተሳስረው ቡድን (ግሩፕ) ሲ-40 (C-40) ተብሎ ይታወቃል፡፡ ከተቋሙ ድረ ገጽ መገንዘብ እንደሚቻለው፣ አዲስ አበባን ጨምሮ የ40ዎቹ ከተሞች...

ሕፃናትን ከመስማት ችግር የሚታደገው የቅድመ ምርመራ ጅማሮ

‹‹መስማት ለኢትዮጵያ›› በጎ አድራጎት ማኅበር በጨቅላ ሕፃናት ደረጃ የመስማት ችግር እንዳይከሰትና በሕክምናውም ዙሪያ በዘመኑ ሕክምና መሣሪያዎች በመታገዝ ሕክምና ለመስጠት ሚያዝያ 2014 ዓ.ም. የተመሠረተ ነው፡፡...