በአማራ ክልል የተፈጸመውን ወረራ ለመመከትና አገሪቱን ከጥቃት ለመታደግ እየታገሉ ያሉ ፋኖን ጨምሮ ሌሎች የፀጥታ ኃይሎችን በሚመለከት፣ ክልሉ አቋሙን አለመቀየሩን አስታወቀ፡፡
ፋኖንም ሆነ ሌሎች የፀጥታ አደረጃጀቶችን በሚመለከት ኢመደበኛ አደረጃጀቶችን ለማፍረስ ይፈለጋል ተብሎ ከሰሞኑ የተናፈሰው ወሬ፣ የመንግሥት አቋም አለመሆኑን ክልሉ አስታውቋል፡፡ መነሻቸው ምን እንደሆነ ለማይታወቅ በየጊዜው ለሚቀርቡ አሉባልታዎችና ያልተጨበጡ ወሬዎች ምላሽ መስጠት አስፈላጊ አለመሆኑን የገለጸው የክልሉ መንግሥት፣ ፋኖን በሚመለከት አቋሙ ከዚህ በፊት እንደነበረው መሆኑን ገልጿል፡፡
ከሰሞኑ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የሚመራው የብሔራዊ ፀጥታ ምክር ቤት አድርጎታል በተባለ ስብሰባ፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተመስገን ጥሩነህ አደረጉት የተባለው ንግግር ከፍተኛ ውዝግብ ማስነሳቱ ይታወሳል፡፡ መንግሥት በህልውና ትግል ወቅት የተፈጠሩ ኢመደበኛ አደረጃጀቶችን ሊቆጣጠር ይገባል የሚል ሪፖርት አቶ ተመስገን አቀረቡ ተብሎ በዋና ዋና ብሮድካስት መገናኛ ብዙኃን መዘገቡ ከፍተኛ ውዝግብ ማስነሳቱ አይዘነጋም፡፡ ይህን ተከትሎ ‹‹መንግሥት ፋኖን ሊያፈርስ አቅዷል›› ቢባልም፣ የክልሉ መንግሥት ግን፣ ‹‹የተቀየረ ነገር የለም›› ብሏል፡፡ የክልሉ መንግሥት ፋኖንም ሆነ ሌሎች በጦርነቱ የሚሳተፉ ኃይሎች በመንግሥት ጥሪ ነው ለህልውና ዘመቻ የተሠለፉት ብሏል፡፡
ጦርነቱ ገና አለማለቁንና ትግሉ መቀጠሉን የጠቀሱት የክልሉ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ፣ ‹‹ለእነዚህ ክልሉንና የአገር ህልውና ለመታደግ የተሳተፉ ኃይሎች በሙሉ ዕውቅና እንሰጣለን፤›› ብለዋል፡፡ የመንግሥት አቋም በመርህ ላይ የተመሠረተ መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው፣ ‹‹በህልውና ትግሉ ወቅት የተፈጸሙ ችግሮች ካሉ እርማት ይደረጋል፡፡ ከዚያ ውጪ ግን ትናንት ያሞገስነውን ኃይል ዛሬ ኃጢያተኛ የምናደርግ ሰዎች አይደለንም፤›› ሲሉ በተለይ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
መንግሥት ኢመደበኛ አደረጃጀቶችን መቆጣጠር ያለው፣ ‹‹በህልውና ዘመቻው ከፍተኛ አስተዋጽኦ የነበራቸው እንደ ፋኖ ያሉ አደረጃጀቶችን የማፍረስ ፍላጎት ስላለው ነው›› በሚል ሪፖርተር ጥያቄ ያቀረበላቸው የክልሉ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ግዛቸው፣ በክልሉ መንግሥትም ሆነ በፌዴራል ደረጃ ይህን መሰል አቋም አለመንፀባረቁን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ነገርየው ዩቲዩበሮች፣ አክቲቪስቶችና ተንታኝ ነኝ ባዮች የፈጠሩት ተራ አሉባልታ ነው፤›› ሲሉ አቶ ግዛቸው አስረድተዋል፡፡
ይሁን እንጂ ይህንኑ አስመልክቶ ጥያቄ ሪፖርተር ያቀረበላቸው የፋኖ አደራጅና መሪ ከሆኑት አንዱ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ፣ ጉዳዩን ለማጥራት ከመንግሥት ጋር ውይይት መጀመሩን ነው የተናገሩት፡፡ ‹‹ከመንግሥት ጋር ንግግር ጀምረናል፣ ስንጨርስ የደረስንበትን ለሕዝብ እናሳውቃለን፤›› ያሉት መቶ አለቃ ማስረሻ፣ ጉዳዩ ከየት እንደመጣና መነሻው ምን እንደሆነ በውይይት ይጠራል ብለዋል፡፡
የክልሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ ግዛቸው ግን፣ ‹‹እኛ አሠራራችን በመርህ ላይ የተመሠረተ ነው፤›› ብለው፣ ውይይትን አስመልክቶ የተደረገ ንግግርም ሆነ አዲስ የውይይት መድረክ አለመኖሩን ገልጸዋል፡፡ ‹‹አሁን ያለንበት ወቅት ክልሉን ለማልማትና መልሶ ለመገንባት ፋታ የማይሰጥ በመሆኑ፣ በህልውና ዘመቻው የሚካፈሉ ኃይሎች በልማት ላይ እንዲረባረቡ ለማድረግ ነው የታሰበው፤›› ብለዋል፡፡
የተያዙ ቦታዎች ገና ተለቀው አለማለቃቸውን፣ ጦርነቱ አለመጠናቀቁንና ድሉም ሙሉ አለመሆኑን ያስረዱት አቶ ግዛቸው፣ ‹‹የእኛ አቋም አሁንም ራስን መከላከልና ለሰላም መስፈን ከመትጋት ጎን ለጎን ለልማት መረባረብ ነው፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡
‹‹በትግል ሒደት የነበሩ ስህተቶችና ጉድለቶች ካሉ ሁሉም እንዲታረም ይደረጋል፡፡ ከዚያ ውጪ አንዱን ጀግና ሌላውን ፈሪ እያልን የምንፈርጅበት አሠራር የለም፤›› ያሉት አቶ ግዛቸው፣ ሰላምና ፀጥታን ከማስፈር አኳያ ግን ‘ጦር መሣሪያ አያያዝ፣ አጠቃቀምና የትጥቅ ባለቤትነትን’ በተመለከተ ዝርዝር አሠራር መንግሥት ያወጣል ብለዋል፡፡ አቶ ግዛቸው በህልውና ጦርነቱ ያሸነፈው ሁሉም ኢትዮጵያዊ መሆኑን ገልጸው፣ ‹‹ሁላችንም ብንሆን ከአገርና ከሕግ በታች ነን፤›› ሲሉም አስረድዋል፡፡
መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ በበኩላቸው፣ ‹‹እኛ አገር አልወጋንም፣ አልዘረፍንም፣ ንፁኃንን አልጨፈጨፍንም፤›› ካሉ በኋላ፣ ፋኖ የአገርን ህልውና ለመታደግ የተደራጀና የተሠለፈ ኃይል መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ጦርነቱና ትግሉ ገና አለማብቃቱን የጠቀሱት መቶ አለቃ ማስረሻ፣ ‹‹ለፋኖ መፍረስ ክፉውን የሚመኙት አገር ለማፍረስ ፊት ለፊታቸው ቆሞ እንቅፋት የሆነባቸው የጠላት ኃይሎች ብቻ ናቸው፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በመንግሥት በኩል የተሳሳተ አቋም ከተያዘ ተቀምጦ በመነጋገር ማጥራትና መግባባት እንደሚቻል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
አቶ ግዛቸው የሰሞኑ ፋኖን ወይም የኢመደበኛ አደረጃጀት ጉዳይን ውዝግብ አጀንዳ ማቀበል፣ የአማራ ክልልን አንድነትና ጥንካሬ ለመበታተን በሚፈልጉ ኃይሎች የተፈበረከ ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን አስረድተዋል፡፡