ድርጊቱ ከመንግሥት ዕውቅና ውጪ በመመሳጠር የተደረገ ነው ይላሉ
‹‹ያነጋገረን አካል የለም፣ ቢሯችን ክፍት ስለሆነ ቀርበው ማነጋገር ይችላሉ››
ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ
በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ጀሞ አንድ፣ ሁለትና ሦስት እንዲሁም ለቡ ጋራ በሚባሉና በተለያዩ አካባቢዎች ነባር ነዋሪዎች መሆናቸውን የሚናገሩ አርሶ አደሮች፣ በሕገወጥ መንገድ መሬታቸውን እንደተነጠቁ ተናገሩ፡፡
ልማትን ምክንያት በማድረግ ከቅድመ አያቶቻቸው፣ አያቶቻቸውና አባቶቻቸው ሲተላለፍ የቆየ ይዞታቸውን ‹‹ዓልሚዎች ነን›› ከሚሉና በመንግሥት ደረጃ ከማይታወቁ ግለሰቦች ጋር በተፈጸመ ሕገወጥ ተግባር ወይም በመመሳጠር ይዞታቸውን መነጠቃቸውን ቁጥራቸው በርከት ያሉ ወጣት አርሶ አደሮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ለተወሰደባቸው የእርሻ መሬት ምትክ ቦታም ሆነ ካሳ ሳይከፈላቸው መሬታቸው መታጠሩንና ‹‹ለተደራጁ ወጣቶች (ቄሮዎች) ልማት የሚውል ነው›› በሚል ሰበብ ለሌላ ወገን ግልጽ ባልሆነ ሁኔታ እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለአካባቢያቸው ወረዳና ለክፍለ ከተማው አቤቱታ ቢያቀርቡም፣ ‹‹አንዱ ሌላውን ጠይቅ›› ከማለት ውጪ ምላሽ ሊሰጣቸው ባለመቻሉ ክስ መሥርተው ፍትሕ እየተጠባበቁ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
አርሶ አደሮቹ እንደሚናገሩት፣ በተለያዩ ቦታዎች ማለትም በጀሞና በለቡ በልማት ስም የታጠሩ ወይም በወረራ መልክ የተያዙ ቦታዎች ስፋት እስከ 200ሺሕ ሜትር ካሬ እንደሚደርስ ጠቁመው፣ የሚመለከተው የመንግሥት አካል ጉዳዩን ተመልክቶና መርምሮ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2013 ዓ.ም. የአርሶ አደር መሬትን በሚመለከት ባወጣው መመርያ፣ አርሶ አደር በያዘው መሬት (ይዞታ) መጠን (ልክ) የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እንዲሠራለት የተደነገገ ቢሆንም፣ እየተሠራ ያለው ግን የተገላቢጦሽ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ክፍለ ከተማውና ወረዳው ለተደራጁ ወጣቶች (ቄሮዎች) እንደሆነ ቢናገርም፣ በቦታው ካርታ የተሠራው ግን ሪል እስቴት አልሚ ነን በሚሉና በውልና ማስረጃ ውል ተፈራርመናል በሚሉ ግለሰቦች ስም መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ነገር ግን ውልና ማስረጃ ሄደው ሲያጣሩ ምንም ዓይነት ስምምነትም ሆነ ውል እንደሌላቸው ስለተገለጸላቸው፣ ጉዳዩን ወደ ፀረ ሙስና ኮሚሽንም እንደወሰዱትም አስረድተዋል፡፡ ይዞታቸው ለበርካታ ዘመናት ሲገበርበት የነበረና የአርሶ አደሮች መሆኑን የሚያስረዱት፣ በሰነዶችና አካባቢውን በሚያውቁ አንቱ በተባሉ የአካባቢው ሽማግሌዎች ጭምር የሚታወቅ በመሆኑ፣ የሚመለከተው አካል እውነቱን አረጋግጦ መብታቸውን እንዲያከብርላቸው ተማጽነዋል፡፡
ልማትን ደጋፊ በመሆናቸውም፣ መንግሥት ባወጣው ዕቅድና ፕላን መሠረት ለማልማትም ብቃቱና ችሎታው እንዳላቸው አክለው፣ ቅድሚያ የማልማት መብታቸው እንዲከበርላቸውም ጠይቀዋል፡፡
አርሶ አደሮቹ ያቀረቡትን ቅሬታና አቤቱታ በሚመለከት ማብራሪያ እንዲሰጡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ነፃነት ዳባ፣ እሳቸው ምንም የደረሰቸውና የሚያውቁት ነገር እንደ ሌለ ተናግረው፣ ቅሬታ ያለበት አካል በቢሮአቸው ሊያነጋግራቸው እንደሚችል ከመናገር ውጪ ለተነሱ ጥያቄዎች ያሉት ነገር የለም፡፡