Wednesday, September 27, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትዮ ቴሌኮም የ5ጂ ኔትወርክ ሙከራ ለማስጀመር የፍሪኩዌንሲ ምደባ እየጠበቀ መሆኑን አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮ ቴሌኮም የ5ጂ አገልግሎት በሙከራ ደረጃ ለማስጀመር የሚያስችለውን የፍሪኩዌንሲ ባንድ ለማግኘት፣ ለኢትዮጵያ ኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣንን ጥያቄ አቅርቦ ምላሽ እየጠበቀ መሆኑን አስታወቀ፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም እ.ኤ.አ. በ2022 መጀመርያ አስጀምረዋለሁ ብሎት የነበረውን የአምስተኛ ትውልድ የኢንተርኔት አገልገሎት ለመስጠት ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ገልጾ፣ ለዚህም የሚያገለግል ፍሪኪዌንሲ ባንድ እንዲሰጠው ለባለሥልጣኑ ከአንድ ወር በፊት ጥያቄ ማቅረቡን ገልጿል፡፡ የኢትዮ ቴሌኮም ቺፍ ቴክኒካል ኦፊሰር አቶ ታሪኩ ደምሴ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ኩባንያው ጥያቄውን ያቀረበው ጊዜያዊ ፈቃድ ለማግኘት ነው፡፡

ኩባንያው ፍሪኩዌንሲ ለማግኘት ቢያቀርብም፣ ባለሥልጣኑ ፍሪኩዌንሲውን ለኩባንያው የሚሸጥበት መንገድን በተመለከተ እስካሁን ውሳኔ ላይ አልደረሰም፡፡ እንደ ኦፊሰሩ ገለጻ ኢትዮ ቴሌኮም ከ125 ዓመታት በላይ ተቆጣጥሮት በቆየው የቴሌኮም ኢንዱስትሪ ተሳታፊ የሚሆኑ ሌሎች ኩባንያዎች በመኖራቸው፣ ባለሥልጣኑ ለ5ጂ የሚሆነውን ፍሪኩዌንሲ ለኢትዮ ቴሌኮም የሚያቀርብበት መንገድ ከዚህ ቀደም ከነበረው የተለየ ሊሆን ይችላል፡፡

ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር ኩባንያው የሚፈልገውን ፍሪኩዌንሲ ዋጋ ባለሥልጣኑ ወስኖ የሚያቀርብ ሲሆን፣ አሁን ግን ፍሪኩዌንሲውን እንደ ሳፋሪኮም ካሉ የቴሌኮም ኩባንያዎች ጋር ማጫረት አማራጭ ሆኖ ሊቀርብ ይችላል፡፡ ይሁንና የኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን ፍሪኩዌንሲውን ያጫርተዋል? ወይስ ዋጋ ተምኖ ለኢትዮ ቴሌኮም በሽያጭ ያቀርበዋል? የሚለውን አለመወሰኑን አቶ ታሪኩ አስረድተዋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም ከሁለት ዓመት በፊት በአዲስ አበባ ከተማ የተወሰኑ ቦታዎች ላይ ብቻ አገልግሎት ሲሰጥ የነበረውን የ4ጂ አገልግሎት በማስፋቱ፣ አሁን 136 ከተሞች የ4ጂ ኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን አስታውቋል፡፡ የኢትዮ ቴሌኮም የ4 ኤልኢቲ አድቫንስድ ከዚህ ቀደም ከነበረው የ3 ኢንተርኔት አገልግሎት 13 እጥፍ የሚልቅ ፍጥነት አለው።

ኩባንያው በ2014 ዓ.ም. የመጀመርያ በጀት ዓመት የተሠሩ ጥሩ ሥራዎች ካላቸው ውስጥ፣ የቀጣይ ትውልድ ቢዝነስ ሰፖርት ሲስተምን (New Generation Business Support System) ተግባራዊ የማድረግ ፕሮጀክት መጠናቀቅ ይገኝበታል፡፡ 43 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ተደርጎበታል የተባለው ይኼ የቀጣይ ትውልድ ሥርዓት ዝርጋታ፣ የኩባንያውን አቅም ለመጨመርና ተወዳዳሪነቱን ለማሳደግ የሚያስፈልግ መሠረታዊ ሥርዓት እንደሆነ፣ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ታምሩ ጥር 12 ቀን 2014 ዓ.ም. የኩባንያውን የ2014 ግማሽ በጀት ዓመት አፈጻጸም ባቀረቡበት መድረክ ላይ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም አዲሱ ሥርዓት ኩባንያው በእ.ኤ.አ. 2022 መጀመርያ አስጀምረዋለሁ ብሎ የነበረውን የ5ጂ ኔትወርክን ለመተግበር በሚያስችል መንገድ የተዘረጋ ነው፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም 5ጂን ለመጀመርያ ጊዜ አዲስ አበባ ውስጥ የተወሰኑ ቦታዎች ላይ እንደሚያስጀምር የተነገረ ሲሆን፣ ይህንን ለመዘርጋት የሚያችለውን ዝግጅት እያጠናቀቀ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ይሁንና የ5ጂ ኔትወርክን ለመተግበር የሚያስችለው ፍሪኩዌንሲ ባንድ ለኩባንያው አልቀረበም፡፡

የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ለመስጠት ወሳኝ የሆነው የሬዲዮ ፍሪኩዌንሲ ስፔክትረም እንደ ስልክ ባለ መሣሪያና የቴሌኮሙዩኒኬሽን ማማ መካከል የሚዘዋወረውን ዳታ የሚሸከም ሞገድ ነው፡፡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኮሙዩኒኬሽን ኢንጂነሪንግ ባለሙያ እንደሚያስረዱት፣ የሬዲዮ ፍሪኩዌንሲ ስፔክትረም እንደ መሬት ውድ የሆነ ሀብት ነው፡፡ መሬት ውስን ሀብት በመሆኑ መንግሥት አገርንና ሕዝብን በሚጠቅም መንገድ ለተለያየ አገልግሎት እንደሚያከፋፍለው ሁሉ፣ ፍሪኩዌንሲም ሀብትነቱንና ውስንነቱን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ምደባ ይደረግበታል ብለዋል፡፡

ለተለያዩ የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎቶች ተስማሚ የሆኑ የተለያዩ ፍሪኩዌንሲዎች እንዳሉ የሚናገሩት ባለሙያው፣ ብዙ አገሮች የ5ጂ አገልግሎትን ለመስጠት እየተጠቀሙበት ያለው ሲ ባንድ የተባለውንና 3.6 ጊጋ ኸርዝ ላይ ያለውን ፍሪኩዌንሲ ነው፡፡ የተለያዩ ፍሪኩዌንሲዎች የተለያየ ስፋት ያላቸው ሲሆን፣ የፍሪኩዌንሲው ስፋት ምን ያህል ተጠቃሚዎች የኢንተርኔት አገልግሎቱን በጥራት ሊስተናገዱበት ይችላል የሚለውን ይወስናል፡፡ ስለዚህም በየአገሮቹ ያሉ የኮሙዩኒኬሽን ተቆጣጣሪ ተቋማት ፍሪኪዌንሲው ያለውን ስፋት ግምት ውስጥ በማስገባት ላሉት የቴሌኮም ኩባንያዎች ያከፋፍላሉ፡፡

ለ5ጂ ኔትወርክ በብዛት ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው የሲ ባንድ ፍሪኩዌንሲ 400 ሜጋ ኸርዝ ባንድ ዊድዝ (ስፋት) እንዳለው የገለጹት ባለሙያው፣ አገር ይህን 400 ሜጋ ኸርዝ ለተለያዩ አገልግሎቶች ከፋፍለው እንደሚመድቡ አስረድተዋል፡፡ ፊንላንድ ለዚህ ጉዳይ በምሳሌነት መጠቀስ የምትችል ሲሆን፣ ለሦስት የቴሌኮም ኩባንያዎች ለእያንዳንዳቸው 130 ሜጋ ኸርዝ ሰጥታለች፡፡

ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር በአገሪቱ የቴሌኮም ኢንዱስትሪ ላይ ብቸኛ የነበረው ኢትዮ ቴሌኮም ለሚሰጣቸው አገልግሎቶች የሚውሉ ፍሪኩዌንሲዎችን ያለ ተወዳዳሪ ያገኝ ነበር፡፡ በአገሪቱ በውድድር ላይ የተመሠረተ የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት አቅርቦት እንዲኖር በመወሰኑ፣ በ2011 ዓ.ም. የወጣው የኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት አዋጅ የኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን የአገሪቱን ወቅታዊና የወደፊት ፍላጎትን ባገናዘበ መልኩ የፍሪኩዌንሲ ምደባ እንደሚያከናውን ደንግጓል፡፡

በዚህም ምክንያት አሁን ለ5ጂ አገልግሎት የሚውለው ፍሪኩዌንሲ ምደባ፣ ከኢትዮ ቴሌኮም በተጨማሪ ሥራ ለመጀመር ዝግጅት ላይ ያለውን ሳፋሪኮምና በቀጣይ ይኖራል ተብሎ የሚጠበቀውን ሌላ የቴሌኮም ኩባንያ ከግምት ውስጥ ያስገባ እንደሚሆን ባለሙያው አስረድተዋል፡፡ ይህ ዓይነቱ የፍሪኩዌንሲ ምደባ ለኢትዮ ቴሌኮምም ሆነ ለኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን አዲስ ልምድ እንደሆነ የገለጹት የኮሙዩኒኬሽን ኢንጂነሪንግ ባለሙያው፣ በዓለም ላይ አራት የፍሪኩዌንሲ ምደባ ቴክኒኮች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በፊት ኢትዮ ቴሌኮም ሲጠቀምበት የነበረው በቀጥታ ጥያቄ ላቀረበ ኩባንያ ፍሪኩዌንሲ መስጠት አንዱ ዘዴ ሲሆን፣ ከዚህ ውጪ ያሉ ሌሎች ሁለት የምደባ መንገዶች በኢትዮጵያ ላለው ሁኔታ ጥቅም ላይ ሊውሉ እንደሚችሉ ባለሙያው አስረድተዋል፡፡ አንደኛው አማራጭ የቴሌኮም ኩባንያዎች ፍሪኩዌንሲው ቢሰጣቸው በምን ዓይነት መንገድ ጥራት ያለው አገልግሎት እንደሚያቀርቡ ከገለጹ በኋላ፣ በዚሁ መሠረት ልየታ የሚደረግበትና ትኩረቱ ጥራት ያለው አገልግሎት ማቅረብ ላይ የሆነ የምደባ አማራጭ ነው፡፡ ሌላኛው ጨረታ ሲሆን ይህ ደግሞ አብዛኛው ትኩረቱ ኩባንያዎቹ ፍሪኩዌንሲውን ለማግኘት የሚያቀርቡት የገንዘብ መጠን ላይ ነው፡፡ እንደ ባለሙያው አስተያየት ይህ ዓይነቱ ዘዴ በኢትዮጵያ ለ5ጂ ለሚደረገው የፍሪኩዌንሲ ምደባ ተግባራዊ የመሆን ዕድል አለው፡፡

የኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት አዋጅ የፍሪኩዌንሲ ምደባ እንዲከናወን በሚቀርቡ ማመልከቻዎች መካከል የጋራ መነጣጠል ካለ፣ ባለሥልጣኑ ከማመልከቻዎቹ መካከል ለመምረጥ ተገቢ ነው ብሎ ያመነውን ዘዴ እንደሚጠቀም ደንግጓል፡፡ ከዘዴዎቹ መካከልም የጨረታ ውድድር፣ ዕጣ ወይም የሚያቀርቡት የአገልግሎት ጥራት ሊካተቱ እንደሚችሉ በአዋጁ ላይ ሠፍሯል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ባልቻ ሬባ (ኢንጂነር)፣ ከዚህ ቀደም የነበረው ሁኔታ የቴሌኮም ዘርፉን አንድ ኩባንያ በብቸኝነት ተቆጣጥሮ የነበረበት፤ አሁን ደግሞ የውድድር ገበያ ያለበት እንደሆነ ተናግረው፣ “እዚህ ነገር ላይ ለመነጋገር (ጊዜው) በጣም ገና ነው፤” ብለዋል፡፡

የኮሙዩኒኬሽን ኢንጂነሪንግ ባለሙያው ኢትዮጵያ ውስጥ አብዛኛው ሰው 5ጂ ኔትወርክን ለመጠቀም የሚያስችል የሞባይል ስልክ የሌለው መሆኑን እንደ አንድ ምክንያት በመጥቀስ፣ ቢያንስ እስከ ቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ኢትዮ ቴሌኮምም ሆነ በቀጣይ ሥራ የሚጀምሩ የቴሌኮም ኩባንያዎች የ5ጂ ኔትወርክ ሊያስጀምሩ ይችላሉ የሚል ዕይታቸውን አጋርተዋል፡፡ በዚህም የተነሳ የኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን የፍሪኩዌንሲ ምደባ ላይ በፍጥነት ላይሠራ እንደሚችል ግምታቸውን ሰንዝረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች