ቅዳሜ ጥር 28 ቀን 2014 ዓ.ም. የተጀመረው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ፣ ዛሬ እሑድ ጥር 29 ቀን 2014 ዓ.ም. በሚያደርገው ቀጣይ ስብሰባው፣ እስራኤል የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ በታዛቢነት እንድትሳተፍ የተሰጠው ዕውቅና ተገቢነት ላይ በዝግ እንደሚመክር ይጠበቃል።
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሐመት ሙሳ ፋኪ እ.ኤ.አ. በ2021 ጁላይ ላይ የእስራኤል መንግሥት ያቀረበውን ጥያቄ በመቀበል፣ በአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ ላይ የታዛቢ አባልነት ዕውቅና እንዲሰጣት መወሰናቸው፣ በኅብረቱ ኮሚሽን አመራሮች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት፣ የኅብረቱ አባል ወደ ሆኑት የአፍሪካ አገሮች መዝለቁን መረጃዎች ያመለክታሉ።
በቀዳሚነትም ደቡብ አፍሪካ የኅብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ውሳኔን በይፋ ተቃውማ ነበር።
የአፍሪካ ኅብረት የሁሉም አፍሪካ አገሮች ተስፋና ፍላጎት መገለጫ እንደሆነ፣ ይህንንም በቻርተሩ የተገለጹ ዓላማዎችን በተለይም የራስን ጉዳይ በራስ የመወሰንና ቅኝ ግዛትን ከማጥፋት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ተግባራዊ እንቅስቃሴ በማድረግ፣ አኅጉሪቱን የሚመራ ተቋም እንጂ፣ ዓለም አቀፍ ሕግና ግዴታዎችን የሚጥሱትን የሚሸልም ተቋም መሆን የለበትም በማለት ደቡብ አፍሪካ ተቃውሞዋን በወቅቱ ባወጣችው ይፋዊ መግለጫ አሳውቃ ነበር።
‹‹እስራኤል በፍልስጤማውያን ላይ የምታደርሰው ጭቆና የበለጠ በከፋበት ወቅት፣ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን እስራኤልን የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ ታዛቢ እንድትሆን የወሰነበትን ምክንያት ለመረዳት አዳጋች ነው። በመሆኑም የደቡብ አፍሪካ መንግሥት የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ይህንን ውሳኔ ለምን እንደወሰኑ ለሁሉም የአፍሪካ ኅብረት አባል አገሮች ማብራሪያ እንዲሰጡ ይጠይቃል፡፡ በዚህም ላይ የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ይወያያል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፤›› ሲል የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ባለፈው ሐምሌ ወር ባወጣው መግለጫ ተቃውሞውን ይፋ አድርጎ ነበር።
በመቀጠልም የደቡብ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት (SADC) ባለፈው ነሐሴ ወር ተመሳሳይ መግለጫ አውጥቶ ነበር።
በዚህም መሠረት ደቡብ አፍሪካና አልጄሪያ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን የኅብረቱ አባል አገሮችን ሳያማክር ለእስራኤል የታዛቢነት ዕውቅና የሰጠበትን ምክንያት፣ ለ35ኛው የአፍሪካ መሪዎች ጉባዔ ሪፖርት እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
ጥያቄው ተቀባይነት አግኝቶም የ35ኛው የአፍሪካ መሪዎች ጉባዔ አንድ አጀንዳ ሆኖ መቅረቡን የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ይህ አጀንዳም እሑድ ዕለት በሚካሄደው በመሪዎቹ ጉባዔ ሁለተኛ ቀን ስብሰባ በዝግ እንደሚካሄድ ለማወቅ ተችሏል።
በመሪዎቹ ጉባዔ ትልቅ ክርክር የሚካሄድበት አጀንዳ እንደሚሆንም ይጠበቃል። ከአፍሪካ ኅብረት ሰነዶች የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በአሁኑ ወቅት አገሮችንና ዓለም አቀፍ ተቋማትን ጨምሮ ሰባ ሁለት አካላት በአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ የታዛቢነት ዕውቅና አላቸው።
እስራኤል በቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (OAU) ወቅት ዕውቅና የነበራት ቢሆንም፣ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እ.ኤ.አ. በ2002 ፈርሶ በአፍሪካ ኅብረት ሲተካ ግን የነበራትን ዕውቅና እንዳጣች መረጃዎች ያመለክታሉ።