ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የሕወሓት አመራሮችን ክስ መንግሥት ለምን እንዳቋረጠ፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በቅርቡ ማብራሪያ እንደሚሰጡ የምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባዔ አስታወቁ፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት መንግሥት በታኅሳስ 2014 ዓ.ም. መጨረሻ በሦስት ክስ መዝገብ ጉዳያቸው ሲታይ ከነበሩ ተከሳሾች ውስጥ፣ ለሕወሓት ከፍተኛ አመራሮች ያደረገው የክስ ማንሳት ውሳኔ፣ ‹‹ተጎጂዎችን ያላገነዘበ ውሳኔ ነው›› በማለታቸውና ከፍተኛ ክርክር በማስነሳቱ ነው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ እንደሚሰጡ የተገለጸው፡፡
ፓርላማው የፍትሕ ሚኒስቴርን የ2014 ዓ.ም. የስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት፣ ጥር 26 ቀን 2014 ዓ.ም. ለመስማት ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ አድምጧል፡፡
የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) ሪፖርት ካቀረቡ በኋላ፣ በርካታ የምክር ቤቱ አባላት በሕዝብ ላይ ጭካኔ የተሞለባት ጭፍጨፋ ያካሄዱ አካላትን ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ነው ተብሎ የተደረሰበት ክስ የማቋረጥ ውሳኔ አግባብ አይደለም ሲሉ ማብራሪያ ጠይቀዋል፡፡
የመጀመሪያው ጥያቄ አቅራቢ አቶ ዳውድ መሐመድ የተባሉ የምክር ቤት አባል ሲሆኑ፣ ‹‹መንግሥት ክስ ስላቋረጠበት ሁኔታ ግልጽ መረጃ እንዲሰጠን እንፈልጋለን፤›› ሲሉ ለሚኒስትሩ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
ሌላው የምክር ቤት አባል ታደለ ቡርቃ (ረዳት ፕሮፌሰር)፣ ‹‹ምንም እንኳ በይቅርታ የማምን ሰው ቢሆንም፣ ይቅርታ ሊደረግለት የሚገባው ሰው በፈጸመው ወንጀል ልክ ሳይሆን የፍትሕ ሥርዓቱ በሚፈቅደው ልክ መሆን አለበት፤›› ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ‹‹በፓርላማ አሸባሪ ተብሎ ለተሰየመ ድርጅት ፓርላማው ውሳኔ መስጠት አልነበረበትም ወይ?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ፓርቲ ተወካይ ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር)፣ ‹‹ውሳኔው ሕይወታቸውን ባጡና የችግሩ ሰለባ የሆኑ ዜጎች ላይ ‹የተፈጸመ ክህደት፤›› ነው ብለዋል፡፡ የፍትሕ ሚኒስትሩ በ2000 ዓ.ም. የወጣውን አዋጅ ቁጥር 953 በመጥቀስ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ክስን ማቋረጥ ይቻላል በሚል ያቀረቡትን ሐሳብ፣ ‹‹በዘር ማጥፋትና በጅምላ ፍጅት የተሳተፉ ግለሰቦችን ክስ የማቋረጥ ሥልጠን አዋጁ ይሰጣል ወይ? ሲሉ አክለው ጠይቀዋል፡፡
በሕወሓት አመራሮች የተፈጸሙ ወንጀሎች በባህሪያቸው ዓለም አቀፍ ይዘት ያላቸው እንደሆነ የጠቀሱት ደሳለኝ (ዶ/ር)፣ ከእስር የተፈቱት ከፍተኛ የሕወሓት አመራሮች ቤታቸው ተቀምጠው ሳይሆን፣ ተንቤን በረሃ ወርደው ከሌሎች የጦር አመራሮች ጋር በመሆን አመራር ሲሰጡ ነበር ብለዋል፡፡
ወጣቶችን ሲያሠለጥኑ፣ የሆነ ሕዝብን ስም እየጠሩና በዚያ ሕዝብ ላይ ጅምላ ጭፍጨፋ እንዲፈጸም ሲያነሳሱና የማንቃት ሥራ ሲያከናውኑ የነበሩ መሆናቸውን፣ እንዲሁም ሜዳ ላይ ተገኝተው ትዕዛዝ ሲሰጡ የሚያሳይ ቪዲዮ መኖሩን ጠቅሰዋል፡፡
‹‹በመሆኑም የቅርብ ጊዜ ሁኔታ እንኳ ቢታይ በጭና፣ በጋሊኮማና በሌሎች አካባቢዎች ጅምላ ዕልቂት ወንጀል የፈጸሙ ሰዎችን እንዴት ለሕዝብ ጥቅም ተብሎ ተለቀዋል ሊባል ይችላል?›› ሲሉ የፍትሕ ሚኒስትሩን ጠይቀዋል፡፡
‹‹መንግሥት የአገር ክህደት ወንጀሉን ውድቅ ለማድረግ ወይም የክሱን ሒደት ለማቋረጥ ወስኗል ብንል እንኳ፣ የጅምላ ጭፍጨፋና የዘር ማጥፋት ወንጀል አይመለከተውም ወይ?›› ሲሉም አክለው ጠይቀዋል፡፡
‹‹የፍትሕ ሚኒስቴርስ ቢሆን በእነዚህ ወንጀሎች ላይ ክስ ለመመሥረት ፍላጎት ያጣው ለምንድነው?›› በማለት የጠየቁት ደሳለኝ (ዶ/ር)፣ ‹‹በአጠቃላይ ሕወሓት ሽብርተኛ ተብሎ ተፈርጆና እነዚህ ሰዎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የድርጅቱ ዋነኛ ጎንጓኝ ሆነው እስከ መጨረሻው ድረስ በሕግ ቁጥጥር ሥር እስኪውሉ ድረስ ሲሠሩ የነበሩ ናቸው፡፡ እነዚህን ወንጀለኞች መልቀቅ በተጎጂዎችና የጅምላ ዕልቂት በተፈጸመባቸው ነፍሶች ላይ ክህድት መፈጸም አድርጌ እመለከተዋለሁ፤›› ብለዋል፡፡
‹‹ሆነም ቀረም እነዚህን ወንጀለኞች ይቅር የማለት ጉዳይ የሞቱና የተጎዱ ሰዎች ጉዳይ እንጂ፣ ማንም ይቅር ሊላቸው አይችልም፤›› ሲሉም አስረድተዋል፡፡
‹‹ዛሬ እናንተ ልትለቋቸው ትችላላቸሁ፣ ነገ ግን በሕዝባችን ላይ ለፈጸሙት ወንጅል ተጠያቂ እንደሚደረጉና ለዚህ ጉዳይም አበክረን እንሠራለን፤›› ብለዋል፡፡
በዚህ አገር ውስጥ ለሚታየው ‹‹ዓይነተ ብዙ›› አመለካከት፣ የፖለቲካ ውይይቶች የሚያስፈልጉ ቢሆንም፣ ውሳኔው ግን ተቃሎ መታየቱ አደገኛ የጥፋት መንገድ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
‹‹የሕዝባችን ደም ካለባቸው አካላት ጋር ውይይትና ንግግር የለም፣ ቢያንስ የወከልኩትን ሕዝብና ፓርቲ መሠረት አድርጌ መናገር እፈልጋሁ፤›› ሲሉም አጠንክረው ተናግረዋል፡፡
ምሕረትና ሰብዓዊነት የሚባለው ነገር በልኩ መታየት አለበት የሚሉት የምክር ቤት አባሉ ደሳለኘ (ዶ/ር) ወጣቶች፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና ጋዜጠኞች ሐሳቦቻቸውን በመግለጻቸው ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ታስረው ያሉበት አገር እንደሆነ በመግለጽ፣ ጉዳዩ ለምን በንፅፅር አይታይም ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
በሕዝባዊ ትግል የወደቀው የሕወሓት አገዛዝ የፍትሕ ሥርዓቱን የፖለቲካ መሣሪያ አድርጎት እንደቆየ በማስታወስ፣ አሁንም ያለው አካሄድ ይስተካከል በማለት ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡
ጋሻው ዳኘው የተባሉ የምክር ቤት አባል፣ በሌላ በኩል ሕወሓት አሸባሪ ተብሎ ተፈርጆ የአመራሮቹ ክስ ሲቋረጥ ድርጅቱን ብቻ አሸባሪ ማለት ይቻላል ወይ? ድርጅቱ አሸባሪ እንዲሆን አስበውና አልመው ሲፈጽሙና ሲያሰፈጽሙ የነበሩ አመራሮች እንደሆኑ እየታወቀ ሲሉም ጠይቀዋል፡፡
በዚህ ደረጃ ድርጅቱን ፀንሰውና ተንከባክበው አሳድገው እዚህ ደረጃ በማድረስ በወንጀል ሲመሩ የነበሩ አመራሮች ላይ የተወሰደው የክስ ማቋረጥ ሒደት፣ በሰብዓዊነትም ሆነ ከኅብረተሰብ ሞራል አንፃር እንዴት ይታያል በማለት ሚኒስትሩን ማብራሪያ ጠይቀዋል፡፡
የፍትሕ ሚኒስትሩ ለተነሱት ጥያቄዎች ማብራሪያ ሲሰጡ፣ ‹‹እዚህ ላይ ያሉ የሐሳብ ልዩነቶችን እገነዘባለሁ፣ እረዳለሁ፣ አከብራለሁ፡፡ መሰል ጉዳዮች ላይ ምክንያታዊ የሆኑ የሐሳብ ልዩነቶች ሊመጡ እንደሚችሉ ይታወቃል፡፡ የሚታየውን ስሜት፣ ቁስልና ቁጭት በማቅለል ወይም የደረሰውን ጉዳት በማቃለል የተወሰነ ውሳኔ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ ክሱ ከተቋረጠባቸው ሦስት መዝገቦች ውስጥ ስድስት የሕወሓት ሰዎች እንዲለቀቁ የተደረገው፣ በአገሪቱ መሠረታዊ የሆኑ ጉዳዮች ላይ በስፋት የሚንፀባረቁ የተለያዩ ቅራኔዎችና አለመተማመኖች በመኖራቸው፣ እነዚህ ቅራኔዎችም ሥር በመስደዳቸውና የተረጋጋ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ የሰከነ ሕይወት እንዳይኖር እያደረጉ ስለሆነ፣ አገራዊ መግባባት ለመፍጠር አገራዊ ምክክር መፈጠር ይኖርበታል ተብሎ በመታመኑ የተወሰነ ውሳኔ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
አገራዊ ምክክሩ አካታች እንዲሆን ስለሚፈለግና ይህን ሁኔታ ለማረጋገጥ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑና አነሰም በዛም ደጋፊ ያላቸው በተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ የአመራርነት ሚና የነበራቸው ተጠርጣሪ የሆኑ ግለሰቦች ክስ ቢቋረጥ፣ እነዚህ ሰዎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በአገራዊ ምክክር ሒደቱ ተሳታፊ ቢሆኑ የአገራዊ የምክክር ሒደቱን አካታችነት፣ ውጤታማትነና ተዓማኒነት የበለጠ ሊያሳድጉ ይችላሉ ተብሎ በመታሰቡ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
በመሆኑም አገራዊ ምክክሩ ተዓማኒ ከሆነ ለአገር የረዥም ጊዜ ጥቅም ሊገኝበት ይችላል በሚል መወሰዱን፣ ውሳኔው ቢያምና ቢቆረቁርም፣ አገራዊ የሆነ ዘላቂ ጥቅም ማስገኘትን ግምት ውስጥ ያስገባ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ባለፉት ሦስት ዓመታት በብሔርና በእምነት ግጭቶች ሳቢያ ከ10,000 በላይ ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ መመሥረቱን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፣ በዚህ ሦስት ዓመት የተገኘው ትምህርት ተጠርጣሪዎችን በመክሰስና በወንጀል ምርመራ ብቻ ፍትሕን ማምጣት እንደማይቻል ነው ብለዋል፡፡
በእነዚህ ዓመታት ውስጥ በነበረው የክስ ሒደት በተለይም በክልሎች አካባቢ የተለያየ የፖለቲካ ጫና በማድረግ፣ ከፍተኛ ወንጀል የፈጸሙ አካላትን ከወንጀል ነፃ የማድረግ ሥራ ሲከናወን እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
በመሆኑም በመደበኛው የወንጀል ሥርዓት ወይም ቅጣት ላይ ያተኮረውን ሥርዓት ተጠቅሞ ለተጎጂዎች ፍትሕ ማረጋገጥ ባይቻልም እንኳ፣ በቀጣይ በሚደረገው የአገራዊ የምክክር ሒደት ውስጥ በሚቀርቡ የፖሊሲ አማራጮች መንግሥት ኃላፊነት ወስዶ የሽግግርና የተሃድሶ ፍትሕ ማዕቀፎችን ተግባራዊ በማድረግ፣ ፍትሕን ማረጋገጥ ይቻላል በሚል የተወሰደ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ከሕወሓት ከፍተኛ አመራሮች ጋር በተገናኘ የተጀመረው ምርመራና ክስ ሲታይ፣ የስድስቱ የክስ መዝገብ ሲቋረጥ ታሳቢ ከተደረጉት ጉዳዮች ውስጥ፣ በግለሰቦቹ ጤንነት ችግር የተነሳ ከፍርድ ቤት ይልቅ ሆስፒታል ማመላለስ ይበዛ እንደነበር አስረድተዋል፡፡
በሌላ በኩል የእነዚህ ሰዎች ዋነኛ ክስ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. በአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ በተደረገው ጥቃት በነበራቸው የተሳትፎ ድርሻ እንጂ፣ ላለፉት ሃያና ከዚያ በላይ ዓመታት ለነበራቸው የፖለቲካ ሚና እንዳልሆነ በመጥቀስ፣ ውሳኔው ከሚያስከትለው ጉዳት ይልቅ ጥቅሙ ይበልጣል ብለዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ በርካታ የምክር ቤት አባላት ጥያቄ ለማቅረብ ፍላጎት ያሳዩ ቢሆንም፣ የምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባዔ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) በቅርቡ ማብራሪያ እንደሚሰጡና በዚያን ወቅት ጥያቄዎቻቸውን ማቅረብ እንደሚችሉ በማስታወቅ ስብሰባው ተጠናቋል፡፡