Monday, May 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉከተጠያቂነት እየሸሸና እያመለጠ ያለው የኢትዮጵያ ፍርድ ቤት

ከተጠያቂነት እየሸሸና እያመለጠ ያለው የኢትዮጵያ ፍርድ ቤት

ቀን:

በላቀው በላይ

የመንግሥት ሦስተኛው አካል እየተባለ የሚነገርለትና ሕግ አውጭውንና አስፈጻሚውን ይቆጣጠራል ተብሎ አመኔታ የተጣለበት የኢትዮጵያ ፍርድ ቤት፣ ሁለቱን የመንግሥት አካላት መቆጣጠር ቀርቶ የራሱን የውስጥ ሥራ እንኳን መሥራት አልቻለም ተብሎ መራራ ትችት እየቀረበበት ይገኛል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከሦስት ዓመት በፊት ወደ ሥልጣን እንደመጡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ፣ ፍርድ ቤት ፍትሕን በገንዘብ ሲቸበችብ ነበር የሚል የመረረ ትችት አቅርበዋል፡፡ በቅርቡ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ የፍትሕ ሥርዓት ከደምና ከገንዘብ ያልተፈታ መሆኑን፣ የፍትሕ ሥርዓት አለ ብሎ መናገር እንደማይቻል ከመናገራቸው በተጨማሪ፣ ምሬታቸውን የገለጹበት አካላዊ እንቅስቃሴ የፍትሕ ሥርዓቱ በምን ያህል ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ የሚያሳይ ነው፡፡

ይህንን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ትችት ተከትሎ በሁለቱም ወገን የተወሰደ የማስተካከያ ዕርምጃ አለመኖሩ ነገሩን እንቆቅልሽ አድርጎታል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፍርድ ቤት በገለጹት ደረጃ የሚገኝ መሆኑን ከተረዱ ሳይውሉ ሳያድሩ የፍርድ ቤት ማሻሻያ ፕሮግራም (Court Reform Program) እንዲጀመር ማድረግ ነበረባቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፍርድ ቤት የሚገኝበትን ደረጃ በዚህ መልክ እየገለጹና ሕዝቡም በፍርድ ቤት አመኔታ እያጣና ተስፋ እየቆረጠ እንዲቀጥል መደረግ አልነበረበትም፡፡

ፍርድ ቤቱ ራሱም ከሦስት አንዱን ዕርምጃ መውሰድ ነበረበት፡፡ የመጀመርያው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለፍርድ ቤት የተናገሩት ስህተት መሆኑን በማሳየት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ተጠያቂ ማድረግና ሕዝቡ በፍርድ ቤቱ ላይ ያጣውን አመኔታ እንዲመልስ ማድረግ ነበረበት፡፡ ፍርድ ቤቱ ይህንን አላደረገም፡፡ ይህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለፍርድ ቤቱ የተናገሩትን እውነትነት የሚደግፍ ነው፡፡ ሁለተኛው የፍርድ ቤቱ ዕርምጃ ፈጥኖ የፍርድ ቤት ማሻሻያ ፕሮግራም መተግበር ነበረበት፡፡ ፍርድ ቤት አዲስ የፍርድ ቤት ማሻሻያ ፕሮግራም መጀመር ቀርቶ፣ አስቀድሞ የተጀመረው የማሻሻያ ፕሮግራምም ቀስ እያለ እንዲረሳ አድርጓል፡፡ የፍርድ ቤቱ ኃላፊዎችና ዳኞች በፍርድ ቤቱ ላይ የተነሳውን የመረረ ትችት ተከትሎ፣ ከላይ የተጠቀሱትን ሁለት ዕርምጃዎች መውሰድ ካልቻሉ/ካልፈለጉ ፍርድ ቤቱን መልቀቅ ነበረባቸው፡፡ ሆኖም ፍርድ ቤቱን የለቀቀ የፍርድ ቤት ኃላፊም ሆነ ዳኛ ስለመኖሩ የተሰማ ነገር የለም፡፡ ለምን ቢባል ግምቱ ከባድ አይሆንም፡፡ ፍርድ ቤቱ የተነገረለት ባህሪውና ተግባሩ ተመችቶታል ማለት ነው፡፡ እንዲያውም ይህንን ባህሪውን የሚያጠናክር ሥራዎችን በመሥራት ላይ መሆኑን ከዚህ በታች ለመመልከት ይቻላል፡፡

ፍርድ ቤት ፍትሕን በገንዘብ ይቸበችብ ነበር ተብሎ፣ ፍርድ ቤት ከገንዘብና ከደም የተፋታ ተቋም አይደለም ተብሎ ተነግሮበት የትኛውንም ዕርምጀ ሳይወስድ በዝምታ በሥራው መቀጠሉ፣ ፍርድ ቤቱን የሞራል ተቀባይነት የሌለው እንዲሆን ያደርገዋል፣ አድርጎታልም፡፡ የሞራል ተቀባይነት ለአንድ ፍርድ ቤት ከፍተኛ አቅሙ ነው፡፡ የሞራል ተቀባይነት ያለው ፍርድ ቤት የሰጠውን ፍርድና ትዕዛዝ ዜጎች በሙሉ እምነት ይቀበላሉ፣ በቀላሉ ይፈጽማሉ፡፡ የሞራል ተቀባይነት የሌለው ፍርድ ቤት በፖሊሲ ጋጋታ ብቻ ውጤታማ ፍትሕ ለማስፈን እንደማይችል በበርካታ አገሮች በጥናት ተረጋግጧል፡፡

በሕዝብ ፊት ተቀባይነት ያለው ፍርድ ቤት መገንባት የሚቻለው ተጠያቂነትን (Judicial Accountability) ያካተተ የዳኝነት ሥራ መርህ (የዳኞች ሥነ ምግባር መርህ) ሲዘረጋና ሲተገበር ብቻ ስለመሆኑ፣ በዚህ ረገድ ከተደረጉ ጥናቶችና የፍርድ ቤት ማሻሻያ ፕሮግራሞች መረዳት ተችሏል፡፡ በኢትዮጵያ ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ የተገኘውን አንፃራዊ ነፃነት ተከትሎ የኢትዮጵያ ፍርድ ቤት ራሱ ፍርድ ቤቱ ለዜጎች ነፃነት የሚሰጥ፣ ተጠያቂነት ያለበት፣ ሕዝብ አመኔታ የሚጥልበት ፍርድ ቤት እንዲሆን ማድረግ የነበረበት ቢሆንም ፍርድ ቤቱ ራሱን የማይነካ፣ የማይወቀስና የማይከሰስ ከማናቸውም ተጠያቂነት ነፃ የወጣ ተቋም እንዲሆን ለማድረግ ተንቀሳቅሷል ለማለት ይቻላል፡፡ ፍርድ ቤት ዕድል ቢሰጠው ጥሩ የአፈና ተቋም የመሆን ፍላጎት ይታይበታል፡፡

ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ ሕዝቡ ያገኘውን ነፃነት ተጠቅሞ በፍርድ ቤቱ ተጠያቂነት ላይ ጥያቄ ማንሳቱ የማይቀር ይሆናል የሚለውን ታሳቢ በማድረግ ይመስላል በ2011 ዓ.ም.፣ “የዳኞች የሥነ ምግባር ደንብ አተረጓጎም መርህ” የሚል ጽሑፍ ተዘጋጅቶ ለፌዴራል ዳኞች ሥልጠና ተሰጥቷቸዋል፡፡ ሥልጠናውን ተከትሎ ጽሑፉ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት “ዳኝነት ቅጽ አንድ ቁጥር አንድ” ብሎ በሚጠራው መጽሔት ላይ ታትሞ እንዲወጣ ተደርጓል፡፡ ጽሑፉ የዳኞች ሥነ ምግባር መርሆች የተባሉትን ነፃነት፣ ገለልተኝነት፣ ታማኝነት፣ የላቀ ሰብዕና፣ ብቃት፣ እኩልነትና ትጋት በማለት የዘረዘረ ቢሆንም የጽሑፉና ሥልጠናው ትኩረት በእነዚህ መርሆች ላይ አይመስልም፡፡ ዋና ዓላማው ወይም ዋናው ትኩረቱ ጽሑፉንና ሥልጠናውን ምክንያት/ሰበብ በማድረግ፣ የዳኞች ሥነ ምግባር ደንብ ሲዘጋጅና ሲተረጎም በዳኛው ላይ ተጠያቂነት የሚያስከትል አሠራር እንዲዘረጋ ከወዲሁ ተፅዕኖ መፍጠር ይመስላል፡፡ የዳኞች የሥነ ምግባር መርሆች የተባሉት እሴቶች አስቀድሞ በፌዴራል የፍትሕ አካላት ባለሙያዎች ሥልጠና ማዕከል እየተዘጋጀ ሥልጠናው ለዳኞች ሲሰጥ የቆየ በመሆኑ፣ ጽሑፉ የተዘጋጀው ዳኞችን በዚህ ረገድ ለማሠልጠን ነው የሚለው ምክንያታዊ አይሆንም፡፡ በጽሑፉ ውስጥ “የዳኝነት ተጠያቂነት” እንደ አንድ የዳኞች የሥነ ምግባር መርህ ሆኖ ሳይካተት መቅረቱ፣ ከዋናው ጽሑፍ በፊት የደንቡ አተገባበር ላይ ትኩረት ያደረጉ አጫጭር ማስታወሻዎች ሰፍረው መገኘታቸው የሥልጠናው ትኩረት ሊመጣ የታሰበውን የፍርድ ቤት ተጠያቂነት ማዳከም እንደነበር ያስገነዝባል፡፡

የፌዴራል ዳኞች ሠለጠኑበት የተባለውን ጽሑፍ ተከትሎ የፌዴራል ዳኞች የሥነ ምግባርና የዲሲፕሊን ክስ ሥነ ሥርዓት ደንብ ቁጥር 1/2013 ወጥቷል፡፡ ደንቡ ዳኞች አስቀድሞ ሠለጠኑበት የተባለው ጽሑፍ ትክክለኛ ቅጅ (Correct Copy) ነው ማለት ይቻላል፡፡ እንደ ደንብ ቁጥር 1/2013 ይዘት ከሆነ በኢትዮጵያ ውስጥ ዳኛን ተጠያቂ ማድረግ የሚችለው በመርፌ ቀዳዳ ማለፍ የሚችል ዕድለኛና የተለየ ሰው መሆን ይኖርበታል፡፡ በአጭሩ ደንቡ ይቻል የነበረን ነገር የማይቻል (Make the Possible Impossible) ያደረገ ነው ማለት ይቀላል፡፡

የቀደሙ የፍርድ ቤት ኃላፊዎች በነበሩበት ጊዜ በተተገበረው የፍርድ ቤት ማሻሻያ ፕሮግራም የዳኝነት ተጠያቂነትና ግልጽነት የዳኝነት ሥራ መርሆች ሆነው ለዳኞች ሥልጠና ሲሰጥ የቆየ ከመሆኑም በላይ፣ የፍርድ ቤት መሠረታዊ መርሆች (Core Values of Courts) ተብለው በፍርድ ቤቱ ግድግዳ እንዲለጠፉ፣ የፍርድ ቤቱ ተገልጋይም እንዲመለከታቸው ተደርገው ነበር፡፡ ሆኖም አሁን ፍርድ ቤቱ ራሱን ከማናቸውም ተጠያቂነት ነፃ ለማድረግ በጀመረው እንቅስቃሴ ተጠያቂነት (Accountability) በሚለው ጽሑፍ ላይ “ታማኝነት (Integrity)” የሚል ጽሑፍ ደርቦበት እንዲነበብ አድርጓል፡፡

ፍርድ ቤቱ ራሱን ከማናቸውም ተጠያቂነት ነፃ ለማድረግ በያዘው ጥረት በመግፋት፣ ዳኞች በሥራቸው በሚያደርሱት ጥፋት ከፍትሐ ብሔር ተጠያቂነት ነፃ የሚያደርግ ሕግ/አዋጅ አፅድቋል (አዋጅ ቁጥር 1233/2013 አንቀጽ 34/1)፡፡ በዚህ ሕግ መሠረት አቶ አሰፋ የተባሉ ከሳሽ በፍርድ ቤት ላቀረቡት ክስ ማስፈጸሚያ በባንክ የሚገኝ የተከሳሹን የአቶ ዓለሙን ገንዘብ 15 ሚሊዮን ብር አሳግደው ነበር እንበል፡፡ አቶ ዓለሙ በባንክ ከታገደው ገንዘብ ውጪ ሌላ ገንዘብ የላቸውም እንበል፡፡ ዳኛውና አቶ ዓለሙ ባደረጉት ስምምነት የታገደው የአቶ ዓለሙ የባንክ ገንዘብ እንዲለቀቅ ዳኛው ትዕዛዝ ሰጡ እንበል፡፡ አቶ አሰፋም የ15 ሚሊዮን ብር ፍርድ ተፈረደላቸው እንበል፡፡ ዳኛው የሰጡትን የዕግድ መነሳት ተከትሎ አቶ ዓለሙ ገንዘቡን ከባንክ ሙጥጥ አድርገው አውጥተው ደብዛውን አጠፉት እንበል፡፡ አቶ አሰፋ ባዶ ፍርድ ብቻ ታቅፈው ቀሩ ማለት ነው፡፡ እንግዲህ አዋጁ አቶ አሰፋን ባዶ ፍርድ ታቅፈው እንዲቀሩ ያደረገውን ዳኛ ከፍትሐ ብሔር ተጠያቂነት ነፃ አድርጎታል፡፡

ዳኛ ከመዝገብ ይነሳልኝ በማለት ቅሬታ በሚያነሱ ተከራካሪዎች ላይ ይግባኝ የሌለበትና እስከ  7,000 ብር ቅጣት የሚጥል ሕግ/አዋጅ ፍርድ ቤቱ አፅድቋል (አዋጅ ቁጥር 1234/2013 አንቀጽ 35)፡፡ ቅጣቱ የሚወሰነው ቅሬታ በቀረበበት ጓደኛ ዳኛ (Colleague Judge) ሲሆን፣ የቅጣቱ መልዕክት ‹‹በማናቸውም ዳኛ ላይ ተመሳሳይ ቅሬታ ቢቀርብ ውጤቱ ይኼው ነው፣ ዳኛውን አትንኩት፣ ዳኞችን አትንኩን፤›› የሚል ነው፡፡ በእጅጉ የሚገርመው ተከራካሪው ይግባኝ የሌለው፣ ምክንያት የሌለው፣ የገንዘብ ቅጣት መቀጣቱ ሳያንስ የቅጣቱ ገንዘብ ካልተከፈለ መዝገቡ አይታይም ተብሎ ይዘጋል፡፡ በተጨባጭ ተዘግቷል፡፡ የቅጣቱን ገንዘብ በስድስት ወራት ውስጥ እየቀናነስኩ ልክፈል የሚል አቤቱታ ቀርቦ ፍርድ ቤቱ ስድስት ወራት የሚጠብቅበት ትዕግሥት የለውም ተብሎ መዝገብ ተዘግቶ እንዲቀር ተደርጓል፡፡ ገንዘብ የተቀጣው ከሳሽ ከሆነና የቅጣቱን ገንዘብ መክፈል የሚችልበት አቅም ከሌለው ክስ ያቀረበበት መዝገብ እስከ መጨረሻው ይዘጋል፡፡ ይህም ከኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 37 ጋር በእጅጉ የሚጋጭ ውጤት አስከትሏል፡፡

ዳኛ በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጉ አንቀጽ 480 በተሰጠው ፍርድ ቤትን የማስከበር ሥልጣን (Contempt/Disciplinary Power) ተጠቅሞ ተከራካሪውን በክርክር ጊዜ እጅህን አወራጨህ በማለትና ይህንን በትዕዛዙ ላይ በማስፈር ችሎት ለክርክር የቀረበን ተከራካሪ 10,000 ብር ቅጣት ቀጥቷል፡፡ ተከራካሪውን በክርክር ጊዜ የተፈጥሮ አካልህ ተንቀሳቀሰ ብሎ 10,000.00 ብር የሚቀጣ ፍርድ ቤት በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ካልሆነ በመላው ዓለም ይገኛል ተብሎ አይገመትም፡፡ ፍርድ ቤት ቀርበው የማያውቁ፣ የተደወለ ስልክ እንዴት መዝጋት እንደሚቻል የማያውቁ እናት በችሎት ስልክ አስጮሁ ተብለው ነፍሳቸው ከሥጋቸው እስኪነጠል በዳኛ የተሳቀቁ ከመሆኑም በላይ፣ ፖሊስ አስሮ እንዲያቆያቸው ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡ አሁን ያለን ፍርድ ቤት እናትን እንኳን የማያከብር፣ እናትን ያህል ሰው አንቺ ብሎ የሚያንጠለጥል ነው፡፡ በዚህ ሁሉ የፍርድ ቤቱ ባህሪ ሕዝቡ ፍርድ ቤት ሲቀርብ መናገር ቀርቶ ለመተንፈስ እየተቸገረ ይገኛል፡፡ ፍርድ ቤቱ ተገልጋዩን እያስጨነቀው ነው፡፡

የፌዴራል ፍርድ ቤቶች በግልጽ ችሎት እንዲያስችሉ የኢትዮጵያ ሕዝብ አስፈላጊውን በጀት የመደበና ፍርድ ቤቶችም በግልጽ ችሎት ለማስቻል የሚያስፈልጉ የሥራ ክፍሎች የተመቻቹላቸው ቢሆንም፣ ይህንን በተመለከተም መመርያ ቁጥር 008/2013 የወጣ ቢሆንም ዳኞች አሁንም ድረስ ጉዳዮችን የሚያዩት በቂ ብርሃንና አየር በሌላቸው ዝግ ቢሮዎች ውስጥ ነው፡፡ በዚህ ረገድ እጅግ በከፍተኛ ሁኔታ የሚወቀሰው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የፍትሐ ብሔር የሥራ ክፍል ነው፡፡ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የፍትሐ ብሔር የሥራ ክፍል በቂ ግልጽ ችሎቶች የተሟሉለት ቢሆንም፣ ሁሉም ዳኞች በሚባል ደረጃ ጉዳይ የሚያዩት በዝግ ቢሮዎች ሲሆን በቢሮ ከተከራካሪዎች ውጪ ሌላ ሰው ሲገኝ በሰውየው ላይ ምን ፈለጉ የሚል ምርመራ ይጣራበታል፡፡ ይህ ሁሉ የሚደረገው ከተጠያቂነት ለመሸሽ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ አሁን ምንም ዓይነት ተጠያቂነት የሌለበት የዳኝነት ሥርዓት የተዘረጋ ስለመሆኑ ስለታመነበት፣ የሚሰጠው ፍርድ የፍሬ ነገር ምዘናና የሕግ ትንተና የያዘ ሳይሆን የዳኛው የፍላጎት መግለጫ (A Declaration of a Will of a Judge) ሆኗል፡፡

የፌዴራል ፍርድ ቤቶችን ውስጣዊ ተጠያቂነት (In-house or Endogenous Accountability) ያረጋግጣሉ የተባሉ የፍርድ ምርመራ (ኢንስፔክሽን) እና የሕግ ጥናትና ምርምር የሥራ ክፍሎች ቢኖሩም፣ ሁለቱም የሥራ ክፍሎች በሥልታዊ መንገድ ኃላፊነታቸውን እንዳይወጡ ተደርገው ይታያሉ፡፡ በጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚገኘው የፍርድ ምርመራ ክፍል ልምዱና ዕውቀቱ ባለው ሰው እንዲሠራ ያልተደረገ ከመሆኑም በላይ፣ ምቹ የሥራ ክፍል ተሰጥቶት ዓይታይም፡፡ የፍርድ ምርመራ ክፍሉ በሥራው ምክንያት የደረሰበትን የፍርድ ጉድለት ለቅሬታ አቅራቢው በጽሑፍ እንዳይሰጥ ተከልክሏል፡፡ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሕግ ጥናትና ምርምር የተባለው የሥራ ክፍል ደግሞ ከፍርድ ቤቱ ዋና የሥራ ቦታ ርቆ በኪራይ ሌላ ቦታ እንዲቀመጥ የተደረገ ከመሆኑም በላይ፣ ጥናትና ምርምርን ለማድረግ በሚያስችል መንገድ እንዳልተደራጀ የሚሠራበት ቢሮ ዝርክርክነት ይናገራል፡፡ ይህ የሥራ ክፍል በአገር ሀብት የሚተዳደር ቢሆንም፣ በዚህ ክፍል የተደረገ ጥናትና ምርምር የፍርድ ቤቱን ችግር ፈታ ሲባል ተሰምቶ አይታወቅም፡፡

በፍርድ ቤቶች ውስጣዊ ተጠያቂነትን ያሰፍናል ተብሎ ሕግ አመኔታ የጣለባቸው የይግባኝና የሰበር አጣሪ የፍርድ ቤት ክፍሎች የመረረው የሥነ ምግባር ችግር የሚታይባቸው ናቸው፡፡ ለይግባኝ የቀረበ ወይም ለሰበር የቀረበ ጉዳይ በሥር ፍርድ ቤት ስህተት አለበት ተብሎ ለምርመራ ያስቀርባል ከተባለ ጉዳዩን ገነትን (Heaven) እንደወረሰ ያስቆጥረዋል፡፡ በኔትወርኩ ውስጥ ለታቀፈው ወይም በደሙ ወይም በገንዘቡ ለመጣው ደግሞ ፍርድ ቤቱ 24 ሰዓት ክፍት ነው፡፡ በአጭሩ የኢትዮጵያ ፍትሕ ሞቶ የተቀበረው በይግባኝና በሰበር ፍርድ ቤቶች አማካይነት ነው፡፡ እነዚህ ፍርድ ቤቶች በመሠረታዊነት የተቋቋሙት የፍርድ ቤትን ውስጣዊ ተጠያቂነት ለማረጋገጥ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቶቹ ዋና የፍትሕ መግደያ ተቋማት ሆነው ይገኛሉ፡፡

ፍርድ ቤትና ዳኞች ለሚያከናውኑት ዳኝነታዊና አስተዳደራዊ ሥራ ለመንግሥት አካላት (ሕግ አውጪና አስፈጻሚ) ለሕዝብ፣ ለሚዲያና ለሲቪክ ማኅበራት ወይም ከእነዚህ አካላት ለተውጣጣ አንድ አካል ተጠያቂነት ያለባቸው ስለመሆኑ በሌሎች አገሮችም ሆነ በእኛ አገር የተዘጋጁ ሰነዶች ያሳያሉ፡፡ በዚህ ረገድ የዳኞችን ውጫዊ ተጠያቂነት (Exogenous Accountability) ያረጋግጣል የተባለው የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ሁለት ሦስተኛ አባላቱ ራሳቸው ዳኞች በመሆናቸው፣ የፍርድ ቤቶችን ውጫዊ ተጠያቂነት የሚያረጋግጥ ተቋም አለ ለማለት አይቻልም፡፡ ለዚህ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በየጊዜው የሚተቹትን ፍርድ ቤት ተጠያቂ ለማድረግ ያልቻሉት፡፡

የኢትዮጵያ ፍርድ ቤት ራሱን ከውጫዊ ተጠያቂነት የሚከላከለው የዳኝነት ነፃነት መርህን በማንሳትና ተጠያቂነት የሌለው ፍርድ ቤት ተጠቃሚ የሆኑ ፖለቲከኞችን በመጠቀም ነው፡፡ የዳኝነት ነፃነት ፍርድ ቤትና ዳኛ በሠራው ጥፋት ወይም ሳይሠራ በቀረው ኃላፊነቱ እንዳይጠየቅ ምክንያት ሊሆን አይችልም፡፡ የዳኝነት ነፃነት ዋናው ዓላማ ፍርድ ቤትም ሆነ ዳኛ ሥራውን ሲሠራ የውጭ ኃይሎች ማለትም ሕግ አውጪው፣ አስፈጻሚው ወይም ሌላ ማናቸውም ኃይል በፍርድ ቤቱ የመወሰን ነፃነት ላይ ጣልቃ እንዳይገባ ከለላ መስጠት ነው፡፡ ፍርድ ቤትና ዳኛ በተሰጠው የዳኝነት ነፃነት ተጠቅሞ በሠራው ጥፋት ወይም ሳይፈጽም በቀረው ኃላፊነቱ መጠየቁ ጭራሽ ከዳኝነት ነፃነት ጋር የሚገናኝ ነገር የለውም፡፡ በዓለም ላይ ከዘጠኝ ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናትን ጨምሮ፣ በሠራው ስህተት የማይጠየቀው የኢትዮጵያ ፍርድ ቤትና ዳኞች ብቻ ናቸው፡፡ ዛሬ አንድ ከዘጠኝ ዓመት በታች የሆነ ሕንፃን እንኳን ለቤተሰቡ አንፃራዊ ተጠያቂነት አለበት፡፡ ሕፃናት ለሚሠሩት ጥፋት ባያፍሩ እንኳን ይፈራሉ፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ያላት ፍርድ ቤት እንደ ሕፃን የማይፈራ እንደ አዋቂ የማያፍር ሆኗል፡፡

ኢትዮጵያ ዛሬ ያሏት ፖለቲከኞችና ባለሥልጣናት ተጠያቂነት የሌለው የዳኝነት ሥርዓትን በእጅጉ ይሻሉ፡፡ ለዚህ ፍላጎታቸው ማስፈጸሚያም ፍርድ ቤት ማንም ጣልቃ የማይገባበት በሕገ መንግሥቱ ነፃ ሆኖ የተቋቋመ ተቋም ነው እያሉ ፍርድ ቤቱን ከየትኛውም ተጠያቂነት ይከላከሉለታል፡፡ መከላከያቸው ወዲህ ነው፡፡ ፖለቲከኞች ወይም ባለሥልጣናት ተጠያቂነት ያለበት ፍርድ ቤት በኢትዮጵያ ምድር ከተቋቋመ፣ በሠራሁት ጥፋት ነገ ሰንሰለት ያጠልቅልኛል በሚል ፍራቻ አላቸው፡፡ የዛሬው ፖለቲከኛና ባለሥልጣን በሠራው ስህተት ነገ ከተጠያቂነት የሚያመልጠው፣ ተጠያቂነት የሌለበት ፍርድ ቤት ሲኖር ብቻ እንደሆነ ያምናል፡፡ እናም ተጠያቂነት የሌለበት ፍርድ ቤት እንዲኖር ይተጋል፡፡

በዚያም ተባለ በዚህ ለፍርድ ቤት ነፃነት ሲባል የፍርድ ቤትንና የዳኞችን ተጠያቂነት ከተውነው ወይ አገር ይፈርሳል፣ ወይ ፍርድ ቤቱ ራሱ ይፈርሳል፡፡ የመንግሥት የሥልጣን በሕግ አውጪው፣ በአስፈጻሚውና በፍርድ ቤት መካከል የተከፋፈለው ተጠያቂነትን ለማምጣት ብቻ ነው፡፡ ፍርድ ቤትንና በውስጡ የሚሠሩ ዳኞችን በጥፋታቸው ተጠያቂ አለማድረግ መሠረታዊውን የሥልጣን ክፍፍል ሕገ መንግሥታዊ መርህ ይጥሳል፡፡ በመንግሥት የሥልጣን ክፍፍል መርህ የትኛውም የመንግሥት አካል ቁጥጥር የማይደረግበት ሥልጣን ፍፁም ሊሰጠው አይገባም፡፡

ሥልጣን ሰውን ያባልጋል፣ በተለይም ፍፁም ሥልጣን (Absolute Power) ፍፁም ባለጌ (Corrupt Absolutly) ያደርጋል የሚል አባባል ያለ ሲሆን፣ ሞንትስክ የተባለ ፈላስፋ ‹‹ሥልጣን የተሰጠው ሰው ቁጥጥር እስካልተደረገበት ድረስ ሥልጣኑን ያላግባብ እንደሚጠቀምበት ጊዜ ፍንትው አድርጎ አሳይቶናል፤›› በማለት የተጠያቂነትን አስፈላጊነት ገልጾታል፡፡

በመሆኑም የኢትዮጵያን ፍርድ ቤትና በውስጡ የሚሠሩትን ዳኞች ተጠያቂ የማድረጉ ጉዳይ ፍፁም ጊዜ የማይሰጠው አጣዳፊ ጉዳይ ሆኖ ይታያል፡፡ ጉዳዩ በአገራዊ ምክክር ሒደቱም በአጀንዳነት ሊታይ ይገባል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመስቀል አደባባይ የመግቢያ ክፍያ ለምን?

ወጣቶች፣ ሕፃናትና አረጋውያን ሳይቀሩ መንፈሳቸውን የሚያድሱበት እንዲሁም ሐሳባቸውን በነፃነት...

በሕገ መንግሥቱ የተዋቀረው ‹‹የብሔር ፖለቲካ›› እና ‹‹ሥርዓቱ›› ያስከተለው መዘዝና መፍትሔው

(ክፍል አራት) በዓቢዩ ብርሌ (ጌራ) ባለፈው ጽሑፌ (በክፍል ሦስት) አሁን ያለው...

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብና የመንግሥት መሪ ምሥል

በበቀለ ሹሜ በ2015 ዓ.ም. መጋቢት ወር ውስጥ ይመስለኛል በ‹ሸገር ካፌ›...

ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ያደረገው አዋጅ የፍትሐዊነት ጥያቄ አስነሳ

በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ስምንት ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ በማድረግ ተቋማዊና...