Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትእንዴት ያለ የህሊና ዓውድ ኢትዮጵያን ይክሳል?

እንዴት ያለ የህሊና ዓውድ ኢትዮጵያን ይክሳል?

ቀን:

በበቀለ ሹሜ

ፊት የለኝም፣ ስም የለኝም፣ አካል የለኝም፡፡ መንፈስ ነኝ፣ ሥጋም ነኝ፡፡ ራሴ ገድዬ፣ ራሴው ሞቼ፣ ለራሴ ሞት ለቅሶ እየደረስኩ ነው፡፡ በራሴው ለቅሶ ላይ ለራሴ ሞት ሙሾ እያወረድኩ ነው፡፡ እኔ ማለት እናንተ ነኝ፡፡ በኢትዮጵያ ምድር አይገድሉ አገዳደል፣ አይጨክኑ ጭካኔ ያልተፈጸመበት፣ አይሞቱ ሞት ያልታየበት፣ እርር ያለ ለቅሶ ያልተለቀሰበት፣ ነጠላ ማዘቅዘቅ/ማሸረጥ፣ ሐዘን መቀመጥ ያልታየበት ሥፍራ የት ነው? እኔ ማለት እናንተ ነኝ ያልኩት ለዚህ ነው፡፡ ፊት የለኝም፣ ገላ የለኝም፣ ስም የለኝም ያልኩት፣ የእናንተ ገላና ፊት የእኔ ስለሆነ፣ እናንተን ስለሆንኩ፣ እናንተን በመሆኔም አገር ስለሆንኩ ነው፡፡ ራሴን ገድዬ፣ ራሴው ሞቼ፣ ለራሴ አልቃሽና ሙሾ አውራጅ ነኝ ስልም አገርነቴን አስተውዬ ነው፡፡ ስለሙሾና ነጠላ ስለማዘቅዘቅ/ስለማሸረጥ ሳወራ እንዲህ ያለው የሐዘን ወግ ሁላችሁ ዘንድ አለመኖሩ የሚሰማችሁ፣ ይህችንም እንከን ብላችሁ ለነቀፋ ያሞጠሞጣችሁ ትኖሩ ይሆናል፡፡ እኔ ወጉን የተጠቀምኩበት በቀላል ሥዕል መልዕክቴን እንዲገልጽልኝ ብዬ ብቻ ነው፡፡

 እያረገድኩ ሙሾ የምደረድረው ስም የለሽ ሰውዬ አሮጌ ሰውዬ ነኝ፡፡ ከሞትኩ የሰነበትኩ የፈረሰም አስከሬን ነኝ፡፡ ገና ሙቅ አስከሬንም ነኝ፡፡ ገና በማጣጣር ላይ ያለሁም ነኝ፡፡ ሙሾ የማወርደው የተረፋችሁኝ ልጆቼና የልጅ ልጆቼ እንዳሸረጣችሁ በለቅሶ ዳስ ውስጥ በዕዝን ንፍሮዬ እንድትፈጣጠሙና አዲስ ፍሬ፣ አዲስ የፖለቲካ ዘይቤ፣ አዲስ መተሳሰብ፣ አዲስ ግንኙነት እንድትፀንሱ፣ የዘላቂ ሰላምና የሚራመድ ኑሮ መፍለቂያ እንድትሆኑ፣ በዚህም የታደሰ ኅብረተሰብና የምትምዝገዝግ አገር ለመገንባት እንድትበቁ ነው፡፡ ሁላችንን በተመለከተ ኢትዮጵያ የምትሰጠን እንዲህ ያለ መልዕክት ይመስለኛል፡፡

  1. ይህንን መሳይ መልዕክት የምትሰጠንም ቁስለቷን፣ ጣሯን፣ ዕጦቷንና ጉጉቷን ዓውዳችን እንድናደርግ፣ ገዳይ፣ ሟችም፣ አልቃሽም በሆነ ገመና ውስጥ ሆነን ሁላችንን የመካስ ነገር ራስን የመካስ ያህል ሆኖ እንዲሰማን፣ ያንን ድባብ ተላብሰንም እንድንመክርና እንድናሰላስል ይመስለኛል፡፡ እንዲህ የምትለንም የዚህ ዓይነት ስሜት ውስጥ መሆን ደግ ነገር ላይ ለመድረስ ስለሚጠቅመን በማለት ብቻ አይደለም፣ ገመናችንም ስለሆነ እንጂ፡፡

ምሁራንና ‹‹ልሂቃን›› ነን የምትሉ፣ የፖለቲካ ቡድኖችና ፓርቲዎች፣ ጋዜጠኞች፣ ሚዲያዎች፣ የማኅበራዊ ሚዲያ ተዋንያን የሆናችሁ ሁሉ፣ ለአካባቢዬ፣ ለብሔሬ፣ ለኢትዮጵያዬ ታላቅ ነገር ሠርቻለሁ የሚል ኩራት ሊኖራችሁ ይችላል፡፡ ከዚያ ዓይነቱ ፎቅ ላይ ወርዳችሁ ምን ያህል አውጋዥ ነገር ተናግሬያለሁ? ጽፌያለሁ? ምን ያህል ሚዛን ያጣና እንደ ሾህ የሚዋጋ ነገር ረጭቻለሁ? ምን ያህል አዛምቻለሁ? መርዘኛ ነገሮች ሰዎችን ሲበክሉና ሲያቆስሉስ ስቆ በማለፍም ሆነ በዝምታ ምን ያህል ተመልካች ሆኛለሁ? ለምክክርስ ይህንን ያህል ጊዜ ማርፈድ ነበረብን?… እያልን ብንጠይቅ አገራችን ውስጥ በተደረጉ ክፉ ነገሮች ውስጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ብዛቱና ክብደቱ የተበላለጠ ድንጋይ እንዳዋጣን ማየት አይሳነንም፡፡ ይህንን የምናገረው በሙሉ ድፍረትና እርግጠኝነት (ራሴን ጨምሬ) ነው፡፡ ይህንን ድፍረቴን እንድታምኑልኝ ‹‹አንተ››፣ ‹‹አንቺ›› እያልኩ በዚህ ጊዜና በዚህ ቦታ እንዲህ፣ እንዲያ ባይ ምላስ ስንዘረጋ ስለመክረማችን መረጃ መደርደር አያስፈልገኝም፡፡ አንድ ትልቅ ጥያቄ ማንሳት ብቻ በቂዬ ነው፡፡

ከመጋቢት 2010 ዓ.ም. የለውጥ ጅምር ተነስቼ ብናገር ያ ወቅት ከእስር መፈታት፣ በስደት የነበሩ የፖለቲካ ሰዎችና ቡድኖች መግባት የታየበት፣ ሚዲያዎች የተበራከቱበትና ብዙ ምላሶች የተዘረጉበት ጊዜ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ቅራኔዎች፣ ንቁሪያዎችና ግጭቶች መገለጫ ሥፍራቸውን እያሰፉ ድግግሞሻቸውንና ክርረታቸውን እየጨመሩ ሲሄዱ ነበር የታዩት፡፡ እናም ፅንፍ የያዙ ዝንባሌዎች፣ ጥላቻዎችና በቀሎች እየፋፉ አውሬያዊ ጥርሳቸው እያገጠጠና እየተሳሳለ ብዙ ጨካኝ ግፎች እየተፈጸሙ፣ ዛሬ የደረስንበት የጦርነት ሁኔታ ላይ ለመድረስ በቅተናል፡፡ ፖለቲካችንና ምላሳችን ፍሬያማ ሥራ ለመሥራት ችሎ ቢሆን ኖሮ፣ ኅብረተሰባችን ይበልጥ እጅ ለእጅ እየተያያዘ፣ የፅንፍና የጥላቻ ኃይሎች እየሳሱና እየተከፋፈሉ ከእነሱ በኩል እየተፈረከሰ ወደ ለውጡ ሠፈር የሚደባለቀው እየጨመረ በሄደ ነበር፡፡

ሁለት ምሳሌዎችን ልጥቀስ፡፡ አንደኛ በተጓዝንበት ያልተረጋጋ የሞቅ ሞቅ ወቅት ጊዜ፣ ‹‹ገዝቶናል›› የሚል ጥቅል ቅሬታና ድፍርስ ስሜት ይነፍስበት ለነበረው የአማራ ሕዝብ ተቆርቋሪ ድምፅ ልሁን ላለ፣ አማራን በተመለከተ ያለውን ጥርጣሬና ሽክረት አቅልሎ ግንኙነትን ከማለስለስ ምን የሚብስ ነበር? ይህንን ተግባር የመወጣትስ ጉዳይ የአማራን ሕዝብ የከፋ ጉስቁልና ሁሉም እንዲገነዘብ ከመጣርና የሕዝቡን የውስጥ ስደት በልማት ለመቀነስ ከመታገል፣ አማራነት በብሽሸቅ ፖለቲካ፣ በአፄዎች ምሽግነት፣ በትናንት ናፋቂነት ጎራ ውስጥ እንዳይፈረጅ አማሮችን ከማንቃት፣ ከፍትሐዊ የፓርላማ ውክልና በቀር የፌዴራል የፖለቲካ ሹመቶችን ልሻማ ከማለት ይልቅ ሌሎች የአገር ልጆች ዕድሉን እንዲያገኙ አጋዥ ከመሆን ማነስ ነበረበት? የዘረፋ/የአድልኦ መሣሪያ ያልሆነ መንበረ ሥልጣን በኢትዮጵያ እንዲገነባ የበኩል ድርሻን ከማዋጣት ጋር፣ እነዚህ ላይ ያተኮረ ሥራ ተሠርቶ ቢሆን ኖሮ፣ የአንዳንድ አኞ ቡድኖችን አቋም መግራት ባይቻል እንኳ፣ በሰፊው ኅብረተሰባችን ውስጥ ስለአማራ ያለው አመለካከት ጉልህ መሻሻል አያሳይም ነበር? በተሻሻለ ዓውድ ውስጥስ በአማራ ከልታሞች ላይ ጥቃት የሚሰነዝሩ ቡድኖች ከማይናቅ ሕዝብ-ገብ ቅዋሜ ጋር የመፋጠጥ ዕድላቸው አይጨምርም ነበር? ሁለተኛ ሕወሓት እየተፈረካከሰ በመሄድ ፈንታ ከዚህ በፊት እያፈነገጡ ወጥተው የነበሩ ሰዎቹ አነሰም በዛ ተመልሰው እየተሰባሰቡ በሕወሓት ዙሪያ መቧደናቸው የፖለቲካችንን ቀሽማዳነት አይናገርም ወይ? ይህ ጥያቄ የአዎንታዊ ፖለቲካ አስተዋጽኦችንን ኮስማናነት መርምሮ ለመታዘብ ፍንጭ አይሰጥም? እነዚህን መሳይ ጥያቄዎች ማንሳታችን በሌላ ገጽ ምን ማለት ነው? ፖለቲካችን ውስጥ ንቁና ሕዝብ አሳታፊ አዎንታዊ ታጋይነት ሲያንኮራፋ፣ ብዙ መሀንነት፣ አበያነት፣ ነገር ሠሪነት፣ የዕይታ ድንክነት፣ ጀብደኛ ብሽሽቅ፣ ጭካኔና ጥላቻ ያለ ኃፍረት ሲሞላፈጡ ነበር እንደ ማለት ነው፡፡

በብልሹነቱ ለከት ላጣ ፖለቲካ የቅጣት ግብሩን የሚከፍሉት ደግሞ ብዙ ጊዜ ተራ ሰዎች ናቸው፡፡ በከፋ ጥላቻና በቀል እንዲሰክሩ ተደርገው ታይቶ የማይታወቅ የጭካኔ ግድያ ጭፍጨፋና ውድመት እንዲፈጽሙ የተደረጉቱም፣ በአበደ ጭካኔ እየተመሳቀሉ ኑሯቸውን ያጡትና የረገፉትም (የፖቲካችን መንታ አዝመራዎች) ተሬዎች ናቸው፡፡ ለእነዚህ የሁለት በኩል ተጠቂ ወገኖቻችን የደምና የሥቃይ ባለዕዳው ፖለቲካችን ነው፡፡ የትኛውም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ቡድንና ፖለቲከኛ ራሱን ንፁህ አድርጎ ወቃሽ ለመሆን አይበቃም፣ ይህንን ማስተዋል አንድ ነገር ነው፡፡

የትኛውም የጎለመሰ ሰውና ቡድን ከበዙ አማራጮች ውስጥ ፈልጎና ይበጀኝ ብሎ የሚመርጥና የሚወስን እንደ መሆኑ፣ ውሳኔውም በውስጡ ካለው ዕምቅ ዝንባሌ ጋር በአብዛኛው የሚሳሳብ እንደ መሆኑ፣ ሰብዕናው ውጪያዊ ሐሳብ/ስሜትና ድርጊት የሚያርፍበት ብቻ ሳይሆን፣ ውጫዊውን ከውስጣዊው ያገናኘ ውሳኔ እየወሰነና ድርጊት እየፈጸመ በሌላው ላይ ተፅዕኖ የሚያሳርፍም እንደ መሆኑ፣ ሆኖ ለሚገኘው ባህርይና ለሚፈጽመው ድርጊት ኃላፊ ከመሆን ድርሻ አያመልጥም፡፡ ‹‹ምን ላድርግ እንዲህ ለመሆን ያበቃችሁኝ እናንተ ናችሁ›› ብሎ በማላከክ ንፁህ መሆን አይቻለንም፡፡ ከዚህ አኳያ የትኞቹም ቡድኖች ለሠሯቸው ጥፋቶችና በደሎች የሚኖራቸው ተጠያቂነትም ከታሪክና ከህሊና ዳኝነት የማያልፍ ወይም ከሁለቱም አልፎ የሕግ ዳኝነትን የሚጨምር ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ ፅንፈኞች ብዙ ሰሚና ተከታይ እንዳይኖራቸው የሚያደርግ ፍሬያማ ሥራ በመሥራት ረገድ ፖለቲካችን ድክመት አሳይቷል፣ ጥፋት ሠርቷል፡፡ የሕወሓት የጥላቻና የማፋጀት ‹‹ፖለቲካ›› ቤኒሻንጉልና አገው/ቅማንት ድረስ ተሻገሮ እንዲያወናብድና ጭፍራ እንዲያበጅ ፖለቲከኛነታችን ፈቅዷል፡፡ ‹‹ፋሽስታዊነት›› ዝም ብሎ ለእነ እከሌ የመጨረሻውን ክፉ ስም ልስጥ ተብሎ (ሕወሓትና ሸኔ እንዳደረጉት) የሚለጠፍ አይደለም፡፡ የተወሰኑ ባህሪያት ያሉት (የተወሰነ ማኅበረሰብን ጠላቴ ብሎ መጥመድ/መጥላት፣ በበቀል መታወር፣ ከዚህም ቅንብር የሚመነጩ ጭፍጨፍዎችና ሌሎች ግፎችን ለመፈጸም መሾርን የሚመለከት) ነው፡፡ ይህንን መሥፈሪያ እነ ማን እንደሚያሟሉ አጥርቶ በማስገንዘብ ረገድ እንኳ ፖለቲካችን ከሰነፍም በላይ ገልቱ ነበር፡፡ እናም የታሪክና የህሊና ተጠያቂነት አለበት፡፡ ግፍ አዳዮቹ ደግሞ ከታሪክም ከህሊና ተጠያቂነትም በላይ የሕግ ተጠያቂነት ዕዳ አለባቸው፡፡ በዚህም ላይ ብዥታ ሊኖር አይገባም፡፡

2. ልጅ ሆኜ የማውቀው አንድ ጅል የንግድ ማስታወቂያ ነበር፡፡ ማስታወቂያው ‹‹የወንጂ ስኳር እንደ ዝሆን ያጠነክራል›› የሚልና በማሸጊያ ላስቲኩ ላይ በአንድ እጅ መዳፉ ዝሆንን መሸከም የቻለ ሥዕል የነበረው ነበር፡፡ ምሥሉንና ቃላቱን የያዘው የስኳር እሽግ በየሱቁና በየጉሊቱ እንደ ልብ ነበር፡፡ አምስት ሳንቲም የሚሽጥም ነበርና እንድንጠነክር ስኳር እንቅም ነበር፡፡ ስኳር ሰርቄ ስቅም እናቴ ይዛኝ ‹‹ለምንድነው ሰርቀህ የቃምከው?›› ብላ አለንጋ ስታነሳብኝ፣ ‹‹እንደ ዝሆን እንድጠነክር ብዬ ነው›› ማለቴ ትዝ ይለኛል፡፡ የሕወሓት ቆሞ ቀሮች ትናንትናም፣ ዛሬም የያዙት ንቃት ‹‹ወንጂ ስኳር እንደ ዝሆን ያጠነክራል›› ከሚል የማይሻል ነው፡፡ ትናንት በተማሪነት ዘመናቸው ያልገባቸውን የኢትዮጵያን ባለብዙ ስለት አገነባብ አገናዝቦ ያልተረዳን ‹‹ኢትዮጵያ የብሔረሰቦች እስር ቤት›› የሚል መፈክር ዕውቀት አድርገው ያዙ፡፡ ‹‹እስር ቤቲቱን›› ኢትዮጵያን በረጋግደው ብሔረሰቦችን ‹‹ነፃ›› ሊያወጡ ጫካ ትግል ውስጥ ገቡ፡፡ ከጫካ መልስ ያንኑ የቂም በቀል ግንዛቤ ያገዛዝ ሥልት አድርገው አፄ ሆኑ፡፡ አፄነታቸው አልፀና ካለ እኛን አይሆኑ አድርጎ ለመበተን የቂም በቀሉን ወጥመድ ዕውቀት አድርገን እንድንይዘው (መጣመድን፣ የቂም ቁስል መላስንና በቀል ማሰላሰሉን የአዕምሯችን አይረሴ ቆሌ አድርገን እንድንይዘው) አደረጉ፡፡ በስተኋላ ሕዝብ ለሕዝብ ተያይዘን ወጥመዱን ሰበርነው፡፡ የእነሱም የቂም በቀል ፖለቲካ፣ የዘመነ አረመኔነት አዘቅት ድረስ ወርዶ ተንኮታኮተ፡፡ የቂም በቀል ፖለቲካቸው እንደሞተባቸው ዛሬም መገንዘብ አልቻሉም፡፡ የሞተባቸው ፖለቲካ ብቻ አይደለም፣ ከ21ኛ ክፍለ ዘመንም ወጥተው የመካከለኛው ዘመን ውስጥ እንደገቡም አልተገለጸላቸውም፡፡

ከሥልጣን ሸርተት ያሉበትን ሰዓት ጠብቀው ኢትዮጵያን ለመበተን ሲሞክሩ አልበተን ያልናቸው መበተን በድህነትና በመታኮስ መማቀቂያችን መሆኑን፣ ማኅበራዊ ደመ ነፍሳችን (የህልውና ነፍሳችን) ነግሮን እንደሆነ አልገባቸውም፡፡ ዛሬም ‹‹ስኳር እንደ ዝሆን ያጠነክራል›› ብሎ የምር በማመን ደረጃ ‹‹ኢትዮጵያ የብሔረሰቦች ጉረኖ ነች›› የሚለውን የቂም በቀል ወጥመድ የተግባር መመርያ እንድናደርገው ይሻሉ፡፡ እነ ፃድቃን ከ21ኛ ክፍለ ዘመንም ከፖለቲካም ተነጥለው የዘመነ አረመኔነት አውሬ በሆኑበት ደረጃ፣ ‹‹ኢትዮጵያ የአገሮች አገር ነች›› ሲሉን ያንኑ ‹‹እስር ቤት›› የሚል (ኢትዮጵያን የማፍረስ) ግንዛቤን አትርሱ፣ ተግባራዊ አድርጉ ማለታቸው ነው፡፡ ስኳር እንደ ዝሆን ማጠንከሩን እመኑና ወጥመዱን እንደ ስኳር ላሱ ነው የሚሉን፡፡ አስደናቂው ምፀት ግን የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጅሉን ወጥመድ ሰባብሮ እንደረጋገጠው፣ መረዳት የተሳናቸውና አሁንም ‹‹ስኳር እንደ ዝሆን ያጠነክራል›› የሚል ጅልነትን እንደ ዕውቀትና እንደ ዕቅድ የያዙት እነሱ መሆናቸው ነው፡፡

በግብርና የረባ ለውጥ አምጥተን ረሃብን ገና ማሸነፍ ባልቻልንበት (ከዕርዳታ ወጥመድ  ባልወጣንበት) አሳረኛ ኑሮ ውስጥ እየዳከርን ነው ያለነው፡፡ ከዚህ የድህነት ወጥመድ መውጫው እጅ ለእጅ ተያይዞ በጋራ ክንድ መታገል መሆኑ ከመቼውም በላይ ገብቶን አንድ ላይ በተመምንበት ሰዓት፣ ‹‹የአገሮች አገር ናችሁ›› እያሉ ሊያቄሉን ይሞክራሉ፡፡ የቂም በቀል ግንዛቤያቸውና ሸራቸው ቄሎ ቄሎ ከነኮተ በኋላ አትዘንጉት ሊሉን ይለፋሉ፡፡ ስኳር ስሰርቅ ተይዤ ልገረፍ ስል ‹‹…እንደ ዝሆን እንድጠነክር ብዬ ነው›› በማለት እናቴን በብልጠት ልበልጥ እንደሞከርኩት፣ አሁንም የኢትዮጵያን ኅብረተሰብ ሊያሞኙ ይሞክራሉ፡፡ ከሁሉ የሚብሰው ደግሞ እነሱ ሲገዙት የኖሩት የትግራይ ሕዝብ ሲሶው በዕርዳታ የሚኖር ሆኖ ሳለ፣ ለራስህ የምትበቃ አገር ነህ ሲሉት ትንሽ እንኳ ዕፍረት ያልፈጠረባቸው መሆኑ!

‹‹ስኳር እንደ ዝሆን ያጠነክራል›› የሚል እንጭጭ ብልጠታቸው ከትግራይም ከኢትዮጵያም አልፎ የአፍሪካ አገሮችን ኅብረትና የአፍሪካዊነት ንቅናቄንም፣ ኃያላን አገሮችንም ሊያሞኝ የሚከጅል ነው፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ የአገሮች በረት ነችና በማፍረስ አግዙን›› ሲሉ የአፍሪካዊነት ንቅናቄ እየተጓዘ ካለበት መንገድ በተቃራኒ መሄዳቸው መሆኑ አልገባቸውም፡፡ ‹‹የአገሮች አገር›› ያሏት ኢትዮጵያ፣ ልዩ ልዩ ቋንቋዎችና ባህሎች ያሏቸው በታሪክ የተሳሰሩ ማኅበረሰቦች ያሏት አገር በመሆን ረገድ ከብዙ የአፍሪካ አገሮች ጋር  ተመሳሳይ መሆኗን ልብ ሳትሉ በእኛ የጅል ብልጠት ተሞኙልን ማለታቸው ነው፣ ወይም ሳያውቁት ብዙ ብሔረሰቦች ያሉባቸውን የአፍሪካ አገሮችን፣ እነ ህንድን ሁሉ ‹‹የአገሮች አገር›› አድርጋችሁ ቁጠሩና በትኑ ማለታቸው ነው፡፡ ኢትዮጵያን ‹‹የአገሮች አገር›› በማለት በውስጠ ታዋቂ በትኑልን ሲሉ አልገባቸውም እንጂ፣ የአገሮች አገር የመሆን ደረጃ ላይ የደረሱትን እነ ‹‹ዩናይትድ ኪንግደም››ን በትኑ እንደ ማለትም ነው፡፡ ኢትዮጵያን ‹‹የአገሮች አገር›› ሲሉ፣ ‹‹ዩናይትድ ኪንግደም›› ውስጥ ምን ያህል የምፀት ሳቅ እንደሚፈጠር አስቡት! በአግባቡ የለሙ ‹‹የአገሮች አገር›› መሆንና አለመሆን ምንና ምን እንደሆነ ያልተረዳችሁም ካላችሁ፣ የኢትዮጵያን ጎጣዊ-ማኅበረሰባዊ የልማት ደረጃ ከእነ ስኮትላንድና ከእነ ኢንግላንድ ጋር ማስተያየት ነው፡፡ እነሱ ይበጀን ብለው አብረው ሲኖሩ የእኛ ታጋይ ተብዬዎች ደግሞ ከእርጥባን እንኳ ሳንወጣ መበጣጠስ ይበጃችኋል ሲሉን ዝቅጠታቸውን አስቡት! ይህንን ዝቅጠት ‹‹ስኳር እንደ ዝሆን ያጠነክራል›› በሚል ማወዳደሪያ ብንገልጸው ማጋነን ይሆናል!?

‹‹ኢትዮጵያ የአገሮች አገር›› የሚል ይህ የቂም በቀል (የብተና) ንቃታቸውና ሥልታቸው፣ የበቀልን ቡድናዊ ጥማት ከማርካት ውጪ የትኞቹንም የኢትዮጵያ ማኅበረሰቦችና አካባቢዎች እሳት ሆኖ የሚበላ፣ ያሉበትን ቤት ከማቃጠል የማይሻል ነው፡፡ ሕወሓቶች ዛሬ የያዙትን ይህንን ቅቤ አይወጋ ዱልዱም ሸር፣ መላው የኢትዮጵያ ተሬ ሕዝብ ልብ እንዳለው ልሂቃን የምንባል ልናጤነው ይገባል፡፡ በደም የተጨማለቁት ቂም በቀለኞች የኢትዮጵያ መበተን ይጠቅማችኋል ‹‹እንደ ዝሆን ያጠነክራችኋል›› ባይ፣ ‹‹ብልጠታቸውን›› እንደ ያዙ ይሞቷታል እንጂ፣ ትልቅ አገርነታችንን፣ የማደግ የመበልፀግ ትልቅ አቅማችንን አንበታትንም፡፡ በእውነተኛ ፌዴራላዊነት በዴሞክራሲና በፍትሐዊ ልማት ይበልጥ እናጠብቀዋለን እናበለፅገዋለን፡፡ ይህ አስተሳሰብና ራዕይ የጋራ ትርታችን መሆን ይገባዋል፡፡

3. ሕወሓቶች በሥልጣን ዘመናቸውና አሁን እንዳየናቸው፣ ሁሉን ነገር በዓይነ ደረቅነትና በበቀል የሚወጡት ይመስላቸዋል፡፡ የፖለቲካቸው ሎሌ ለመሆን ያልፈቀደን በተለያየ ሥልት ያጠቁ እንደነበር (ሥራን፣ ንግድን፣ ቤትንና ብረትን በተለያየ ማመካኛ ከማሳጣት አንስቶ፣ ከአገር አስመርሮ እስከ ማባረር፣ አስሮ እስከ ማማቀቅና ደብዛ እስከ ማጥፋት ድረስ በቀል አያልቅበት እንደነበሩ)፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ላስረዳ ቢባል ለቀባሪው እንደ ማርዳት ይሆናል፡፡ ሕወሓቶች ያገጠጠ የበላይነት ገመናቸውን ጭምር ‹‹ፉርሽ ያደርጉ›› የነበረውም በዓይነ ደረቅ ሽምጠጣ እንደነበር ሁሉም ያውቃል፡፡ ‹‹የፖለቲካ እስረኛ የለም…፣ እከሌ ቤቱ የፈረሰው ሕገወጥ ግንባታ ስለነበረ ነው…፣ እከሌ ከሥራ የተባረረው በከባድ ጥፋት ነው…፣ ‹በፍትሕ ውስጥ መንግሥት ጣልቃ አይገባም›…፣ ‹የቡድንም የብሔርም የበላይነት የለም/የብሔሮች እኩልነት ተረጋግጧል›…›› በሚሉ ዓይነ ደረቅነት የሕወሓቶች ገዥነት ‹‹የተካነ›› (ምንተፍረት ያልፈጠረበት) እንደነበርም አገር ያውቃል፡፡ አሁንም እንደዚያው ናቸው፡፡ አምባገነንነቱና ፋሽስታዊ ምግጠቱ የእነሱ ባህርይ ሆኖ ሌላውን አምባገነንና ፋሽስት ይላሉ፡፡ በትምክህቱና በመሬት ተስፋፊነቱ ቀንደኞቹ እነሱ ሆነው ሌላው አደረገው እያሉ ኡኡ ይላሉ (በእነሱ ቤት ሌላውን ወንጃይ ሆኖ በሚጮህ አጎዛ፣ የራሳቸውን ወንጀለኛነት መሰወራቸው ነው! በዚያው፣ ‹‹ስኳር እንደ ዝሆን ያጠነክራል›› በሚል ብልጠት)፡፡

ኢትዮጵያን ለመበተን የፈለጉት ምን በድላቸው ነው? በ1967 ዓ.ም. ወደ በረሃ የገቡት ትግራይን ከኢትዮጵያ በዳይነት ለማላቀቅ ከነበረ በ1983 ዓ.ም. ዕድሉ ነበራቸው፡፡ ተልዕኳቸው ፍትሕ፣ እኩልነትና ግስጋሴ ሆኖ ቢሆን ኖሮም፣ የኢትዮጵያን ሕዝቦች አግባብተውና አንቀሳቅሰው ሊያስወድሳቸው የሚችል ስንት ሥራ መሥራት በቻሉ ነበር፡፡ ይኼ ቢቀር ከበፊቶቹ ገዥዎች በተሻለ ልማት እየተብለጨለጩ ‹‹ሲሾም ያልበላ…›› የተሰኘውን ብሂል በደንብ ተጠቅመውበታል፡፡ ሥልጣን ይዘው በቆዩባቸው 27 ዓመታት ውስጥ ትርፍ በሚያራቡ የንግድ ኩባንያዎች መረብና በማይንቀሳቀሱ ንብረቶች ደርጅተዋል፡፡ ጥሬ ገንዘብ አልበው ባህር ማዶ ድረስ አሻግረዋል፡፡ ሥልጣኑንና በርቀት መማሩን አንድ ላይ ማስኬድ ችለዋል፡፡ ልጆቻቸውን ባህር ማዶ አስተምረዋል፡፡ ዘመድ አዝማዳቸውን ውጭ ለመላክ ሥልጣናቸውን ተጠቅመውበታል፡፡ በኢትዮጵያ ስም የድርጅታዊ መረባቸውን ሰዎች ወፍራም ደመወዝ በሚያስገምጡ ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ ለመሰካካት ችለዋል፡፡ ከሥልጣን ሸርተት ሲሉ ይህንን ሁሉ ኢትዮጵያ ‹‹ልጠይቅ›› አላለችም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ያሉት ነገር ቢኖር፣ መጠፋፋት ሳይከተል ወደፊት ለመራመድ ሲባል በዕርቅና በይቅርታ አብራችሁ እየሠራችሁ፣ ኑሮን በሚያነሳ ልማት በዴሞክራሲና በፍትሕ ግንባታ ካሱን ነበር፡፡

በኩርፊያና በዕብሪት ማገንገኑ ጭራሽ በእነሱ ብሶ፣ ኢትዮጵያን ለመበተንና ትግራይን ለመነጠል ማሴርና ማድባት ውስጥ ገቡ፡፡ ማን በበደለ? በ27+3 ዓመታት የሥልጣን ዘመናቸው ኢትዮጵያ የትግራይን ሕዝብ አልበደለችም፡፡ የትግራይ ውስን ከተሞችን በሕንፃ እንዲያሸበርቁ ከማድረግ ባለፈ የሕዝብ ኑሮ ከምግብ ዋስትናና ከመጠጥ ውኃ መሠረታዊ ችግሮች ሳይላቀቅ የቀረው በእነሱ ገዥነት ጊዜ ነው፡፡ መቀሌ ውስጥ ከመሸጉ በኋላ የክልሉን በጀትና የሕዝብን ጉርስ እየተሻሙ የጦርነት መሰናዶ ሲደግሱና በኢትዮጵያ ውስጥ ቁርቁስ ሲያባዙ የቆዩት እነሱ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያን በመበታተንም ሆነ ትግራይን በመነጠል ለትግራይ ሕዝብ የሚያስገኙት ውጤት ከሰላምም ከልማትም መራቅ መሆኑ ቁልጭ ያለ ሀቅ ነው፡፡ ትግራይን ከመቁረጥ ዕቅድ ጎን ‹‹የአገው…››፣ ‹‹የቅማነት…›› እና ‹‹የአፋር…›› ምንትስ የሚሉ ቅጣይ እጆች ያበጁት በምዕራብም፣ በደቡብም በምሥራቅም በኩል ሰፊ ግዛት ለመቦጨቅ ነበር፡፡ የሚገርመው ግን ሊልፏቸው ባሰቧቸው አካባቢዎች ላይ ዘምተው አይደረግ ግፍ ፈጸሙ፡፡ ለዚህ ነው የሕወሓት ወፈፌዎች የበቀል ባሪያ ሆነው በቀልን ከማስፈጸም በቀር ኦናቸውን የቀሩ ናቸው (ትግራይንም ሆነ ሌላውን የሚፈይዱ አይደሉም) የምንለው፡፡

ኢትዮጵያን በመበተን ሊበቀሉ እንደሚሹ ሁሉ ለዚሁ ዓላማቸው ቢጠቅመን ብለው፣ የምሥራቅ አፍሪካ ሥልጣኔ አንድ ማዕከል የነበረውን የአክሱም ሥልጣኔ በዓይነ ደረቅ ስርቆት ትግራዊ ሥልጣኔ ሊያደርጉት ይሻሉ፡፡ ክፋቱ እንደ ዕቃ ታሪክን ሰርቆ ማጓጓዝ አይቻልም፣ ወይም የታሪኩ ቅርሶች ዛሬ የእኔ ማኅበረሰብ ውስጥ ስለተገኙ ታሪኩ የእኔ ማኅበረሰብ ብቻ ነበር ማለትም መርቻ አይሆንም፡፡ የግሪክ ሥልጣኔ የዛሬ ግሪካውያን የብቻ ቅርስ ነው፣ የሮማውያን ሥልጣኔ ባለቤቶችም የዛሬ ጣሊያኖች ነው ቢባል አስቂኝ ነው፡፡ የአክሱም ሥልጣኔን ይዘትና የተራክቦ ስፋት በደንብ አጥንቶ ለትውልድ ማስተማር ኃላፊነት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ጥንታዊው ሥልጣኔ ለስርቆት የማይመች ቅርሶች ትቷል፡፡ ከአክሱም ወደ ስንትና ስንት ቦታ ይዘመት እንደነበርና ከስንትና ስንት ሥፍራ ምርኮኛ የሆነም፣ ያልሆነም ሕዝብ ወደ አክሱም ይጎርፍ እንደነበር (አክሱም የብዝኃ-ሕዝብ መገማሸሪያ እንደነበረች) የሚናገሩት የድንጋይ ጽሑፎች ብቻቸውን በዚህ ጉደኛ ትርክት ስቀው አያባሩም፡፡ ሕወሓታዊ የሌባ ዓይነ ደረቆችን ለማሳመን መባዘን ግን ‹‹ስኳር እንደ ዝሆን ያጠነክራል፣ በአንድ መዳፍ ዝሆን ለመሸከም ያስችላል›› ብሎ ድርቅ ላለ ሰው ኧረ ተሳስተሃል ብሎ ለማስረዳት መልፋት ይሆናል፡፡ በጥላቻና በበቀል አይሠራ ግፍ እየሠሩ፣ በቡድን ከመድፈርና ከማረድ እስከ ጅምላ ጭፍጨፋ የሰፋ ግፍ እያስፈጸሙ (በበሉበት ምጣድ ላይና በጠረጴዛ ላይ መፀዳዳትን፣ ባደሩበትና በበሉበት ቤት ውስጥ ገድሎ መቅበርን ዕርካታና ኩራታቸው አድርገው) ሳሉ፣ ከሌላ የበለጠ ‹‹የሠለጠንን›› ቢሉ አሁንም የወንጂ ስኳርና የዝሆን ጥንካሬ ነገር መምጣቱ ነውና ከእነሱ ጋር ክርክር መግጠም አይጠበቅብንም፡፡ የሚጠበቅብን እነዚህ ናላ የለሽ ወንጀለኞች በትግራይ ማንነት ላይ ያደረሱትን በአረመኔያዊ ነውሮች መጉደፍና በባህልም በደምም ታሪካዊ ዘመዶቹ ላይ የደረሱትን ጉዳቶች ማከምና ማፅዳት ነው፡፡

አሮጌ ዘመን ውስጥ የዘቀጡት የሕወሓት ወንጀለኞች የትግራይን ሕዝብ እንደ ዓሳ በመረብ ይዘውታል፡፡ አያያዛቸው እንዳይሞትም እንዳያመልጥም የተጠመደበትን መረብ ውኃ ውስጥ የማቆየት መሳይ ነው፡፡ መረቡ ከጠርናፊ ሰንሰለት የተሠራ ብቻ አይደለም፡፡ ህሊናና ልቦናን እየወሰወሱ በጥላቻና በበቀል ከመመረዝም የተሠራ ነው፡፡ የጥላቻና የበቀል ውስወሳቸው በትግራይ ሰዎችና ወጣቶች ላይ ያደረሰው ጉዳት ከሰው ዳር እስከ ማውጣት የሰብዓዊ ርኅራኄና የምንተፍረት ውስጣዊ ፈትላቸውን እስከ መቀረጣጠፍ የከፋ ነው፡፡ አንድ ፍሬ ሕፃናት እናታቸውንና አያታቸውን እየደፈሩ መሳደብ እንዲቻላቸው አድርገዋል፡፡ የጎረመሱና የጎለመሱ ሰዎች በሕፃናት ልጆቻቸውና በትንንሽ እህቶቻቸው ዕንባ ላይ እየሳቁ የወሲብ ስሜት ለመወጣት ተችሏቸዋል፡፡ መረሸንና ማረድ ቆሎ እንደ መቁላት ቀሏቸዋል፡፡ የትግራይ ሕዝብ ክብሩን፣ ጨዋነቱን፣ ሃይማኖተኛቱንና ልጆቹን እስከዚህ ድረስ ነው የተነጠቀው፡፡

እጅግ አሳዛኙ ነገር ደግሞ፣ ለፍትሕና ለሰው ልጅ በመቆርቆር ግንባር ቀደም ነን እያሉ የሚመፃደቁት አሜሪካና ውስን ምዕራባዊ አገሮች (ተመድን ጨምሮ) የግፈኛው ቡድን ቀጥተኛና ኢቀጥተኛ አጃቢ በመሆን፣ የትግራይ ሕዝብ በዚህ ቡድን ሥር ለሚደርስበት ዕልቂትና አበሳ አጋዥ ሆነው መቆየታቸው ነው፡፡ በአማራና በአፋር ሕዝብ ላይ ቡድኑ ያደረሰውን ፈርጀ-ብዙ ግፍ እንዳልሰማና እንዳላየ ዝም ሲሉና ከሚዲያዎቻቸው ጋር ተጣምረው ለሕወሓት ወንጀለኞች የዓዞ ዕንባ አዳናቂ (ቃል አቀባይ) የመሆን ያህል ኃፍረት ያጣ ሚና ሲጫወቱም የትግራይን ሕዝብ ፍዳ ማገዛቸው ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ከመላ ኅብረተሰቡ ጋር ተያይዞ ወደ ዴሞክራሲና ልማት የሚያደረገውን ጉዞ መተናነቃቸውም ነው፡፡ ከሕወሓት ግፈኛ ጦረኞች ጋር ተደራደሩ ሲሉም በእነዚህ ግፈኞች ሥር የትግራይ ሕዝብ መቀርቀቡ ይቀጥል፣ የዚህ ቡድን ግፍ አምራች ጦረኝነት ለቀረው ኢትዮጵያም የተዳፈነ እሳት ሆኖ ይቆይ ማለታቸው ነው፡፡

ምዕራባውያኑ የሚሉትን ከግፈኛ ወንጀለኞች ጋር መደራደርን የሚደግፍ ሰው፣ ወይ ከዕባብ ዕንቁላል እርግብ ለማግኘት ያለመ ነው፣ ወይ የግፈኞቹ አጫፋሪ መሆኑን ማመኑ ነው፣ አለዚያም ሕወሓት በወንጀል ሳይጠየቅ ደም የማይጠግብ አገዛዙን በትግራይ ሕዝብ ላይ እንዲቀጥል መፍረዱ ነው፡፡ የለውጡ መንግሥትና የኢትዮጵያ ሕዝቦች እነ ፃድቃን ገብረ ትንሳዔና ደብረ ጽዮን ከሚመሩት ፀፀትም ኃፍረትም ከሌለው ወንጀለኛ ቡድን ጋር በሥልጣን ከመቆየት ጋር የተገናኘ ድርድር ለመቀመጥ ከፈቀዱም፣ የዚያ ሁሉ ግፍ ምንጭ የሆኑት አውራዎች ከሕግ ተጠያቂነት እንዲተርፉ መፍቀዳቸውና ሥልጣንን ከግፈኞች ጋር መሸነጋገያና መወዳጃ ማድረጋቸው ነው፡፡ ይህንን ማድረግ ማለት ደግሞ ከሕግ በታችና ከተጠያቂነት ሥር ሁሉን ያዋለ ዴሞክራሲ ለመገንባትና ፍትሕን ለማስፈን የተደረገውን መፍጨርጨር ሁሉ ወደ ገደል መስደድ ነው (በነገራችን ላይ ይህንን ማጤንና የኢትዮጵያን መንግሥት በዚህ የጥፋት ጉዞ መጠርጠር በጣም የተለያዩ ነገሮች ናቸው)፡፡

በአማራና በአፋር አካባቢዎች ውስጥ በሕወሓት ዘመቻ የተፈጸሙትን ወንጀሎች ከአንጀት እሰይ እስከ ማለትና ለዚህ ዓይነት የግፍ ሥራ የልጆቻቸውን መማገድ ከጀግንነት የሚቆጥሩ፡፡ ለሕወሓት ጦረኝነት አንገብርም ያሉ በሥውር መታደናቸውን ልክ የሚሉ የትግራይ ሰዎች የደረሰባቸው የመንፈስ ምንጣሮ ከፍተኛ ነው ማለት ነው፡፡ እንዲህ ያለ ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ጥቂት እንደማይሆኑም መገመት ይቻላል፡፡ ይህንን ያህል ደፍረን ከርቀት የምንናገረው በሕወሓታዊ መንገድ ውስጥ ሕዝብን ወደ ሰላምና ወደ ዴሞክራሲያዊ ነፃነትና ወደ ኑሮ ዕድገት የሚወስድ ፖለቲካ አለመኖሩ ዕውቅ ስለሆነ (ግፈኛው ቡድን የትግራይን ሕዝብ የያዘው በአጭበርባሪ ፕሮፓጋንዳ እየነዘነዘ፣ ከእሱ ትንፋሽ ውጪ ሌላ እንዳይሰማና እርስ በርሱ እንዳይመክር በነጭ ለባሻዊ መረብ ሰቅዞ መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ስለሆነ) ነው፡፡

እናም ለሕዝብ መገነዣ እየዋሉ ያሉትን ሥልቶችና ማጭበርበርያዎች በደንብ ለይቶ ውልቅልቃቸውን እያወጡ፣ ከሕወሓት ጋር የአዲስ ሕይወት (የሰላም፣ የነፃነትና የግስጋሴ ዕድል) እንደሌለ ለሕዝብ ማሳየት ያሻል፡፡ ማሳየት ትርጉም የሚኖረውም ሕዝብ ዘንድ ከማድረስና ሕዝብ መላወሻ መተንፈሻ ቀዳዳ ከማግኘቱ ጋር ሲገናኝ ነው፡፡ በዚህ ረገድ በሕወሓት አረመኔያዊ ጦረኞች ግፍ ያፈሩና ከግፉ የሸሹ አፈንጋጮችንና ተቃዋሚዎችን በአገራዊ ምክክሩ ማሳተፍና በምክክሩ የተገኘውን ፍሬ ለትግራይ ሕዝብ ማድረስ ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ ለትግራይ ሕዝብ ማድረስ ሲባል ወሬ ከማሰማት በላይ በሕዝብ ውስጥ አዲስ ተስፋ ማብራትና የጦረኞቹን ቀጣፊ ፕሮፓጋንዳ ማንኮታኮት ማለት ነው፡፡ እንዲህ ያለው ሥራ ከርቀት ሊጀመር ቢችልም የሕወሓትን የስቀዛ መዋቅርና የታጠቀ ጉልበት በማድቀቅ ሥራ ሊታገዝ ይገባል፡፡ በሌላ አነጋገር ለትግራይ ሕዝብ የመድረስ ተግባር የትግራዋይ ብቻ ያልሆነ ሁሉንም የለውጥ ፓርቲ/ምሁርና የመንግሥትን የተቀናጀ ሥራ የሚጠይቅ ነው፡፡ ይህ ተግባር የትግራይ ሕዝብ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ አንድ አካል ስለሆነ ኃላፊነት አለብን ከሚል ማዕዘን ብቻ የሚታይም አይደለም፡፡ ለውጣችን የትግራይን ሕዝብ እስካላካተተ ድረስ፣ አዛላቂ ፌዴራላዊ አገረ መንግሥት፣ አዛላቂ ሰላምና ልማት የመገንባት ጥረታችን አሸዋ ላይ መሠረት ከመጣል እጅግም ያልራቀ (እየባነኑ ከመኖር ያልተላቀቀ) ከመሆን አያመልጥም፡፡

4. አንዳንድ የዞረባቸው ሊያዞሩብን እንደሚሞክሩት አገራዊ ምክክሩ የኢትዮጵያን አገርነት እንዴት እናድርገው? አስተሳሰቦች ገጥመው ባሸነፈ ሐሳብ የኢትዮጵያ ዕጣ ይወሰን የሚል አይደለም፡፡ ያሸነፈው መስመር ከለየ ቆየ፡፡ ከውስጣችን የተነሱ የብተና ኃይሎች በውጭ ሽሪኮቻቸው ታጅበው እንበትናችሁ ሲሉን፣ ባለ በሌለን አቅም ሁሉ እየተነባበርን የተዋደቅነው ዓብይ አህመድ አንገቱን እንዳይቀላ ብለን ወይም ዓብይ አህመድና ብልፅግና ፓርቲ በፕሮፓጋንዳ እያቄሉም ሆነ በግዳጅ እያጋዙ ማግደውን አልነበረም፡፡ የብተና ጥቃት ሲመጣብን ሆ ብለን የተነሳነው፣ መበታትን ከሰላምም ከጥንካሬም ከዕድገትም አርቆ ወደ ሥርዓተ አልባነት እንደሚያንሸራትተን፣ (እናም ለመሬት ተቀራማቾችና ለጦረኞች መጫወቻነት እንደሚያጋልጠን) ከማንንም በላይ የህልውና ደመ ነፍሳችን ነግሮን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ነገር፣ ከዳር ዳር ተነስተን ህልውናችንን ለማትረፍና ለማስቀጠል በደምና በአጥንት ያካሄድነው ተጋድሎ ነው፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ አሸነፈች!››፣ ‹‹አንድነት ለድርድር የማይቀርብ መሆኑ ተረጋገጠ!›› ሲባልም፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ከሞላ ጎደል በመለስተኛ ጉዳዮች ሳይታመሱ አንድ ላይ በመትመም፣ በፌዴራላዊ አገርነት መቀጠል የሞት ሸረት ጉዳያቸው መሆኑን በአጥንትና በደማቸው ፈረሙ ማለት ነው፡፡ ሙሉ ሥዕል በሚሰጥ መልክ መናገር ካስፈለገም፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የትግራይ ልጆችን ጨምሮ (ሕወሓት ከአገታቸው የትግራይ ነዋሪዎች በስተቀር) ብሔር፣ ሃይማኖት፣ ፆታ ሳይለያያቸው የየአካባቢ ዘብ ከመሆን አንስቶ ወደ ውትድርና ወደ ዘመቻ በመፍሰስ፣ ያለ የሌላቸውን ለዘማች ስንቅ፣ ለተፈናቃይ ጉርስ፣ ለመልሶ ማቋቋምና ለመልሶ ግንባታ በማዋጣት፣ የአሜሪካንና የአባሪዎቿን ተፅዕኖና ጣልቃ ገብነት ሳይታክቱ በመቃወም ረገድ፣ ከውስጥ እስከ ውጭ ተያይዘው ያካሄዱት ባለ ብዙ ገጽ ተጋድሎ፣ የኢትዮጵያ መቀጠል፣ ህልውናችን፣ ደኅንነታችንና ግስጋሴያችን የሚል ምልዓታዊ ውሳኔ ሕዝብ የሰጡበት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ አንዳንድ ያልበሰሉ ፖለቲከኛ ነን ባዮች ግን  የኢትዮጵያ ሕዝቦች ከዳር ዳር ተፈንቅለው የተንቀሳቀሱበትን ትልቅ አገር ሆኖ የመቀጠል መልከ-ብዙ ተጋድሎ የተወሰኑ የፖለቲካ ቡድኖች መስመር ማሸነፍ አድርገው ያሳስቱታል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝቦች ትልቅ አገርነታችንን አናስነካም ያሉት የሆነ ፓርቲ አቋም ዛር ሆኖ ወርዶባቸው እንዳልሆነ ሁሉ፣ የፖለቲካ ቡድኖችም ከሞላ ጎደል አንድ ላይ የተባበሩት የአንደኛቸው ፓርቲ አቋም ስላሰገራቸው አይደለም፡፡ አስተባባሪው ነገር ኢትዮጵያን ከማዳን ጋር አንድ ሆኖ የመጣው ህልውናችንን የማትረፍ ተግባር ከምንም ነገር በላይ ተቀዳሚና አንገብጋቢ ሆኖ መምጣቱ ነው፡፡ ተግባሩና ወቅቱ ሌላ ሌላ ጉዳያችሁን አቆዩና አገራዊ ህልውናችሁ ላይ ተረባረቡ ብሎ ማዘዙ ነው እንጂ፣ ሁሉም ፓርቲዎች ውስጥ ያልተግባቡ፣ የሚያጎናትሉና ብስልና ጥሬ፣ ግልብና ገንታራ የሆኑ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ የተዋደቅንለት እንደ አገር የመቀጠል ጉዳይም ፌዴራላዊነትና ዴሞክራሲያዊነት በማሟላት ረገድ ብዙ ነገሮች ተነጋግሮ መግባባትና የመሠረት ግንባታ ገና ያለበት ነው፡፡ በፌዴራላዊት ኢትዮጵያ ማዕቀፍ ውስጥ ሊስተናገዱ የሚችሉ የፖለቲካ ፍላጎቶችን የማቀራረብና የማግባባት ሥራም አለብን፡፡ ይህ ሥራ መነጠልን ከሚከጅሉ ጋር ተቀራርቦ እስከ መምከር የሰፋ ነው፡፡ ከመበታተን የመትረፍ የህልውና ጉዳያችን በሕይወት መስዋዕትነት ከተገኘ ድል ባሻገር ብዙ ችግሮችን በምክክር ያቃለለ ድልም ይፈልጋል ማለት ነው፡፡ ድል መገኘት የሚችለው ለምክክር በአገር ደረጃ ጉባዔ የሚቀመጡት ሰዎች፣ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ በአጥለቅላቂ የተጋድሎ እንቅስቃሴና በመስዋዕትነት ካርድ ለኢትዮጵያ መቀጠል የሰጠውን የተጋድሎ ድምፅ እስካልዘነጉት/አክብሮት እስከሰጡትና ሁሉም ባለፍላጎቶች ለሚነሱ ብሶቶችና ጥያቄዎች ሁሉ በኢትዮጵያ ማዕቀፍ ውስጥ አግባብነት ያለው መፍትሔ ለመፈለግ ከአንጀት እስከጣሩ ድረስ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ