Friday, February 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

መንግሥት ከሸክም በላይ የሆነውን የዋጋ ንረት መላ ይበልልን!

ለዓመታት ሲንከባለል የመጣው የዋጋ ንረት ከልክ በላይ እየሆነ ነው፡፡ የሸማቾችን የመግዛት አቅም እየፈተነ ብቻ ሳይሆን በአቅም ሸምቶ መኖር በእጅጉ ከባድ ሆኗል፡፡ በሁሉም ረገድ እያደገ የመጣው የዋጋ ንረት አብዛኛው ሕዝብ የሚሸከመው አይደለም፡፡

በእርግጥ አገሪቷ ከነበሩባት ውስብስብ ችግሮች አንፃር የዋጋ ንረቱ ከዚህም በላይ ቢሆን ላይገርም ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ መንግሥትም የዋጋ ንረቱን ለመቆጣጠር በርካታ ዕርምጃዎችን ባይወስድ ኖሮ ከዚህም የከፋ የዋጋ ንረት ውስጥ ሊገባ እንደሚችል ይታመናል፡፡

 ነበር ግን የዋጋ ንረቱን ለመቆጣጠር የተደረጉ ሙከራዎች ችግሩን በተወሰነ ደረጃ እንዳይሰፋ ከማገዝ ባለፈ ዘላቂ መፍትሔ እየመጣ ያለመሆኑን ገበያው በደንብ እየነገረን ነው፡፡

በግብይት ውስጥ ያሉ ምርቶች በሙሉ ዋጋቸው በየጊዜው እየተሰቀለ ነው፡፡ በተለይ ሁሉንም ሸማች የሚመለከተው የምግብ ነክ ምርቶች ዋጋ አልቀመስ ብሏል፡፡ የዋጋ ንረቱ መጠን ከ40 በመቶ በላይ መዝለቁ የሚያሳየን ንረቱን ለመቆጣጠር የተደረጉ ጥረቶች በተወሰነ ደረጃ ጊዜያዊ መፍትሔ ሰጥተው ይሆናል እንጂ እየጋለበ ላለው የኑሮ ውድነት መፍትሔ የሚሆን ልጓም ያለመበጀቱን ነው፡፡

ንረቱን ለማረጋጋት ተብለው የተወሰዱ ዕርምጃዎች ጊዜያዊ መፍትሔ በሆኑበት ወቅት ረገብ ያለ የመሰለው የዋጋ ንረት በየጊዜው እየጨመረ መሄዱን ይፋዊ የሆኑ መረጃዎች ጭምር እያረጋገጡልን ነው፡፡ እኛም የየዕለቱን ገበያ ምስክር ማድረግ እንችላለን፡፡

እየከፋ ያለውን የኑሮ ውድነት ለመቀነስ ሌላው ቢቀር ከዚህ በላይ አድጎ የቀውስ ምንጭ እንዳይሆን አሁንም ብዙ መሠራት ያለበት መሆኑን ማስገንዘብ ጠቃሚ ነው፡፡ አገሪቱ አሁን ካሉባት በርካታ ችግሮች አንዱ ይኸው ከዋጋ ንረት ጋር ተያይዘው እየመጡ ያሉ ተግዳሮቶች ናቸውና መንግሥት ቅድሚያ ከሚሰጣቸው አጀንዳዎች መካከል አንዱ ሊያደርገው ይገባል የምንለው ችግሩ ውሎ አድሮ የማኅበራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ምንጭ ስለሆነ ነው፡፡

ለፖለቲካውም ቢሆን ፈተና ሊሆን እንደሚችል ማንም አይጠፋውምና ነገሩን እሳት በማጥፋት ብቻ መዝለቅ አይቻልም፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ አሁን የሚታየው የዋጋ ንረት መሠረታዊ ከሚባሉ ምርቶች መወደድም በላይ እየሆነ ስለመምጣቱ በግልጽ መታወቅ አለበት፡፡

በዋጋ ንረት ምክንያት ብዙ ሥራዎች እየተስተጓጎሉ ነው፡፡ ለምሳሌ የግንባታ ሥራዎች ላይ እየተፈጠረ ያለውን ጫና ልንጠቅስ እንችላለን፡፡ ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ በተፈጠረው ክፍተት አንዳንድ ፕሮጀክቶች ለጊዜው እዲታጠፉ ቢደረግም፣ ተጀምረው መጠናቀቅ አለባቸው ተብሎ ሥራ ላይ ያሉ ግንባታዎች በተፈጠረው የዋጋ ንረት ሳቢያ የግንባታ ወጪያቸው በእጅጉ መጨመር ግንባታ የሚያካሂደውንም አስገንቢውንም እየፈተነ ነው፡፡ ብዙዎችንም ሥራውን ወደማቆም እየወሰዳቸው ነው፡፡ ሥራ ያቆሙም አሉ፡፡ ይህም ብዙዎችን ሥራ አልባ ያደርጋል፡፡

  የኮንስትራክሽን ዘርፍ ደግሞ የያዘው የሰው ኃይል ችጅግ በርካታ ከመሆኑ አንፃር ሥራዎች የማይቀጥሉ ከሆነ ሊፈጠር የሚችለው ቀውስ ቀላል አይሆንም፡፡  ይህ የዋጋ ንረቱ አደጋዎች በተወሰነ ቦታ ላይ እንደማይቆይ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡

የዋጋ ንረቱ የዘይትና የጤፍ መወደድ ብቻ አይደለም፡፡ የአገልግሎት ዋጋ መጨመርን ብቻ የሚመለከትም አይደለም፡፡ ስለዚህ በተቻለ መጠን መሠረታዊ የሚባሉ ምርቶችን ዋጋ ለማረጋጋት በየጊዜው እየተወሰዱ እንዳሉት የተለያዩ ዕርምጃዎች ሁሉ የዋጋ ንረቱ በሌሎች ዘርፎች ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት በቅጡ መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡ ንረቱ እንዲሁ ከቀጠለ ነገ በአጠቃላይ የሚፈጥረውን ቀውስ ከወዲሁ በማሰብ በዚህ እጅግ አሳሳቢ በሆነ ጉዳይ ላይ መንግሥት ከከዚህ ቀደሙ የበለጠ መሥራት ይኖርበታል፡፡

ዛሬ በሁሉም የቢዝነስ ዘርፎች ላይ ቢኬድ ያልጨመረ ነገር የለም፡፡ በዚህ ጭማሪ ብቻ እየተስተጓጎሉ ያሉ ማምረቻዎችንም ማሰብ ያስፈልጋል፡፡

በአንድና በሁለት ዓመት ልዩነት ውስጥ የአንዲት ብሎን ዋጋ በአራትና በአምስት እጥፍ አድጓል፡፡ ብዙ ጥሬ ዕቃዎች በትንሹ በእጥፍ ጨምረዋል፡፡ በዚህ መንገድ እየተመረተና እየተገዛ የሚገባ ምርት ሸማቾች ጋር ሲደርስ ምን ያህል እንደሚሰቀል ማሰቡ አያቅትምና የዋጋ ንረቱ ያልነካካው ነገር ስለሌለ ይህን ለማስተካከል ምልከታችንን ሰፋ አድርጎ መራመድ የግድ ይላል፡፡

ስለዚህ በዚህ አካባቢ ያለው ችግር ውሎ አድሮ ትልቅ አደጋ ስለሚሆን ለየት ያለ ዕርምጃ ያስፈልገዋል፡፡

ከሁሉም በላይ በእጅጉ ሊታሰብበት የሚገባው ነገር የኑሮ ውድነቱ እንዲህ በተሰቀለበትና ዜጎች እየተፈተኑ ባለበት ሰዓት የአብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል ገቢ እዚያው ላይ ቆሟል፡፡ በተለይ በደመወዝ የሚተዳደረው የኅብረተሰብ ክፍል ገቢውና ወጪው ፈጽሞ ሊጣጣምለት አልቻለም፡፡

ተቋማት ቢያንስ አሁን ያለውን የኑሮ ውድነት ሊያግዝ የሚችል የደመወዝ ጭማሪ  ማድረግ ቢጠበቅባቸውም ይህንን እያደረጉ አይደለም፡፡ ሌላው ቀርቶ የዋጋ ንረቱን ሰበብ አድርገው ለአገልግሎቶቻቸው የሚያስከፍሉትን ዋጋ ያሳደጉ ተቋማት ሠራተኞቻቸውን ዘንግተዋል፡፡ በመሆኑም ኑሮ የከበደውን ሠራተኛ ቢያንስ የዋጋ ንረቱን ለመቋቋም የሚችልበትን የደመወዝ ጭማሪ ማድረግ ይገባል፡፡

የኢኮኖሚ ባለሙያዎች እንዲህ ባለ ወቅት የደመወዝ ጭማሪ ማድረግ ሌላ ችግር ይሆናል ቢሉም፣ ዜጎች ከዚህ ትንታኔ ጀርባ ‹‹እኮ ምን እንሁን?›› ማለታቸው አይቀርም፡፡ በመሆኑም ሠራተኞች ቢያንስ የኑሮ ውድነቱን ሊደግፋቸው የሚችል ጭማሪ መኖር ይገባዋል፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት