Sunday, May 26, 2024

በብሔራዊ ምክክሩ ላይ ያጠሉት ያለፈው ምርጫ ቅራኔዎችና መውጫ መንገዶች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ሲመጡ እሳቸውን ወደ መንበሩ ያወጡ ለውጦችና ያሳዩዋቸው የለውጥ ተግባራት፣ በአገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ሊያረጋግጡ የሚችሉና ከስንት ጊዜ አንዴ የሚመጣ ዕድል ያስገኙ ዕርምጃዎች ናቸው ሲባሉ በበርካቶች ዘንድ ተሞካሽተዋል፡፡

አንዳንዶችም የታየውን ለውጥ ከ1960ዎቹ የተማሪዎች እንቅስቃሴና ንቁ የፖለቲካ ሚና፣ ከንጉሣዊ ሥርዓት መወገድ ይዞት መጥቶ ከነበረው የለውጥ ዕድል፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባርን (ኢሕአዴግ) ወደ ሥልጣን ካመጣው የ1983 ዓ.ም. ለውጥ ጋር ያመሳስሉታል፡፡

በርካቶችም አገሪቱ ከአሁን ቀደም የነበሯትን ዕድሎች በአግባቡ ሳትጠቀም መቅረቷንና እስከ ዛሬ ድረስ በተመሳሳይ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች ተወጥራ መገኘቷን በማውሳት፣ አሁን የተገኘው ዕድል መባከን አይገባውም በማለት ሲያስጠነቅቁም ከርመዋል፡፡ ከጅምሩ አንስተው ስለብሔራዊ ምክክርና ብሔራዊ መግባባት ሲለፍፉ የነበሩ የፖለቲካ ስብስቦችና ግለሰቦች ለዚህ በር ከፋች ይሆናል ብለው የጠበቁት አንድ ሁነት ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ነበር፡፡

ምርጫውን በተለምዶ እንደሚባለው ‹‹ነፃ፣ ፍትሐዊና ተዓማኒ›› ከማለት የተቆጠበው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ‹‹ሰላማዊና ተዓማኒ›› ምርጫ የማድረግ ሕዝብ በምርጫ ያለውን አመኔታ የመመለስ ግብ አስቀምጦ በ50 ሺሕ ያህል የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች ምርጫ ለማድረግ ሲዘጋጅ ቆይቶ፣ ምርጫውን በሁለት ዙር በሰኔ 2013 ዓ.ም. እና በመስከረም 2014 አከናውኗል፡፡

ሆኖም ምርጫውን ተከትሎ ሪፖርተር ከፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ጋር ያደረጋቸው ቃለ መጠይቆች እንደሚያስረዱት፣ ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ በመጠናቀቁና ተዓማኒ ሒደት በመሆኑ ብቻ ‹‹ኢትዮጵያ አሸነፈች›› እንደተባለና ምርጫው ፍትሐዊነት እንዳልነበረው ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ራሔል ባፌ (ዶ/ር) ከሪፖርተር ጋር አድርገውት በነበረው ቆይታ ምርጫው ጉድለቶች የታየበት እንደነበር፣ ችግሮች የታዩትም በታችኛው አስተዳደራዊ መዋቅር ላይ መሆኑን አውስተው ነበር፡፡ የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ኃላፊም ከአሁን ቀደም ለሪፖርተር በሰጡት ቃለ መጠይቅ፣ ምርጫው ፉክክር የታየበት ነው የሚል ብዥታ መፈጠር እንደሌለበት አውስተዋል፡፡

ነገር ግን በኮሚሽን ተዋቅሮ ሊከናወን ያለው ብሔራዊ የምክክር መድረክ በምርጫው ውጤት ሳቢያ ተፈጥሮ የነበረው ድብታ ቀንሶ ዳግም መነቃቃት እንዲታይ ያደረገ ቢሆንም፣ በምርጫው የታየው ችግር ወደ አገራዊ መግባባቱም እንዳይመጣና ውጤት አልባ እንዳያደርገው ሥጋቶች አሉ፡፡

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ጥሩነህ ገምታ ከሪፖርተር ጋር በነበራቸው አጭር ቆይታ፣ ‹‹ብሔራዊ ውይይቱም እንደ ምርጫው እንዳይሆን ሥጋት አለ፤›› ይላሉ፡፡ ለዚህም ምክንያታቸው በሒደቱ አካታችነት ላይ ጥያቄ ስላለ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

‹‹በዚህ አገር ሰላም እንዲመጣ የምንፈልግ ከሆነ በብሔራዊ ውይይቱ ሁሉም ትጥቅ ያነሱ ኃይሎች ሊሳተፉበት ይገባል፤›› የሚሉት አቶ ጥሩነህ፣ ፓርቲያቸው የትጥቅ ትግልን ባይደግፍም አምባገነን መንግሥት ሲኖር እንዲህ ያለ ሁኔታ ይኖራል ይላሉ፡፡

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ራሔል ባፌ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ባለፈው ዓመት ወደ ምርጫው ሲገቡ ከገዥው ፓርቲ ጋር የተፈራረሙትን የቃል ኪዳን ሰነድ ተማምነው የነበረ ቢሆንም፣ ስምምነቱ በማዕከል ብቻ ታጥሮ እንደቀረና ምርጫ ወደሚደረግባቸው የወረዳና የቀበሌ የታችኛው የአስተዳደር መዋቅሮች እንዳልደረሰ ያመለክታሉ፡፡

‹‹ተቃዋሚ ፓርቲዎች የቃል ኪዳን ሰነዱን ሲያከብሩ ገዥው ፓርቲ ግን አላከበረም ነበር፤›› በማለት ራሔል (ዶ/ር) ያስታውሳሉ፡፡

በዚህም ምክንያትና አባላቶች ታስረውብናል በማለት በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ራሳቸውን ከምርጫው አግልለዋል፡፡ ሆኖም ምርጫው ተመልሶ ስለሚመጣ ትኩረት ተደርጎ የነበረው፣ ከምርጫው ይልቅ በአገራዊ ጉዳይ ላይ እንደነበርና ብልፅግና ፓርቲ በፈለገበት መንገድ ቢሄድም ሚዛን የደፋው የአገሪቱ ጉዳይ ነበር ይላሉ፡፡

‹‹አሁንም ያ እንዳይደገም ሥጋት አለ፡፡ እንደ ጋራ ምክር ቤትም ለብልፅግና ፓርቲም ሆነ ለመንግሥት ያለንን ሐሳብ አቅርበናል፤›› የሚሉት ራሔል (ዶ/ር)፣ ‹‹ብሔራዊ ምክክሩ ከፓርቲና ከምርጫ ያለፈና አገራዊ ጉዳይ ስለሆነ፣ መሟላት ያሉባቸውን ጉዳዮች ቅድመ ሁኔታ አቅርበናል፤›› ሲሉ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ውይይቱ ከፓርቲና ከመንግሥት በላይ በመሆኑም ኅብረተሰቡን ሰቅዘው የያዙ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ወደ ውይይት ጠረጴዛው እንዲመጡ ያስገነዝባሉ፡፡

‹‹ሒደቱ ብሔራዊ መግባባትን ማምጣት አለበት፡፡ እንደ ምርጫው የሚያገል ከሆነ ግን አይሠራም፤›› የሚሉት የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢዋ፣ ለዚህ እንዲያግዝ ደግሞ ከመነሻው የጋራ መግባባት ሊፈጠር እንደሚገባ ያሳስባሉ፡፡

በሌላ ወገን ደግሞ ይኼንን ለማሳካት መልካም ግንኙነት መፍጠር እንደሚበረታታ በማስገንዘብ፣ ‹‹ከብልፅግና ፓርቲ ጋር ያለው ችግር ማውራት እንጂ፣ መደማመጥና መተማመን የለም፡፡ ማውራት ብቻ ምንም አይጠቅምም፤›› በማለት፣ ሒደቱ ከሕዝብ እሴት ጋር መጣጣም ያለበት መሆኑን በደብዳቤና በቃል ለመንግሥት እንዳሳወቁ ይገልጻሉ፡፡

የአገራዊ ምክክር ሒደቱ አካታችነት በተለያዩ መድረኮች የሒደቱ ወሳኝ አካል እንደሆነ ሲነገር የቆየ ሲሆን፣ ረቡዕ ጥር 25 ቀን 2014 ዓ.ም. በራዲሰን ብሉ ሆቴል የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚደረግ ውይይት የሚመራበትን መመርያ ለማፅደቅ በጠራው የውይይት መድረክ ላይ ተመሳሳይ ሐሳቦች ሲንፀባረቁ ተስተውሏል፡፡

በመመርያው መግቢያ ላይ፣ ‹‹የፖለቲካ ፓርቲዎች በመካከላቸው ያለውን ልዩነት በማጥበብ፣ በአገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሚመራው ሁሉን አቀፍ የምክክር መድረኮች ግብዓት የሚሆኑ የስምምነት ሐሳቦችን ለማቅረብ እንዲችሉ›› ያግዛል ተብሎ መስፈሩ አከራካሪ ሆኗል፡፡

በመድረኩ ከኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የተሳተፉት ጀቤሳ ገቢሳ፣ ፓርቲያቸው በብሔራዊ ውይይት ሒደት ውስጥ እየተሳተፈ ባለመሆኑ ይኼ አገላለጽ ከመመርያው ጨርሶ እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡

‹‹እኛ ከኮሚሽኑ ጋር እየሠራን አይደለም፣ ስለዚህ ሦስተኛ ወገን መግባት የለበትምና ይኼ አገላለጽ ይውጣ፤›› ብለዋል፡፡

በመድረኩ አስተያየታቸውን የሰጡት የኦፌኮ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጥሩነህ በበኩላቸው በሰነዱ፣ ‹‹በአገሪቱ እየተካሄደ ባለው ለውጥ (Reform) ምክንያት የተከሰቱ ችግሮች ላይ ተወያይቶ በጋራ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ሐሳቦችን በጋራ ለማዳበር›› እንደሚያግዝ የተቀመጠው አገላለጽ ልክ እንዳልሆነና ምንም ለውጥ/ሪፎርም በአገሪቱ እንደሌለ በመጥቀስ የተከራከሩ ሲሆን፣ ለውጥ የተባለው በጣም አናሳና እዚህ ግባ የማይባል ነው በማለት ተችተዋል፡፡

‹‹አሁንም የአውራ ፓርቲ አስተሳሰብ አለ፤›› ብለው በዚህም ምክንያት፣ ‹‹የቦርዱና የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ሥራ ባይደባለቅ፤›› በማለት አሳስበዋል፡፡ ሆኖም ኮሚሽኑ ከቦርዱ ግብዓት የሚፈልግ ከሆነ ጥያቄ ማቅረብ ይኖርበታል ብለዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም በመመርያው ሁሉን አቀፍ ምክክር ተብሎ የተቀመጠው አገላለጽ፣ ቦርዱ ምን ያህል ሁሉን አቀፍ ይሆናል ብሎ እርግጠኛ ሆኖ እንዳስቀመጠውም ጠይቀዋል፡፡

ብልፅግና ፓርቲን ወክለው በውይይቱ የተገኙት አቶ ዛዲግ አብርሃ፣ በአገሪቱ በርካታ ውስብስብ የፖለቲካ ችግሮች እንዳሉ ዕሙን እንደሆነና ለውጥም በአገሪቱ እንዳለ በመናገር፣ ‹‹ሪፎርም አልተደረገም ማለት ራስ ዳሸን ተራራን መካድ ነው፤›› ሲሉ ወርፈዋል፡፡

ፓርቲያቸው ሪፎርም ተደርጎ አልቋል ብሎ እንደማያምንና ሊደረስበት የሚገባ ትልቅ ደረጃ ቢኖርም፣ የተሠራችውን ሪፎርም ግን ዕውቅና እየሰጡ መሄድ መልካም እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ለምክክር ኮሚሽኑ ሐሳቦች ይቀርባሉ መባሉ መልካም ዕድል ተደርጎ መወሰድ አለበት የሚሉት አቶ ዛዲግ፣ ‹‹ውይይቱ ሁሉን አካታች ማድረግ ግን የእኛ ነው፤›› ይላሉ፡፡

‹‹ሁሉንም በጥርጣሬ፣ ሁሉንም እንደማይሆን ካየነው ምንም ነገር አይሠራም፡፡ ነገሮችን የምናይበትን መንገድ በተወሰነ መልኩ መቀየር መልካም ይመስለኛል፤›› ያሉት አቶ ዛዲግ፣ ‹‹በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚደረግ ውይይት ጉንጭ አልፋ እንዳይሆን፣ የሆነ ቦታ ፍሬ የሚያፈራ እንደሚሆን የሚያሳይ ነው፤›› ሲሉ በመደገፍ፣ ‹‹ከኋላ ስሙና ምግባሩ አልተጣጣመም ብሎ መተቸት የአባት ነው፡፡ ግን ገና ከአሁኑ እንደ ጥንቆላ አስቀድሞ አንድ ነገር ላይ አሉታዊ ሐሳብ ማቅረብ ስህተት ነው፤›› በማለት ተችተዋል፡፡

ስብሰባውን የመሩት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ በበኩላቸው፣ ከአሁን ቀደም በነበሩ ውይይቶች የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት ከብሔራዊ ምክክር መድረክ ጋር እንዴት ሊጣጣም እንደሚችል ጥያቄዎች ቀርበው ስለነበር፣ የውይይቱ ውጤቶች ለምክክር ኮሚሽኑ በግብዓትነት ማቅረብ የሚለው ሐረግ በመመርያው ተካቷል ብለዋል፡፡

ራሔል (ዶ/ር) የሚደረገው ብሔራዊ ምክክር ከማኅበረሰባዊ እሴቶች ጋር መጣጣም እንዳለበት በማውሳት፣ ይኼንን በጽሑፍና በቃል ለመንግሥትና ለገዥው ፓርቲ ማሳወቃቸውን ይናገራሉ፡፡

‹‹ኢትዮጵያ ይኼንን ዕድል ማባከንን ትከሻዋ አይችለውም፡፡ እጅግ ተስፋ ተደርጎበታልና ካልተሳካ ኢትዮጵያ አትሸከመውም፤›› በማለት፣ ውይይቱ ከፓርቲና ከመንግሥት ጥርነፋና ጣልቃ ገብነት የፀዳ ገለልተኛ ሒደት መሆን እንዳለበት፣ በጥንቃቄ መከናወን እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡ ለዚህም መንግሥት ሎጂስቲክስና አስተዳደራዊ ኃላፊነቱን ከመወጣት ባለፈ እንደ አንድ ባለድርሻ አካል መሳተፍ ስላለበት፣ ኃላፊነት የተሞላው ሆኖ የሁሉንም ሐሳቦች ተቀብሎ ወደ ጠረጴዛው መምጣት አለበት ብለዋል፡፡

ብልፅግናም እንደ ፓርቲ የጋራ ምክር ቤቱ አባል ነውና ራሱን ነጥሎ ከፓርቲ ሳጥን ያለ መውጣትና በምርጫው እንደታየው ማድረግ የለበትም የሚሉት ራሔል (ዶ/ር)፣ በኮሚሽኑ በሚመሩ ውይይቶችም እንደ ባለድርሻ ነው መገኘት ያለበት ይላሉ፡፡

‹‹መንግሥት በቁም ነገር ስለወሰደው ብሔራዊ ውይይቱ ተስፋ ተደርጎበታል፣ ግን በተግባር ማየት አለብን፤›› የሚሉት የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢዋ፣ ከሕዝቡ የሚጠበቅ ኃላፊነት ቢኖር ሕዝቡ ሳይሰጋና ነገ ምን ይደርስብኛል ብሎ ሳይሳቀቅ በነፃነት ተናግሮ ችግሩ እንዲፈታለት ለማገዝ ጣልቃ ገብነት እንዳይኖር ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ ያስገነዝባሉ፡፡

ብሔራዊ ምክክሩ አካታች እንዲሆን ከተፈለገ ሁሉም በትጥቅ ትግል ላይ የሚገኙ ኃይሎች እንዲሳተፉ መደረግ እንዳለበት የሚገልጹት ደግሞ የኦፌኮ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጥሩነህ፣ መንግሥት ትልቁን መንገድ መሄድ አለበት በማለትም ይሞግታሉ፡፡ ስለዚህም መንግሥት የሚቃወሙትን ሁሉንም ጠላት አድርጎ ከመፈረጅ ለውይይት ክፍት ይሁን ሲሉም ጠይቀዋል፡፡

እንደ አቶ ጥሩነህ እምነት አካሄዱ ከጅምሩ አካታች እንዳልሆነና ይኼም ትክክል ባለመሆኑ፣ የኮሚሽኑን መቋቋም ሕጉ ከወጣ በኋላ እንዳወቁና ቀድመው አውቀው ቢሆን ኖሮ አስተዋፅኦ ያደርጉ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

‹‹ሥርዓቱን በመቃወም የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ግብ ግብ ውስጥ ያሉ ኃይሎች፣ የብልፅግናና የሕወሓትም የሥልጣን ግብ ግብ ነውና ወደ ድርድር እዲመጡ እንፈልጋለን፡፡ ያ ማለት ሕወሓት ኢትዮጵያን አልበደለም ማለት አይደለም፡፡ ወደ ሰላም መጥተን ያለችንን ሀብት ለጦርነት መማገድ የለብንም፣›› ብለዋል፡፡

ብሔራዊ ምክክሩን በተመለከተ አስተያየታቸውን የሚሰጡ ታዛቢዎች አካታችነት ሲባል የሐሳብ ውክልናን ነው?  ወይስ ስለሰዎች ስለቡድኖች ውክልና ነው የሚወራው? ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡

ከአሁን ቀደም በማይንድ ኢትዮጵያ ተነሳሽነት አባል የነበሩት ራሔል (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ አካታችነት በሐሳብም በሰዎች ውክልናም የሚገለጽ ነው በማለት፣ ‹‹የተዘለለ ሐሳብ ሊኖር አይገባም፣ ሳይካተቱ መቅረት የለባቸውም፤›› ይላሉ፡፡ ሆኖም ሕዝቡ ውስጥ ያለ ሐሳብ መጥቶ የሚያዩ ሰዎች ቁጥር ደግሞ ትንሽ መሆን የለባቸውምና ሁሉም የኅብረተሰብ አካላት መወከል አለባቸው ይላሉ፡፡ ሐሳቦችን ወደ ጠረጴዛ የሚያመጡትም እነዚህ ሰዎች መሆናቸውን አልሸሸጉም፡፡

በትጥቅ ትግል ላይ ያሉም አካላት ሕዝቡ እነሱ በትጥቅ ትግል ለመፍታት የሚፈልጓቸውን ችግሮች በውይይት ለመፍታት ከተቻለ፣ ትጥቅ ትተው የማይመጡበት ምክንያት የለም ብለው እንደሚያምኑ ይናገራሉ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአፈ ጉባዔ ጽሕፈት ቤት አማካይነት 632 ለኮሚሽኑ የሚሆኑ ኮሚሽነሮች ጥቆማ የደረሰው ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል 42 የሚሆኑትን መርጦ ዓርብ ጥር 27 ቀን 2014 ዓ.ም. ይፋ አድርጓል፡፡ በእነዚህ 42 ዕጩዎች ላይ ሕዝቡ አስተያየት ከሰጠባቸው በኋላ 14 አባላት ለኮሚሽነርነት ይመረጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -