የፍም ግንድ ሆኖ – እጄ በወገብሽ
የቀስተዳመና – ያቀፈሽ ሲመሥልሽ
ሣቅ – ከከንፈራችን – እንደ አደይ ሲፈካ
የመልአክት ሰራዊት ዙሪያችን ሲዘምር
ውሸት ነበር ለካ
ገነት የሞሸርን የመሠለን ዕለት
በዚያ ሁሉ ፌሽታ- በዚያ ሁሉ ድምቀት፣
ለካስ ከአበቦቹ- ማር አልተጋገረም
ቢራቢሮ የሆንነው እውነት አልነበረም፣
ዓይንሽ ኮከብ ሆኖ- ትግ ትግ እያለ
ልቤን ሲያቃጥለው፣
ትንፋሽሽ እንደአውሎ- ነፍሴን አንከባልሎ
ከቅጥርሽ ሲጥለው፣
ሰማዩ ሲጠብ ምድር ቅንጣት ስትሆን
ጠጠርን አክላ፣
በጉንጫችን መሀል ስናንከባልላት
እንደ ከረሜላ፣
ለካስ- ውሸት ነበር ፍቅር አልነበረም
ስሜቱ- ስፋቱ ገና አልተመተረም፡፡
መብረቅ ስንጋልብ- በሰማዩ ሜዳ
ስንበርር እንደ እሞራ ከፀሐይ ጨረሮች
ውሃ ስንቀዳ፣
ሀረግ ከግንድ ሆነን- የት እንዳለን ጠፍቶን
መልአክ በተዐምር- መንገድ አሳስቶን፣
በሰማያት መሀል- ቀዳዳ ፈልገን
ምድር ስንመጣ፣
የጻድቃንን ምንጮች ተራራ ፈንቅለን
ቆፍረን ስንጠጣ፣
ያኔም ገና ነበር- ፍቅር አልተወለደም
ማህፀኑም የለ፣
ይኸው አሁን- ገና … መለየት ሲሸተን
ፍቅር ተጀመረ
ናፍቆት ተደወለ፡፡
- ደረጀ በላይነህ