ኮንፉሲውስ የሚባለው በጥንት ዘመን የነበረው ትልቁ የቺና አገር ፈላስፋ ከዕለታት አንድ ቀን ከወንዝ ዳር ተቀምጦ ውኃውን እየተመለከተ ሲተክዝ ተማሪዎቹ ደረሱና መምህር ሆይ የሚፈሰውን ይህን የወንዝ ውኃ የምትመለከተው ስለምንድነው? ምን አዲስ ነገር አገኘህበት? የወንዝ ውኃ ጥንትም እንዲሀ ነበር፣ ዛሬም እንዲህ ነው፣ ወደፊት ደግሞ እንዲህ ሆኖ ይኖራል አይለወጥም ብለው ተናገሩት፡፡
ኮንፉሲውስም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፡፡
አሁን የተናገራችሁት ቃል እውነት ነው፡፡ የወንዝ ውኃ ጥንትም ዛሬም ወደፊትም እንደዚሁ ሆኖ ይኖራል አይለወጥም፡፡ ይህንንም የሚስተው ሰው የለም፡፡ ግን በፈሳሽነት የሚጓዘው የወንዝ ውኃና እውነትን የምታስረዳ የፍልስፍና ትምህርት የሚመሳሰሉ መሆናቸውን ሰው ሁሉ የሚያውቀው አይመስለኝም፡፡ የወንዞች ውኃ ሁሉ ሳያቋርጥ ሁልጊዜ ወደፊቱ ይገሠግሣል፡፡ ግሥገሣውም ሌሊትም ሆነ ቀንም ሆነ አያቋርጥም፡፡ በመጨረሻም ከሰፊ የውቅያኖስ ባሕር ውስጥ ገብቶ ይቀላቀልና ይጠፋል፡፡ እውነትን የምታስረዳ ትምህርትም እንደዚሁ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ስትወርድ ስትዋረድ ከትውልድ ጋር ተያይዛ መጥታ እስከኛ ደረሰች፡፡ እኛም ደግሞ ለሚከተሉት ልጆቻችን ለማስተማርና ለማስረዳት ብለን ይኸው እንደክማለን፡፡ ልጆቻችን ደግሞ በተራቸው ከነሱ በኋላ ለሚመጣው ትውልድ አስተምረው ያወርሳሉ፡፡ እንደዚህ እያለ የሰው ልጅ ትውልድ እስከ ተፈጸመ ድረስ ይህች እውነትን ለሰው ልጆች የምታስረዳ ትምህርት ስትተላለፍ ትኖራለች፡፡
– ከበደ ሚካኤል ‹‹የዕውቀት ብልጭታ›› (1999)