አንዲት ዳክዬ በአንድ ሐይቅ ዳርቻ ላይ ዕረፍት በማድረግ ላይ ሳለች፣ ቀንዳውጣዎችን በማደን ላይ ከነበረ ወገኑ ከአሞራ ቤተሰብ ከሆነ ከአንድ አንገትና ቅልጥመ ረዥም አሞራ ጋር ይገናኛሉ፡፡ አሞራውም ረዥም አንገቱን በማስገግ ዳክዬዋን ለትንሽ ጊዜ በመገረም ተመለከታትና፤
‹‹አንቺ ደግሞ ከየት ነው የመጣሽው?› ብሎ ጠየቃት፡፡
‹‹ከመንግሥተ ሰማይ!›› መለሰች ዳክዬዋ፡፡
‹‹እዬት ነው ያለው?›› ጠየቀ አሞራው፡፡
‹‹ይገርማል! ስለ መንግሥተ ሰማይ ሰምቼ አላውቅም ነው ምትለው?›› አለችውና ስለ ታላቂቱ ዘላለማዊት ከተማ ትገልጽለት ገባች፡፡ እንደ መስተዋት ብርሃን በሚያስተላልፍ ንጹሕ ወርቅ ስለተሠራው አውራ ጎዳና፣ በከበሩ ድንጋዮች ስለታነጹት በሮች፣ ስለሕይወት ውኃ ወንዝ፣ እንደ ብርጭቆ ጥርት ስላለው የሕይወት ውኃ፣ በወንዙ ግራና ቀኝ ስላለው ሕዝቦችን ስለሚፈውሰው የሕይወት ዛፍ፣ በዚያኛው ዓለም ስለሚኖሩት ሕዝቦች ባማሩ ቃላት አብራራችለት፡፡ አሞራው ግን አንድም ስሜት አልሰጠውም፡፡
በመጨረሻ፤ ‹‹ለመሆኑ እዚያ ቀንዳውጣዎች ይገኛሉ?›› ሲል ይጠይቃታል፡፡
‹‹ቀንዳውጣዎች!›› ዳክዬዋ ደገመች፣ ‹‹የሉም! በርግጥ እዚያ ቀንዳውጣዎች አይገኙም›› አለችው፡፡
‹‹እንግዲህ ከሆነማ፣ እኔን ተይኝ እቴ፣ አንቺ መንግሥተ ሰማይሽ ይኑርሽ፣ እኔ ቀንዳውጣዎችን ነው ምፈልገው›› ብሏት በባሕሩ ዳርቻ ወደ ቀንዳውጣ ፍለጋው ተመለሰ፡፡
– የኃይል ከበደ ‹‹ምስካይ›› እንደተረከው (2004)