የአፍሪካ ነፃ ንግድ ስምምነትን በሥራ ላይ ለማዋል 345 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ የጭነት ተሽከርካሪዎች መገዛት እንዳለባቸው ተጠቆመ።
ሰኞ ጥር 30 ቀን 2014 ዓ.ም. በተካሄደው አምስተኛው የአፍሪካ ቢዝነስ ፎረም፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ይፋ ባደረገው ጥናት እንደተገለጸው፣ 55 የአፍሪካ አገሮች ነፃ ግብይቱን እንዲተገብሩ 2.2 ሚሊዮን የጭነት ተሽከርካሪዎች ያስፈልጓቸዋል። ከእነዚህ ውስጥ 1.8 ሚሊዮን ጭነት መኪኖች በብትን የሚንቀሳቀሱ ምርቶችን ለማጓጓዝ የሚውሉ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ ኮንቴነሮችን ለማንቀሳቀስ ይውላሉ ተብሏል።
የአፍሪካ አገሮችን የእርስ በርስ ንግድ ከ50 በመቶ በላይ በማሳደግ ጥቅል ምርታቸውን በ2.5 ትሪሊዮን ዶላር እንደሚያሳድገው የሚጠበቀው የአፍሪካ ነፃ ንግድ ስምምነትን ለመተግበር፣ መሠረተ ልማቶችን መገንባት አስፈላጊ መሆኑን ኮሚሽኑ አስታውቋል።
የኮሚሽኑ ዋና ጸሐፊ ቬራ ሶንጉዌ የቢዝነስ ፎረሙን በከፈቱበት ወቅት እንደተናገሩት፣ ስምምነቱ ላይ የተቀመጡ ዕቅዶችን በተግባር ላይ ለማዋል የትራንስፖርት አገልግሎቶችን ማሟላት ግዴታ ነው።
በዚህም መሠረት ከ2.2 ሚሊዮን በላይ የጭነት መኪኖች በተጨማሪ፣ 169 ሺሕ 339 የባቡር ዋገኖች፣ 136 መርከቦችና 243 አውሮፕላኖችን ሟሟላት ያስፈልጋል ብለዋል። ይህንንም ዕውን ለማድረግ በአጠቃላይ 411 ቢሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚጠይቅ አክለዋል።
ካዛንቺስ አካባቢ በሚገኘው የኮሚሽኑ ዋና መሥሪያ ቤት በተካሄደው የቢዝነስ ፎረም ላይ፣ የተለያዩ የአፍሪካ አገሮች መሪዎችና የአኅጉሪቱ የፋይናንስ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች የተገኙ ሲሆን፣ ነፃ ንግድ ስምምነቱን ለመተግበር በሚያስፈልጉ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተደርጓል።
ውይይቱ በዋነኝነት ትኩረት ያደረገው በአየር ትራንስፖርትና ቱሪዝም ላይ ነበር፡፡ እንደ ኮሮና ቫይረስ ያሉ ችግሮች ያስከተሉት ቀውስን ከመቀነስ አኳያ መወሰድ ያለባቸው ዕርምጃዎች ላይም ውይይት ተደርጓል። የኬንያ ኤርዌይስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አላን ኪላቩካ በውይይቱ ወቅት እንደተናገሩት፣ የአፍሪካ አገሮች የጋራ አየር መንገድ ማቋቋም ይኖርባቸዋል፡፡ ይህም ገበያውን በራሳቸው እጅ ለማድረግና የትራንስፖርት ዘርፉን በጋራ ለማዘመን ይረዳቸዋል ብለዋል።
በአላን ሐሳብ የተስማሙት የአፍሪ ኤግዚም ባንክ ፕሬዚዳንት (ፕሮፌሰር) ቤኔዲክት ኦምራህ፣ የጋራ አየር መንገድ ከማቋቋም ባሻገር፣ የአፍሪካ አገሮች የጋራ የክፍያ ሥርዓት ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል። ይህንንም ዕውን ለማድረግ የፓን አፍሪካ የክፍያ ሲስተም አፍሪ ኤግዚም ባንክ ዘርግቷል ያሉት አምራህ፣ አገሮቹም ለትኬት ግዥና ለመሰል አገልግሎቶች መጠቀም ይችላሉ ሲሉ አክለዋል።