ባለፉት ስድስት ወራት 73 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያላቸው አገር በቀል ኩባንያዎች በብረታ ብረት ምርት ዘርፍ መሰማራታቸውን፣ የብረታ ብረት ልማት ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
ኩባንያዎቹ በስድስት ወራት ውስጥ ወደ ብረታ ብረት ማምረት ዘርፍ የተቀላቀሉ መሆናቸውን፣ የፋብሪካ ግንባታ መጀመራቸውንና በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ወደ ምርት እንደሚገቡ በብረታ ብረት ልማት ኢንስቲትዩት የዕቅድ፣ ፖሊሲ ጥናትና መረጃ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጥላሁን ዓባይ ገልጸዋል።
ወደ ምርት በሚገቡበት ወቅትም ኩባንያዎቹ በዓመት ከ800 ሺሕ ቶን በላይ የተለያዩ የብረታ ብረት ምርቶችን ማምረት እንደሚችሉ አስረድተዋል። ዘርፉን የተቀላቀሉት 11 ኩባንያዎች እንደሆኑ፣ ከ700 ሺሕ ቶን በላይ በዓመት የሚያመርቱት ሰባት ፋብሪካዎች መሠረታዊ ብረታ ብረት የሚያመርቱ መሆናቸውን፣ እንዲሁም ሦስቱ በማሽነሪ፣ አንድ ደግሞ በኤሌክትሮኒክስ ዘርፍ የሚሰማሩ እንደሆኑ ገልጸዋል።
ወደ ዘርፉ የተቀላቀሉት ሁሉም ኩባንያዎች አገር በቀል መሆናቸውን የገለጹት አቶ ጥላሁን፣ በተለይ ከውጭ የሚመጣን ከፍተኛ መጠን ያለው የብረታ ብረት ምርት ለመቀነስ እንደሚረዳ ጠቁመዋል። በአገር አቀፍ ደረጃ በዓመት ጥቅም ላይ እየዋለ የሚገኘው የብረታ ብረት ምርት ከአሥር ሚሊዮን ቶን በላይ እንደሚሆን፣ ከዚህም ቢያንስ 70 በመቶ የሚሆነውን በአገር ውስጥ ለመሸፈን እየተሠራ እንደሚገኝ አክለዋል።
የብረታ ብረት ፋብሪካዎች በተለይ የግብዓት አቅርቦትና የውጭ ምንዛሪ እጥረት ትልቁ ፈተናቸው መሆኑን የገለጹት አቶ ጥላሁን፣ ፋብሪካዎቹ ማምረት ከሚችሉት በአማካይ 17 በመቶ ባልበለጠ አቅማቸው እንደሚሠሩም ተናግረዋል።
ይህንን ችግር ለመቅረፍም የአገር ውስጥ ብረትን በግብዓትነት መጠቀም እንዲቻል በየቤቱ ከሚሰበሰቡት በተጨማሪ፣ በመንግሥት ተቋማት የሚገኙ ቁርጥራጭ ብረቶችን ወደ ማቅለጫ በማስገባት ለፋብሪካዎቹ ለማቅረብ መታቀዱን ገልጸዋል።
አሁን ወደ ዘርፉ የተቀላቀሉትን ጨምሮ የብረታ ብረት ልማት ኢንስቲትዩት ለ28 ፋብሪካዎች የቴክኒክ ድጋፍ እንደሚያደርግ፣ ምርት ያቆሙትም ወደ ምርት እንዲመለሱ እየሠራ መሆኑን አቶ ጥላሁን ገልጸዋል።
በዚህም መሠረት ባለፉት ስድስት ወራት በመለዋወጫ እጥረትና ሌሎች ምክንያቶች ማምረት አቁመው የነበሩ ስምንት ፋብሪካዎች ወደ ምርት መግባታቸው ተገልጿል። ፋብሪካዎቹ ዓመታዊ የማምረት አቅማቸው ከ619 ሺሕ ቶን በላይ እንደሆነ፣ 615 ሺሕ ቶን የሚሆነው መሠረታዊ ብረታ ብረት፣ እንዲሁም ቀሪው በማሽነሪና በኤሌክትሮኒክስ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ፋብሪካዎች የሚያመርቱት እንደሆነ አቶ ጥላሁን አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ በየዓመቱ የብረታ ብረት ምርትን ለማስገባት አሥር ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ የሚወጣ ሲሆን፣ በአገር ውስጥ የሚመረተው ከውጭ ከሚመጣው ጋር ሲነፃፀር ከአምስት በመቶ እንደማይበልጥ የኢንስቲትዩቱ መረጃ ያሳያል።