Sunday, April 14, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ከፓን አፍሪካኒዝም አስተሳሰብ የመውረድ አባዜና መዘዙ!

አፍሪካ በአንድ ቀን ሁለት ታላላቅ ጉዳዮችን ከፍፃሜ አድርሳ፣ ወደ መደበኛ ሕይወት ለማቅናት ዕርምጃዋን ጀምራለች፡፡ የመጀመሪያው በአዲስ አበባ ከተማ ለሁለት ቀናት የተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ መጠናቀቅ ሲሆን፣ ሁለተኛው በካሜሩን ለአንድ ወር ያህል ሲከናወን የቆየው የአፍሪካ ዋንጫ በሴኔጋል አሸናፊነት መጠናቀቁ ነው፡፡ ሴኔጋል እሑድ ምሽት የአኅጉሩን የእግር ኳስ በአሸናፊነት የበላይ ስትሆንበት፣ ከዚያ ቀደም ሲል ቅዳሜ ቀን ፕሬዚዳንቷ ማኪ ሳል የኅብረቱን ሊቀመንበርነት በመረከባቸው ተደራራቢ ድል ሆኖላታል፡፡ ኢትዮጵያ በከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ትግል ያዘጋጀችውን የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ በድል ስታጠናቅቅ፣ እንዲሁም በእጅጉ ለቀዘቀዘው የቱሪዝምና የሆቴል ዘርፍ ማነቃቂያ ሊሆን የሚችል መጠነኛ ጥቅም አግኝታለች ተብሎ ይታሰባል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አንፃራዊ የሆነ ሰላምና መረጋጋት እንዳላት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በማሳየት፣ ከትናንት ነገ የተሻለ እንዲሆንላት በተስፋ ታጅባ እንግዶቿን ሸኝታለች፡፡ አፍሪካዊነት ሲቀነቀንባት በከረመችው ኢትዮጵያ የሚቀጥለው ሕይወት ግን የዋዛ እንዳልሆነ በርካታ አመላካቾች አሉ፡፡ ፓን አፍሪካኒዝም በተቀነቀነበት አፍ በብሔርና በእምነት እየተቆራቆሱ አሰልቺው ንትርክ መቀጠሉ አይቀሬ ይመስላል፡፡ ኢትዮጵያዊነትና አፍሪካዊነት በጋራ ሲወደሱ እንዳልከረሙ፣ በሴራ ፖለቲካ ማንነትና እምነት ውስጥ በመሸጎጥ ትንቅንቁ እንደሚቀጥል ምልክቶች ይታያሉ፡፡

ለአገራቸው የሚቆረቆሩ በርካቶች ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነፃነት ተምሳሌትና ፈርጥ ሆና እንድትቀጥል ቢመኙም፣ አገርን ከሥልጣንና ከቡድናዊ ጥቅም በታች የሚያሳንሱ ደግሞ ዓላማቸው ሌላ ነው፡፡ አገርን የሚያስተዳድረው መንግሥትና ፓርቲ ውስጥ ካሉ አስመሳዮች ጀምሮ፣ ለይቶላቸው ሌላ ዓላማና ራዕይ እስካነገቡት ድረስ ለመግለጽ የሚያዳግቱ አደገኛ ባህሪያት ይስተዋላሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን በማንነታቸው ብቻ እየተለዩ ከመታሰር፣ ከመሳደድና ከመገደል የሚታደጋቸው ባጡበት በዚህ ጊዜ በምን ዓይነት ሥሌት አፍሪካዊነት እንደሚቀነቀን ግራ ያጋባል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ገዥው ፓርቲም ሆነ ተፎካካሪዎቹ፣ በተለያዩ አደረጃጀቶች የተሰባሰቡም ሆኑ ልሂቃን ነን የሚሉ ግለሰቦች፣ እንዲሁም ምልዓተ ሕዝቡ ቆም ብለው የሚያስቡበት ጊዜ ላይ መደረሱን ማወቅ አለባቸው፡፡ አፍሪካውያን የጥንቱን የኢትዮጵያ ውለታ አስበው በአንድነት በመምጣት እንደገና ሲሰባሰቡቧት፣ ፖለቲካዊም ሆነ ሌላ ፍላጎት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ወርደው መገኘት የለባቸውም፡፡ ትናንት አፍሪካውያንን ለማስተናገድ ሽርጉድ ሲል የነበረው መንግሥት፣ ዛሬ ደግሞ አገር በሕግና በሥርዓት የምትመራበት ቁመና እንዲኖራት የማድረግ ግዴታ አለበት፡፡ ከሕግ ያፈነገጡና ለሥርዓተ አልበኝነት የሚዳርጉ አደገኛ አሠራሮችን በማስወገድ፣ ተጠያቂነትና ኃላፊነት ያለባቸው አሠራሮችን ማስፈን ይኖርበታል፡፡

በቅርቡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በኦሮሚያ ክልል በከረዩ አባ ገዳና በሌሎች ወገኖች ላይ፣ ከሕግ ውጪ ግድያዎች መፈጸማቸውን ተጎጂዎችንና የዓይን ምስክሮችን እማኝ በማድረግ ሪፖርት አቅርቧል፡፡ ከዚያ በፊት የክልሉ መንግሥት ለግድያዎቹ ኃላፊነቱን ወደ ሌላ ወገን ማስተላለፉ የሚታወስ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ በጉዳዩ ላይ ምርመራ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡ ኦሮሚያ ውስጥ በተደጋጋሚ ኦነግ ሸኔ በሚባለው ኃይል በጣም በርካታ የአማራ ተወላጆች ላይ ግድያ መፈጸሙን፣ ጎጆዎቻቸውና ንብረቶቻቸው መውደማቸውን፣ እንዲሁም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቅለው ሜዳ ላይ መውደቃቸውን ኮሚሽኑ በተደጋጋሚ ሪፖርት አቅርቧል፡፡ የክልሉ መንግሥትም ሆነ የፌዴራል መንግሥት ሕጋዊ ዕርምጃ ወስደው ድርጊቱን እንዲያስቆሙ አሳስቧል፡፡ በተጨማሪም ከፍተኛ ሥጋት ያለባቸውን አካባቢዎች በመጠቆም ጥበቃ እንዲደረግ ቢያሳስብም፣ ተግባራዊ መደረግ ባለመቻሉ በተደጋጋሚ ዜጎች ለጉዳት መዳረጋቸውን በቁጭት እየደጋገመ ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡ እንዲህ ዓይነት አሳዛኝ እሮሮዎች በቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ በደቡብና በሌሎች ክልሎችና አካባቢዎች በተደጋጋሚ ተሰምተዋል፡፡ የአፍሪካ የነፃነት ፈርጥ በሆነች አገር ውስጥ ነውረኛ ድርጊቶችን ማስቆም ሲያቅት፣ ሌሎች አፍሪካውያን ወንድሞችና እህቶች እንዴት ነው ኢትዮጵያውያንን ሊያምኑ የሚችሉት የሚለው ካልታሰበበት ችግሩ እየሰፋ መዘዙ ይከፋል፡፡

በተደጋጋሚ የሕግ የበላይነትን አስመልክቶ ብዙ ጉዳዮች ተወስተዋል፡፡ የሕግ የበላይነት የአንድን ግለሰብ መብት፣ ክብርና ደኅንነት ከማስጠበቅ ጀምሮ፣ የአገርን ሰላምና ጥቅም እስከ ማስከበር የሚደርስ ሰፊ ጽንሰ ሐሳብ ነው፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊ በገዛ አገሩ መብቱ ተጠብቆለትና ተከብሮ እንዲኖር ደግሞ፣ በሕግና በሥርዓት የመተዳደርንና የማስተዳደርን አስፈላጊነት መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ በአገሩ ውስጥ በፈለገው ሥፍራ የመንቀሳቀስ፣ የመኖር፣ የመሥራትና ሀብት የማፍራት ሕጋዊም ሆነ ተፈጥሯዊ መብቱ መረጋገጥ አለበት፡፡ ማንም እየተነሳ በገዛ ክልሌ፣ ዞኔና ወረዳዬ እያለ አንዱ ሌላውን መጤና ተሳዳጅ ከማድረግ አልፎ፣ በአንድ ጊዜ ጥቃት በመቶዎች የሚቆጠሩ ንፁኃን በማንነታቸው ምክንያት መጨፍጨፍ እንደ ተራ ጉዳይ እየታየ ነው፡፡ በመንግሥታዊው መዋቅር ውስጥ በተፈጠረ አደገኛ ብልሽት ሳቢያ፣ የፓን አፍሪካኒዝም ጥንስስ አገር የነውረኞች መፈንጫ እየሆነች ነው፡፡ ትናንት ኢትዮጵያውያን አንተ ትብስ አንቺ ተባብለው አገራቸውን ከወራሪዎችና ከተስፋፊዎች በአንድነት እንዳልተከላከሉና የከፈሉት ክቡር መስዋዕትነት አፍሪካውያንና መላው ጥቁር ሕዝቦችን ለነፃነት እንዳላንቀሳቀሰ፣ የዚህ ዘመን ኢትዮጵያውያን የሴራ ፖለቲካ ሰለባ በመሆን አገራቸው ወደ አደገኛ ምዕራፍ እየነጎደች ነው፡፡ ይህንንም አፍሪካውያን በፅሞና መታዘባቸው አይቀርም፡፡

ፓን አፍሪካኒዝምን ማቀንቀንና ውሉ በማይታወቅ ቡድናዊ አስተሳሰብ ውስጥ መቀርቀር የተለያዩ ናቸው፡፡ የአፍሪካዊነት ዓላማ በቀደሙት ዘመናት አፍሪካን ከቅኝ አገዛዝ በማላቀቅ፣ በፖለቲካና በኢኮኖሚ የጠነከረች ግዙፍ አኅጉር በአንድ አገርነት መመሥረት ነበር፡፡ ለዚህም አፍሪካውያን ቅኝ ገዥዎች ባሰመሩላቸው ድንበሮች ሳይወሰኑ የሰው ኃይላቸውንና የተፈጥሮ ሀብታቸውን በማቀናጀት፣ አዲሱን ትውልድ በዕውቀትና በቴክኖሎጂ የማብቃት ራዕይ ተሰንቆ ነበር፡፡ አፍሪካውያንን በመከፋፈል ከቀድሞ ቅኝ ገዥዎች በማይሻሉ አምባገነኖች ማሰቃየት፣ ከድህነት የሚያላቅቁ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ሳይሆን ጦር የሚያሰብቁ ግጭቶችን መቀስቀስና ቅኝ አገዛዝን የሚያስናፍቁ ስሜቶችን መፍጠር፣ በአፍሪካ ላይ የተዶለቱ ሴራዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ሴራዎች ተግባራዊ እየተደረጉ አፍሪካ የበርካታ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥቶች መናኸሪያ፣ በነፃ አውጭነት ስም ብረት አንስተው የሚያተራምሱ ጉልበተኞች መጨፈሪያ፣ በውጭ ኃይሎች የሚዘወሩ መሪ ተብዬ አሻንጉሊቶች መጫወቻና የበርካታ አሰቃቂ ድርጊቶች መከወኛ ሆና ዘልቃለች፡፡ እነዚህ አልበቃ ብለው በማንነትና በእምነት ከለላ የሚንቀሳቀሱ ነውረኞች፣ ኢትዮጵያን በመሰለች የነፃነት ተምሳሌት አገር ውስጥ ለመስማት የሚያዳግቱ አስነዋሪ ድርጊቶችን እየፈጸሙ ነው፡፡ የአፍሪካውያን መሰባሰቢያ የሆነው የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ የሆነችው ኢትዮጵያ፣ እንዲህ ዓይነቱን ነውር ታቅፋ ነው ስለፓን አፍሪካኒዝም የሚተረክባት፡፡

በሌላ በኩል ሰሞኑን ከትግራይ ክልል የእምነት መሪዎች በኩል የተሰማው፣ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የመገንጠል እንቅስቃሴ አስደንጋጭ ክስተት ነው፡፡ ይህ ክስተት የአንዲት ቤተ ክርስቲያን ውስጣዊ ጉዳይ ተደርጎ የሚወሰድ ሳይሆን፣ የመላው ኢትዮጵያውያን ትኩረት ሊቸረው የሚገባ ነው፡፡ የፖለቲከኞች ቁርሾ በሰላማዊ መንገድ መፈታት ሲገባው፣ ጦር አማዞ ከፍተኛ ዕልቂትና ውድመት መድረሱ ይታወቃል፡፡ መፍትሔ ያጣው ችግር ወደ እምነት መሪዎች ተጋብቶ የአገር ህልውናን የሚፈታተን ውሳኔ ላይ ሲደረስ ግን፣ እጅን አጣጥፎ መቀመጥ ተገቢ አይደለም፡፡ ፖለቲካና ሃይማኖት ዳር ድንበራቸው ተጥሶና ውላቸውን መለየት አቅቶ ሲደበላለቁ፣ ውጤቱ በጣም አደገኛ ሊሆን እንደሚችል በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ ልምዶች አሉ፡፡ በዚህ ዘመን ማስተዋልና አርቆ አሳቢነት እየጎደለ እዚህ ደረጃ ላይ ሲደረስ፣ ቢያንስ የአገር ጉዳይ የሚያሳስባቸው ኢትዮጵያውያን ተባብረው የመከላከል ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ገደብ አልፈው የሚሄዱትን መገሰፅና ማስቆም ይጠበቅባቸዋል፡፡ የፓን አፍሪካኒዝም እርሾ የነበረችው ኢትዮጵያ ማንም እየተነሳ በብሔርና በእምነት እየተቧደነ ሲከፋፍላት፣ አፍሪካውያን ወንድሞችና እህቶች እነዚህን ሰዎች ምን ነካቸው ብለው ግራ እንደሚጋቡ ማስተዋል ካቃተ መዘዙ ከሚታሰበው በላይ ነው!    

  

    

 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ከሴራ ፖለቲካ በስተጀርባ ጥቅማቸውን የሚያስጠብቁ ኃይሎች

በመኮንን ሻውል ወልደ ጊዮርጊስ የአፄ ቴዎድሮስ መንግሥት የወደቀው ከመቅደላ በፊት...

ስለዘር ፖለቲካ

በሀብታሙ ኃይለ ጊዮርጊስ  ‹‹በቅሎዎች ዝርያችን ከአህያ ነው እያሉ ይመፃደቃሉ›› የጀርመኖች...

አማርኛ ተናጋሪዋ ሮቦት

በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው የሳይንስ ሙዚየም፣ ሚያዝያ 2 ቀን...

ወዘተ

ገና! ከእናቴ ሆድ ሳለሁ፤ ጠላት ሲዝትብኝ ሰምቻለሁ። በዳዴ ዘመኔም፣ በ'ወፌ ቆመችም!'፤ አውዴ ክፉ ነበር...

የአስፕሪን ታሪክ

በቤት ውስጥ የሚገኝ የመድኃኒት መደርደሪያ፣ ምንም ቢሆን፣ እስፕሪንን ሳይጨመር...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የማፍረስ ዘመቻው በብልሹ አሠራሮች ላይም ይቀጥል!

መንግሥት በኮሪደር ልማት አማካይነት የአዲስ አበባ ከተማን ዋና ዋና ሥፍራዎች በማፍረስ፣ አዲስ አበባን ከኬፕታውን ቀጥሎ ተመራጭ የአፍሪካ ከተማ ለማድረግ መጠነ ሰፊ ሥራ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡...

ለድጋፍ ብቻ ሳይሆን ለተቃውሞም ማስተንፈሻ ይሰጥ!

በሕዝብ ድምፅ ተመርጦ ሥልጣን የያዘ መንግሥት ዋነኛ ሥራው በሕግ መሠረት የተሰጡትን ኃላፊነቶች በብቃት መወጣት ነው፡፡ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ፣ የአገርን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ማስከበር፣...

የፖለቲካ ምኅዳሩ እንዳይዳፈን ጥንቃቄ ይደረግ!

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር አሁንም ጤና አልባ ሆኖ የተለመደው ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ውስጥ ነው የሚገኘው፡፡ ካለፉት ሃምሳ ዓመታት ወዲህ ሊሻሻል ያልቻለው የፖለቲካ ምኅዳር ሰሞኑን አዲስ...